እውቀትም እምነትም አያስፈልጉም የሚባሉ ነገሮች አይደሉም

እውቀትም እምነትም አያስፈልጉም የሚባሉ ነገሮች አይደሉም፡፡ ለመዳን እምነት አስፈላጊ መኾኑን ከተግባባችሁ የእውቀትን ነገር ለመፍታት ደግሞ ሁለታችሁምእውቀትየምትሉት የትኛውን ነው የሚለው ወሳኝ ነው፡፡ በደፈናው እውቀት አያስፈልግም አይባልም፤ ለድኅነት የሚያስፈልግ እውቀት አለ፤ የማያስፈልግ እውቀት አለ፡፡ እውቀት ሁለት ነው፡፡

የእግዚአብሔር እውቀት አለ፡፡ የጠቢባን እውቀት አለ፡፡ የቀደመው ሕይወት የሚገኝበት እውቀት ነው፡፡ የኋለኛው ከንቱ እውቀት ነው፡፡ የቀደመው እውቀት መጻሕፍትም፣ መምህራንም፣ ሐዋርያትም ነቢያትመ የተላኩለት ለዚሁ ነው፡፡ ይህ እውቀት በአንድ መንፈሳዊ ሰው የድኅነት ጉዞ ውስጥ አስፈላጊ ባይኾን ኖሮ ከነቢያት ዠምሮ እስከዛሬ የእግዚአብሔር ልፋቱ ለከንቱ ነው ለማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን አስቀድሞ ሐዋርያትን፣ ኋላም ነቢያትን ከዚያም መምህራንን ላከ የተባለው ለዚሁ ነው፡፡ እውቀት አስፈላጊ ስለኾነ፡፡ ሁለተኛው እውቀት የጠቢባን እውቀት የሞኝ እውቀት ነው፡፡ እግዚአብሔር የዚህን ዓለም ሰዎች እውቀት ሞኝ አድርጎታልና የተባለለት፡፡ ዳግመኛም ጠቢባን ነን ሲሉ የወደቁ ኾኑ የተባለለት ከንቱ ዓለማዊ እውቀት ነው፤ በድኅነት ውስጥ ምንም ፋይዳ የለለው ነው፡፡

ስለዚህ አስቀድማችሁ የትኛውን እውቀት ማለታችሁ እንደኾነ አጥሩና ምናልባት እኔ እንደምገምተው ልዩነታችሁን ልትተዉት ትችላላችሁ፡፡

ካልኾነ ግን የእግዚአብሔር እውቀት ላልነውም ቢኾን ሁለት ዓይነት አለው፡፡ በተፈጥሮ ሰው ኾነን ስንፈጠር በልቡና ጽላት ተጽፎ የሚገን ምንጩ እግዚአብሔር ራሱ የኾነ ስለራሱ ስለእግዚአብሔር የሚተርክ እውቀት አለ - ለእምነት የሚያበቃ እውቀት - አስፈላጊ እውቀት፡፡ ዳግመኛም ከምምህራነ ወንጌል፣ ከመጻሕፍት ወዘተ .. በስብከት በትምህርት ከእግዚአብሔር ቃል የሚገኝም አለ፡፡

ስለዚህ ባጭሩ

1.
ከመስማት የሚገኝ እውቀት አለ፤

2. ከተፈጥሮ የሚገኝ አለ ለማለት ነው፡፡

የትኛውን እውቀት ነው አያስፈልግም የምትሉት፡፡ ለሁለቱም ለእነዚህ እውቀቶች ምስክርነት ሲሰጥ ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡፡

1.
በተፈጥሮ በልቡና ተጽፎ ያለሰባኪና ያለአስተማሪ ስለሚገኘው እውቀት

እግዚአብሔር ስለ ገለጠላቸው፥ ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው በእነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና። የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤ ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፤ ባለው ይታወቃል፡፡ ሮሜ 119-21 ያለመምህር፣ ያለመጽሐፍ ያለሰባኬ ወንጌል በልቡና የሚገለጥ የእግዚአብሔር እውቀት - አዳኝ እውቀት፡፡


2. በትምህርተ መምህራን በመጻሕፍት በመገሥፃን በሚነገር ቃለ እግዚአብሔር እውቀት ደግሞ

እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ? ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ? እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ነገር ግን። እስራኤል ባያውቁ ነው ወይ? እላለሁ። ይላል፡፡ ሮሜ.1014-19

ለአንድ ኦርቶዶክሳዊ ምእመን እምነትንና እውቀትን አየነጣጠለ አንዱን እየወገነ አንዱን እየነቀፈ መከራከር የሚረባው:

1. “
እውቀት የተባለው የዚህ ዓለም ጠቢባን ነን የሚሉ ሞኞች እውቀት ከኾነ:

2. “እምነት የተባለው ደግሞ መልካም ሥራ የተለየው ምውት እምነት ከኾነ ብቻ ነው፡፡

ያለዚያ ግን ሁለቱም በመዳን ሕይወት ውስጥ እጅግ አስፈላጊ ናቸው፡፡ ሌላው መዘንጋት የለለበት ነገር ቢኖር እነዚህ ሁለቱ አንዳቸውም ብቻቸውን ለመዳን አይበቁም፡፡ ሁለቱም ተጣምረው እንኳ በቂ አይደሉም - እንኳንስ አንዱን ጥሎ፡፡ ካስተዋልን! ሁለቱም አጋንንት እንኳ አላቸው፡፡ ከእውቀት ብትሉ ከእኛ የተሻለ እውቀት አጋንንት አላቸው - ረቂቃን ናቸውና የተሰወረ ብዙ ለእነርሱ ግን ግልጥ የኾነ አለ፡፡ እግዚአብሔርንም ገጽ ለገጽ ያውቁታል፤ አዋርተውታልም - ጽድቁንም ርትዑንም አይተዋል፡፡ ከእምነትም ደግሞ ፍጹም እምነት አላቸው፤ ሐዋርያና ረድኡ ቅዱስ ያዕቆብ አጋንንትስ እንኳ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል እንዳለው፡፡ ሰው የሚድነው እነዚህ ሁለቱ ማለትም እውቀቱ አሊያም እምነቱ በእነዚህም ብቻ ቢኾን ኖሮ አጋንንት ኹላቸው ይድኑ ነበር፡፡ ነገር ግን ሰው በእነዚህ በሁለቱ ላይ ከአጋንንት የሚበልጥ ምን ነገር ሊኖረው ይችላል - እነርሱ የማይኖራቸው ርሱ የሚኖረው ሲባል ግን በምግባሩ በፍቅር ሥራው እንላለን፡፡ ይህ እውቀትና እምነቱ በመልካም ሥራው በፍቅር ተግባሩ ሲገለጹ ነው ለድኅነት የሚበቃው፡፡

ያወቀ ሰው እውቀቱ አያድነውም፡፡ እውቀቱ በእምነት መታተም አለበት፡፡ ያመነም ሰው እምነቱ ብቻ አያድነውም፡፡ በበጎ ሥራ መገለፅ አለበት፡፡ ድኅነት/ጽድቅ የሚገኘው የመጨረሻው ደረጃ ሲደርስ ነው፡፡ እስከፍጻሜው የሚጸና ይድናል እንደተባለ፡፡ ዳግመኛም ሐዋርያና ረድኡ የሚኾን ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ፡

ወንድሞቼ ሆይ፥ እምነት አለኝ የሚል፥ ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? ነገር ግን አንድ ሰው። አንተ እምነት አለህ እኔም ሥራ አለኝ፤ እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፥ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል። አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል። አንተ ከንቱ ሰው፥ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደ ነበረ፥ በሥራም እምነት እንደ ተፈጸመ ትመለከታለህን? መጽሐፍም። አብርሃምም እግዚአብሔርን አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት ያለው ተፈጸመ፤ ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ። እንደዚሁም ጋለሞታይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው። -- ያዕ.214-26 ይለናል፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር!

አስተያየቶች