(የቃልና የሥጋ ተዋሕዶ) --- “አንቀጸ ትስብእት”፣ …. “አንቀጸ መለኮት”




የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ሁል ጊዜም ቢሆን በተከታዮቹና በማያምኑትም ዘንድ ከፋፋይ ሆኖ ይኖራል፡፡ ጌታ በምድር ላይ ቤተ ክርስቲያኑን በመሠረተበት ጊዜም ይህንን ጠቋሚ የሆነ ነገር ተናግሯል፡፡ በፊልጵስዩስ ቂሳርያ ደቀ መዛሙርቱን ሰዎች ማን እንደሚሉት በጠየቀበት ወቅት ከተከናወነው ይህን ማወቅ ይቻላል፡፡

ቤተ ክርስቲያን በምሥረታዋ ወቅት የወልድን ማንነት መሠረት አድርጋ መቋቋሟ የሚናገረው ነገር እስከ ዓለም ፍጻሜ የወልድን ማንነት እየነገረች ሰዎች በዚያ ሃይማኖት የእግዚአብሔር ልጆች የመባልን ሥልጣን እያገኙ እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ሁል ጊዜም ቤተ ክርስቲያን የጌታችንን ማንነት ስትጠይቅ፣ ስትጠየቅ፣ ስትመልስም፣
ስታስመልስም ሁሉን የምትመረምረው ሰው የሚድነው እንዴት ባለ የወልድ ማንነት ነው ከሚለው አንጻር ነው፡፡ በዚህም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥግው ቃልነት (ሰው የሆነ አምላክ፤ አምላክ የሆነ ሰውነት) የተለየ ምንም ዓይነት ባሕርይ አትቀበልም፡፡ እንደ አብ መለኮታዊ፣ እንደ አዳም ሥጋዊ፤ (ከአምላክነት ምንም ያልተጓደለበት፣ ከብቻዋ ከኃጢአት በቀር የሰውን ማንነት ማንነቱ ያደረገ፤ ሁለቱን በአንድ ያስተባበረ፤ በእግዚአብሔር ምሳሌ የሚኖር ነገር ግን የባርያውን አርአያ የነሳ፣ ፍጹም ሰው የሆነ ፍጹም አምላክ፤ ፍጹም አምላክ የሆነ ፍጹም ሰው) ብላ አጠንክራ ታምናለች፡፡

ቤተ ክርስቲያን እምነቷንና አምልኮቷንም ሁሉ በዚህ ነገር ፍጹም እውነተኛነት ላይ ስለመሠረተች ራሷን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ብላ ትጠራለች፡፡ ኦርቶዶክስ ቃሉ ግሪክ ሲሆን እውነተኛ እምነት ማለት ነው፡፡ ተዋሕዶ ደግሞ ሰማያዊ ቃል ሥጋ ሆኗል፤ በዚህም ለምድራዊው ሥጋ ክብርን ሰጥቷል፤ እንግዲህስ ሥጋም አምላክ ሆኗል ማለት ነው፡፡ ሁለቱን በአንድ ስናነብ የሚሰጠን ትርጉም የሰማይም የምድርም አቅኚ እውነት አንድ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ ሰው መሆን ነው የሚል ነው፡፡

ቃል ቀዳማዊ፣ ዘላለማዊ ነው፡፡ ቃል አይራብም አይጠማም አይደክምም፡፡ ቃል ፈጣሪ ነው፤ የሆነው ሁሉ በእርሱ ሆኗል፡፡ ከቃል በቀር ከሆነው አንዳች ስንኳ አልሆነም፡፡ ቃል በዘመንና በቦታ አይወሰንም፤ ሕያው የባሕርይ ፍጹም አምላክ ነው፡፡ ሥጋ ደግሞ ዘላለማዊ አይደለም፤ የተፈጠረበት ዘመን አለ፤ መዋቲ ነው፤ ይራባል፤ ይጠማል፤ ይደክማል፤ ሕማም፣ ድካም፣ ጻርና ጻማ ይስማማዋል፡፡ ይህን አንድ በሉ፡፡

በሌላ በኩል ቃል ፈዋሴ ነው፤ መድኃኒት መሆን ይችላል፤ ኃጢአትን ከባሕርዩ ማስተስረይ ይችላል፤ ለአዳም ቤዛነት የሚፈለገው የመለኮት ባሕርይ ባሕርዩ ነው፡፡ ሰው ደግሞ መድኃኒት መሆን አይችልም፤ ፍጡር ስለሆነ፡፡ ለአዳም ቤዛ የሚሆን ምንም ገንዘብ የለውም፡፡ (በመጀመሪያም አዳምን ከገነት ውጣ ያለው እግዚአብሔር ነው፤ ግባ ብሎ ሊፈቅድለትም የሚችለው እርሱው ነው፡፡) ስለዚህ ሰውን ሊቤዥ ወደ ምድር የመጣው ቃል መዋቲ (የሚሞት ስላልሆነ፤) አንድም መሥዋዕቱ በመስቀል ላይ በሚሆን ሞት በመሆኑ የመዋቲውን ባርያ ገንዘብ ገንዘቡ በማድረግ ተዋሕዶታል፡፡ ተዋሕዶውም ፍጹም ነው፡፡ ባይሆን ምን ይሆናል ቢሉ … ባይሆንማ የቃልና የሥጋ አብሮነት፣ ተራ ጓደኝነት፣ ጉርብትና፣ አብሮ ማደር ይሆናል፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ከርስቲያን አስተምህሮ ግን አንዱ ባሕርይ ሌላውን ባሕርይ ፍጹም የገዛ ገንዘቡ አድርጎታል እንላለን፡፡ ከቃል ወደ ሥጋ ሥናወራ ሁሉንም የመለኮት ባሕርያት ለሥጋ እንቀጽላለን፤ ከሥጋ ወደ መለኮት ስናወራ ግን ዘእነበለ ኃጢአት ባሕቲታ፣ ከብቻዋ ከኃጢአት በቀር እንላለን (ዓላማውም ኃጢአትን ማስወገድ በመሆኑ ነው)

ታዲያ የመለኮትና የትስብእት (የቃልና የሥጋ) ተዋሕዶ ፍጹም ነው ማለት መለኮት ቢፈውስ መለኮት ብቻ ሳይሆን ሥጋም ፈውሷል የሚያሰኝ፤ መለኮት ወደላይ ቢያርግ ሥጋም አርጓል እንድንል የሚያሰኘን ነው፡፡ ሥጋ ቢርበው መለኮትም ተርቧል፤ ሥጋ ቢደክም መለኮትም ደክሟል እንላለን፡፡ ይህም አብሮ በመኖር፣ በመጎራበት፣ በመጎዳኘት ሳይሆን ፍጹም የሥጋን ባሕርይ መለኮት ባሕርዩ በማድረጉ፣ የመለኮትን ባሕርይ ሥጋ ባሕርዩ በማድረጉ ነው፡፡ ከተዋሕዶ በፊት የነበረው የሁለቱ ባሕርያት ልዩነት ከተዋሕዶ በኋላ የለም፡፡ ከተዋሕዶ በኋላ ይህን ያደረገ ቃል ነው፤ ይህን ግን ሥጋ ነው አንልም፡፡ የሆነው ሁሉ የሆነው በዋሕደ ባሕርይ ዘእግዚአብሔር ቃል ሥግው ነው (ሥጋ የሆነው የአንዱ የእግዚአብሔር ቃል ባሕርይ) ነው፡፡ ውኃውን ወደ ወይን የለወጠው መለኮት፣ ደክሞት ውኃ ስጡኝ ያለ ሥጋ እንደሆነ የሚናገሩ ሰዎች ኋላ ላይ ማስረዳት የሚያቅታቸው ዋናውን ነገር ነው - በመስቀል ላይ የሆነውን ቤዛነት፡፡

የቤተ ክርስቲያን ይህ ሁሉ ጥንቃቄ ታዲያ መስቀል ላይ የሆነው ምንድን ነው የሚለውን ሳያንሻፍፉ ለመመለስ ነው፡፡ የተቸነከረው ማን ነው፤ ሥጋ ነው፤ መለኮት ነው፤ እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ሥግው ቃል ነው፤ ማለት ሥጋም ቃልም ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሥጋ ተቸንክሮ ዓለም ስለማይድን፡፡ ሥጋ ዓለምን ለመቤዠት የሚፈልገው መድኃኒትነት ያለው መለኮት ስለሆነ ነው፡፡ መለኮትን ደግሞ ማንም ችሎ ስለማይቸነክረው ሊቸነከር የሚችለውን ባሕርየ ሥጋን ገንዘቡ ማድረግ ስለሆነ ነው፡፡ በሥጋው ተሰቀለበት፤ በመለኮቱ አዳነበት ማለት የምንናገረው ሁኔታ አንድ በተዐቅቦ (በመጠባበቅ) ብቻ ነው፡፡ ተዐቅቦ ማለት ዓለም እንዲድን እጅግ አስፈላጊ የሆነ የተዋሕዶው ሁኔታ ነው፡፡ በዚህም መለኮት ሥጋን ፍጹም ሲዋሐደው መለኮትነቱን ጠብቋል (አላጠፋም) ሥጋም መለኮትን ሲዋሐድ ሥጋነቱን ጠብቋል (አልተወም) ነው፡፡ በቀረው ግን ያለመለወጥ፣ ያለመደባለቅ፣ ያለመቀላቀል፣ ያለመደመር፣ ያለመደረብ፣ ያለመተዳደር (ዘእንበለ ኅድረት) ይህ ፍጹም ተዋሕዶ ሆኗል፡፡ ከተዋህዶ በኋላ የቃልና የሥጋን ድርሻ በፍጹም፣ በፍጹም፣ በፍጹም፣ ለያይተን አንናገርም፡፡

ታዲያ አንቀጸ ትስብእት … አንቀጸ መለኮት ምንድን ነው፤

ለትምህርት ጉዳይ በጌታችን ባሕርይ ያሉ ነገሮችን ከምን የተነሣ እንደሚሆኑ በመናገር ሂደት ወደ ኅድረት (ማደር) እንጎተታለንና የንስጥሮስ ሃይማኖት ይሆንብናል፡፡ ምክንያቱም ጌታችን ሲራብ ለምሳሌ የተራበው ሥጋ ነው፤ መለኮት ነው፤ ብለን አንለይም፤ ሁለቱም ባሕርይ አንድ ባሕርይ ስለሆነና ሥግው ቃል ስለተባለ ያ አንድ ባሕርይ ተርቧል፤ በዚህም መለኮትን ረሃብ አግኝቶታል እንላለን፡፡ ነገር ግን ረሃብ የየትኛው ባሕርይ እንደነበረ መናገር ግዴታ ነው፡፡ ምክንያቱም ቃል/መለኮት ስለማይራብ … ስለዚህ ሊቃውነቱ ከሥጋው የተነሣ ተራበ፣ ከሥጋው የተነሣ ተጠማ የሚል አገላለጥ ይጠቀማሉ፡፡ ማን ተራበ ላይ የባሕርይ ምንታዌን አያስተምሩም፤ ይጠነቀቃሉ፡፡ ከማን የተነሣ ተራበ ላይ ግን ቅድመ ተዋሕዶ የቃልና የሥጋ ባሕርይ የሆኑትን ጠቅሰው ያስተምራሉ፡፡ ከዚያም ሞተ በሥጋ ይላሉ፤ ከሥጋው የተነሣ ሞተ፤ ከመለኮቱ የተነሣ ደግሞ ሕያው ሆነ፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ጊዜ ጌታችንን የሚገለጥበትን መንገድ ከተመለከትን ብዙ ጊዜ ሥግው ቃልነቱን (ሁለቱንም ባሕርይ በአንድ ያስማማ) አገላለጥ እንመለከታለን፡፡ እነዚህም “ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ዘየአትት ኃጢአተ ዓለም የዓለምን ኃጢአት የሚያርቅ የእግዚአብሔር በግ” ፤ ወዘተ ያሉት ናቸው፡፡ እነዚህ ተዋሕዶን መሠረት ያደረጉ፤ ብዙ ጊዜ ትርጓሜ የማይፈልጉ ናቸው፡፡

ነገር ግን አንዳንዴ መለኮታዊ ባሕርዩን ብቻ ወይም ደግሞ ሥጋዊ ባሕርዩን ብቻ መሠረት አድርጎ ሲገልጥም እንመለከታለን፡፡ መለኮታዊውን ባሕርይ ብቻ መሠረት ያደረጉ ማለትም “ውስተ እለ ዚአሁ መጽአ የእርሱ ወደ ሆነው መጣ የእርሱ የሆኑትም አልተቀበሉትም” እንዳለው ዓይነት ናቸው፡፡ እነዚህን አንቀጾች ስንመለከት ክርስቶስ ከላይ የመጣውን የቃል ባሕርይ ብቻ የሚገልጹ ከምድር የነሣውን ባሕርይ ሳያመለክቱት የሚያልፉ ይመስላሉ፡፡ ምክንያቱም ከላይ ያልወረደም የሥጋ ባሕርይ አለውና፡፡ “አብርሃም ሳይኖር እኔ አለሁ” ያለውንም ብንመለከት ያው ነው፡፡ አብርሃም የነበረው ይህ ንግግር ከሚነገርበት ቀን 2000 ዓመታት አስቀድሞ ነው፡፡ ያ ከማርያም የነሣውና የተዋሐደው ሥጋ ያኔ ህልው አልነበረም፡፡ ያኔ የነበረው መለኮታዊ ባሕርዩ፤ ማለት ዘላለማዊ አካላዊ ቃል ወልድ ነው፡፡ ስለዚህ ትስብእቱን ሳያመለክት አውርቷል፡፡ እነዚህ ታዲያ የአውጣኪን ሃይማኖት የሚያጭሩብን ጸዋጋት ቀለማት ናቸውና ብዙዎች ዋጠው መጠጠው ለማለት ይሰናከሉባቸዋል፡፡

አንዳንዴ ደግሞ ሥጋዊ ባሕርዩን (ሰውነቱን) ብቻ መሠረት አድርጎ ሲናገር እንመለከታለን፡፡ እነዚህም “ወመንፈስ መልዓ ላዕሌሁ መንፈስ በላዩ መላበት” የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ክርስቶስ ወሀቤ ጸጋ ጸጋን የሚሰጥ አምላክ ሳለ ነገር ግን መንፈሰ ኃይል እንደተቀበለ አድርጎ ከጊዜ በኋላ እንዳገኘ አድርጎ ይናገራልና ይህ ደግሞ ሥጋውን እንጂ መለኮቱን መሠረት ያላደረገ ኃይለ ቃል ነው፡፡ ከእኔ አብ ይበልጣል፤ የፍርድን ቀን ከአብ በቀር ወልድ እንኳ አያውቅም፤ መንግሥትን ለአባቱ ያስረክባል ወዘተ. ያሉት ደግሞ ጌታችን ከጊዜ በኋላ እንደጸደቀ የሚመስሉ የንስጥሮስን የአካልና የባሕርይ ምንታዌ እስከማስተማር ብዙዎች ተሰነካክለው የሚወድቁባቸው ናቸው፡፡

በእነዚህ በሁለቱ ስሕተቶች አደጋ ላይ የወደቀ ነገር ቢኖር የሰው ልጅ ድኅነት ተፈጽሟል ወይስ አልተፈጸመም የሚለው ጥያቄ ደግሞ ደጋግሞ መነሣቱ ነው፡፡

በዚህ ምክንያት ኦርቶዶክሳውያን አባቶቻችን በመጻሕፍት የሰፈሩ ተዋሕዶን የሚመለከቱ አገላለጦች በሙሉ በዚህ በሁለት መልኩ ይገልጧቸዋል፡፡ አንቀጸ መለኮትን መሠረት አድርገው የተነገሩ ቃላተ ተዋሕዶ እና አንቀጸ ትስብእትን መሠረት አድርገው የተነገሩ ቃላተ ተዋሕዶ፡፡ ምንም እንኳ ከተዋሕዶ በኋላ ይህ ግብር የቃል ግብር ነው፤ ይህ ግብር የሥጋ ነው ብለን ባንለይም ነገር ግን ስለ ዋሕደ ባሕርይ በሁለት መንገድ ማለትም ግብሩ የሚያጠይቀውን ባሕርይ ጠቅሶ በመናገር ተዋሕዶን ማመልከት እና ቃል ሥጋን ከመዋሐዱ የተነሣ በሁለቱ ባሕርያት የሆኑትን አዲስ ገንዘቦች ማለትም የሥጋን መድኃኒት መሆንና የቃልን መዋቲ (ሊሠዋ የሚቻል) መሆን በማመልከት እንናገራለን፡፡

በእነዚህ በሁለቱ አገላለጾች በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ድካምና ሕማም የመሳሰሉትን አላዋቂ ሥጋን መዋሐዱን ሲያጠይቅ እያልን የዚህን ግብር መምጫውን ምንጩን እናስረዳበታለን እንጂ ነገሩን አጡዘነው በእግዚአብሔር ወልድ ላይ የባሕርይ ተወራጅነት ትምህርት ለማስተማር ውጤት አንጠቀምበትም፤ እንዲህ የሚያደርጉትንም ፍጹም እንወቅሳቸዋለን፡፡ በአንጻሩ ደግሞ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ቤዛነት፣ ፈዋሽነት፣ ሁሉን አድራጊነት የመሳሰሉትን የቃልን ገንዘብ ገንዘቡ አድርጓልና ብለን የዚህንም መምጫውን ምንጩን እናስረዳበታለን እንጂ ነገሩን አጡዘን ከማርያም የነሣው ሥጋ ተዋጠ ተመጠጠ የሚል ትምህርት አናስተምርበትም፡፡

አንድም ሐዋርያት ወንጌልን ለአይሁድ ሲለብኩ አይሁድ ለአንድ ቅዱስ መሠዋት የለመዱ ናቸውና፤ አሁን ለአብ ይሉናል፤ አሁን ለወልድ፤ አሁን ደግሞ ለመንፈስ ቅዱስ ይሉናል፤ ለየትኛው እንሠዋለን ብለው ወንጌልን ከመቀበል እንዳይሰንፉ የጌታችንን ባሕርይ ሲገልጹት ቃለ መጽሐፉን ነጠላ ንባቡን ስንመለከተው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከጊዜ በኋላ ጸጋን እንደተቀበለ፤ እንዳገኘ የሚመስሉ አንቀጸ ትስብእት አንቀጸ ሥጋን መሠረት ያደረጉ ቃላትን ይጠቀማሉ፡፡ እውነታው ምንድነው ቢሉ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ አገኘ የምንለውን ሀብታት ሁሉ ከመለኮት የነሣው ከተዋሕዶ (ከብሥራት/ጽንሰት) ጀምሮ ነውና፡፡ ከተዋሕዶ በፊት ሥጋ እንዲህ ያለ የመፈወስ ሀብት አልነበረውም፡፡ ከተዋሕዶ በፊት ቃልም እንዲህ ያለ ድካምና ሕማም የሚስማማው ባሕርይ አልነበረም፡፡

ወንጌልን ለአሕዛብ ሲሰብኩ ደግሞ ለብዙኃን ጣዖታት መሠዋትን ለምደዋልና ወደ አንዱ ለመሳብ የእግዚአብሔር ወልድን ቀዳማዊ ባሕርይ መሠረት ባደረገ ቃል ይሰብኳቸዋል፡፡ በዚህም በመጽሐፍ ቅዱስ የሰፈሩ መልእክታት እያንዳንዳቸው የተለያየ ምክንያተ ጽሒፎት (የአጻጻፋቸወ ዓላማ) ተጣርቶ በየአስተምህሮዎቹ ላይ ግንዛቤ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡

ከተዋሕዶ በኋላ ግን ጥንት ያልነበረውንም ሥጋ ጥንታዊ ቀዳማዊ እንለዋለን፤ ዘመን የማይቆጠርለትን መለኮትም ዘመን እንቆጥርለታለን፡፡ ለምን ቢሉ ተገናዝበዋልና፡፡

አንዳንዴም አባቶቻችን ኅድረትንና ውላጤን ተጠንቅቀው ሲያስተምሩ ኃደረ የሚለውንና ኮነ የሚለውን አሳስበው ተዋሕዶን ያብራራሉ፡፡ ማለት አንቀጸ ተዋሕዶ ኀደረ እንደሚል ሲሆን ኮነ በሚለው ይስቡታል፡፡ አንቀጸ ተዋሕዶ ደግሞ ተለወጠ እንደሚል ሲሆን ኀደረ በሚለው ይስቡታል፡፡ ወነስአ አርአያ ገብር የባርያውን አርአያ ነሳ የሚለውን ቃል ሥጋ ኮነ ብለው እንደሚተረጉሙት ነው፡፡

ስለዚህ ሦስት ነጥቦች፡

ትስብእትና መለኮትን በሚመለከት ምንም ቢሆን የማይለወጡ እውነቶች፡፡ 

1) የናዝሬቱ ኢየሱስ የአብ አካላዊ ቃል የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ከሁለት አካል አንድ አካል ነው፡፡ ዳግመኛም ቅድመ ዓለም ከአብ ቀዳማዊ ልደትን ያለ እናት ተወልዷል፤ በዓለምም ከማርያም ደኃራዊ ልደትን ያለ አባት ተወልዷል፡፡

2) ኀደረና ኮነ አንዳንዴ መጻሕፍት ኀደረ የሚመስል አንዳንዴም ኮነ የሚል ቃል ይጠቀማሉ፡፡ የሚፈቱት ተዋሐደ በሚለው ነው፡፡ በዚህም ላይ የባሕርይና የአካላት (የሁለቱንም) ምንታዌ ክደን እናስተምራለን፡፡ ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ከሁለት አንድ አካል ነው፡፡

3) ሐዋርያት ለምን እንዲህ አደረጉ፡ እንደሚሰብኩለት ማኅበረ ሰብእ አይሁድ ቢሆኑ ግሪካዊ ሲሠዉ እንደኖሩበት ልማድ ይለያያል፡፡ ከዚህም ባሻገር አንዳንዴ የጌታችንን መከራ በመከራ ውስጥ ለመጽናት እንደ ምሳሌ አድርገው ምእመናንን ሲያስተምሩ የራሳቸውን መከራ ጠቅሰው እንደሚያስተምሩ ሁሉ የጌታንም ያስተምሩበታል፡፡ በመከራ ብትጸኑ ጸጋና ሀብትን ከእግዚአብሔር ትቀበላላቹ ሲሏቸው እርሱ ለሞት እንኳ ያውም እንኳ በመስቀል ለሆነው ሞት የታዘዘ ሆነ ስለዚህም እግዚአብሔር ያለመጠን ከፍ ከፍ አደረገው ብለው ያስተምሯቸዋል፡፡ ለእነዚህ ክርስቶስ ለዓላማ የመጽናት ተምሳሌት እንደሆነ አድርገው መንገራቸው ነው እንጂ ለምግባር ለትሩፋት የተጠቀሰውን ለዶግማ ወስደን ሥላሴ ላይ የአካላት አንድነትና የባሕርይ ትሥልስት ማምጣት ፍጹም ክህደት ነው፡፡

አስተያየቶች

  1. በጣም ጥሩ ትምህርት ነው።ቃለ ሕይወት ያሰማልን።

    ምላሽ ይስጡሰርዝ

አስተያየት ይለጥፉ