የቤተ ክርስቲያን መደበኛ እና ኢመደበኛ መዋቅሮች ኢንተርፕሌይ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ አገልግሎት ተልእኮ
መደበኛ መዋቅር ሊደርስባቸው የማይችሉ የተልእኮት ተግባራትን በኢመደበኛ መዋቅር ለመድረስ ስለመጣር መደበኛና ኢመደበኛ ቅይጥ ጨዋታ ወይም ወግ፤
አዲስ ወልዴ (ነሐሴ 2012 ዓ.ም.)
- አጠቃላይ
- መደበኛና ኢመደበኛ መዋቅሮች፤
- ችግሩ ይለይ፤
- ምን ይደረግ፤
- አሁን ምን ምን አለን፤
- የሚያስፈልጉን ምን ምን ናቸው፤
- ማን ምን ያድርግ፤
አጠቃላይ

የቤተ ክርስቲያን ተልእኮቷ በምድር ላይ ሁነኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ምስክር በመሆን አሕዛብ እግዚአብሔር የሚገኝበትን እምነትና ሕይወት ገንዘብ ማድረግ እንዲችሉ ማድረግ ነው። በዚህ ረገድ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዚህ የሐዋርያት ተልእኮት ተረካቢ ሆና ይህን ስታከናውን ብዙ ታሪካዊ ሂደቶችን አልፋ መጥታለች። በያዝነው ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ ይህን ሚና የምትጫወተው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሚናውን ለመጫወት የተወሰኑ በጎ ዕድሎችና የተወሰኑ መታለፍ ያለባቸው ውጣ ውረዶች አሉባት። 

በጎ ዕድሎች እውነተኛ የሐዋርያት እምነትና ትክክለኛ የእግዚአብሔር አምልኮት፥ ጠንካራ ረጅም መሠረት ያለው ሐዋርያዊ ታሪክ፥ ሰፊ የሕዝብ መሠረት፥ ሁነኛ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ትምህርት፥ ለዚህ ተገቢ የሆነ ተቋማዊ ይዞታና ትውፊት ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። 

ፈታኝ ሁኔታዎች ተቋማዊ አደረጃጀቷን የሚያንቀሳቅስ የሰው ኃይል ዘርፈ ብዙ ውሱንነቶች (የዕውቀት፣ ሞያ፣ ክህሎት፣ አመል፣ ሃይማኖት ወዘተ. - በአማርኛ ሲነገር ያልተማረ፣ መናፍቅና ስግብግብ ሰው መዋቅሩ ውስጥ አለመታጣቱ/መብዛቱ በሚያግባባን)፥ ፖለቲካዊና ማኅበረሰባዊ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች የሚያደርሱት ተጽዕኖና (ከመደብ፣ ዘርና ጎሳዊ ማንነት ጋር አፋቶ የሚያያት መጥፋቱ፤ ይህን የታከከ ፖለቲካዊ ጡዘት ሲመጣ ቀዳሚ ተጠቂ መሆኗ) የተደማጭነት መቀነስ (በተለያየ ምክንያት በዋነኛነት ግን በአገልጋዮች ስብእና - ወይም እምነቱን በተግባር ያለመኖር ውጤት)፥ ክብረ ክህነት ሌሎች የሚያስተናግዳቸው ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች፥ ዓለማዊነትና ልዕለ ዓለማዊነት በቴክኖሎጂ ኃይል እየታገዙ የሚያሳዩት ዕድገት ለሐዋርያዊ ተልእኮ የሚልካቸው አሉታዊ ግልባጮች ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው።

የዕድሎችን በጎ ጎን ቀምሮ ጥቅም ላይ በማዋል በኃይል ተልእኮቱን ማከናወን አስፈላጊ የሆነውን ያህል ፈተናዎቹንም በጥበብ የሚያልፍና በጎ ዕድሎች የሚፈጥር አካሄድም ያስፈልጋል።

መደበኛና ኢመደበኛ መዋቅሮች፤

በእነዚህ በሁለቱ የመፍትሔ መንገዶች ረገድ ታዲያ መደበኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር በራሱ ሊያስገኝ የሚችላቸውን ውጤቶች የሚወስንብን በዋነኛነት ሁለት ፈተናዎች ይኖሩብናል። መፍትሔዎቹንም ከእነዚያው ጋር ማኖር ይቻላል። 

መደበኛ መዋቅር የምንለው ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ የቅዱስ ፓትርያርክ ጽ/ቤት፥ የቋሚ ሲኖዶስ ጽ/ቤትና የመንበረ ፓትርያርክ ጽ/ቤት፣ መምሪያዎች፥ ሌሎች የሥራ ክፍሎች፥ አህጉረ ስብከት፥ የክፍለ ከተማ ጽ/ቤቶችና አጥቢያዎች እንዲሁም ማናቸውም መሰል/አከል ጊዜያዊና ቋሚ የተግባር ቡድኖች ናቸው። 

ኢመደበኛ የምንላቸው ደግሞ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ይህ መዋቅር ውጪ ባሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ወገኖች በግለሰብም ሆነ በተደራጀ መንገድ በተነሣሽነት የሚከናወኑ የማኅበራት አገልግሎቶች፥ የማኅበረሰብ ድረ ገጽ የግልና ያልተዋቀሩ አካላት ጥረቶች፥ የምእመናንም ሆነ የካህናት፥ የምሩቃን ወይም የሌሎች ማናቸውም አገልጋዮች ጥምረቶች፥ የወጣቶችና የሌሎች ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጥምረቶች ሌሎችም ከመዋቅር ውጪ በራስ አመራር (በመጠነኛ ወይም ምንም ቁጥጥር) ተግባራቸውን የሚያከናውናው የመደበኛ መዋቅር ከልካይነት የሌላቸው/የሚያንሳቸው ነጻ አካላት ናቸው። 

ችግር ሲለይ፤

ፈተና 1፡ የመደበኛ መዋቅር ተፈጥሯዊ ውሱንነት፤
መፍትሔ 1፡ ዓሣን በብልሀት መብላት ምንም ካለመብላት/በረሃብ ከመሞት …።

አንደኛው የመደበኛ መዋቅር የራሱ ውሱንነቶች ናቸው። መደበኛ መዋቅር በተለምዶ ተቋማዊ ቀጣይነትን አስጠብቆ ከመሄድ ያለፈ ሚና በግድ ባይሰጠው በብዙ የመርሕም ሆነ የነባራዊ ሁኔታ ምክንያቶች ተመራጭ ይሆናል። በዚህም የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር የቤተ ክርስቲያኒቱን ስብእና አስጠብቆ እንዲቀጥል ከሆነ በቂ መሆን ይኖርበታል። ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንደ ቤተ ክርስቲያን አለች እንዲባል፤ ተደማጭ እንድትሆን፤ እንደ አንዲት ብሔራዊት ታሪካዊት ሰፊ ሕዝባዊ መሠረት ያላት አካል መኖሯንና የሐዋርያት አገልግሎትን ለማገልገል የሚያስፈልጋት “የመኖር ሁኔታ” ካሟላላት በቂ መሆን ይገባዋል። ከዚህ ባለፈ ግን መደበኛ መዋቅር ከለውጦች ጋር እኩል ራሱን እያሳደገ ትልልቅ ግቦችን ቢያሳካ ደግ! ባያሳካ ግን ምን ልትል ነው የሚለው ነው የኔ ጥያቄ። ማደግ የሚችለውን ያህል እንዲያድግ እንፍቀድለት፤ እንትጋለትም። ግን ሳያድግ ሲቀር ጣት መቀሰሪያና መዘበቻ እያደረጉ ሥራ መፍታት ሁላችንንም ስንኩል ያደርገናል። መሥራት የሚችልና የሚገባው ትውልድ የመዋቅሩን ደካማ ጎን ሲተችና ትንተና ሲሰጥበት በምሬትና በመታከት ብቻ ዘመን ቀድሞናል፤ እንዳይደርበን ያሰጋል። 

ብዙዎች ምሳሌ የሚያደርጓት የሮም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን ተቋማዊ ጥንካሬ የፈጠረው ብዙውን እጅ ከውስጣዊ መዋቅሯ ጀምሮ ሳይሆን ቀድሞ የዳበረው ኢመደበኛ ተነሣሽነቶች (Informal Initiatives) ናቸው። ኢመደበኛ መዋቅሩ የተለያዩ ሚሽኖችን (ተልእኮዎችን) ዓላማ አድርገው በሚያነግቡ የምግባረ ሠናይ፥ የትምህርተ ወንጌልና ዕቅበተ እምነት፥ የማኅበረሰብ ጤና፥ የትምህርት፥ የማኅበረሰብ መሠረተ ልማት፥ ሌሎችም (በተለይ ከአውሮፓ ተሐድሶ ጀምሮ ብዙ አማኝ በገፍ ማጣት ስትጀምር በሌሎች ክፍላተ ዓለም ለማካካስ በተነሣችበት ጊዜ ያነገበቻቸው እነሆ ዛሬም አላወረደቻቸውም)፡፡ እነዚህ ተልእኮዎች ብዙዎቹ ዛሬ እኛ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሚያስኮንነን መልኩ ከመደበኛ መዋቅሩ ብቻ እየጠበቅን ስናጣው የምንደነፋበት ተግባራት ሁሉ እዚያ ሲጎለብት ይሄው የኢመደበኛ መዋቅር ጥንካሬውን ወደ መደበኛው መዋቅር ያጋባበታል። ያን ጊዜ የምንመለከተው የቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጣዊ መዋቅር ጥንካሬ የተገኘው በዚህ ነው። ለማስታወስ ያህል አገራችን ውስጥ ግድንግድ “የመዝሙር ኮንሰርት” የሚያዘጋጀውና ቦሌና ዐራት ኪሎ ላይ ያበደ ቢልቦርድ የሚሰቅለው የሆነ ብሔራዊ ወይም ዓለማቀፋዊ ቸርች ወይም የፕሮቴስታንት ሲኖዶስ ወይም ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት እንዳይመስልህ፡፡ ከእነጌትሽ ሠፈር ዝቅ ብለህ ባለው ኬር መንገድ ወደ ግራ ቀጥ ብለህ ስትገባ መንደሩ ውስጥ ቆርቆሮና ኬሻ ወጥሮ ትንቢት መናገር የጀመረው “የዝጋቤር ሰው ነቢዩ ቢዶ ክጶ” ነው፤ ሎል፡፡ ይቅርታ ወጣት ቢዶ ክጶ ላሰበው የትንቢት ሥራ እንዲረዳው ስሙን በይፋ በጋዜጣ አስቀይሮ አሁን ነቢዩ ጳውሎስ ዘኢየሱስ ነው የሚባለው (ሕገ መንግሥት የፈቀደለት መብቱ ነው አክብርለት፤ የአባቱን ስም ግን አላልኩም፤ ያው እሷ ትንሽ ዳኛውን በግራ አስመስለህ በቀኝ መሸልቀቅ ትጠይቃለች፤ የተወሰነ ሌባ፣ መናጢ፣ ዐይኑን በጨው አጥቦ ፍጥጥ ብሎ በሐሰት የሚመሰክርልህ ከሃዲ ምስክር ይጠይቅሃል)፡፡ ለማንኛውም ምናገባኝ ልልህ የፈለኩት፣ ስቴድዮም ሞልቶ ኮንሰርት ለማዘጋጀት የሚያስፈልገው የፕሮቴስታንት አዘጋጅ ደሳሳ አዳራሽ ያለው ሞራላም ፓስተር ነው፡፡ 

መደበኛ መዋቅር ቢሮክራቲክ ተቋም ስለሆነ ቢሮክራሲን በሩቲንነት (በእለት የድግግሞሽ ግብርነት) ከማከናወን ባለፈ ዕቅበተ እምነትን ተከታትሎ እንዲያደርግ፥ ማኅበረሰባዊ ችግሮችን ጠልቆ እንዲፈታ፥ በብዙ በጀት፥ ሞያና ስልት የሚተገበሩ የሰው ኃይል፥ የክህሎትና መሰል ተቋማዊ ውሱንነቶችን እንዲቀርፍ ያን ያህል ጠንካራ የቤት ሥራ በራሱ ያሳካል ብለን ባናስታጥቀው ከምናስታጥቀው ይልቅ እጅግ ጥሩ ይሆናል። 

ቤተ ክርስቲያን የሰፈር ዕድር፣ ወይም የትንሽ መንደር አደረጃጀት አይደለችም፡፡ ብሔራዊት፥ ብሎም ዓለም አቀፋዊት ስለሆነች የመዋቅሯ ወሰንም ያንኑ የሚያካልል ነው፡፡ መሥራት የሚጠበቅባት እያንዳንዱ ተግባርም ብሔራዊነት ወይም ዓለም አቀፋዊነት ዕዳ አለበት። ይህ ማለት አንዲት ትንሽ ተግባር በሚጢጥዬ መዶሻ ኩርንችት መምታት ቢሆን እንኳ ቤተ ክርስቲያን እንድትሠራው የሚጠበቅ ዓይነት ከሆነ በሀገር አቀፍ ወይም በዓለም አቀፍ ደረጃ መሠራት የሚገባት ትሆናለችና በአንድ ጊዜ ቀላሏ ተግባር ውስብስብ መዋቅርን እንኳ የምታስደነብር ወደ መሆን ታድጋለች፡፡ ይህ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንተዋትና የትኛው ሀገር በቀል፣ መንግሥታዊ ይሁን መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ወይም አካል ነው ከኢትዮጵያ ምድር መንጭቶ፣ ከብሔራዊነት አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬታማ ተጽእኖ አድራሽ ወደ መሆን ደረጃ ከፍ ያለ ህልውና ያለው ስንል ዝቅተኛ ነው። ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መደበኛ መዋቅሯ እንዲሆን የምንፈልገውና የምንመኘው ቫይታሊቲ ላይ በምትሐት እንዲደርስ (አንዳንዱ ካሜሮን ሄዳ መስበክ አለባት .. ጊኒ ኮናክሬን ታጥምቅ፣ ኒጀርን ኦርቶዶክስ ታድርግ ቅብርጥሶ ሲል ስለምሰማ ነው…) ከኢትዮጵያ አፈር መንጭቶ እንዲህ ዓይነት ፓዮኒር የሆነ ተግባር ማሳካት የቻለ ሌላ ምን ምሳሌ ተቋም አለና ነው፤ (ዝም ብለን የኢትዮጵያ አየር መንገድን እንየው፡ ብዙ ፕሪሲሽን በሚጠይቅ ቴክኖሎጂ ኢንቴንሲቭ ዘርፍ ውስጥ እየሠራ በውጪ ሀገር ሞያና ስልት ተፀንሶ ከግማሽ ክ/ዘ በላይ ካገለገለ በኋላ እንኳ ምንም ጥሩ ደረጃ ደርሶ ቢታይም ከእነዚህ ሁኔታዎች አንጻር ግን ያን ያህልም ሆኖ ሊታየን ይገባል።)

የዓለም የተለያዩ አገራት መንግሥታት ሲቪል ሰርቪስ መዋቅራቸውን በአንዳንድ ለአገር በሚያስፈልጉ ተግባራት ላይ ሊያምኑት ካለመቻላቸው የተነሣ ለፕራይቬት ሴክተር ጉልሕ ድርሻ ሰጥተው የመቆጣጠር ኃላፊነት ብቻ ወስደው ብዙውን ፍላጎት በእጅ አዙር ያሳካሉ፡፡ ብዙውን አገር ብንመለከት ከመንግሥታዊ መዋቅር ይልቅ የአገሪቱ ሕይወት ላይ ጉልሕ ተጽእኖ የሚይዘው ፕራይቬት ሴክተር ነው፡፡ መንግሥት እንደ ማእከላዊ መዋቅር ሀገር መምራትን እንኳ ባልሠለጠኑ አሳፋሪ ዛዛቴያም ቢሮክራሲዎች እየከወነ ገና ከፕራይቬት ሴክተር የሚጠበቀው ፕሮአክቲቪቲ ኢኮኖሚ ውስጥ ሊኖረው ይገባል ብለህ ካሰብክ ሂድና ሰው ሳይሰማህ ብቻህን ተጃጃል፡፡ ስለዚህ አንዳንዴ ቤተ ክርስቲያንን ተዋትና በመንግሥት ደረጃ እንኳን ከመደበኛ ተቋም አደረጃጀት የምንጠብቀው ግብ ድጋሚ ድግምጋሚ መፈተሸ አለበት።

ፈተና 2፡ የመደበኛ መዋቅሩ አንቀሳቃሾች ማንነት የፈጠረው ውሱንነት፤
መፍትሔ 2፡ የኢመደበኛ መዋቅርን ፖቴንሻል ተሳታፊዎች አቅም እስከመጨረሻው አሟጦ መጠቀም።

ሁለተኛ ደግሞ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን መደበኛ መዋቅሩ ላይ በብዛት አንቀሳቃሾች ሆነው የተሰየሙት መደበኛ መዋቅርን ስኬታማ ለማድረግ ከሚያስፈልግ ሞያና ክህሎት አንጻር እነማን ናቸው የሚለው ነው። ብዙዎቹ ካህናት፥ መነኮሳት፥ የወንጌል ሰባኪዎች ዋነኛ ሥልጠናና ትምህርታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ ትውፊታዊ የአብነት ትምህርት ዘርፍ የሆነ ነው። ሌላ ትምህርት ካላቸው ያልተወሳሰበ የሆነ ዲፕሎም ምናምን ነው፤ የጥቂቶቹን ላይገልጽ ይችላል፡፡ የተወሳሰበ የአስተዳደር ሥራ ሥልጠና፥ ሞያዊ ክህሎት ወዘተ. ኖሯቸው የተሰየሙ አይደሉም። በአርእስትነት የምንጠቅሳቸው የየዘርፉ አርእስት (ብፁዓን አበው) በየመምሪያዎቹ የተሴሙ መነኮሳት (ቆሞሳት ጭምር)፥ ቀሳውስትና መምህራን የአስተዳደር ስብእናቸው በበቂ ሁኔታ ለምንመኘው ሥራ በሚሆን መልኩ የተገነባ ነው ወይ ብለን እንጠይቅ። 

ዛሬ እጅግ የተወሳሰበና የናረ የ21ኛ ክ/ዘ መዋቅራዊ አደረጃጀት ላይ አንቀሳቃሽ የሆኑት ሰዎች የጉብዝና ጊዜያቸውን ቁምጣ ለብሰው፥ አጎዛ ጎዝጉዘው፥ ደበሎ ለብሰው፥ በውርጭና ረሞጫ ባዶ እግር በሙጀሌ ፍርሐት እየዞሩ በበእንተ ስማ ለማርያም ኮፋዳ ሞልተው የሚበሉ የነበሩ ምስኪኖች ነበሩ። በእንደዚያ ዓይነት እጅግ ሲምፕል እጅግም ሀምብል በሆነ ላይፍ ስታይል ውስጥ ተቀርጸው ወጥተው ዛሬ እጅግ ሶፊስቲኬትድ የሆነ፥ የናረ የከረረ የሥራ አመራር ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ አደረጃጀት ላይ በወሳኝ አካልነት ይቀመጣሉ፤ ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ምሕዳር ያለው ሥራ ሊመሩ ነው እንግዲህ። ዳዊት እየደገሙ፥ እንግዳ እየተቀበሉ፣ ንፍሮ እያነፈሩ መኖር የሚያምርባቸው አብርሃማውያን የፖለቲከኛና የካድሬ የሚመስል የቢሮ ሥራ ላይ ውጤት ተጠብቆባቸዋል። አይመደቡ ማለቴ አይደለም፤ የሆነ ሰው ደግሞ እረኛው ዳዊት፣ ዳኛው ሙሴ ምናምን እያለ በሎጂክ ሊረታኝ የሚሟሟት አድርቅም ስላለ፡፡ ግን ምናልባት ምን ድረስ ውጤት እንጠብቅባቸው የሚለውንስ መወሰን የለብንም ወይ የእኔ ጥያቄ ነው፡፡ የሚታየው የሚና መዘበራረቅ ከፍተኛ ነው። ብዙው የተማረና ሥራ ሲመራ የሚያምርበት ሰው ያለው ከመደበኛ መዋቅሩ ውጪ በሕዝቡ መካከል ነው። ስለዚህ ከመደበኛ መዋቅሩ የምንጠብቅበት ሊሳካ የሚገባው ግብ ድጋሚ ተፈትሾ አማራጩ በሌላኛው ጎራ ሊፈለግ ይገባዋል።

ምን ይደረግ፤

ከዚህ ይልቅ ኢመደበኛ ተቋማትን በኢመደበኛ ተነሣሽነት በየአገልግሎት ዘርፉ እያዋቀሩ ከመደበኛ መዋቅር ውጪ ያሉ አገልጋዮች፥ ምእመናንና ማኅበረሰቦች አለኝ የሚሉትን እንዲሠዉለት ማድረግ ውጤት ያስገኛል። ኢመደበኛ መዋቅር ፖቴንሻሊ ሊሳተፉበት የሚችሉ 65 ሚልዮን ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሳውያን አሉት። መደበኛውን መዋቅር እያንቀሳቀሱ ያሉት ቁጥራቸውም ትንሽ ነው፤ ሊያሳትፍ የሚችለውም ብዛት ያንኑ ያህል ነው። ያንን ሁሉ ሕዝባዊ መሠረት ጥቅም ላይ ለማዋልና ለሆነ ዓይነት ግብ ለመበየን የግዴታ ከመደበኛ መዋቅሩ ውጪ ይህን ሪሶርስ ጥቅም ላይ ሊያውሉ የሚችሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢመደበኛ መዋቅራዊ ተነሣሽነቶች በየቦታው ያስፈልጋሉ። በሌላ አባባል ሕዝቡና ከመደበኛ መዋቅር ውጪ ያለው አገልጋይ ወደ ትክክለኛ ሥራ መግባት አለበት። በዚህም ሁሉም በየፊናው አፈራበታለሁ በሚለው ሁሉ ኃይሉን እያስተባበረ የቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ዘርፎች ላይ በሙሉ ቢዘምትበት ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደ ቤተ ክርስቲያን መድረስ የምትችልበት የማኅበረሰብ የሕይወት ገጽታ በጣም ይበራከታል። ለዚህ የሁሉም ነገር መማከል አለበት አስተሳሰባችን ትንሽ ብርጭቆ ወረቀት ሄድ ሊልበት ይገባል ባይ ነኝ፡፡

ቤተ ክርስቲያን ለምን አትረዳቸውም የሚባሉ ሕፃናትና አረጋውያንን ራሱ መርዳት የሚችልበትና ቤተ ክርስቲያንን የማይጠብቅበት፤ ጣቱን የማይቀስርበት፥ ቤተ ክርስቲያን ለምን አትሰብክም አታስተምርም በሚልበት ጠረፋማና ሩቅ ሥፍራዎች ሁሉ የራሱ ሚጢጢ አቅም ከብጤዎቹ ጋር ተደምራ መምህራንን ማድረስ የሚችልበት፥ ቤተ ክርስቲያን ለምን አታማክርም ብሎ በሚወቅስበት የማኅበረሰብ ግንባታ ዘርፍ ራሱ ያንን ማድረግ የሚችልበት በቂ ፕላትፎርም በኢመደበኛ መዋቅራዊ ተነሣሽነት ብቻ ሊሳካ የሚችል ስለሆነ ይህን ካሳካን ቤተ ክርስቲያን ቤዛ የማትሆንበት ምንም የቤዛነት መሥመር አይኖም፤ የማይደረስበትም ገጽታዋም አይኖርም። ቤተ ክርስቲያን ለማኅበረሰብ ልትደርስለት በምትችልበት መሥመር ሁሉ ማካለል የሚቻለው በመደበኛ መዋቅር ብቻ ነው ወይም መሆን ይቻላል ብሎ የሚያምን ሰው በዚህ ሰዓት የቤተ ክርስቲያን ጠላት ነው። 

ብዙ ይህን መቅረፍ የሚችሉ መምህራን በታናናሽ መጽሐፍ የመጻፍ፥ መጽሐፍ የማረት፥ ፌስቡክ ላይ የመጻፍ፥ አለፍ ካለ የሆነ መቂና ሻሸመኔ ደርሶ ወዲያው የመመለስን የመራጠብ ማራጠብ ተግባር እንደ ሐዋርያነት ግልግሎት አጋንነው ይጽናኑበታል። ይሄ ሁሉ ትልልቅ መምህር ወደ ሥራ መግባት አለበት። ቢያንስ እርሾ ሆኖ ኢመደበኛ ተነሣሽነቶች እንዲፈለፈሉ መንሥኤ መሆን አለበት፤ ይሄንንም ተጣምሮ ማሳካት አለበት።

ከዚህ ባሻገር ከሥር እንደምንመለከተው ጠልተን ዝም ብንለውና ባንፈልገውም እንኳ ይሄ ኢመደበኛ የሆነ መዋቅር ኦሬዲ እየፈላ መጥቷል፤ ይህም መርሕ ባላስቀመጥንለትና አገዛዙን ባላወቅንበት ዐውድ ውስጥ እየተፈጠረ ያለ ስለሆነ ዝም ካልነው በኋላ ለመቆጣጠርም ያዳግተናል። አሁኑኑ ቅድሚያ ወስደን ራሳችን መልክና ምሳሌ ሰጥተን ካልፈጠርነውና በሚፈለግ የመርሕ መንገድ እያስኬድን ባሕሉን ካልሰጠነው ኋላ ያስከፋናል። ስለዚህ ብንወድም ባንወድም ኢመደበኛ መዋቅራዊ ተነሣሽነቶችን እየተፈጠሩ ስለሆነ ጥያቄው እንዴት አቅጣጫ እናስይዛቸው የሚለው ነው።

አሁን ምን ምን አለን፤

አሁን ባለው ሰዓት ከበቂ እጅግ በጣም በታች የሆኑ ቢሆኑም ወቅታዊ ችግር እየፈቱ ዘላቂ መፍትሔ መሆንም የሚችሉ አንዳንድ ተነሣሽነቶች ይስተዋላሉ። በማኅበረ ቅዱሳን በኩል ለአንድ ተቋም/ተነሣሽነት ከአቅም በላይ ተብለው ሊወሰዱ በሚችል መልኩ የተንዛዙ ዓላማዎችና ተግባራት የታጨቁበት ትልቅ ተነሣሽነት አለ። ሚድያውም ላይ፥ አብነት ትምህርት ቤቱም ላይ፥ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ላይ፥ ሰንበት ትምህርት ቤትም ላይ፥ ጉዞም ላይ፥ ባዛሩም ላይ፣ ኅትመቱም ላይ፥ ሬድዮውም ላይ ወዘተ. እረም ብሎ ሠፍሮበታል። ማኅበሩ ይህን ማድረጉ አያስነቅፈውም ባይ ነኝ። የሚሠራው እስከሌለ ድረስ የቻለው ሁሉ ላይ እየገባ የመክሊቱን ፍሬ ለማየት ከጸሎት ጋር መጣሩ ያስመሰግነዋል። ደግ ቀን እስኪመጣ ድረስ ይቀጥል። ሌሎችም ተነሣሽነቶች በእነዚህ በጫካ መንጣሪው በፈተና ተለይተው በታወቁ የአገልግሎት ዘይቤዎች ላይ እያንዳንዳቸው ውጤታማ ሆነው ለመንቀሳቀስ ኃይላቸውን ቢያስተባብሩ መልካም ነው። 

ሌላው የደጆችሽ አይዘጉ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ከፈታ እና የካህናት/አገልጋዮች ሥልጠና ነው። ይህ በዚህ ጨዋታዬ መልእክት ውስጥ እንደ ሞዴል የሚሆነን ተነሣሽነት ነው፤ ግልጽ፣ ውሱን ዓላማ ያለው ሥራነቱ ግን ሰፊና ጠቃሚ። የጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብር አስጠባቂና የመብቷ ተሟጋች፥ ወልዳ አፋረዋ ኦሮሞ፥ ወልዳ አቦቲ፥ ወዘተ. እንዲሁ ጊዜው ራሱ እያመጣቸው ያሉ ዓይነተኞች ተነሣሽነቶች ናቸው። ሰሜን አሜሪካና ሌሎች ቦታዎች ላይ በሌሎች ቋንቋዎች የሚተገበሩ ለአብነት እንኳ እንደ ዋይ. ኦ. ቲ. ሲ. እና ዩ. ኦ. ዋይ. ሲ. ሌላም ቦታ ሌሎችም ተልእኮዎችን እየተመለከትን ነው፤ ያለምልምልን። እንደ ዘመድኩን በቀለ ዓይነት ስብእናዎች እያንቀሳቀሱት ያለው ሌላ ኢመደበኛ ተነሣሽነት ግራ በሚያጋባ መሥመር ተስፋ የሚያጭር እንቅስቃሴ እያደረገ ያለ፥ እንዳንኮንነው ውጤትና ፖቴንሻል በግልጽ እያሳየ የነፈዘውን እየተኮሰ እያስነሣ ያለ፤ እንዳንሰግድለት መጨረሻው በአጭር ጊዜ ውስጥ የማይታወቅ የሆነም አለ። እንዲህ ዓይነቱ ተነሣሽነት የፕሮስ ኤንድ ኮንስ አናሊሲስ ላይ አጥርቶ ለማየት ለሚሞክር ያግዛል። እዚህ ጨዋታ ላይ ግን ጉልሕ ድርሻ እንዲህ ዓይነቱም ተነሣሽነት ይኖረዋል፤ ሐቅ ነው - እንዋጠው። 

የሚያስፈልጉን ምን ምን ናቸው፤

ስለዚህ ከላይ የለየናቸው ተጠናክረው በውጤታማነት አቅጣጫ እየዳበሩ በቀጣይ ግን የቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ተልእኮዋ እየተጠናና ወቅታዊ ፈተናዎቿ ከግምት እየገቡ ብዙ የአገልግሎት ኢመደበኛ ተነሣሽነቶች መከናወን ይችላሉ። ሁላችንም ዝንባሌያችን ወደመራን፥ መክሊታችን ወደሳበንና ፈቃደ እግዚአብሔር ወዳገበረን እየተሳብን ከምናከናውናቸው መሃል ለምሳሌ ያህል፡ 

- ዐራት አምስት ሰዎች ሥራዬ ብለው የሚያንቀሳቅሱትና ሁላችንም በየጊዜው የምንሳተፍበት ሕዝብ የእኔ የሚለው ብዙዎች የሚያደምጡት በሞባየል አፕ ወይም በሌላ ቀላል መንገድ የሚገኝ የዕቅበተ እምነትና ስብከተ ወንጌል የሬድዮ ፖድካስት (በፈጠረህ 24 ሰዓት እንዳትለኝ፤ አያስፈልግም - የተወሰነች ቅልብጭ ያለች)፤
- ዕቅበተ እምነትና ስብከተ ወንጌል ብቸኛ ሥራው የሆነ የቴሌቭዥን ኔትዎርክ፤ እንደቤታችንና እንደ እረፍት ቀናችን አድርገን የምንወደው ሰላማችን የሆነ፤
- ጠንካራ የስብከተ ወንጌልና ዕቅበተ እምነት ተነሣሽነቶች፤ (ሌሎች ልዩ ልዩ አንጻሮች የተከተሉ - ስታስብ ጠይቀኝ እነግርሃለሁ፤ አለሁበትም)
- ወደርትዕት ሃይማኖት የመልስ ጉዞ የሚያመቻች ኔትዎርክ፤ (ከጆቫ እምነት የመጣ አንድ ሰው ከሥራ፣ ከቤተሰብም ተባረረ፤ በአንድ ጊዜ ወዳጁም ቤተሰቡም ማርያም ሆነች፤ ሰው ስላልነበረው ግን በጣም ተጎዳ፡፡ አየህ ይህ ተነሣሽነት ፈጥረነው ቢሆን ኖሮ እጅ አስተባብሮ ጥቂት ማቆያ የኪስ ገንዘብ፣ ሥራ እስከማፈላለግ፣ ማቋቋም፣ የምክር አገልግሎት ወዘተ. መስጠት ችለን ነበር፡፡ እምነት ቀይሮ ወደ ኦርቶዶክስ መምጣት ዝም ብለህ የማሕተብና የነጠላ ነገር ብቻ አታድርገው፤ ዘርፈ ብዙ ማኅበረሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነ ልቡናዊና ሌላም ፋክተሮች ይዞ ይመጣል፡፡ ማን ይጨነቅበት፤)
- የሥነ ጾታ፥ የጋብቻና ቤተሰብ ትምህርትን ተጠቅሞ ማኅበረሰብን የሚደግፍ (ዝሙት በዝቷል፣ ጋብቻ ቀልሏል፤ ይህ እንደማኅበረሰብ የመጥፋት ምልክት ነው፡፡ በተለይ ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከዚህ በላይ መርዶ የላትም፤ ተራክቦ ድጋሚ ሊፈታለት ይገባል ለዚህ ትውልድ፡፡ ጋብቻ እንደ አዲስ ሊተረጎምለት ይገባል፡፡ ተራክቦ ቅድስናው ካልተጠበቀ፣ ጋብቻ በክብሩ ካልተያዘ ቤተሰብ ይታወካል ማኅበረሰብ ይፈርሳል፣ ሀገር ላይታወስ ይረሳል፤)
- የሕፃናትና የሴቶች ድጋፍ አገልግሎት ተነሣሽነቶች (በአጭር ቋንቋ በዚህ ኦርቶዶክሳውያን ልንታማ አይገባም ነበር፤ አዝናለሁ፡፡)
- ለቤተሰብ ደኅንነት፥ ለማኅበረሰብ ጤንነትና ለሰብአዊ ዋስትና መሠረት የሆኑ የክርስቲያናዊ ግብረ ገብነት ጉዳዮ ተነሣሽነት (በምዕራቡ ኣለም ፕሮላይፍ፥ ፀረሰዶም ወዘተ. የተለመዱ ናቸው፤ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም በዚህ የምትፈተንበት ዘመን ላይ ነን፤)
- የልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተደራሾችን በየቦታቸው ግብ ያደረገ የስብከተ ወንጌል ሐዋርያዊ አገልግሎት፤
- አፍሪካውያንን ለኦርቶዶክሳዊነት የሚያበቃ ሐዋርያዊ ተልእኮት፤
- የትምህርት ቤት፥ የጤናና የውኃ መሠረተ ልማቶችን በተለይ ችግር ባለባቸው የሚያስፋፋ ተነሣሽነት፤ 
- የሞያ አጠቃቀምን አቅዶ የሚተገብር ግብረ ሠናይ (ኦርቶዶክሳውያን በሞያቸው ዐሥራት ማውጣት ቢፈልጉስ፤ ለምሳሌ ቤተ ክርስቲያኒቱ ደሀ በነጻ/በሰበካ ጉባኤ አባልነት መታወቂያ ብቻ የሚታከምበት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ብትገነባ ኦርቶዶክሳውያን የጤና ባለሞያዎች በሞያቸው በዓመት /ለ3 ቀን/ ፕሮቦኖ አገልግሎት በነጻ እንደ ዐሥራት የሚሰጡበትን ሁኔታ የሚያስተባብር ሕዝባዊ ተቋም ቢኖር አገልግሎቱ በማኅበረሰብ ውስጥ ውጤታማ ይሆናል ቤተ ክርስቲያኒቱም ትታይበታለች፤ ይህ ለሕግ፣ ለአርክቴክቸር ወዘተ. ሞያም ይሆናል) 
- ጠንካራ የሊደርሺፕና የሞያ ማኅበረሰብ (ቤተ ክርስቲያን ለካህናቷ፣ ለአገልጋዮቿም ሆነ ለአማኞች የሚያስፈልጋትን በሥልጠና ሊገኝና ሊዳብር የሚችል የሕይወት ክህሎትና የስብእና ማጎልበቻ ሥልጠናና ማብቂያ የሚሰጥ አግረሲቭ የሞያ ማኅበረሰብ/ተቋም፡፡ ፍሬንድ ብዙ ቤተ እምነት ሃይማኖቱን ትተው ሞቲቬሽን እያስተማሩ ነው ስብሰባ ያደሩት)፤ 
- የጥናትና ዲቨሎፕመንት ተቋም፥ በየዘርፍ ልዩ የሆኑ (ስፔሻላይዝድ) የልሕቀት ማዕከላት፤
- የቴዎሎጂ ኢንስቲትዩት፥ ሴሚነሪ፥ ኮሌጅ፥ ዩኒቨርሲቲ፥ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት ወዘተ.፤
- የቤተ መጻሕፍትና መዘክር አገልግሎት፤ (የመጻሕፍትና የቅርሶቹ እመቤት ቤተ ክርስቲያን በዓለም አንደኛ የሆነ ተቋም ይገባት ነበር፤ ተኛህ እንጂ)
- ሰፊ የማኅበረሰብ ድረ ገጽ (የዩቲዩብ)፣ የሌሎችም ማካነተ ድር የስብከተ ወንጌልና ዕቅበተ እምነት ግላዊና ተቋማዊ ተነሣሽነቶች፤

ማን ምን ያድርግ፤

አንደኛ መደበኛው መዋቅር የኢመደበኛ መዋቅርን አስፈላጊነት እንዲረዳው፥ ውሱንነቶቹን እንዲተነብየውና አስተዳደሩን እንዲዘጋጅበት ማድረግ። መደበኛው መዋቅር ኢመደበኛ መዋቅሮች መኖራቸውን ተገንዝቦ ሊያስተናግዳቸውና አቅማቸውን ሊጠቀምበት በሚችል መልኩ ራሱን ዝግጁ አድርጎ መጠበቅ፤ ቢቻል ኢመደበኛ መዋቅራዊ ተነሣሽነቶችን ሞደል ሆነው በሚተከሉበት አጀማመር ራሱ ማስጀመርና መስደድ፤

ሁለተኛ አሁን የሚገኙ ከላይ የጠቀስናቸውና ያልተጠቀሱ ሌሎች ተነሣሽነቶች ሌሎችን አዳዲሶች መቀበል፥ ማበርታት፥ በሚቋቋሙበት መጠን ማጠንከርና መርዳት፥ ግብአት መስጠት፤

ሦስተኛ ታዋቂ የቤተ ክርስቲያኒቱ መምህራንና ግለሰቦች ከመስበክ፥ ከመጻፍ፥ ከመምከርና ከአነስተኛ እጅን የሚፈትኑ ተግባሮቻቸው አልፈው እንዲህ ዓይነት ኢመደበኛ ተነሣሽነቶች እንዲያቆጠቁጡና ያሉት ፈር እንዲይዙ ከሚሰሟቸው ሰዎች ሁሉ ጋር መሥራት ይጀምሩ፤

ዐራተኛ ሁሉም አማኝና አገልጋይ በኢመደበኛ መዋቅሮች ውስጥ መርጦ እየገባ ለቤተ ክርስቲያን ክብርና ለተልእኮቷ መሳካት የበኩሉን አስተዋጽዖ ማበርከት እንደሚገባው መረዳትና ባሕሉን እያዳበሩ መቆየት፤ ጠንክሮ መሳተፍ።

በዚህ ሂደት ውስጥ የሚድያ ተነሣሽነቶቹ ፊት ይሠለፋሉ፥ የትምህርትና ልሕቀት ተነሣሽነቶች ይከተላሉ። እነዚህ ሁለቱ ሌሎችን በማበርታትና በማብዛት ሥራ ብዙዎችን ይፈጥራሉ። በአጭር ጊዜም ባሕሉ ይዳብርና ቤተ ክርስቲያን ምስጉን ትሆናለች። አስተውሉ አሁንኮ በግድ ነው ቤተ ክርስቲያን የሚገባትን ታሪካዊ ዋጋ እንኳን ሀገሪቱ ውስጥ በግድ እያሰጠን ያለነው (ትምህርት ሚኒስቴር ነበረች፥ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ነበረች እያልን፤) ዛሬ እየሠራነው እናሳይ እንጂ፤ እንዴኤኤኤኤ! የለህምኮ ማኅበረሰቡ ውስጥ! ማኅበረሰቡ ብቻውን ነው ማኅበረሰባዊ አረንቋው ውስጥ እየተድፈጠፈጠ ያለው። በሱስ ተወርሮ ዝቅጥ ያለ ስብእና የያዘ ወጣት ስታይ ከመታዘብና ስም ከመስጠት ያለፈ ሚና የለህም፤ ዝሙት ተስፋፍቶ ሰው ሲዋረድ ከማየት ያለፈ ምንም አላመጣህም፤ የቤተሰብ ጤንነት፥ የማኅበረሰብ ዋስትና አደጋ ላይ ሲወድቅ ዝም! ድሀ የሚበላው አጥቶ ሆዱን ቋጥሮ ሲያድር ምንም! እለት የከበደበት ሕዝብ ይዘህ፣ ሕሊና ተጨንቆ አሲድ ማመንጨት ድረስ የተጨነቀበት ሕዝብ ይዘህ፣ ችግር ኦርቶዶክሳዊ ወገንህን እያሳደደ ሲያድነው ዝም! በዚህ መሐል ሊጠቀሙበት የሚፈልጉ ዱርዬ የአዳራሽና የቲቪ አርበኞችም አለበት ድረስ እየሄዱ ከየዋሑ ባለማሕተብ ጋር ፎቶ እየተነሡበት ፌስቡክ ላይ ያበሽቁሃል፤ አንተ አይገባህም። የስድብ ምላሽህ እንኳ ምንም አያጽናናም፤ ትምህርት ሚኒስቴር ነበረችኮ ቤተ ክርስቲያን፣ መከላከያ ነበረች እያልክ ትበጠረቅና ጭራሽ ሌላ ጨለማ ሕሊናችን ላይ መጋረድ፤ ምን ያለኸው ነህ አንተ!

መታወቅ ያለበት ፈታኝ ሁኔታ፤

ሁልህም በኢመደበኛ መዋቅር ገብተህ ሥራላት፡፡ በመሠረቱ ኢመደበኛ መዋቅር ባለበት ዐውድ ውስጥ መደበኛ ሆኖ መኖር እንደ መደበኛ ሆነህ ስታስበው ፈታኝ ነው። ሁሉም በመሰለው ስለሚያገለግልና ሁሉም የግዴታ የመደበኛ መዋቅሩን ስጋቶች እኩል ተረድቶ በጤነኛነት ሊሄድ አለመቻሉ ሲታሰብ በራሱ ትልቅ ፈተና ነው። አንዳንዴ ኢመደበኛ መዋቅሮች የመደበኛውን መዋቅር ህልውናም ሊያሰጉ ይችላሉ፤ ሁሌ አያንጹትም። የታዛዥነት መንፈስ ከሌለ ለቁጥጥር የሚያዳግት ሥርዓትም ሊፈጠር ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሁሉም አካል የሚያስፈልገንን ነገር ግብ ያደርገዋል፤ ሁሌ ገንቢ ሚና ብቻ ይጫወታል የሚል የዋሕነትም ሊኖረን አይገባም። ኦርቶዶክሳዊ ትውፊትንና ዘይቤን ጠብቆ መጓዝ ብዙ ድካም የሚጠብቅብን ነገር ሊሆን ይችላል። 

መፍትሔ፤

ሕልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም እንዲባል የኢመደበኛ መዋቅራዊ ተነሣሽነቶችን አቅም ለቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ገንዘብ በሚሆንበት መልኩ ሳንጠቀመው በምንቀርበት ጊዜ ሁሉ የሚተርፈን ዕዳ ብዙ ነው፤ አንችለውምም። አሁን እንኳ ብዙ መፍቀሪያነ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ሰቀቀንና ጭንቀት ስለእናት ቤተ ክርስቲያን እያተረፍን እንገኛለን። ችግሮች መፍለቂያቸው ብዙ ነው፤ እንደ ጭንቁር ልባችንን የሚወጋን ብዙ ነገር አለ፤ ስለቤተ ክርስቲያን የምናየውና የምንሰማው ሁሉ እንቅልፍ አያስተኛም። በአንጻሩ ተስፋ ይሰጠን ዘንድና እንጽናና ዘንድ ልባችንን የምናረጋጋበት የመፍትሔ ምንጭ ስናማትር ይባስ በሚያስደብር ሁኔታ ተስፋችን ይበልጥ ይጨልማል። ከሚፖሰትብን ፖስት ይልቅ ራሳችን የምንኮምተው ኮሜንት አሳፋሪና ውርደታም እየሆነ ተደብረናል፡፡ በአሁን ሰዓት ኦርቶዶክሳዊ መሆን ብዙ የሕሊና ሸክም ይዞ መኖር ነው። በዚህ ሁሉ ሰማዕትነት ውስጥ የምንጸናው ስንቶች እንደሆንን ጌታ ይወቅልን። 

ከላይ የተነሡት የኢመደበኛ መዋቅር ስጋቶች ደግሞ አሁን ዝም ብንልም መምጣታቸው አይቀርም። ከላይ እንዳነሣነው ኢመደበኛ መዋቅሮች ብቅ ብቅ እያሉ ነው። ብቅ ብቅ ማለታቸው ደግሞ አሳዪነቱ ነገ ፈልተው የመሙላታቸውን እውነታ ነው። ዛሬ እንኳ በጣት የሚቆጠሩትንና ትናንሾቹን እናቁማችሁ ብንላቸው ምን ያህል ቀላል ተግባር ይሆን፤ ነገ ድግሞ ባሕሉን ባልፈጠርንበትና ቶኑን ሴት ባላደረግንበት ከባቢ አየር መጥተው ቢዳብሩ ለእኛው አደገኛ መሆናቸው አሁንም ያለ ሐቅ ነው። ይልቅ የሚሻለው ፈጥኖ ብርጭቆውን መሙላት ነው። መጨረሻ ላይ ተጠቃሚ ሊያደርግ ስለሚችል። ይልቅ ጠንካራ ባሕል ፈጥሮ እዚያ ውስጥ የመደበኛ መዋቅሩ ብሂልና ብያኔ ዋጋ የሚያነሣበትን አግባብ አሁን ፈጥሮ መጀመር ይሻላል።

ሕዝቡና አገልጋዩ ቶሎ ወደ ተግባር መግባትና አቅሙ፥ ዕውቀቱ፥ ጊዜው፥ ገንዘቡ ሁሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን ጥቅም መዋል አለበት። በዚህም መደበኛው መዋቅር በጎውን የቤተ ክርስቲያን ፍላጎት አስጠብቆ መጓዝ የሚችልበትን መንገድ ቀምሮ በመዘጋጀት ይተባበር። ሌላህ ግን እያንዳንድህ ጥለቴን መቀነቴን ሳትል፥ ቆረጠኝ ወጋኝ አቁምና ሁለት ሺህ ዓመት ለተሰበከ ወንጌልና እስከ ጌታ ቀን ለሚመሰከር የመንግሥቱ ዜና ዘብ መቆም አለብህ። አለኝ የምትለውን ማገዶ አድርገህ ማግድ፥ ችቦ አድርገህ አቅርብ። መድረክ ላይ ያለህ መምህርና አገልጋይ ሁሉ ይህን መልክ በማስያዝ ረገድ የጎንዮሽ እየተመካከርክ ቶሎ እየወሰንክ፥ የበታች ደግሞ እየመራህና እያስተባበርህ፥ ከዚያም በመንገድ ላይ አንድህ ለአንድህ ገንዘብ እየሆንከው መጓዝ እንጀምር። ብዙ መጽሐፍ ጽፈን፥ ብዙ ሲዲ ሸጠን፥ ብዙ ዐውደ ምሕረት ላይ ፏልለን፥ ብዙ ቤተ መቅደስ አጣበን፥ ብዙ ቢሮ ውስጥ ተወዝፈን ኖረን፥ ብዙ ኪ.ሜ. ኳትነን አሁንም የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን አሳሳቢ ቅርጽ ላይ ነች። ነጻ ዋይፋይ አገኘሁ ብለህ ካሜራ ፊት በፌስቡክ ላይቭ ተገትረህ 1 ሰዓት 1 ሰዓት ከ13 ደቂቃ ስትጮህብን የዘነጋኸው ነገር እሱን ቪዲዮ ለመመልከት 113 የኢት.ብር እንደማይበቃን ነው፡፡ ማንም አያህም ፍሬንድ! 63ቱም ሼሮች ያልከው ስለተሰማ እንዳይመስልህ፤ በቃ የኛ ሰው ዝምብሎም ሼር ያረጋል፡፡ መንገድህን ቀይር። እኔ በበኩሌ እነዚህን ሁሉ ተግባሮች የዳር ተመልካች ሽሙጦች ወይም ደግሞ የሜዳ ዳር ቲቮዞ ጩኸት ብዬ መዝግቤአቸዋለሁ። ከላይ የጠቀስኳቸው ተግባራዊ እርምጃዎች በማኅበረሰባችን ውስጥ ዳብረው ባሕል ሆነው መጓዝ ካልጀመሩ አዎን እነዚህ ብቻቸውን ሲሠሩ ብቻቸውን ስለሆኑ ከድጋፍ ጩኸት ወይም ከሚያደነቁር ትችት ያለፈ ዋጋ የላቸውም። አንባቢዬ ሆይ! እዚህ ጽሑፍ ውስጥ ራስህን የሆነ ቦታ መድበው፤ ሚና ውሰድ፤ እግዚአብሔር ይርዳህ። ማንም ለማንም ዋናውን ሥራ ትቶ እርሱ ዳሩን አይሠራም። ግባና ተምቦራጨቅ።

አስተያየቶች