“ተፈስሒ ኦ መድኃኒታ ለሔዋን” የሔዋን መድኃኒቷ ሆይ ደስ ይበልሽ -- ቅዱስ ኤፍሬም ሦርያዊ


“ተፈስሒ ኦ መድኃኒታ ለሔዋን”
የሔዋን መድኃኒቷ ሆይ ደስ ይበልሽ

“በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘሯም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ” -- ዘፍ.3፥15


ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም ሦርያዊ የአምላክን እናት ማርያምን ሲያመሰግን “የሔዋን መድኃኒቷ ሆይ ደስ ይበልሽ” ይላል። በዚህ አንድ መስመር ነጠላ ንባብ ውስጥ ሁለት ሴቶች አሉ። ደስ ይበልሽ የተባለች እናታችን ማርያም አንዷ ናት። ሌላዋ ደግሞ የሕያዋን እናት ሔዋን ናት። መድኃኒት የተባለች ማርያም አሸናፊ፥ ልዕልና ያላት፥ ለሌላ መትረፍ የምትችል ናት። በአንጻሩ ሔዋን የተሸነፈች፥ ከክብር የተዋረደች፥ ለራሷም መድኃኒት የሚያሻት ናት። ሁለቱም እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የገባቸው ሁለት ኪዳናት ጀማሪዎች ናቸው። በቀደመው ኪዳን ውድቀታችን በሐዲሱ ትንሣኤያችን ስለሆነ እመቤታችንን መድኃኒት አሰኛት።


1.    ሁለቱም ሴቶች መላእክት አናግረዋቸዋል። ወደ ሔዋን የመጣ በመላእክት ዘንድ አለማመንን ያመጣ ሳጥናኤል፥ ወደ እመቤታችን የመጣው ደግሞ በሃይማኖት መላእክትን ያጸና ገብርኤል ነው፤ (ሁለቱ መላእክት ይተዋወቃሉ፤ ተዋግተዋልም። ሳጥናኤል አምላኩን ንቆ በሐሰትና በትዕቢት በመውደቁ፥ ገብርኤል ደግሞ በእውነትና በእምነት በማጽናት በማረጋጋትና ለእግዚአብሔር ቀንቶ በመቆሙ ነው።)


2.   ሁለቱም ወደ ሴቶቹ ሲመጡ ሳጥናኤል ራሱ አስቀድሞ የተዋረደበትን ያለማመንና የትዕቢት ቃል ለሔዋን ይዞ መጣ፤ ገብርኤል ደግሞ በዚያ አጋጣሚ መላእክትን ያረጋጋበትን የጸጥታና የመጽናት፣ የእውነት ቃልን ለእመቤታችን ያመጣ ነው።


3.   ሁለቱም ወደ ሁለቱ ሴቶች እጅግ ታላቅ ቃልን ይዘው ነበር የመጡት። እባቡ ሔዋንን “አምላክ ትሆኛለሽ” ሲላት አብሣሪው መልአክ ደግሞ ማርያምን “ወላዲተ አምላክ/የአምላክ እናት” ትሆኛለሽ ይላት ነበር።


4.   ሁለቱም ወደ ሴቶቹ ሲመጡ ሔዋን ለሚጠይቃት ሁሉ መልስ የምትሰጥ ሞኝ ነበረች፤ ይህ ተፈቅዶልናል፤ ይህን ተከልክለናል እያለች። እናታችን ግን ለሚነገራት ሁሉ ጥብቅ ጥያቄ እየጠየቀች መልስ ትጠብቅ ነበር፤ ምን ዓይነት ሰላምታ ነው? ይህ እንዴት ይሆናል? ወንድ አላውቅም፤ እያለች። በሔዋን እርሱ ጠያቂ እርሷ መላሽ ስትሆን፤ በእመቤታችን ደግሞ እርሷ ጠያቂ፥ እርሱ መላሽ ነበሩ። እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በእውነቱ የነበረችበት ሁኔታ ከሔዋን ይልቅ የሚከብድ ነበር። ምክንያቱም ሔዋን ባትመልስና ዝም ብትል መልካም ነበር፤ አትዋረድም። እናታችን ግን ጸጋን የመላብሽ፥ ደስ ይበልሽ፥ አንቺ ከሴቶች ክብርት ነሽ፤ … እያለ ከፍ ያለ ሰማያዊ ሰላምታ ይሰጣት ነበር እንጂ ጥያቄ አይደለም። ዝም ብትል ግን መልካም አልነበረም። ጥያቄ የሚጠየቅ ሰው መመለስ እና አለመመለስ በእጁ ነው፤ ውዳሴ የሚወደስ ግን ዝም ካለ ከንቱ ይሆንበታል፡፡ እናታችን ውዳሴውን በዝምታ ከመቀበል ይልቅ፥ እንዴት ይሆናል እያለች ጠየቀች። ምን ያክል በእምነት የተሰናዳችና በትሕትና ያጌጠች እናት እንደሆነች ይህ አሳዪ ነው። እባቡ ከጥንትም በትዕቢቱ የሚታወቅና የተጣለ ነውና ሔዋንን ሊያጠቃት የሞክረውም በዚሁ በትዕቢት ነው። እናታችን ማርያም ግን ከሔዋን በላቀ የውጊያ አውድማ ውስጥ ሆና እንኳ በትሕትና ዝቅ በማለቷ ከማሸነፏም በላይ ሔዋን ታደርግ ዘንድ ይገባት የነበረውን ሁሉ በማድረግ ተቤዠቻት/መድኃኒት ሆነቻት።


5.   ሁለቱ ሴቶች የመጣላቸውን ዜና የተቀበሉበት መንገድ እጅጉን ለየቅል ነው። ሔዋን አምላክነትን እጅግ አጥብቃ ፈልጋ ከመቋመጧ የተነሣ ምንም ነገር እንዲያዘገያት እንኳ አልፈቀደችም። ነገሩን በፍጥነት በማከናወን የተባለችውን ለመሆን አሰፈሰፈች። እናታችን ማርያም ደግሞ ነገሩን አጥብቃ ከመመርመሯም ባሻገር መልአኩ በልቧ ትልቅ ሥፍራ የምትሰጠውን የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነት ባስታወሳት ጊዜ ለእግዚአብሔርና ለባሕርዩ እውነትነት ተሸነፈች። እንደ ሔዋን የርሱን ታላቅነት ለራሷ ከመፈለግ በተቃራኒ ታላቅነቱ ሲመሰከርላት ብቻ ፈቅዳ ተረታች። አስተውሉ እንግዲህ! ተሸነፈች ማለት ከቶ ምን ማለት ነው? “የአምላክ እናት ትሆኛለሽ” ያለውን ቃል አምና ተቀበለች ማለት አይደለምን? ነው። የአምላክ እናት መሆንን ከተቀበለች ታዲያ ስለምን ይሆን በመጨረሻ መልአኩን ስትሸኝ “እንደ ቃልህ ይሁንልኝ እኔ የጌታ እናቱ ነኝ” ያላለችበት ምክንያት? ይልቁንም “… እኔ የጌታ ባርያ ነኝ” ብላለችና። የመልአኩን ቃል ከተቀበለች፣ የመውለዷም ነገር እሙን ከሆነ በኋላ እንኳ ራሷን የጌታ እናት ሳይሆን የጌታ ባርያ ብላ ጠርታለች። ዲያብሎስ ከሰማይ የተዋረደበትንና ሔዋንን ጠልፎ የጣለበት ትዕቢት እመቤታችን ጋር በለስ አልቀናውም፤ በትሕትናዋ ተሸነፈ። እግዚአብሔርም ፍጥረትን ሁሉ የሚቤዥ፥ የትንሣኤያችን አበጋዝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደምን ከዚህች ቅድስት ሴት ይገኝ ዘንድ እንዳለው ለዓለም ያረጋግጥ ነበር።


6.   ሔዋን አምላክ ልሁን ብላ ስለቋመጠች ተዋረደች፤ ከመዋረድም በላይ ባልሽ ይግዛሽ ሲላት የጸጉሩን ቀለም እንኳ ሽበት ማድረግ ለማይቻለው ለምስኪኑ ሰው አዳም ተገዢ ባርያ አደረጋት። ብርቱዎችን የሚያዋርድ፥ በልባቸው አሳብ የሚመኩ ትዕቢተኞችን የሚበታትን፥ ባለጠጎችን ባዶ እጃቸውን የሚሰዳቸው ነውና። እናታችን ማርያም ግን ባርያ ነኝ ብላ ስለተዋረደች በርግጥም ወላዲተ አምላክ አደረጋት፤ ስለዚህም ለባርያው በጎ ነገር አድርጓልና ፍጥረት ሁሉ ብጽዕት ይሏታል።


7.   ሔዋን ታናሽ፥ ምስኪን ፍጥረት ሳለች ትልቅነት የሚያቋምጣት፥ መሆን የማትችለውን ለመሆን የጣረች ነበረች። ማርያም ግን በተገባ የአምላክ እናት የተባለች ብትሆንም በትሕትና ዝቅ ብላ ባርያ የምትሆን የዋሕት ርግብ ነች። ሁለቱ እናቶች በየኪዳናቸው የተወጡት ሚና የጨለማና የብርሃንን ያክል የሚለያይ ነው።

8.   ሔዋን ዕፀ በለስን ለመብላት ሁለት ነገሮችን ማለፍ ይጠበቅባት ነበር። አንደኛ ይህ የሚያነጋገረኝ እባብ እውነተኛ ነው፤ ቃሉም የታመነ ነው ብሎ ማመንና መቀበል። ሁለተኛ ደግሞ ያ ቀድሞ ያናገረንና አትብሉ ያለን አምላክ ሐሰተኛ ነው ብላ ማመንና መካድ ነው። ያለዚያማ በለሲቱን ወደ መብላት እንዴት ትራመዳለች። እነዚህ ሁለቱ ደግሞ በፍጥረት ታሪክ ታላላቆቹ ውንብድናዎች ናቸው፤ ሐሰቱን ጽድቅ፥ ጽድቁን ሐሰት የማለት ያለማመን ውድቀት። እናታችን ማርያም ግን በእምነትና በትሕትና ሁሉን የፈተሸች የማመን ተምሳሌት፤ የእስራኤል የማመናቸው ሁሉ ጥግ ነበረች። ይህንም ለመግለጥ ኤልሳቤጥ መንፈስ ካደረባት በኋላ ሰላምታዋን በሰማች ጊዜ “… ያመነች ብፅዕት” በማለት አመስግናታለች፤ ሉቃ.1፥45።


9.   ሔዋን በትዕቢትና ባለማመን ወደ ሰው ዘር ሞትን፥ መከራንና እርግማንን ስታመጣ እናታችን ማርያም ደግሞ በትሕትናና በማመን እነዚህን ከሰው ልጅ ተፈጥሮ አራቀች። የሔዋን ኃጢአት ከጎኑ በወጣችበት በአዳም ሞት ፍጽምና አግኝቷል፤ የእመቤታችን ጽድቅ ከሆዷ በወጣ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ፍጽምና አግኝቷል፡፡


10.  ሔዋን በቀደመው ኪዳን፥ ባልተሳካው፥ ይልቁኑም በከሸፈው ኪዳን የፍጥረት ሁሉ እናት ስትሆን እናታችን ማርያም ደግሞ አንዴ ከተገባ የማይታበለው የዘላለማዊው፥ ሕያው ሆነን ተስፋ የሰነቅንበት የአዲሱ ኪዳን የፍጥረት ሁሉ እናት ናት።

በእርግጥም በእመቤታችን በድንግል ማርያምና በቀደመው ኪዳን ቀዳማዊት እናት ሔዋን መካከል ያለው ንጽጽር ብዙ የሐዲሳትና የብሉያት ሊቃውንትን ያስደመመ ረቂቅ አምላካዊ ምሥጢር አለው። በተለይም ሰሞኑን የምናከብረው የቃና ዘገሊላ በዓል ዐውድ ውስጥ የቀዳማዊት እናት የሔዋንና የዳግሚት ሔዋን ማርያም ነገር እጅጉን ተገልጦ መወራት የሚችልበት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ምዕራፍ ሁለት ላይ ያሰፈረበትን መንገድ ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ የፍጥረትን ልደት በተናገረበት በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ ሁለት ላይ ቃሉን ካሰፈረበት መንገድ ጋር ስናናብበው ምሥጢሩን እናገኛለን።
  1.   ሙሴ የፍጥረትን ልደት “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” ብሎ ጥንተ ፍጥረትን ጠቅሶ ከጊዜ መቆጠር ጀምሮ ይጽፋል። ዮሐንስ ወንጌላዊም የሐዲሱን ፍጥረት ዳግም ልደት/ጅማሬ ማውሳት በሚጀምርበት ጊዜ እንደዚሁ “በመጀመሪያ ቃል ነበረ” በማለት ከፍጥረተ ዓለም በፊት የነበረውን ህላዌ ጠቅሶ ይጀምራል። በአጀማመራቸው የሁለት ተፈጥሮንና የሁለት ልደትን ነገር ያጠይቃሉና ማስተዋል ይገባል። “ወለደነ ዳግመ” ዳግመኛ ወለደን እንዳለ ቀድሞ በ6 ቀን የፈጠረን አምላክ በመከራና በስቃይ አምጦ በ6ኛ ቀን በመስቀሉ ላይ ሆኖ ድጋሚ ፈጥሮናልና።

  2. ሙሴ በመጀመሪያ ብሎ የጊዜን ጅማሬ ከጠቀሰ በኋላ በምዕራፍ አንድ ላይ ብቻ ስድስት ቀናትን ይቆጥራል። ፍጥረታት በስድስት ቀን ተፈጥረው እንዳለቁ ሲጽፍ … ቀንም ሆነ ማታም ሆነ አንድ ቀን … ሁለት ቀን … ሦስት ቀን እያለ የፍጥረትን ልደት ይናገራል። (ዘፍ.1፣5 ፤ 8 ፤ 13 ፤ 19 ፤ 23 ፤ 31) ወንጌላዊ ዮሐንስም እንዲሁ በመጀመሪያ ብሎ ጊዜን ጠቅሶ ከተናገረ በኋላ በምዕራፍ አንድ ላይ ብቻ ዐራት ቀናትን ይጠቅሳል። እንዴት ቢሉ በምዕራፍ አንድ ቁ. 29 ላይ “በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ” ይላል። “በነገው” ሲል ሁለተኛ ቀን መሆኑ ነው። ምክንያቱም ቀድሞ ከፈሪሳውያን ዮሐንስን ሊጠይቁ እንደመጡ ይገልጥልን ነበረና። ቀጥሎ ደግሞ በቁ. 35 “በነገው ደግሞ ዮሐንስ፥ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር” ይላል። አሁንም “በነገው” ሲል ሦስተኛ ቀን ይሆናል። በቁ.44 “በነገው ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊወጣ ወደደ” ሲል ዐራተኛ ቀን ሆነ። በጠቅላላው ሙሴ በምዕራፍ አንድ ላይ ስድስት ቀናትን ቆጥሮ ይጨርሳል፤ ዮሐንስ ወንጌላዊ ደግሞ ዐራት ቀናትን ይቆጥራል።

3. ሙሴ በምዕራፍ አንድ ላይ በመጀመሪያ ብሎ ተነሥቶ ስድስት ቀናትን ቆጥሮ ምዕራፍ ሁለትን ሲጀምር ሰባተኛው ቀን ላይ የሆነውን በመናገር ይጀምራል። ወንጌላዊ ዮሐንስ በምዕራፍ አንድ ላይ በመጀመሪያ ብሎ ተነሥቶ ዐራት ቀናትን ቆጥሮ ምዕራፍ ሁለትን ሲጀምር “በሦስተኛውም ቀን …” ብሎ በመጀመር ቀድሞ በምዕራፍ አንድ ላይ በቆጠራቸው ዐራት ቀናት ላይ ሦስት ሲያክል ሰባተኛ ቀንን ይጀምራል።


4. ሙሴ በምዕራፍ ሁለት ላይ በሰባተኛ ቀን ካለ በኋላ እግዚአብሔር ከአዳም ጎን አጥንት ወስዶ ሔዋንን እንደ ፈጠረና ጎኑን በሥጋ እንደመላው፥ አዳምም ከእንቅልፉ በነቃና ሴቲቱን በተመለከታት ጊዜ ደስ ተሰኝቶ “ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፤ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርሷ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል” ብሎ ሔዋንን ተቀበላት። ባልና ሚስት ሆኑ። አዳምም እንዲህ አለ “… ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።” እንደዚሁ ሁሉ ወንጌላዊው ዮሐንስም በምዕራፍ ሁለት ላይ ሰባተኛ ቀን ካመለከተ በኋላ “በቃና ገሊላ ሠርግ ሆነ” በማለት የጋብቻን ምሥጢር ይነግረናል። ሁለቱም በሰባተኛ ቀን የጋብቻን ዐውድ ይጽፋሉ።

5. ሙሴ በሰባተኛው ቀን ባመለከተው ጋብቻ ላይ የቀደመው ኪዳን ጀማሪዎች አዳምና ሔዋንን ጠቅሷል። በዚያም አዳም ሔዋንን “ሴት” በሚል የክብር አጠራር ጠራት፤ ከጎኑ የተገኘች አካሉ አጥንቷ ከአጥንቴ ሥጋም ከሥጋዬ ሲል ነው። ወንጌላዊው ዮሐንስም በሰባተኛው ቀን ባመለከተው ጋብቻ ላይ ዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስና ዳግሚት ሔዋን እመቤታችንን ጠቅሷል። በዚያም ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ ዳግሚት ሔዋን እመቤታችን ማርያምን “ሴት” በሚል የትንቢት ስሟ ጠርቷታል፤ “አንቺ ሴት፤ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ”፤ ዮሐ.2፣4። (ቃሉ እጅግ የክብር ቃል ነው። የእሺታ መንፈስ የሚገለጥበት ቃል ነው። ከማናቸውም ስሟ “ሴት” የሚል ስሟ እዚህ ቦታ ላይ መጠራቱ ፋይዳው ከፍ ያለ ነው። ነቢያት የሚያውቁት ስሟ ነውና፤ አዳምም ሔዋንን ያላት ሱባኤ የተቆጠረበት ስም ነው።)

6.በሙሴ ዘንድ ከአዳም ጎን የተገኘችና ሴት የተባለች የገዛ አካሉ ሔዋን ባጠፋችው ጥፋት ምክንያት አዳም ለፍጥረት ሁሉ ውድቀት መንሥኤ ሆነ። በዮሐንስ ወንጌላዊ ዘንድ ዳግሚት ሔዋን ከዳግማዊ አዳም የተወለደች ሳትሆን ይልቁኑም ዳግማዊ አዳም ራሱን በመውለዷ ከአካሏ የተከፈለ የሚሆን አንድ ልጅ ከተወለደባት በኋላ ክርስቶስ ለሰው ዘር ዳግም ትንሣኤ ሆነ።

7. በሙሴ ዘንድ አዳም ከአርሱ የተከፈለችውን ሔዋንን “ሴት” ብሎ ሰየማት። የቀደመውና ያልተሳካው ኪዳን ቀዳማዊት እናት ሆነች። በዮሐንስ ግን ዳግማይ አዳም እርሱ እርሷን ሳይሆን ዳግሚት ሔዋን እርሷ እርሱን ከአካሏ የተከፈለውን “መድኃኒት” በሚል ስም ኢየሱስ ብላ ሰየመችው። በነሣው ሥጋ ዓለምን ያድንበታልና። እርሷም የዘላለማዊው የሐዲሱ ኪዳን ቀዳማዊት እናት ሆነች።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በነገረ ድኅነት ውስጥ ስላላት ቁልፍ ሚና መረዳት የሚፈልግ ሰው የሔዋንን ሁኔታ ልብ ብሎ ያጢን። ሔዋን በውድቀታችን ላይ የነበራት ሚና ምን ያክል እንደነበር ገልጦ መናገር ከተቻለ፥ እመቤታችን በትንሣኤያችን ላይ ሊኖራት የሚችለውን ሚና ማኖር ቀላል ይሆናል። ምክንያቱም የቀደመው ኪዳን ርእሱ አዳም ነበር፤ እርሱም ሞትና ኃጢአት በሰዎች ነግሠው እንዲኖሩ ያደረገ ነው። የአዲሱ ኪዳን ርእስ ደግሞ ክርስቶስ ነው፤ በእርሱም ጽድቅና ሕይወት ነግሠዋል። ስለዚህ የእመቤታችን ሚና በሔዋን አንጻር ከልጇ ከክርስቶስ ጋር የሚነገር ነው። አዳም ሞትንና ኃጢአትን ሲያሠለጥንብን ከአካሉ የተከፈለች ሔዋን ለሰይጣን በመሸነፍ ቀድማዋለችና። እርሷ ለሰይጣን ተሸነፈች፥ እርሱ ደግሞ ለሚስቱ ስለተሸነፈ የሞትን በር ገርበብ አድርጋ በመክፈት ለባሕርይ ድቀት ያበቃችን ሔዋን ነች።

እመቤታችን ግን የክርስቶስ ታሪክ የትንሣኤና የሕይወት በመሆኑ ሚናዋም በዚያ አንጻር ሊነገር የሚገባ ነው። በውድቀታችን ሔዋን ከአዳም አካል ተከፈለች። በትንሣኤያችን ላይ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ ከዳግሚት ሔዋን ማርያም ተከፍሎ ያለወንድ ዘር በድንግልና ተወለደ። ከወንድ ጎን የተገኘች ሴት ሚስቱ ስትባል ከሴት ሆድ የተገኘ ወንድ ደግሞ ምንጊዜም ልጇ ይባላል። በውድቀታችንም ሔዋን አዳም ለሴትነቷ ባለው ስስት ምክንያት እንዲሸነፍና እንዲስት አደረገች። ከሴቶች ሁሉ ተለይታ የተባረከች እናታችን ማርያም ግን ቤዛ ይሆነን ዘንድ በሁሉ ተራዳኢት ሆነች፤ አብራው በበረት ተጣለች፤ ተሰደደች፤ ተሳቀቀች፥ ተሰቃየች፥ በሕማሙም ጊዜ አብራው ቃተተች።

አዳም በምኞት ሐሳብ በወደቀ ጊዜ ሔዋን በሚስትነቷ አቋምጣ ለፈቃደ ሥጋ እንዲረታ አድርጋ የኩነኔን ተግባር እንዲፈጽም ምክንያት ሆነችው፤ መመኘትን አፋፋመች። ዳግሚት ሔዋን ማርያም ግን ልጇ ለመከራ በመታዘዝ የሚቤዠን ነውና እናት ሳለች የልጇን ውርደት፥ የላቡን መንጠብ፥ የደሙን መንጠባጠብና የሥጋውን በላዩ ላይ መቆራረስ፥ የእጆቹና የእግሮቹን ችንካር በዐይን እየተመለከተች የእናት እንባ በስቃይ አነባች፤ አብራው ታመመች። ድል የሚያደርግና በሞት ላይ የሚነግሥበት ተዋርዶ በትሕትና እየወደቀ ነውና በገብርኤል ብሥራት ጊዜ በትሕትናና በእምነት የጀመረችውን የሔዋን መድኃኒትነት አሁንም ሁሉን የሚያደርግ ልጇን ሁሉን ሲያደርጉት እያየች፥ አብራው እየታመመችና እየተሰቃየች ንግሥት ሆና ተከተለች። አሁንም በስተመጨረሻ “ሴት” አላት “አንቺ ሴት እነሆ ልጅሽ።” (ዮሐ.19፥26) በወልድ ላመንን ለሁላችን የወልድ እናቱ ደግሞ እናታችን ትሆነን ዘንድ ተሰጠችን፤ አሜን - ይሁን/ይደረግልን።

­­­­­­­­­­­­­­
“ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን፥ የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘሯ የቀሩትን ሊወጋ ሄደ።”
ራእ.12፥17


አስተያየቶች