ያዕቆብ፣ ዮሳ፣ ስምዖንና ይሁዳ በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ ጌታችን በትውልድ አገሩ ሲሰብክ ሳለ በናዝራውያን ወገኖች “ወንድሞቹ” ተብለው እንደተጠሩ እናነባለን፡፡ (ማቴ. 13፣55) ኹሉም ባይኾኑም አንዳንድ ፕሮቴስታንት ወንድሞች ይህን ገጸ ንባብ በመያዝ፣ ከዚሁም ጋር በሌላ ቦታ ዮሴፍ እመቤታችንን “እስከምትወልድ ድረስ አላወቃትም” (ማቴ.1፣25) ከሚለው ንባብ ጋር በማናበብ ከወለደች በኋላ ግን ዐወቃት ወደሚል እኩይ አገባብ ጠምዝዘው እመቤታችን ከጌታ በተጨማሪ ከዮሴፍ የወለደቻቸው የሥጋ ወንድሞቹና እኅቶቹ አሉ ብለው ስሕተት ይናገራሉ፡፡ ትምህርቱ ልክ ከማይኾንባቸው ምክንያቶች መካከል የተወሰኑት፡
1. ሌላ እናት? …
ያዕቆብና ዮሳ በድጋሚ በማቴ.27፣55 ላይ ተጠቅሰዋል፤ ያኔ በጌታችን በስቅለቱ ጊዜ “እናታቸው” ተጠቅሳለች፤ እመቤታችን ግን አልነበረችም፡፡ ምክንያቱም የያዕቆብና የዮሳ እናት ይህችኛዋ ማርያም ከኾነች አባታቸው ደግሞ ሉቃ.6፣15 እልፍዮስ እንደኾነ ይናገራል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ እነዚህን ገጸ ንባቦች ይዘው ዐራቱ የእመቤታችንና የዮሴፍ ልዦች ናቸው የሚሉ ሰዎች አባታቸው እልፍዮስ ኹኖ መገኘቱ እንዴት እንደኾነ የማስረዳት ሸክምም አለባቸው ማለት ነው፡፡
ያዕቆብ የተባለው በገላትያ መልእክት ላይ (ገላ.1፣19) ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን ጳውሎስ ወደኢየሩሳሌም በሄደ ጊዜ ከ12ቱ ወገን ያገኘው ብቸኛው እርሱ እንደኾነ የጠቀሰው ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ሲኾን እርሱንም “የጌታ ወንድም” ብሎ ይጠራዋል፡፡ ከ12ቱ ወገን ደግሞ ያዕቆብ የሚባሉ 2 ናቸው፤ 1ዱ የዘበዴዎስ ልዥ፣ ማለት የወንጌላዊ ዮሐንስ ወንድም ያዕቆብ ወልደ ነጎድጓድ ሲኾን (ማር.1፣19) ሌላኛው ደግሞ የእልፍዮስ ልዥ የተባለው ታናሹ ያዕቆብ ነው (ሉቃ.6፣15)፡፡ እነዚህ አባቶቻቸው እንዲህ ከታወቁ ከዮሴፍና ከማርያም የተወለዱ የሚሉ ወገኖች ይህ እንዴት እንደኾነ ማስረዳት አለባቸው፡፡ ታዴዎስ የተባለው ይሁዳ የያዕቆብ የሥጋ ወንድም ከኾነ (ሉቃ.6፣16) በዚሁ አኋኋን ይታያል ማለት ነው፤ እርሱም የጌታ የሥጋ ወንድሙ አይደለም፡፡
2. ልማደ እስራኤል
ሪቻርድ ባልኮም የተባለ ፕሮቴስታንት መምህር እነዚህ ሐዋርያት የሥጋ ወንድሞቹ ናቸው የሚለው አሳብ ታሪካዊም ያይደለ እንደኾነ ጽፏል፡፡ እንደሱ አባባል በእሥራኤል ልማድ በሥጋ ወንድማሞች መሃል ታናሽ የሚኾነው ታላቁን አይገሥፅም፣ አይመክርም፣ አያርምም፡፡ በተለይ ደግሞ ሕዝብ በተሰበሰበበት ይህን ማድረግ ለሥጋ ታናሽ ወንድም ፈጽሞ ኩነኔ ነው፡፡ በእሥራኤል ዘንድ ብኵርና ከፍተኛ ማዕርግ፣ ልዩ ፋይዳ ያለው በመኾኑ በኵር የቃልኪዳን ተቀባይ መፈጸሚያ እንደሚኾን በደምብ በብሉይ አይተናል፡፡ እነዚህ ሐዋርያት የጌታ የሥጋ ወንድሞቹ ቢኾኑ ኖሮ ኹሉም ታናናሾቹ ነበር የሚኾኑት፡፡ ምክንያቱም በማቴዎስ ጌታችን የድንግል የበኵር ልዧ እንደኾነ ተነግሮናል፡፡ (ማቴ.1፣25) ከዚህ አንጻር በዮሐ.7 ላይ እነዚህ ወንድሞቹ ጌታን ሲያርሙት ማየታችን በራሱ ታናናሽ የሥጋ ወንድሞቹ ናቸው የሚለው ዘበት እንደኾነ ይነግረናል፡፡
3. እስከምትወልድ ድረስ አላወቃትም
ይህ ማለት ከወለደች በኋላ ግን ዐወቃት ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም ጠንከር ላለ ምክንያት ከዚያ በኋላ ዝር አላለባትም እንድንል ያስችለናል፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት “እስከ” የሚለውን ቃል አንዳንዴ ዘጊ አጠቃቀም ይጠቀሙታል፤ አንዳንዴ ቀጣይነት ያለው አጠቃቀም ይጠቀሙታል፡፡ ኹል ጊዜ በአንድ አካሄድ ብቻ ይህን ቃል መተርጐም አደገኛ ስሕተት ላይ ይጥላል፡፡ ለአብነት ያክል 1ኛ ቆሮ.15፣25 ላይ ጌታችን ኢየሱስ “…ጠላቶቹን ከእግሩ በታች እስከሚያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባል፤” ይላል፡፡ ይህ ማለት ክርስቶስ ጠላቶቹ ከእግሩ በታች ከኾኑ በኋላ ንግሥናው ያበቃል ማለት አይደለም፤ ምክንያቱም ሉቃ. 1፣33 ላይ “… ለዘላለም ይነግሣል” ተብሏልና፡፡ በሌላም አጋጣሚ 1ኛ ጢሞ.3፣13 ላይ መምህረ ወንጌል ጳውሎስ ልዡ ጢሞቴዎስን “…እስከምመጣ ድረስ ለማስተማር ተጠንቀቅ” ይለዋል፡፡ ይህም ስመጣ ግን አትጠንቀቅ ተብሎ መተርጐም ፈጽሞ አይቻልም፡፡ 2ኛ ሳሙ.6፣23 ሜልኮል እስከምትሞት ድረስ ልጅ አልወለደችም (መካን ኾነች) ይላታል፡፡ ከሞተች በኋላ ግን ወለደች ብሎ ይህንን መተርጐም ሞኝነት ነው፡፡
4. የእሥራኤል ወንድሞች
እሥራኤላውያን ብዙ ጊዜ የቅርብ ዘመድ ወይም የሃይማኖት አቻን ወንድም፣ እኅት እያሉ ይጠራሉ፡፡ ሐዋርያ ጳውሎስ ብዙ ጊዜ ወንድሞቻችን ሆይ እያለ ምእመናነ ክርስቶስን ሲጠራቸው እናያለን፡፡ በሌላ በኩል በዮሐ. 19፣25 ላይ የቀለዮጳን ሚስት ማርያምን የእመቤታችን ድንግል ማርያም እኅት ይላታል፡፡ ይህች ሴት የእመቤታችን የሥጋ እኅቷ ከኾነች ወላጆች በአንድ ቤት ውስጥ የሚወልዷቸውን እኅታሞች ሁለቱንም በተመሳሳይ ስም “ማርያም” ብለው ጠርተዋል ወደሚል የማይመስል ትምህርት ይወስደናል፡፡ አብርሃምና ሎጥ የአጐት ልዦች ቢኾኑም ወንድሞች ተብለው ነበር፡፡ የእሥራኤላውያንንና የክርስቲያኖችን ልማድ ጠንቅቆ መረዳት እዚህ ጋር ያለው ሚና ይህን ያክል የማይባል ትልቅ ነው፡፡
5. የአይሁድ ምስክርነት በትክክል ምስክርነት ነው ወይ
እነዚህ ሐዋርያት ወንድሞቹ ተብለው እዚህ ቦታ ላይ ስለተጠቀሱ በቀጥታ እመቤታችን ወንድሞቹ የሚኾኑ ሌሎች ልዦች አሏት ወደሚል ፈጣንና ግራ የሚያጋባ ድምዳሜ ከዘለቅን፣ እንዲሁ ዮሴፍም እዚያው ቦታ አባቱ ተብሎ ተጠቅሷልና ዮሴፍም የኢየሱስ የሥጋ አባቱ ሊባል ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ኦርቶዶክሳዊም ይኹን፣ ካቶሊክም ይኹን፣ ተሐድሶም ይኹን የየትኛውንም የክርስቲያን ወገን ዶግማዊ አስተምህሮውን የሚንድበት ነው (እዚህ ጋር የሙስሊም ወገኖችንም ዶግማ ማለት እንችላለን)፡፡ ማንም ክርስቲያን ይህን ዮሴፍ የጌታ የሥጋ አባቱ ነው የሚለውን ሲያስተምር ተሰምቶ አይታወቅም፡፡
ከ16ኛ መቶ ክ.ዘ. ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ዠማሪዎች መሃል ዦን ካልቪን፣ ማርቲን ሉተር፣ ኡልድሪክ ዝዊንግሌይ እና ዦን ዊስሌይ የመሳሰሉት እመቤታችን ተጨማሪ ልዦች እንዳልነበሯት አበክረው ከሚያስተምሩት መሃል ነበሩ፡፡ (Calvin, John (2009). Commentary on Matthew, Mark, Luke -
Volume 2. Grand Rapids, MI: Christian Classics Ethereal Library) አንዱ የሚባለው ዦን ካልቪን እነዚህ ማቴ.13 ላይ የተጠሩ ሐዋርያት በአንድም ኾነ በሌላ አኋኋን የእመቤታችን ልዦች ናቸው ብለን ማንበብ አንችልም የሚል ግልጽ አቋም ነበረው፡፡ ሌላኛው ሪፎርመር ማርቲን ሉተር ደግሞ እስከሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ እመቤታችን ወትረ ድንግል መኾኗን አጠንክሮ የሚያስተምርና የሚከራከር ነበር፡፡
ታዲያ ለምን “እስከምትወልድ ድረስ አላወቃትም” ተባለ
መጽሐፍ ቅዱስ ክስተቱን በዚህ አኋኋን መግለጡ ጠቀሜታዎች አሉት፤ እንዲያውም እንዲህ ብሎ ባይገልጠው ኖሮ ችግሮች ይፈጠሩ ነበር፡፡
ከኹሉም በላይ ኹላችንም እንደምናውቀው ሴት ልዥ እንዳረገዘችና ልትወልድ እንደኾነ ስናይ ወዲያውኑ ከዚያ ከርግዝናዋ ወራት ፊት በአንዳች ሰሙን ወንድ እንደደረሰባት/በግብር እንዳወቃት እንረዳለን፡፡ ተፈጥሯዊ አካሄዱ እንዲያ ነው፡፡ ወንድ ካልደረሰባት/ካላወቃት ግን ዘር ስለማታገኝ መጽነሷ ልትወልድም መድረሷ ተፈጥሯዊ ያልኾነ ተአምራዊ ክስተት ስለኾነ ማድነቅ ይገባናል፡፡ በንዲያ ያለ አወላለድ የተወለደ በሥነ-ፍጥረት ታሪክ የዓለም ቤዛ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ የናዝሬቱ ኢየሱስ በድንግልናና ወንድ ልዥ ባልተሳተፈበት ንጹሕ አወላለድ መወለዱ “ክርስቶስ”ነቱ “የእግዚአብሔር ልዥ”ነቱ ለሰዎች የተገለጠበት አንዱኛው መንገድ ነው፡፡ ድንግላዊ ልደት የናዝሬቱ ኢየሱስ የአብ አካላዊ ቃል የባሕርይ ልዡ እንደኾነ በግልጥ የታየበት አንዱ መንገድ ነው ነው፡፡
ታዲያ ደካሞች በእመቤታችን በጽንሰቷ ዐውድ ውስጥ እጮኛ ተብሎ የመጣ ወንድ (ዮሴፍ) እንዳለ ሲነገራቸው በድካማቸው ተስበው ለልደቱ ምክንያት መንሥኤ (ለያውም ደግሞ የዘርዓ ብእሲ መንሥኤ) እንደሚያበጁለት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ቀድሞ ስለሚያውቅ እስከምትወልድ ድረስ የወንድ ዘር አላገኛትም፣ ወንድ አልደረሰባትም በማለት የጌታችን ልደት ድንግላዊ ልደት እንደኾነ በማያሳስት መልኩ አስቀመጠ ማለት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ባለው ጊዜ ዐወቃት አላወቃትም ለሚለው ግን አእምሮ ያለው አማኝ ሰው የኃያላን ኃያል ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ፍጥረትን በፈቃዱ ፈጥሮ የሚገዛ፣ ገዝቶ የሚያሳልፍ፣ አሳልፎም እርሱ ግን ሕያው ኹኖ የሚኖር አምላክ ሥጋና ነፍስን በነሳበት፣ ገብቶ ባደረበትና የአእላፍ ነገደ መላእክትን ጥዑም ቅዳሴ ዙፋኑ አድርጎ ባዳመጠበት ማሕፀን ሌላ ተራ ሰው አድሮበታል ብሎ ማሰብ፣ ሳይጥሰው ተፈትሖ በሌለበት መወለድ አልፎት የወጣውም ማሕተመ ድንግልና ማሕፀን በግብረ ብእሲ ሌላ ሕፃን አስተናግዷል ብሎ ማሰብ የእምነትን ፈጽሞ መሸርሸር ማለቅ የሚጠይቅ ክህደት ያለበት እሳቤ ነው፡፡ ይህ በእመቤታችን ላይ በጠላትነት ከመነሣት የሚነገር ቢኾንም ትቃቱ ግን በቀጥታ ባለቤቱን ነው፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ለሰዎች ክብሩን ከሚገልጥባቸው መንገዶች አንዱ እርሱ በተቀመጠበት ዙፋን ማንም የማይቀመጥ መኾኑን ማጠየቅ ይገኝበታል፡፡ እርሱ በሚሄድበት መንገድ ማንም የማይሄድ መኾኑ፡፡ (ሮሜ.11፣33) እርሱ በገባበት በር ማንም ደግሞ የማይገባ መኾኑ ኹሉ በቅዱሳት መጻሕፍት የእግዚአብሔርን እግዚአብሔርነት የሚገልጡ መኾናቸው ተገልጦ እናገኛለን፡፡ ለአብነት ያክል በሕዝቅኤል “ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተ ውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ፤ ተዘግቶም ነበር። እግዚአብሔርም። ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም፥ ሰውም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል።” -- ሕዝ.44፣1-2 ይላል፡፡ ይህን ቃል በሚመለከት በ2ኛው መቶ ክ.ዘ. የኖረው ቅዱስ አምብሮስ ይህ በቀጥታ ለጌታችን ልደት የተመሰለ ምሳሌ እንደኾነ አብራርቷል፡፡ እነአባ የሮምዮስና ሌሎችም እንዲህ አድርገው መጻሕፍትን የተረጐሙ ሊቃውንት ናቸው፡፡ በሺሆች ዘመናት የክርስቲያኖች ምስክርነት ያለውን የወትረ ድንግልና ትምህርት ዘመን ባመጣው በቂም በተነሣሡ ፍልስፍናዎች መተካቱ ግን ኩነኔ ነው፡፡
“ወንድሞቹ” ለምን ተባሉ
በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እነ ዮልዮስ አፍሪቃዊ (ጁሊየስ አፍሪካኖስ) እና በ2ኛው መቶ ክ.ዘ. እነ ሄጌሲጶስ የመሳሰሉት ክርስቲያኖች “ወንድም” የሚለው ቃል አንዳንዴ ለቅርብ ዘመዶች ኹሉ የሚጠቀስ አንዳንዴም አንድ እምነት የሚከተሉ ሰዎች ኹሉ የሚጠቅሱት እንደኾነ የሰጡትን ምስክርነት እነ አውሳብዮስ ዘቂሳርያ በታሪክ መዝግበውታል፡፡
(Eusebius of Caesarea, Historia Ecclesiae, 1:7:11, 1:7:13–14)
ወንድም የሚለው ቃሉ በእሥራኤላውያንና በቀደምት ክርስቲያኖች (በአሁኗም ቤተ ክርስቲያን) ያለው የትርጕም ስፋት አንዱ ኾኖ፣ ነገር ግን እንደነ ሮበርት ሺህል የመሳሰሉ ጥንታውያን ልሳናት ላይ ያጠኑ ሰዎች ጌታችን ኢየሱስና የወቅቱ ሰዎች የተጠቀሙበት የአረማይስጥ ልሳን እንደ ብዙዎቹ የሴማውያን ቤተሰብ ቋንቋዎች ኹሉ እርሱም የአጎት ልዥ የአክስት ልዥ ለሚለው ቀጥተኛ መጠሪያ የለውም፡፡ ስለዚህ በኹሉም አጋጣሚዎች “ወንድም” የሚለው በምሥጢራዊ አፈታት (ከጊዜ በኋላ በተገኘ ትርጒም) ተክቶት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ለዚህም ከብዙዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ አብነቶች መሃል ከላይ ያነሣናቸው ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ዕድሜ ይስጥልኝ!
የካቲት 2008 ---
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ