መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ገድላት


ሰዋስዋዊና ምሥጢራዊ ፍች
ገድል የሚለው ቃል ገደለ - አቈሰለ፣ አረደ፣ አነቀ፣ እገደል ጣለ ከሚለው የግእዝ ቋንቋ ቀዳማይ ግስ የተገኘ ነው፡፡ ዕብራይስጥ ጋድል ይለዋል፡፡ “ወገደለ ንጉሥ እምጥሪተ ዚኣሁ፣ ወመላእክትኒ ገደሉ ለሕዝብ” ከሚለው ይህ ይታወቃል ፪ዜና. ፴፭፥፯፡፡ ትርጕሙም በቀጥታ ትግል፣ ፈተና፣ ውጊያ፣ ሰልፍ፣ ድልና አክሊል እስኪገኝ ድረስ የሚደክሙት ድካም፣ የሚሠሩት ሥራ፣ የሚቀበሉት መከራ ማለት ይኾናል፡፡

መጻሕፍተ ገድል (ቅዱሳት ገድላት) የሚባሉት በሕይወታቸው እግዚአብሔርን ያከበሩ ቅዱሳን/ት  ሰዎች ያለፉበትን የመከራ ሕይወትና በክርስትናቸው ምክንያት ያገኛቸውን ፈተና ያለፉበትን ወንጌላዊ ጥበብ የሚተርክ፤ ለአማኒያን መማሪያ ለቅዱሳን መዘከሪያ ኾነው የሚቀርቡ ቅዱሳት መጻሕፍት አዋልድ ናቸው ምሳ. ፲፥፯፡፡

ስለዚህ ገድላት ሦስት ዐበይት ጠቀሜታዎች/ዓላማዎች አሏቸው፡፡ አንደኛውና ዋናው የክርስቶስን ክብር መግለጥ ነው፡፡ ሁለተኛው ለምእመናን ትምህርት ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ለቅዱሳኑ ተዝካር/መታሰቢያ ይኾን ዘንድ ነው፡፡

ክርስቶስን ለመግለጥ
በአጭር ቋንቋ በገድላት የክርስቶስ ክብር ይገለጥባቸዋል እንጂ ገድሉ የተነገረለት ቅዱስ ብቻ ክብር አይደለም፡፡ “አመ ይመጽእ ይሴባሕ በቅዱሳኒሁ ወይትአኰት በእለ የአምኑ ቦቱ” ፪ተሰ. ፩፥፲ በቅዱሳኑ ይገለጽ ዘንድ በሚያምኑበትም ይመሰገን ዘንድ በመጣ ጊዜ 
በዚያች ቀን ስለ እናንተ የመሰከርነው ምስክርነታችን ይታመንልናል፡፡ “አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዝ ዓለም፤ ወከዐዉ ደሞሙ በእንተ ክርስቶስ ንጉሥ፤ ወተዐገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግሥተ ሰማያት” በእውነት ሰማዕት የዝህችን ዓለም ጣዕም ናቁ፤ ስለንጉሥ ክርስቶስም ደማቸውን አፈሰሱ፤ ስለ መንግሥተ ሰማያትም መሪር ሞትን ታገሡ እንዳለ ኤፍሬም ሦርያዊ በውዳሴ ማርያም፡፡ የኾኑትን ኹሉ ስለ ክርስቶስ እምነት ኾኑ፡፡


ለምእመናን መማሪያ ለቅዱሳን መዘከሪያ
ቅዱሳት ገድላት ማኅቶተ ወንጌል (የወንጌል ብርሃኗ) ይባላሉ፡፡ በጥጥ የተያዘ ዘይት ሥራው የሚታወቅ እሳት ሲነድድበትና ሲያበራ እንደኾነ ቅድስት ወንጌልም “ጽኑ! ታገሡ! መከራን ቻሉ! አክሊል ትቀዳጃላችሁ!” እያለች ስታስተምር ቅዱሳት ገድላት ደግሞ “ጸና! ታገሠ! መከራን ቻለ! አክሊል ተቀዳጀ!” እያሉ የትእዛዘ ወንጌልን ፍጻሜውን ለማየት የሚያበቁ ናቸው፡፡ ረድኡ ጢሞቴዎስ ኹሌም የቅዱስ ጳውሎስን ገድል እያሰበ ይጸና ነበር፡፡  ሐዋርያውም “ወበእንቲአሁ አሐምም ወኢይትኀፈር” ፪ጢሞ. ፩፥፲፪ ስለ እርሱ መከራዬም እቀበልለት ካለሁበት መከራ የተነሣ አላፍርም፤ ያመንኩትን ዐውቃለሁና … በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅርና ሃይማኖት ፀንተህ ከእኔ ዘንድ የሰማኸው ያ የሕይወት ቃል አብነት ይሁንህ … አርበኛ በሚገባ ካልተዋጋ ምስጋና አይገባውም ፪፥፭ … እያለ የራሱን ገድል እየጠቀሰ ጢሞቴዎስን እንዲፀና ይወተውተው ነበር፡፡

መጻሕፍተ ሐዲሳትን ማንበብ መማር መልካም ነው፤ ያስመሰግናል፡፡ ሐዋርያው ትምህርቱን የተከተሉለትን “ወአንተሰ ተለውከ ትምህርትየ” ፪ጢሞ. ፪፥፲ አንተ ግን ትምህርቴን ተከትለሃል እያለ ያመሰግን ነበር፡፡ ትምህርቱን ያልተከተሉና የሸሹትን ግን “ወበቀዳሚ ነገርየ አልቦ ዘኀብረ ምስሌየ” ፬፥፲፮ በመጀመሪያ ስብከቴ የተባበረኝ የለም፤ ኹሉም ተዉኝ እንጂ፤ ይህንም እግዚአብሔር ይቅር ይበላቸው እያለ በስመ እግዚአብሔር ይገሥፃቸው ነበር፡፡ ስለዚህ ትምህርቱን አምኖ መቀበል ደገኛ ነገር ነው፤ ሐዋርያትን ያስደስታቸዋል፡፡

ነገር ግን ትምህርት ብቻ በክርስቶስ በኩል አርበኛ አያደርግም፤ ይልቁኑ በተግባርም ሐዋርያትን እንድንመስል ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ሐዋርያው ትምህርቴን ተከትለሃል ካለ በኋላ ይቀጥልና “ወተመሰልከ በግእዝየግብሬንም ይዘሃል፤ በአስተማርሁህ ትምህርት ፀንተህ በፍቅር በትዕግሥት በዝግታ ኾነህ በመሰደድ፣ መከራን በመቀበል መስለኸኛል ፫፥፲ እያለ ይልቁኑ በመከራ ስለሚመስለው አብልጦ ያመሰግነዋል፡፡ ሐዋርያው ይቀጥልምና “ተአምር መጠነ ረከበኒ በአንጾኪያ፣ ወበኢቆንያ፣ ወበልስጥራን” ፫፥፲፭ በአንጾኪያ፣ በኢቆንያ በልስጥራን ያገኘኝን መከራ መሰደድንም እንደታገሥኩ ታውቃለህ፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ ሊድኑ የሚወዱ ኹሉ መከራን ይቀበላሉ ብሎ የገዛ ራሱን መከራና ተጋድሎውን መማሪያ አድርጎ ለጢሞቴዎስ ይተርክለታል፡፡ ስለዚህ የቅዱሳን ተጋድሎ/ገድል ለሌሎች ምእመናን መማሪያ፣ መፅኛ ይኾናልን ከዚህ እናውቃለን፡፡

ወንጌልን ብቻ አንብቦ የጨረሰ ሰው ወእመኒ ዕዴከ ታስሕትከ ምትራ፣ ወእመኒ ዐይነከ ታስሕትከ ምልሓ” ማር. ፱፥፵፭ እጅህ ብታሰናክልህ ቊረጣት፤ ዐይንህ ብታሰናክልህ ጐልጕለህ አውጣት፣ ብላ ስትሰብከው ጊዜ ኧረ ይሄስ ጭንቅ ነው፤ እንደ የት ይቻላል፤ ብሎ እንዳይፈራ ቅዱሳት ገድላት ከሰው ወገን ሰው ኾነው ተወልደው ይህን ኹሉ የቻሉና ያሳዩ አብነቶችን እየጠቀሱ ያበረታሉ፡፡ በትምህርት ብቻ አርበኛ መኾን እንደማይቻል ነገር ግን በግብርና በተጋድሎም ቅዱሳንን መምሰል የክርስትናችን ግብ ዓላማ ስለኾነ ይህን ስናደርግ ሐዋርያት ይልቁኑ ደስ ይሰኛሉ፡፡

ታሪክና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት
ገድላት ከብሉይ ኪዳን ዠምሮ ታላቅ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ በተለይም “መጽሐፈ ልዑላን” (የያሽር መጽሐፍ) ኢያ. ፩፥፲፫፣ “የእግዚአብሔር የጦርነት ታሪክ” ፩ነገ. ፲፩፥፵፫፣ “የእሥራኤልና የይሁዳ ነገሥታት ታሪክ” ፩ነገ. ፲፭፥፳፫ ፪ነገ. ፰፥፳፫፣ “ዜናሁ ለሙሴ” ይሁ. ፰ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እነዚህ በብሉይ ኪዳን ያገለገሉና መጽሐፍ ቅዱስም ምስክርነት የሰጣቸው፤ ያጣቀሳቸው ናቸው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰናይቲቱን ሐዲስ ኪዳን ከሠራ በኋላ የመዠመሪያውን የገድል መጽሐፍ የጻፈው ሐዋርያው ቅዱስ ሉቃስ ሲኾን የጻፈውም የገድል መጽሐፍ የ፲፪ ቅዱሳንን ወንጌላዊ ተጋድሎና ወንጌልን ስለመስበክ ምክንያት የደረሰባቸውን መፈተን የሚያስዘክረው “ገድለ ሐዋርያት” (የሐዋርያት ሥራ) የተባለውና ከ፹ወ፩ዱ አሥራው ቅዱሳት አንዱ የኾነው መጽሐፍ ነው፡፡

ከዚህ የገድል መጽሐፍ በፊት በመጽሐፍ መልክ ጽፎ አያኑራቸው እንጂ ማኅቶተ ቤተክርስቲያን ጳውሎስ ከመዠመሪያ አንሥቶ የነበሩ የቅዱሳንን ስም እየጠራ ገድላቸውን እየጠቀሰ በቃልም በመልእክትም ያስተምር ነበር፡፡ ዕብ. ፲፩፥፴፪

“እንግዲህ ምን እላለሁ፤ የጌዴዎንን፣ የባርቅን፣ የዮፍታሔን፣ የሶምሶንን፣ የዳዊትን፣ የሳሙኤልን የሌሎችንም ነቢያት ነገር ልነግራችሁ ቀን ያጥርብኛልና፡፡ በሃይማኖት የተጋደሉትን ነገሥታትን ድል የነሡትን ዋጋቸውን ያገኙትን ትሩፋት የሠሩትን ተስፋቸውን ያገኙትን የአንበሶችን አፍ የዘጉትን ዋዕየ እሳትን ያጠፉትን፣ ከጦር ስለት የዳኑትን፣ በመከራቸው የፀኑትን በሰልፍ ጊዜ የበረቱትን፣ የጠላቶቻቸውን ጭፍራ ያሳደዱትን ነገር እንዳልነግራችሁ ቀን ያጥረኛል፡፡” “ከመከራ እንዲድኑ አልወደዱምና፤ የገረፏቸው የዘበቱባቸው፣ አስረው ያጋዟቸውም አሉ፤ በመጋዝ የሰነጠቋቸው፣ በድንጊያ የደበደቧቸው፣ በሰይፍ ስለት የገደሏቸው አሉ፤ ማቅ የተልባ እግር የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ተጨነቁ፣ ተቸገሩ፣ መከራ ተቀበሉ፣ ተራቡ፣ ተጠሙ፡፡” ዕብ. ፲፩፥፴፪
ብርሃነ ዓለም ጳውሎስ እንዲህ እያለ በጠቅላላው እግዚአብሔርን ስለማመናቸው ምክንያት ቅዱሳን ላይ የደረሰባቸውን መከራና የቻሉትን መቻል ካስዘከረ በኋላ ገድላቸውን እያሰብን እንድንማርበትና እኛም አሰረ ፍኖታቸውን እንድንከተል ቀጥሎ “ስለዚህም እንደደመና የሚከቡን እነዚህ ሁሉ ምስክሮች ያሉን እኛ የኃጢአትን ትብትብና ሸክም አውርደን እንጣል፤ ሃይማኖት ወደሚያስገኝልን ወደሚጠብቅልን ተስፋችን በትዕግሥት እንገሥግሥ” ይለናል፡፡ ፲፪፥፩

ሐዋርያው የቅዱሳኑን ገድል አስፋፍቶና አጥልቆ አልጻፈልንም፤ በጻፈም በወደደ ነበር፡፡ ያልጻፈበት ምክንያቱም ስለ ሦስት ነው፡፡

አንደኛው ከአቤል የዠመረ ነውና የነዚህ ታሪካቸው በመጻሕፍተ ነገሥት ቀዳማዊና ካልእ፣ በዜና መዋዕል በሳሙኤል መጻሕፍት፣ በሄኖክ፣ በኩፋሌና በሌሎችም ብሉያት በዝርዝር የተዳሰሰ ስለነበር ጠቅሶ ብቻ ለንባባቸው መተዉ ነው፡፡ ሁለተኛው እርሱ በሰበከበት መዋዕለ ስብከት ቤተ ክርስቲያን ያልተረጋጋች፣ በሩጫና በስደት ላይ ያለች፣ ክርስቲያኖችም በሰላም ተሰባስበው የሚጸልዩበት መርጊያ ቦታ እንኳ ያልነበራቸውና በየጥጋጥጉና በየዱሩ የሚያድሩ፣ በአላውያን እየታደኑ የሚገደሉ ስለነበር እነርሱን በሐዲሱ እምነታቸው የማጽናቱ ተግባር ቅድሚያ ይስሰጠው ስለነበር ነው፡፡ ሦስተኛም ውሻ ወደ ትፋቱ እንዲመለስ በሐዋርያት ከሕዝብም ከአሕዛብም ከሚጨመሩት አዳዲስ ክርስቲያኖች ብዙዎች ቀድሞ ወደነበረ ልማዳቸው እየተመለሱ፣ አይሁድ ኦሪታቸውን አሕዛብ ጣዖታቸውን፣ ጽርዕም ጥበብ ፍልስፍናቸውን እየናፈቁ ስላስቸገሩ የቃል ሥጋ ኮነን ነገር አበርትቶ መናገሩ ላይ ስለተጠመደና ይህም ቅድሚያ ይስሰጠው ስለነበር ነው፡፡

ሐዋርያው ግን አሁንም ቅዱሳንን እንድናስብና እነርሱን እንድንመስል አበክሮ በማስተማር በኋላ ዘመን የቅዱሳን ሰዎች ገድል እየተነገረ ክርስቲያኖች እንዲበረቱበት መሠረቱን ጥሏል፡፡ “ተዘከሩ መኳንንቲክሙ ዘነገሩክሙ ቃለ እግዚአብሔር፤ ወእንዘ ትሬእዩ ሠናየ ግእዞሙ ተመሰሉ በሃይማኖቶሙ” ዕብ. ፲፫፥፯ የእግዚአብሔርን ቃል የነገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፤ የሕይወታቸውን ፍሬ እየተመለከታችሁ በሃይማኖታችሁ እነርሱን ምሰሉ ይላል፡፡ የቀደሙ ክርስቲያኖችን ሕይወት ማጥናትና እነርሱን መምሰል በክርስትና ውስጥ እጅግ አስፈላጊ ልማድ ነው፡፡ ምክንያቱም እነርሱን መምሰል ማለት ሊቀ ካህናችን ክርስቶስን መምሰል ስለኾነ፡፡ “ተመሰሉ ኪያየ በከመ አነ እትሜሰሎ ለክርስቶስ” ፩ቆሮ. ፲፩፥፩ እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ ብሎ ሐዋርያው ሰብኮናል፡፡ ታዲያ ዋኖቻችን ቅዱሳንን ለማሰብ፣ የሕይወታቸውንም ፍሬ አይተን በሃይማኖታችን እነርሱን ለመምሰል ሁለት ነገሮች ያስፈልጉናል፡፡ የቅዱሳንን ነገር እያስታወሱ የሚያስተምሩን መምህራንና ገድላቸውን የመዘገቡ መጻሕፍት፡፡

የቅዱሳን ገድል በመከራ ውስጥ የመፅናትና፣ በጭንቅ ውስጥ የመታገሥ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ እምነት የመጽናትና አላውያንና መናፍቃንን እምቢኝ ለክርስቶስ የማለት ታሪክ ነው፡፡ አዘውትሮ ይህን የሚያነብና የሚሰማ ክርስቲያን በመከራ ውስጥ የመቻልና በፈተና ውስጥ የመታገሥን ስብእና ገንዘብ ስለሚያደርግ ክርስትናው የምትደነቅ ትኾንለታለች፡፡

ቅዱሳት ገድላት ከዘመነ ሊቃውንት ወዲህ
ከመዠመሪያው የሐዲስ ኪዳን የገድል መጽሐፍ ከገድለሐዋርያት የሐዋርያት ሥራ በኋላ በተለያዩ አዝማን የተነሡ የክርስቶስ ብርቱ ደቀ መዛሙርት ሲነሡ ገድለ እገሌ (ገድለ ጊዮርጊስ የጊዮርጊስ ሥራ፣ ገድለ እስጢፋኖስ የእስጢፋኖስ ሥራ፣ ገድለ አርሴማ የአርሴማ ሥራ) እየተባለ ይጻፍላቸዋል፡፡ በተለይ በቀዳሜ ሰማዕት እስጢፋኖስ በ፴፬ ዓ.ም. ሀ ብሎ የዠመረውና ክርስቲያኖች እንደቅጠል የረገፉበት፣ ደማቸው ደመ ከልብ የኾነበት ዘመነ ሰማዕታት በተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ሰማዕትነት በ፫፻፲፩ ዓ.ም. ከተጠናቀቀ በኋላ ዘመነ ሊቃውንት (የቤተ ክርስቲያን ጠበቆች/አፖሎጂስትስ ዘመን) ሲመጣ ቤተ ክርስቲያን አንፃራዊ ሰላም በማግኘቷ ምእመናንም በተረጋጋ ሕይወት በሙሉ የሥርዓተ ክህነት ደንብ እያከናወኑ በኤጲስ ቆጶሳት ጠባቂነት መንጋ ኾነው መኖር ሲዠምሩ ሐዋርያው ቀን አጥሮበት የተወላቸውን መጻሕፍተ ገድላትን ለመጻፍ ችሎታው ተገኘ፡፡ ይኼኔ ባሳለፍነው የዘመነ ሰማዕት የረገፉትን ብርቱዎች ክርስቲያኖች ገድል በመጻፍ አፖሎጂስትስ/ሊቃውንት ነዋሪውን ምእመን ማስተማርና ማጽናት ዠመሩ፡፡

አስረጂ ከሚኾኑልን መሃል ታሪክ ጸሐፊው አውሳብዮስ የብዙዎቹን ሐዋርያት ገድል ጽፏል፡፡ አግናጥዮስ የፖሊካርፐስን ገድል ሲጽፍ፤ ይህንንም አውሳብዮስ መዝግቦታል፡፡ የአግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ፣ የተፍጻሜተ ሰማዕት ጴጥሮስ ገድላት በዚህ ዘመን የተጻፉ ናቸው፡፡

ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ የአባ እንጦንስን ታሪክ ሲጽፍ አባ ሄሮኒመስ የአባ ጳውሊን፣ የቅዱስ ሂላርዮስን፣ አባ ማልኮስን ገድላት ጽፏል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ከእርሱ በፊት ስለነበሩና ሰማዕትነትን ስለተቀበሉ ቅዱሳን ለምሳሌ ስለ ሰማዕቱ ባቢላስ፣ ስለ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ፣ ስለ ቅዱስ መላጥዮስ፣ ስለ ቅዱስ ኤዎስጣቴዎስ ዘአንጾኪያ በዕለተ ዕረፍታቸው (በበዓላቸው ቀን) ተጋድሏቸውንና ሕይወታቸውን በተመለከተ ያስተማራቸው ትምህርቶች ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም ስለ ቅዱሳኑ ስለሮማኖስና ስለበረላም ስብከቶችን ሰብኳል፡፡

ቅዱሳት ገድላት በዘመናችን
ቤተ ክርስቲያን በጌታችን ትእዛዝና በሐዋርያት ስብከት መሠረት ተቀብላና ያቆየችው የቀደሙ ብርቱ ክርስቲያኖችን ተጋድሎ ማስዘከርና ገድላቸውን መጻፍ፣ መተርጐም፣ ማስተማሩን አሁንም ድረስ ገፍታበት ትገኛለች፡፡ ነገር ግን ቅዱሳት ገድላት በዘመናችን ሁለት ፈተናዎችን የመቋቋም የቤት ሥራ ተጋርጦባቸዋል፡፡ አንደኛው አያስፈልጉም የሚሉ ወገኖች ትምህርታቸውን በማስፋት ላይ በመኾናቸው ምእመናን ለአክሊል ከበቁ ቅዱሳን ትምህርት የሚያገኙባቸውን ኹነኛ ምንጮች ማብጠልጠላቸው ሲኾን ሁለተኛው ደግሞ ለትምህርት ይኾኑ ዘንድ በየመዘክሩና በየምእመኑ እጅ ቤተ ክርስቲያናችን አብዝታ ያደረሰቻቸው ቅዱሳት ገድላት በመናፍቃን ቅሰጣ እየተከናወነባቸው፤ ያላሉትን አሉ እየተባለና ንባብ ከትርጓሜ እንዲጣላባቸው የመሰረዝና የመደለዝ ክፉ ተግባር እየተከናወነባቸው መኾኑ ነው፡፡

ስለዚህ ክርስቲያኖች የመናፍቃንን ገድላትን የማጣጣል ተግባር ከላይ ያስቀመጥነውን መጽሐፍ ቅዱሳዊና ጥንተ ትውፊታዊ መሠረታቸውን ጠንቅቆ በመረዳት እንዳይሸበሩ ያስፈልጋል፡፡ ስለቅሰጣው ደግሞ መንጋውን እንዲጠብቁ አላፊነት ወደ ተሰጣቸው አባቶቻችን ቀረብ እያሉ ስርዝ/ድልዞቹን ከጤነኞቹ እየለዩ በጥንቃቄ ማንበቡን እንዲያጠነክሩ ያስፈልጋል፡፡


ለመናፍቃን ደግሞ ቅዱሳት ገድላት በክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አላስፈላጊ ነገሮች ናቸው ብሎ የሚያምን ካለ መጻሕፍቱን በመቀሰጥ፣ በመሰረዝ፣ ባዕድ የኾነ ንባብ በውስጣቸው በማተም፣ በማቃጠል፣ በመስረቅና ይህን በሚመሳስሉ ሌሎች የስለላና የደባ ድብቅ ስልቶች ሳይኾን በግልጥ  መጽሐፍ ቅዱስን በአግባቡ በመመርመር፣ አሥራው መጻሕፍት ስለገድላት ያላቸውን ምስክርነት እስከምን ድረስ መኾኑን በማጣራት መሞገት ያሻቸዋል፡፡ በደሙ የዋጃትን የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን ይጠብቅልን አሜን! ስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡