ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ሌላ ምንጭ ለምን?

እንደምን ሰንብታችኋል!የሥርዓት ባለቤቷ፣የአምልኮታችን ማዕከል፣የሀብታችን ኹሉ መገኛ፣ባለሥልጣኑ አምላካችን እግዚአብሔር ይመስገን፤አሜን!

ሠሙኑን አንድ ወንድማችን የድንግል ማርያም ልደት ግንቦት አንድ መኾኑን እንዴት ታውቃላችሁ፤ሲል ጠየቀ፡፡ እነሆም ዛሬ ስለትውፊት መጻሕፍት በጥቂቱ እናወጋለን፤እሊህም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ቤተ ክርስቲያን እንደ ሥርዓትና እምነቷ ምንጭ አድርጋ የምትጠቀምባቸው ገድላት፣ድርሳናት፣መዛግብተ ታሪክ፣ሃይማኖተ አበውና
ሌሎችም የሐዋርያት ትውፊት ናቸው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ የሚባለው ዘመኑ እስከ ፩ሺ፭፻ ዓመት በሚደርስ የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ በተለያዩ አበው ሲጻፉ የኖሩ የሰማንያ አንድ መጻሕፍት ድምር ነው፡፡ እሊህ ታዲያ የታመኑ ምንጮች፣የክርስትና አስተምህሮና ሥርዓት ኹሉ መገኛ አምላካውያት መጻሕፍት ናቸው፡፡ ሥረው መጻሕፍት ወይም አሥራው መጻሕፍት  የሚሏቸውም አባቶች አሉ፡፡ ሥረው ወይም አሥራው  ያሏቸውም “ሥሮች”  ማለት ፈልገው ነው፡፡ ወፍ ብሎ አእዋፍ፣ዕፅብሎ ዕፀው/ዕፅዋት እንዲል ሥር ብሎ ሥረው/አሥራው ይላል፡፡ሥሮች መባላቸውም ለሌሎች መጻሕፍትም ጽኑዕ መሠረት/ሥር ናቸውና ነው፡፡ ከእነርሱ ውጪ ያሉ ኹሉ የትውፊት መጻሕፍት  አዋልድ መጻሕፍት አልያም አዋልደ መጽሐፍ ቅዱስ ይባላሉ፤ይህም በቀጥታ የመጽሐፍ ቅዱስ ልጆች ማለት ሲኾን ልጅነታቸው ልጅ ወላጆቹን መስሎ እንዲወጣ እነርሱም የመጽሐፍ ቅዱስን ያክል የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው መጻሕፍት፣ለበጎ ሥራ እንድንዘጋጅ፣ለተግሣፅና ልብንም ለማቅናት፣በጽድቅም ላለው ምክር የሚኾኑ ፪ኛ ጢሞ ፫፥፲፬ ተብሎ የተመሰከረላቸው ናቸው፡፡

ትውፊት የሚለው ቃል አወፈየ - አቀበለ የሚለው ግሥ/ርባ የተገኘ ባዕድ ከምዕላድ ነው፤ሲኾንም ፍቺው ቅብብል ማለት ነው፡፡ ይህም በቀጥታ በቅብብል የሚተላለፍን አስተምህሮ፣እምነትና ሥርዓት ለመጠቆም ነው ማለት አባት ለልጁ፣ልጅም ለሚወልደው ልጅ፣ያሃም ደግሞ ለሚከተለው እያቀበለ ትውልድ ከትውልድ የታመነውን ትምህርት ሳይበርዙ፤ባለውም ላይ ሳይጨምሩበት፣ከተቀበሉትም ሳያጐድሉ በኃላፊነትና እግዚአብሔርን በመፍራት የሚያወርሱት የእምነት፣የሥርዓትና የትምህርት ውርስ ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ላለው የትውልድ ቅብብል ወይም ውርስ ቀና እና በጎ አመለካከት አለው፡፡ እንዳለውም ታዲያ በብዙ ክፍሉ ላይ ተዘግቦ ከምናገኛቸው አንደኛው በኦሪት ዘዳግም ምዕ. ፴፪፥፯ ላይ ተዘከሮ ለአቡከ፤ወይነግረከ … ልጄ ሆይ! አባትህን ጠይቅ ይነግርህማል፤ያለውተጠቃሽ ነው፡፡ ስለዚህ ልጅ ከአባቱ እንዲማር መጽሐፍ ቅዱስ አደራ ሰጥቷል ማለት ነው፡፡ በዚህ አኳኋን ትውልድ ኹሉ አባትን እየጠየቀ የሚያገኘውን ትውፊት አክብሮ ይኖራል፤የመጽሐፍ ቅዱስም ምኞት ይኸው ነው፡፡

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ዐቃቤ ሰዓት ካብቴ በአንድ ወቅት የቀደሙ አባቶቻችን የሰጡንን ለእነርሱም ሊቃውንት የሰጧቸውን ለሊቃውንትም ሐዋርያነ አበው የሰጧቸውን፣ለሐዋርያነ አበውም ሐዋርያት የሰጧቸውን፣ለሐዋርያትም የፍጥረት ኹሉ ኤጲስ ቆጶስ የሚኾን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጣቸውን የቀናች የሃይማኖት ትምህርትን እንጽፋለን ሲሉ ገልጠዋል፡፡

ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በቃል የተላለፈላቸውን ትውፊት የተጻፈውን መጽሐፍ ቅዱስን ያክል አክብረው ይቀበሉታል፤ሐዋርያው ዮሐንስ ሲናገር በመጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈው ሌላ ጌታ ኢየሱስ ያደረገው ብዙ ሌላ ነገርደግሞ አለ፤ኹሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለናል ዮሐ.፳፩፥፳፭ አለ፡፡ ስለዚህአቅም ገድቦት እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነገረ ድኅነት ከዚህም አብልጦ በነገረን በተደሰተ ነበር፤ቅሉ የሥነ-ጽሕፈት ሕግጋት አገዱት፡፡ በዚህም ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ሳይወሰኑ በቃል የሰሙትንና በትውፊት መዛግብት የተዘገቡትንም በጥንቃቄ ይጠብቃሉ፡፡ ይህንንም ያዘዙ ከሊቀ ካህናችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተማሩ ራሳቸው ንዑዳን ሐዋርያት ናቸው፡፡ እነርሱም በቃላችንም ቢኾን በመልእክታችንም የተማራችሁትን ወግ ያዙ ፪ተሰ. ፪፥፲፭ አሉ፡፡ በዚህ ታዲያ መሠረተ አሳባቸው ብቻ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፉትን ነገሮች ዝርዝር ኹነታቸውን በምልዓትና በስፍሐት ከሚያስተምሩ ከአዋልድ መጻሕፍት ወይም ከቅዱስ ትውፊት እናገኘዋለን ማለት ነው፡፡


ታዲያ ከእኛ መሃል አንዱ ጎበዝ ተነሥቶ የትውልድ ቅብብል የሚባል የለም፤ተዉ! ቢል ኦሪት ዘዳግምን፣መልእክታተ ሐዋርያትና ሌሎችንም አብነቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ዝርዝር ካልሰረዘ በቀር ትምህርቱ የተነቀፈች ትኾናለች ማለት ነው፡፡ በሌላ አባባል መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ በቂ ነው፤መጻሕፍት አበዛችሁ፤ቀንሱ በማለት ለመጽሐፍ ቅዱስ ጠበቃ የኾነለት የሚመስል ቢኖር እርሱ ራሱ የመጽሐፍ ቅዱስን አደራ በማንሻፈፍ ስሕተት ውስጥ ወድቋል ማለትነው፡፡

ለኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ የታመነ ምንጯ ነው፡፡ ከምንጮችም ኹሉ የሚበልጥ ታላቁ እርሱ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በቤተ መቅደስ እርሱ ሲነበብ እንኳ እንደ ሌሎች መጻሕፍት እንደነ ስንክሳር ወይም እንደነ ሃይማኖተ አበው አይደለም፤ይልቁኑ ሥርዓቱ ልብን የሚነካና ቤተክርስቲያኒቱ የሰጠችው ክብርና ልዕልና ምን ያክል መኾኑ እስኪያስደንቅ ድረስ ነው (ጸልዩ በእንተ ወንጌል ካለው የዲያቆኑ ጥሪ አንሥቶ እስከ ሃሌ ሉያ ቁሙ እና የንፍቁ ካህን የሰሚዓ ወንጌል ቡራኬ ያለው የጸሎተ ቅዳሴ የወንጌል አነባበብ ሥርዓትን ያስተውሏል)፡፡

ይህ ማለት ግን መጽሐፍ ቅዱስ ብቸኛው ምንጭ ነው ማለት አይደለም፤አልያም ሌሎች ምንጮች ሊኖሩ አይገባም ማለት አይኾም፡፡ የእምነትና የሥርዓት ምንጭ ሊኾን የሚገባው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ቢኾን ኖሮ መጽሐፍ ቅዱስ መጻፍ የጀመረ ገና በሊቀ ነቢያት ሙሴ ዘመን ነበርና ከዚያ ፊት የነበሩ ሕዝብ እምነትና ሥርዓት አልነበራቸውም ማለት ሊኾን ነው፡፡ እነርሱ ግን ከእምነትም የእኛን የሚያስንቅ እምነት፣ከሥርዓትም የእኛን የሚያስንቅ ሥርዓት ያላቸው እነ ዮሴፍ፣እነ ያዕቆብ፣እነ ይስሐቅ፣እነ አብርሃም፣እነ ኖኅ፣እነ ሄኖክ፣እነ አቤል እስከ አዳም ድረስ ያሉ ሌሎችም አድባር ቅዱሳን ናቸው፡፡ ታዲያ እሊህ ለሚደነቅ እምነታቸውና ደገኛ ሥርዓታቸው ምንጭ ከየት አገኙለት ቢባል ከቅዱስ ትውፊት፡፡

ትውፊት ለክርስትና እምነት እንደ ምንጭ ማገልገል ካልቻለ መጽሐፍ ቅዱስም ይህን ማድረግ ሊያቅተው ነው፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስንም ራሱን ያገኘን አበው አቀባብለውን ነው፡፡ አበው ይህ ነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚባለው ብለው ባያወራርሱን ኖሮ እንዴት ልናውቀው እንችል ነበር፤ነቢያት ወሐዋርያት ሲጽፉት አጠገባቸው የነበረ ምስካሪ ከእኛ መሃል አንድም አልነበረምና፡፡ አንዳንዶች የትውፊት መጻሕፍትን መቀበል ሐዋርያት ያልሰበኩት ዓይነት የሰዎችን ተራ ፍልስፍና ጭምር እንድንቀበል በር ይከፍትብናልና ይቅር ይላሉ፡፡ በርግጥ እንዲህ ያለው በር መከፈቱ የታመነ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የትውፊት መጻሕፍት ብቻ ክፍተት አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም ጭምር እንዲህ ያለው ውሱንነት እንዳለው ከታሪክ እንረዳለን፡፡

የጽርዕ ፈላስፎች የነበሩ ግኖስቲኮች ያስተምሩት የነበሩትን ትምህርት ማስፋፋት እምቢ ሲላቸው የታመኑትን ክርስቲያኖች ትምህርት አስመስለው ለማቅረብ የሞከሩበት አብነት ማሳያ ነው፡፡ ለምሳሌ ያክል በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሐዋርያው የቶማስ ወንጌል እና የማርያም መግደላዊት ወንጌል ብለው የጻፉት ግኖስቲኮች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ታዲያ እሊህን አበው ለይተው መጻሕፍት አምላካውያት አይደሉም ብለው አምላካውያቱን አሰባስበው፣በቀኖና ሠፍረውና ቈጥረው የለዩአቸው ገና በዐራተኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡ እስከዚያ ድረስ ክርስትና በቃል ትምህርት ሲስፋፋኖረ እንጂ መጻሕፍትስ ያሉበትም  አይታወቅ፣በሰው ኹሉ እጅ በምልዓት አይገኙም ነበር፡፡ ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያም ሲናገር በትውፊት ዐርባእቱን ወንጌል ዐወቅኋቸው፤እነርሱም እውነት ናቸው፤አለ፡፡ ስለዚህ ለመጽሐፍ ቅዱስ ትውፊት ያስፈልገዋል ማለት ነው፡፡

ታዲያ ክርስቲያኖች በትውፊት ስም ማንም ፈላስፋ የተፈላሰፈውን ኹሉ ትውፊት ብለን እንዳንቀበል እንደ መጽሐፍ ቅዱስ መሰል  ቀኖና አበጅተንለታል፡፡ የትውፊት ቀኖናዎች እሊህ ናቸው፡፡

፩. ትውፊት ኹሉ ከሐዋርያት ጀምሮ ተያይዞ የመጣና ክርስቲያናዊ ምልክት ያለው መኾን አለበት፤
፪. ከጥንት ጀምሮ በየትም ቦታ በኹሉም ጊዜ በዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን የታመነ፣የተጠበቀና ተግባር ላይ የዋለ መኾን አለበት፤
፫. በዓለም አቀፍ ቤተክርስቲያን ዘንድ መለወጥና መቋረጥ ያልተደረገበት መኾን አለበት፡፡

በእሊህ በሦስቱ ተመዝኖ የወደቀውን ቤተ ክርስቲያን አትቀበለውም፡፡ ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን የተባለች አማናዊት ርትዕት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ስለ እመቤታችንቅድስት ድንግል ማርያም ካወቅነው ብዙውን በሐዋርያት ትውፊት ዐወቅነው፡፡ ልብ ብለን ከተመለከትን መጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፈ ዮዲት፣መጽሐፈ አስቴር፣መጽሐፈ ሩት እያለ በአንዳንድ ሴቶች ስም ምሉዕ መጽሐፍ ሲያስጽፍ መጽሐፈ ማርያም ብሎ በአምላክ እናት ስም አለመጻፉ በርግጥም ከእሊህ ሴቶች አሳንሷት አይደለም፡፡ ከሴቶች ይልቅ ቡርክት ሉቃ ፩ መኾኗን ከተረዳን ታሪኳ በአሥራው መጻሕፍት በምሥጢር፣በትውፊት ደግሞ በምልዓት የተጻፈ ስለኾነ ነው፡፡

የሥርዓት ባለቤት አምላከ አበዊነ ቀደምት እግዚአብሔር ባከበራት በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቃል ኪዳን ይጠብቀን፤አሜን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር ልዑል!