ክርስቲያን ፌስቡክን መጠቀም ያለበት እንዴት ነው? |
ይህ ጽሑፍ በአንድ ወቅት አንድ መንፈሳዊ ማኅበር ላይ የተሰጠ ትምህርት ነው፡፡ በድምፅ ቀድተው ያቈዩት ልዦች ኑረዋል፤ በከፊል በጽሑፍ ተይበው አደረሱኝ፤ ምንም ሳልጨምር ሳልቀንስ (የፊደል እርማት ብቻ ማለፍ ስለማይሆንልኝ አድርጌ) አድርሻችኋለሁ፡፡ እነሆ!
ይህን
ጥያቄ ራሴን ጠይቄው አላውቅም ነበር፡፡
ሁሉም
ሰው ራሱን በፌስቡክ ላይ የሚገልጥባቸው መንገዶች ጠቅለል ሲደረጉ ሦስት ይሆናሉ፡፡ 1ኛው በጣም ቀላሉና ለመረዳት ብዙም ያልተወሳሰበው
በሚለጥፋቸው ልጥፎች (ፖስትስ) ነው፡፡ እነዚህ ሌጣ ጽሑፎች ሊሆኑ ይችላሉ፤ አሊያም ደግሞ ምሥሎች/ሥዕሎች፣ ድምፅ ወምሥል (ቪዲዮዎች)
አሊያም ደግሞ የድምፅ ሰነዶች (ኦዲዮ ፋይልስ - ዕድሜ ለሳውንድክላውድ)፡፡ እነዚህ ሁሉም በዋናቅጂነት ራሱ ለጣፊው የደረሳቸው
ሊሆኑ ይችላሉ ወይም ያጋራቸው፤ ለውጥ የለውም፤ ሁለቱም ስብእናውን ይገልጣሉ፡፡ 2ኛው ራስን የሚገልጥበት መንገድ በመተያየቢያ ሳጥን
(ቻትሩም) ውስጥ ከጓደኞቹ ጋር በሚያደርጋቸው ምልልሶች ነው፡፡ 3ኛው በሚመርጣቸው ጓደኞች ዓይነት፣ በሚወዳቸው ገጾችና (ፌስቡክ
ፔጅስ) እንዲሁም በሚያዘወትራቸው ሌሎች ድረ-ገጾችና መተግበሪያዎች (አፕሊኬሽንስ) ይሆናል፤ ምክንያቱም ፌስቡክ እገሌ ይህን ወደደ፣
ይህን ፈቀደ እያለ ያቃጥራል፡፡ ስለዚህ እኩይ እኩይ ገጾችን ከወደድክ ጠቅለል ባለ መልኩ ምርጫህንና ውስጣዊ መሻትህን ይገልጣል
ተብሎ ይወሰዳል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ገጾችን መውደድ “ላይክ” ማድረግ ከዚያ ገጽ በቋሚነት መረጃ ለማግኘት ሊኾን ይችላል፤ ስለዚህ
እገሌ ዴቪድ ቤካምን ያፈቅረዋል ማለት ላይኾን ይችላል፤ ወይም ቢዮንሴን ወይም ሻኪራን ወዘተ. ይሄ ግን ለምሳሌ ለዝሙትና ለሌሎች
የአመንዝራ ገጾች አይሠራም፤ ወይም አንድ ክርስቲያን ከነዚህ ምንጮች ምንም መረጃ ሊፈልግ አይገባም፤ መረጃው ስለሚታወቅ ማለት ነው፡፡
በእነዚህ
ሁሉ ታዲያ አንድ ሰው ስብእናውን ተደራሽ ላደረጋቸው ሁሉ
ይገልጣል አሊያም ደግሞ ተደራሾቹ ማወቅ በፈለጉ ጊዜ ሁሉ ስብእናው እንደመጽሐፍ
ተከትቦባቸው የሚቀመጥባቸው እንደ መጻሕፍት ገጾች ልንላቸው እንችላለን - መሣሪያዎች ናቸው፡፡
ታዲያ
እንዳልኳችሁ አንድ ክርስቲያን ፌስቡክን መጠቀም ያለበት እንዴት እንደሆነ ራሴን በቀጥታ ሳልጠይቅ ቈየሁ፤ አንዳንድ የማልኮራባቸውን
ልጥፎች እየለጠፍኩም ማለት ነው፡፡ በባሕሪዬ የሰው ክብር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚነካ ነገር ብዙም ማድረግ የማልፈልግ ዓይነት
ስለሆንኩ በጥቂቱ ተርፌያለሁ ማለት እችላለሁ፡፡ ነገር ግን ምንም ዓይነት ነቀፋ የሌለበት ንጹሕ ክርስቲያን ለመሆን ግን ይህ ብቻ
በቂ አይደለም - የሚገዛ ነገር፣ መርሕ ያስፈልጋል፤ የሆነ ቀኖና ወይም ሚዛን ዓይነት፡፡ “ፖስት” የምትለዋን ሰማያዊ ነገር ከመጫናችን
በፊት፤ ልጥፉ እኛን መግለጥ አለመግለጡን፣ ምግባር መጠበቅ አለመጠበቁን፤ ሰዎች ይህን ከእኔ እንዲሰሙት ወይም ከዚህ ልጥፍ ጋር
የእኔ ስም እንዲያያዝ እፈልጋለሁ ወይስ አልፈልግም የሚለውን መዝኖ የሚነግረን ነገር ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ወደክርስቲያናዊ አስተምህሮዎች
ዘወር ብለው ሳያጣቅሱ አይገኝም፡፡
አንድ
ሰው ፌስቡክ ላይ ክርስቲያን መሆን የሚገደደው ለምንድን ነው? (ግዴታው ውዴታዊ መሆኑን ሳንረሳ ማለት ነው)
ክርስትና
ማንነት ነው፡፡ አንድ ሰው ከክርስትና ሌላም ማንነት ሊኖረው ይችላል፤ ኢትዮጵያዊነቱ ማንነቱ ነው፣ ሥሩ፣ ወንድነት/ሴትነቱ ማንነቱ
ነው፣ ወጣትነት ማንነት ነው፣ ሰውነት በራሱ ማንነት ነው፣ ኦሮሞነት፣ ጉራጌነት፣ ትግሬነት፣ አደሬነት ወዘተ. በአጠቃላይ ሰው ራሱን
የሚገልጥባቸው ዳራዎች ማንነት ናቸው፡፡ ማንነት ስንል፤ በአጭሩ አንድ ሰው “ማን ነህ” ሲባል ወይም ራሱን እንዲያስተዋውቅ ሲጋበዝ
ወይም ማስተዋወቅ ባለበት አጋጣሚ ሁሉ ማንነቱን ይገልጡልኛል ብሎ የሚያስባቸው ስብእናውን የቀረጹ፣ ስብእናው የተመሠረተባቸው መደቦች
ናቸው፤ ወይም ደግሞ አንድ ሰው ስለሌላ ሰው ማን መሆን ማወቅ ሲፈልግ ማንነቱን የሚመዝዝባቸው ምንጮች፡፡ ክርስትናም ማንነታችን
ነው ማለት ነው፡፡
ነገር
ግን ክርስትናን ከሌሎቹ ከሁሉም የሚለዩት አንድ ትልቅ ነገር አለ፡፡ ሁሉም ማንነቶች የተወሰነ ቦታ አስፈላጊ የተወሰነ ቦታ አላስፈላጊ
ሲሆኑ ክርስትና ግን በጊዜውም አለጊዜውም፣ በቦታውም አለቦታውም ሁል ጊዜ ተከትሎን የሚሄድ ለአፍታም የማይተወን ማንነታችን ነው፡፡
በዚህ ደግሞ እርሱ ብቻውን ነው፡፡ ልዩ የተለየ ማንነት ነው ማለት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ቅዱሳን ሆይ እያለ
ይጠራቸው ነበር፡፡ ክርስቶሳዊ ማንነታቸው ከምድር ስለሚለያቸው፣ ወይም ለእግዚአብሔር ስለሚለያቸው እንጂ እንደ ባለትሩፋቶቹ አይነት
ቅዱሳን ማለቱ አይደለም፡፡ ስለዚህ ክርስትና በምድርም እንሁን፣ ሰማይ ላይ እንውጣ፣ ማርስ እንሂድ፣ ጁፒተር እንምጣ፤ … አንድ
ቦታ ማንነትህን የገለጠልህ ነገር ሌላ ቦታ ይገልጥልኛል ብለህ የምታቀርበው አይሆንም፡፡ አሜሪካ ብትሄድ ጉራጌነትህ ምንም ማለት
አይሆንም፡፡ መንግሥተ ሰማያት ስትሄድ ኢትዮጵያዊነት ማንነት ሆኖ ተከትሎህ ሊሄድ አይችልም፤ ሌሎቹም፡፡
ሁሉም
የሥጋ ማንነቶች፣ ሥጋን የሚገልጡ ናቸው እንጂ የነፍስም ማንነት፣ ነፍስንም የሚገልጡ አይደሉም፡፡ ክርስትና ግን አንድ ጊዜ “ክርስቶስ
ወልደ እግዚአብሐር ሕያው” ብለን ካመንን ዜግነታችንን ሰማያዊ ጭምር ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ቦታ ክርስቲያን አንዳንድ ቦታ
ኢክርስቱን እንድንሆን አይፈቅድልንም፡፡ ወይም ኢክርስቱን በሆንንበት አጋጣሚ ሁሉ ክርስቲያን የሆንንበትን አብነት አጉድለናል ማለት
ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ ክርስቲያን፣ ፓርቲ ቤት ኢክርስቱን፣ … ጃንሜዳ ክርስቲያን ስቴዲዮም ኢክርስቱን፣ .. በማኅበር
ክርስቲያን በፌስቡክ ኢክርስቱን ልንሆን አንችልም ማለት ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን ፓርቲ ቤት ቢገኝ እንኳን ኢክርስቱን መሆን አይችልም፤
ፓርቲ ቤት ተገኝቶ ግን ክርስቲያን መሆን ይችላል … እንዴት? በጊዜሁ ወዘእንበለ ጊዜሁ ገሥፅ ወተዘለፍ ያለውን የወንጌል አደራ
ተከትሎ እየጮኸ በመስበክ፣ በመገሠፅ፣ አስሰምቶ ዳንኪረኞቹን በመዝለፍና ሰማዕትነትም ከመጣ ተቋቁሞ በመቀበል ክርስቲያን መኾን ይችላል፡፡
ክርስትናችንን ይዘነው የሄድንበት ቦታ ሁሉ ልንወስደው ይገባል፤ ስለዚህ ፌስቡክ ውስጥ ሁል ጊዜ ክርስትናችን ሊገለጥ ይገባል ማለት
ነው፡፡
ፌስቡክ
ላይ ክርስቲያን መኾን ከእነዚያ ከሦስቱ አንዱን ለማየት ያክል በዋነኛነት በምንለጥፋቸውና በምናጋራቸው ልጥፎች ይገለጣል፡፡
እነዚህን
ነጥቦች አስተውሉልኝ፡፡
1. የሰውን ክብር የሚነኩ ልጥፎች -
የመዠመሪያው ይህ ልጥፍ በሕይወት ከኖሩም ሆነ ከሚኖሩ የሰው ልዦች (የአዳም ዘሮች) በሙሉ
ክብሩን የሚያቃልልበት ይኖር ሆይ ብሎ መጠየቅ ነው፡፡ ጓደኛ ሊሆን ይችላል፣ ወዳጅ፣ ቤተሰብ፣ ታዋቂ ሰው፣ አሜሪካዊ፣ አውሮጳዊ፣
ኳስ ተጫዋች … የሥላሴን አርአያና ምሳሌ ይዞ የተፈጠረን ፍጡር ከክፉ ተግባሩና ከሥራው ይልቅ ተፈጥሮውን የሚሳደቡ ወይም የሚያንቋሽሹ
ልጥፎች (ቆንጆ ምሳሌ የሚሆነን ኳስ ተጫዋቹ ሉዊስ ሱዋሬዝ የተናከሰ ሠሙን ሁላችንም የለጠፍናቸው ልጥፎች ናቸው - እኔ ኅሊና ስገዛ
ቶሎ ብዬ አጥፍቻቸዋለሁ/መማርም ጥሩ ነው) የእንግሊዝን ብዙኃን መገናኛ ተከትለን ሆይ ሆይ ያልናቸው ምሥሎች በሙሉ ሰውየውን በአውሬ
አምሳል የሚሥሉ ነበሩ፤ ቴክኖሎጂው ስለተገኘና ለመሥራት ቀላል ስለሆነ ብቻ ምንም ነገር መሥራት የለብንም፡፡ መዠመሪያ ክርስቲያናዊ
ሕይወታችንና ክርስቲያናዊ ማንነታችን ያን ልጥፍ ይደግፈዋል ወይ ብሎ መጠየቅ አለብን፡፡ በዚህ ቀኖና/መለኪያ መሠረት ልጥፎቻችንን
ከቃኘናቸው ከአዳም ዘር በሙሉ አንድስ ስንኳ በእኛ ላይ ነቀፌታ የሚኖረው አይኖርም ማለት ነው፡፡
በነገራችን ላይ ስለሰዎች ክብረ ቢስ ልጥፎችን ስንለጥፍ ስብእናችንን የሚያዋርድብንና የሚያስንቀን
በተለጣፊዎቹ ሰዎች ዘንድ ብቻ አይደለም፤ ልጥፉን የሚያይ ሰው ሁሉ ሚዛን ላይ ያስቀምጠናል፡፡ ስለዚህ ራሳችንን አሳልፈን ለሚያዩን
ሰዎች ሁሉ ዳኝነት ሰጠን ማለት ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ መተዉስ ምን ከፋ? በጣምም ቧልተኛ፣ ከልክ በላይ ቀልደኛ፣ እና በሰዎች መልካም
ስምና ጥሩ ዝና ላይ ርሕራሔ የሌለው ጨካኝ ተደርገን በሰዎች እንዳንሣል መጠንቀቅ አለብን፡፡ የሚከታተሉን ሰዎች ያን ነገር ከክርስትናችን
ጋር፣ ወይም ከጽዋ ማኅበረተኛነታችን ወይም ከሰንበት ተማሪነታችን ጋር ሲያጣምሩት ስለምናምነው አምላክ በጎ ያልሆነ መልእክት ስለሚሰጣቸው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በእናንተ ክፉ ተግባር ምክንያት የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ ዘንድ እየተብጠለጠለ ይገኛል ይላቸዋል፡፡
ለምሳሌ ሠሞኑን አንድ ፓስተርና አቀንቃኝ የሆነ ግለሰብ በሆነ ኃጢአት ተገኘ አሉ፡፡ ይህን
ታሪክ ለሌሎች ሰዎች ማጋራት ምን ያክል እንደሚያቋምጥ አስቡት፡፡ ደስ ይላል፤ አይደል? ጉዳቸውን ማውጣት፡፡ … የዚህ ልጥፍ ብቸኛው
ዓላማ ዜናውን ለሌሎች መንገርና ሰውየው እንዲዋረድ ብቻ ከሆነ ክርስትናችንን አይገልጠውምና ከማይበረታቱት ልጥፎቻችን ውስጥ አንዱ
ይሆናል፡፡ በሠፈርከው ቁና ማለት ነገ አንዱ ጳጳሳችን ወይም ዲያቆናችን በዚህ ግብር ቢገኝ ጓዳ ልንገባ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ
ደረጃ አውጪዎች አንሁን፤ ይህ ፈረንጆች “ስታንዳርድ” የሚሉት
ነገር፡፡ ዜናው በፍጹም አይጋራም ማለት አይደለም፤ ለምሳሌ ይህ ዝንባሌ በጣም እየተለመደ ከመጣና ብዙዎች ሰለባ እየሆኑ ከሆነ መፍትሔ
ወሳጅ አካላትን ለማንቃት አሊያም ብዙኃኑን ለማስገንዘብ በሚል ጠቅለል ተደርጎ ዜናው ሊቀርብ ይችላል - ለማስጠንቀቅ፡፡ ከዛ በተረፈ
ግን እኔ የፌስቡክ ጽሑፍ የምጽፍበት ጊዜ ካለኝና የምለጥፍበት አጋጣሚ ካገኘሁ ለምንድነው ስለአንድ ተራ መናፍቅ ውዳቂ ወሬ እያወራሁ
ጊዜ የማባክነው? ምሥጢረ ሥላሴን ማን ይናገርልኝ? ሥጋዌን ማን ይናገር? ይሄ ሰውዬ ማን ስለሆነ ነው እኔ የማወራለት ወይም ጊዜየ
የሚገባው ማን ስለሆነ ነው፡፡
2.
ከንቱ ብሶትና የቅሬታ መአት -
አንዳንድ ጊዜ ንጹሕ የሚመስሉን ነገር ግን ክርስቲያናዊ ስብእናችን ላይ አንዳች ጥቁር
ነገር የሚረጩ ልጥፎች አሉ፡፡ አዘውትረን “ቀኑ ደበረኝ” “የተረገመ ቀን” “ሆዴን ባር ባር አለው” ወዘተ እያሉ ለኢንተርኔት ማኅበረሰብእ
መለጠፍ -- ጥቅም ሊኖረው ይችላል (አሁን ለእኔ ሊገለጥልኝ ያልቻለ) - የሚረባ ጥቅም ግን የለውም፤ ስለዚህ አንድ ክርስቲያን
ሊያደርገው አይገባም፡፡ አሕዛብም ብሷቸው እኛም ብሶን -- በክርስቶስ ማመናችን ትረጒሙ/ጭማሬው ምን ላይ ሊሆን ነው፡፡ በክርስቶስ
ማመናችን አንገታችንን ቀና ካላደረገው፣ የነጻነትና ደስ የመሰኘት ስሜትን ካልሰጠን ምን ለውጥ አለው፡፡ እኛን የሚያነቡ አሕዛብ
መንፈስ መርቷቸው ማኅበራችንን መቀላቀል ቢፈልጉ እንኳን የሚቀላቀሉት ድንኳን ምን ዓይነት እንደሚሆን እየሣልንላቸው ነው፤ ፌስቡክ
ላይ፡፡ የማያቋርጥ ብሶትና የሆድ ባርባርታ ድንኳን ከሆነ ማንም ሊቀላቀለን አይፈልግም፡፡ ክርስቲያን ነን ብለን ካወጅንና ክርስትናችን
ከታወቀ በኋላ የምናደርጋት እያንዳንዷ እንቅስቃሴ ሁሉ ከምናመልከው አምላክ ጋር እየተጣመረች እንደምትነበብ እናስተውል፡፡
ከእስልምና ወደ ክርስትና የተለወጠች አንዲት ግብፃዊት ሴት ያለፈ ታሪኳን ስትተርክ “ክርስቲያኖችን
ሳያቸው ሁል ጊዜ ደሜን የሚያፈላውና ውስጤን በፍርሐት የሚመላኝ ነገር ቢኖር ፊታቸው ላይ የሚነበበው ሰላም፣ ጸጥታ፣ እርጋታና በራስ
መተማመን ስሜታቸው ነው” ትል ነበር፡፡ መጨረሻዋ ግን ኦርቶዶክሳዊት የተዋህዶ እምነት አማኝ ሆና መጠመቅ ሆነ፡፡ አታማርሩ! ደስ
ይበላችሁ በቃ፤ የዓለም ሕይወት ላይሞላ ይችላል፤ ሁሉም ነገር ላይሰምር ይችላል፤ እግዚአብሔር ዝም ብሏችሁ ሊሆን ይችላል፤ የጸለያችሁት
ተደምጦ ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በሰጠን በትንሽየዋ ነገር ደስ ይበለን፡፡ የሐዲሳት መጻሕፍትን ልብ ብለን ካነበብን
እለት እለት ቤዛነቱን፣ መድኃኒትነቱን፣ አቸናፊነቱን እያስታወስን ደስ እንድንሰኝና ስለውለታውም እንድናመሰግነው እንጠየቃለን፡፡
እለት እለት ሞቱን፣ ትንሣኤውን፣ ቤዛነቱን እያሰበ የሚኖር ክርስቲያን ደግሞ “ተደበርኩ” “ተሰላቸሁ” እያለ ሰው መነዝነዝ የለበትም፤
ቢቻል ሁሉም ሰው ደስታችንን ብቻ ቢሰማ ጥሩ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ልጥፎች በክርስትናችን ምክንያት የተሰጡንን ወንጌላዊ አደራና
ለአሕዛብ ነፍስ በመራራት በብርሃን ልንሰብክ የሚገባን ደቀ መዛሙርት መሆናችንን የረሱ ዝንጉ ልጥፎች ናቸውና ሊታረሙ ይገባል፡፡
3.
ክፉ አመልንና ስድነትን ገልጠው የሚያሳዩ ልጥፎች -
መቼም ጠላት የሞት መንገዶቹ ብዙ ናቸው፡፡ የጠላት የሞት ድግሶች ብዙ ናቸው፤ ታዳሚዎቹም
ብዙዎች፡፡ ታዲያ አስገራሚው ነገር ታዳሚዎቹ የሰው ልጆች የሞትን ድግስ ስንታደመው የምንታደመው ትድምት የሞት መሆኑን ማወቅ አይደለም
መጠርጠር እንኳ አለመቻላችን ነው፡፡ እንደጥሩ እንግዳ ተስተናግደው ብቻ መውጣት፡፡ በአንድ ወቅት በእኛው በዚህ ማኅበር ልዦች እኅቶቻችን
የሚለጠፉ ልጥፎች ዐይንን በቃሪያ ጥፊ የሚማቱ ነበሩ፡፡ አንዲት ክርስቶሳዊት እኅት እንደዚህ ባለ አለባበስ፣ እንደዚህ ባለ አኋኋን
ፌስቡክ ላይ ለመውጣት ብዙ ደረጃዎችን ማለፍ አለባት፡፡
መዠመሪያ ያን የለበሰቸውን ቁራጭ ጨርቅ ልብሴ ብላ ከልብሶቿ መዘርዝር መክተት አለባት፤
ከዚያ በሆነ አጋጣሚ ይህን ነው የምለብሰው ብላ መወሰን፣ ከዚያ ኅሊናዋም፣ የተማረችው ያ ሁሉ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት፣ እጆቿም፣
ሰውነቷም ሊተባበሯትና ልትለብሰው ይገባል፤ ከዚያ ወጥታ አውራ ጎዳና ላይ የሰውን ትዝብት ገጭቶ የሚመልስ ልቡና፣ ከዚያም ፎቶ ፊት
በልበ ምሉዕነት መቆም፣ ከዚያ ፎቶውን መለጠፍ፡፡ መቼም በእነዚህ ሁሉ ሂደቶች ውስጥ የሆነች ዓይነት ትንሽ የኅሊና ወቀሳ ውልፍ
አላለችም ማለት አይቻልም፡፡ ቢቻል በአንዳቸው ደረጃዎች የሚገዳደረንን ኅሊና በጀ ብለነው ነገሩን ብናቆም፤ ባይቻል ግን የዚህ ጽሑፍ
ዓላማ የፌስቡክ ምግባር ስለሆነ ስንለጥፈው ጥያቄ ራሳችንን እንድንጠይቅ፤ (ሁላችንም ተመክረን የቀናን የቤተ ክርስቲያን ልዦች ስለሆን
ምክርን መስማት ጥሩ ነው ያቀናናል፤ እኛ ምክር በመስማታችን ተጠቅመናል - እኔም ተው ተብዬ የተውኩት የሆነ ሱሪ ነበረኝ - ክፋቱን
አልነቃሁበትም ነበር፡፡ አንዳች የሚነቀፍ ነገር ሊኖርብን መቻሉ ሰው መሆናችንን ያረጋግጥልን እንደሁ እንጂ ክፉ አይደለም፤ ፍጹማን
ብንሆን ቦታችን የጽዋ ማኅበር ወይም ሰንበት ት/ቤት አልነበረም፤ ከነ ቅዱስ ሄኖክ ጋር፣ ከነ ቅዱስ አቤላክ፣ ከነ ቅዱስ አረጋዊ
ጋር ብሔረ ሕያዋን በሆን ይቻል ነበር፡፡)
4.
ለዓለማውያን የማይገባቸውን ሰፊ ቦታ የሚሰጡ ልጥፎች -
ለዓለምና ዓለማውያን እንዲሁም ዓለማውያን ለሆኑ ነገሮች የምንሰጠውን ዋጋ የሚያካርሩ
(ፈረንጆቹ “ኦብሴሽን” የሚሉት አይነት) እኔ “መነደፍ” እለዋለሁ፤
በምድራዊ ነገር ፍቅር መነደፋችንን የሚያሳብቁብን ልጥፎች፡፡ ስፖርት ልንወድ እንችላለን፤ ስፖርት መውደድና መደገፍ ኃጢአት ነው
ወይስ አይደለም የሚሉ ሙግቶች በትልልቅ መድረኮች ጭምር እንደተነሡ አስታውሳለሁ፤ ችግር የለውም ከሚሉ መምህራን አንሥቶ ጥንቅር
አድርጋችሁ ተዉት በደረሰበት አትድረሱ የሚሉም መምህራን አሉ፡፡ ሁለቱም ጥሩ ጥሩ ጥቅሶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ይጠቅሳሉ፤ .. ሁሉንም
ተዉት (ስፖርት መውደድ ችግር አለው ወይስ የለውም የሚለውን ርእሱን ለሌላ ቀን እናቈየውና) በስፖርት ፍቅር መነደፍ ግን አይፈቀድልንም፤
እንደ አንድ ክርስቲያን፡፡
የክርስትና ትምህርት መሠረቱ ዓለምንና ዓለማውያንን በመናቅ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ዓለምንም
ክርስቶስንም እኩል ልንወዳቸው አንችልም፡፡ ሁለቱ አብረው ሊሄዱ አይችሉም አንዱ የአንዱ ጠላት ነው፡፡ ክርስቶስ የዓለም ጠላት ነው፤
ቢጠላውም ነው ሊቀይረው፣ እንደአዲስ በደም ሊሠራው የመጣው፡፡ ለዓለምም ጥሩ ትምህርት ይዞ አልመጣም፣ ሃብትህን ሸጠህ ተከተለኝ፣
ሁለት ጥብቆ እንኳን አይኑርህ እያለ ነው የመጣው፤ ስለዚህ ዓለምም ወዳጁ ሊሆን አይችልም ገድሎ ሰቅሎታል፡፡ ክርስቶስን ገድሎ ከሰቀለ
ዓለም ጋር አንድ ክርስቲያን ቅልልልጥ ያለ ፍቅር ውስጥ ሊገባ አይችልም፡፡
የሰው ልዦች በምድር ሳለን በጊዜ ሥርዓት ውስጥ የምንተዳደር ፍጥረቶች ነን፤ ማለት በጊዜና
በቦታ ሕጎች የምንተዳደር ነን፡፡ በጊዜ ጊዜ ይገድበናል፤ በቦታም በአንዴ ሁሉም ቦታ ልንገኝ አንችልም፡፡ የዚህን (ስፓሺዎቴምፖራል
ትወራ) ዝርዝር እንተወውና ለክርስትናችን ምን ይተርፈዋል የሚለውን እንይ፡፡ በአጭር ቋንቋ ለክርስቶስ የሆንነውን ያክል ለዓለምም
ለዓለማውያንም ደግሞ ጨምረን ልንሆን አንችልም፡፡ ማለትም ለዓለም የምንተጋላትን ያክል ትጋት ለእግዚአብሔር ከምንተጋለት ትጋት ካልቀነስን
በስተቀር ከየትም አናመጣላትም፡፡
ትጋት የምንለው 1ኛ ፍላጎት ማሳደር 2ኛ ጊዜ መሠዋት፣ 3ኛ ሌሎች ጥሪቶችን (ገንዘብ
ጉልበት …) መሠዋት፣ 4ኛ ውለታን አለማቊጠርና 5ኛ ዋጋ መጠበቅ ናቸው፡፡ ለዓለም ተጋን ሲባል እኒህን ሁሉ ሰጠን ማለት ነው፤
እኒህ ግን የተትረፈረፉ አይደሉም፤ ወይም በበቂ ሁኔታ የሉንም፤ ስለዚህ ፕሪሚየር ሊግ ማየት ከፈለግን መርሐ ግብር መቅረት አለብን
… ወይም ኢትዮጵያ ስትጫወት ማየት በጣም ከፈለግን ሰዓታት ማደሩን ትተን ቲኬት ተሰልፈን ማደር አለብን ወዘተ.፡፡ ይሄ ነው ለዓለም
በተጋንላት መጠን ከክርስቶስ ላይ ትጋት እንቀንስበታለን ማለት፡፡ ስለዚህ ምን እናድርግ ዓለሙን ሁሉ፣ ቤተሰቡን፣ ትዳሩን፣ ልዦቹን፣
ጓደኞችን፣ ቤተዘመዱን ሁሉን ትተን ቤተ ክርስቲያን እንዋል እንደር? በፍጹም፡፡ ነገር ግን ዓለም ከምትዘረዝርልን ትጋታችንን ጠያቂ
አካላት ሁሉ ተቀዳሚነት ላላቸው ጥቂት ነገሮች ብቻ በልኩ እንትጋላቸውና በቀረው ለክርስቶስ እንትጋ፡፡
5.
ምንም መልእክት የሌላቸው ልጥፎች -
አንዳንድ ልጥፎች ቢታዩ ቢታዩ ምንም ምን ነገር የማይመስሉ፣ ተነብበው ተነብበው ዐራት ነጥብ ጋር
ሲደርሱ የሚጨበጥ አንዳች ዓይነት ነጥብ/ትርጒም የማያልፍባቸው ይሆኑና ግር ይላሉ፡፡ ስለፌስቡክ ልጥፎች አንድ ማወቅ ያለብን ነገር
ሲበዙ ጥሩ አለመሆናቸውን ነው፤ ወይም የሆነ ዓይነት “ልዩ”ነት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወይም በሆነ መንገድ ለታዳሚዎቻቸው ጣዕም የሚሰጡ
ወይ የሚያዝናኑ፣ ወይ የሚያስተምሩ፣ ወይ መልእክት የሚሰጡ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ሁል ጊዜ ቊምነገረኛ ብቻ ይሁን ማለት አለመሆኑን
ያስተውሏል፤ ለዚያ ነው የሆነች ዓይነት ትንሽም ብትሆን መልእክት ትኑረው የሚባለው፡፡ በተራ ተርታ ልጥፎች ሰዉን አሰልችተነው ፍሬ
ያለው ነገር ስናገኝ ሳንታይ እንዳንታለፍ መፍራት ነው፡፡
6.
ካልታየሁ፣ ካልተነበብኩ ባይ ልጥፎች -
ፌስቡክ ተጠቃሚዎች ሁላችን እጅግ አድርገን ልንጠነቀቅ የሚያስፈልገን ነገር ብዙ የመታየት ረሃብንና
ብዙ የመደነቅ ጥማት/ጥሜትን ነው፡፡ ብዙ ሰው ጋር ለመድረስ መጣር እና ብዙ ላይክ ማግኘት ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ያሃ
ብዙ ታዳሚ ማበርከት፣ ጥሩን መልእክት ብዙ ሰው ጋር እንዲደርስ መዘየድ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ሕልም ነው፤ ዝም ብሎ ቅዠት፡፡ ብዙ
ላይክ ለማግኘት ብቻ ተብሎ አይለጠፍም፤ ይሄ መሣሪያ ነው እንጂ በራሱ ብቻውን ትልም ሊሆን/ዒላማ ሊሆን አይችልም፡፡ ልጥፉ ለማስተላለፍ
የሚፈልገው አንዳች መልእክት - ገዢ አሳብ ሊኖረው ይገባል፡፡ ያለበለዚያ ብዙ ላይክ የሚያስገኘውን ከፈለግን አጓጕል የሆኑ ነገሮችን
በግድ እንድንለጥፍ ሊገፋን ይችላልና መጠንቀቅ ነው፡፡
7.
አሕዛብ ታዳሚዎቻችንን ታሳቢ ማድረግ -
ክርስቲያን ሁል ጊዜ መስበክ አለበት፤ ሁል ጊዜ፡፡ በጊዜውም ያለጊዜውም ስበክ አስተምር
ተብለናል፡፡ ስለዚህ ክርስትናን ለአማኒ የምንናገረው ኢአማኒ ፊት ግን ትንፍሽ የማንለው ነገር አይደለም፡፡ ከእኛው አንደበት ሁሉም
ሰው ክርስትናን ሊሰማው ይገባል፤ ይህ እንዲሆን ደግሞ ማረጋገጥ ይጠበቅብናል፡፡ ነገር ግን አሕዛብ የሚስሰበኩበትና አማንያን የሚስሰበኩበት
መንገድ አንድ አይደለም፡፡ ሲዠመር አማንያንን ማጽናት፣ ማጠንከር፣ ማስገንዘብ እንጂ እንደአዲስ መስበክ አይጠበቅብንም፤ ያን ደረጃ
ተላልፈውታልና፡፡ አሕዛብ ግን በስልት/በዘዴ ነው የሚስሰበኩት፡፡ አሁን አሁን የተለመደው ይሄ “እናሲዝ ታማልዳለች!” አይነት
… ፕሮፖጋንዳ ሳይሆን -- አንድ ክርስቲያን እኮ አንዲትን ነፍስ ለማዳን መዠመሪያ ሊያድናት ስላቀዳት ነፍስ ስስትና ጥንቃቄ መውደድ
ሊኖረው ይገባል፤ ፍቅር፡፡ የሰውየውን ደመነፍስ ቱግ በሚያደርግ ነገር ፍሕም ካደረግነው በኋላ የትኛውን ወንጌላችንን ታግሦ እንዲሰማን
ነው የምንፈልገው? አንዳንድ ጊዜ እውነት ወንጌልን ለመስበክ ወይስ ሰው ለማናደድ ብለን እንደምንናገር ግራ ያጋባል፡፡ ለመሳደብ
ከሆነ ክርስትና ሳይሆን ጀብደኝነት፣ “ሌላ ግሩፕ” ውስጥ ነው ያለነው ማለት ነው፡፡ ክርስትና እንደ ዘር አይደለም - እኛና እነሱ
ተባብሎ የሚወራወሩበት (አሕዛብን ወንጌል መስበክ ራሱ ሰፊ ርእስ ስለሆነ ይህንም እናቈየው)
በፌስቡክ ላይ ለአሕዛብ የምንወስዳቸው መሠረታውያን ጥንቃቄዎች አሉ፡፡ 1ኛ በቀጥታ እነርሱን ተደራሽ
የሚያደርጉ ልጥፎቻችንን -- ከቻልን ልናውቅባቸው፣ ካላወቅን እስክናውቅ ልንተዋቸው ይገባል፡፡ በቀጥታ እነርሱ ላይ ያነጣጠረ ልጥፍ
አለመለጠፍ፡፡ 2ኛ የአሕዛብን ሃይማኖት የሚያብጠለጥልና እኛ በምናምነው እምነት ላይ ቀጥተኛ የሆነ አጸፋን ግድ የሚያስብሉ ልጥፎችን
ፈጽሞ መተው፤ ሃይማኖታቸውን ካንቋሸሽከው እኮ ... የአንድ ክርስቲያን ትልቁ በትሩኮ ሰዎች ለርሱ ያላቸው በጐ የኾነ አመለካከት
ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ሃይማኖትን ሲሰብክ ልብ ሊነካ የሚችለው፡፡ ሰውን በጠላትነት ካስነሣ በኋላ ሃይማኖትን መስበክ ሃይማኖትን
ማስነቀፍ ነው፡፡ 3ኛ መልካም ምኞትን ስንመኝላቸው - ለበዓላት ወዘተ. ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ ምኞታችንን የምንገልጥባቸው ቃላት
እኛን የነሡ ሃይማኖት ውስጥ የሚጐትት ምኞት አለ፤ “ረቢ ሰለላ.
.. ወሰለም” ምናምን እያሉ መመኘት፤ ምን ማለት መሆኑን ምን ታውቃለህ አንተ? እውነቱን ለመናገር አንተ ክርስቲያን ነህ፡፡
በቃ ሌላ ምንም አይደለህም፡፡ ማንም ካንተ ዐረቢኛ ምናምን የሚጠብቅ ሰውም የለም፡፡ የጌታ ኢየሱስ ልደት እለት “መልካም ገና!”
የሚል መደዴ የሆነ መልእክት እየላክልኝ የመሐመድ ልደት ለት በዐረቢኛ ብትቀባጥር ቀላወጥክ እንጂ ጥሩ ሰው ሆንክ አያስብልህም፡፡
“እንኳን ደስ አለህ” “መልካም በዓል ይሁንልህ” እና ሌላ ሥነ-መለኰታዊ ወይም ሃይማኖታዊ ፋይዳ የሌላቸው ምኞቶችን በአጭር የስልክ
መልክትም ቢሆን በፌስቡክም ቢሆን መመኘቱ ልቡናቸውን ቀና ያደርጋል፤ እንጂ ሃይማኖቱን ሃይማኖትህ እንድታደርግ አትገደድም፡፡
በጣም ብዙ ነው፤ ቶሎ መጨረስ ስላለብን በአጭሩ ፌስቡክን ስንጠቀም አንደኛ ክርስትናችን
እንዲገለጥ ያስፈልጋል፣ ሁለተኛ ክርስትናችን በበጎ እንዲገለጥ ሆን ብለን ተዘጋጅተን የምናደርጋቸው ነገሮች ሊኖሩ ይገባል፤ ሦስተኛ
ክርስትናችን በክፉ እንዳይገለጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፤ ይቈየን፡፡