በጾም የሚገኘው ትልቁ ቊም ነገር …



ኢትዮጵያዊ ባሕታዊ በጾምና በጸሎት

በጾም ምክንያት የሚገኘው ትልቁ ስጦታ ራስን በመግዛትና የሥጋን መሻት በመዋጋት (fighting temptations) የመንፈስ ጽናትና፣ የነፍስ ብርታት ነው፡፡ ጾም ማለት ክርስቲያኖች መከራ ቢኖርም ባይኖርም ወድደው ወደስብእናቸው የሚያመጡት መከራ ነው፡፡

የሰው ልዥ ደካማ ፍጥረት ነው፤ ሥጋው ሲደላው ሞራሉ ይወድቃል፤ ሆዱ ሲሞላ መንፈሱ ስልቹ ይኾናል፤ የሥጋው መሻት ሞልቶ ጨ…ቅ… ሲል ጠባዩ ልውጥውጥና ኃይለኛ ይኾናል፡፡ እግዚአብሔርን መናቅና ማቃለል ይዠምራል፡፡ ያዕቆብ በኦሪት ዘዳግም ላይ እንደምናነበው “የላሙንም ቅቤ፥ የመንጋውም ወተት፥ ከጠቦት ስብ ጋር፥ የባሳንንም አውራ በግ፥ ፍየሉንም፥ ከስንዴ እሸት ጋር በላ፤ ከወይኑም ደም ያለውን ጠጅ ጠጣ። ይሹሩን ወፈረ፥ ረገጠ፤ ወፈረ፥ ደነደነ፥ ሰባ፤ የፈጠረውንም እ.ግ.ዚ.አ.ብ.ሔ.ር.ን. ተ.ወ.፤ የመድኃኒቱንም አ.ም.ላ.ክ. ና.ቀ.።” ይላል ዘዳ. 32፣14-15 በልማዳችን እንኳ ትዕቢተኛውን ሰው “ጠግበሃል!” አይደል የምንለው፤ የጠገበ ሰው ሥጋዊ የአተያይ አንጻርን ይጠቀማል፡፡ የአእምሮው መመዘኛ ሚዛን፣ ንግግሩ፣ ዓላማው፣ ብሂሉ ኹሉ ከወንጌል የተራቆተ፣ በፍቅር ያልተቃኘ ሥጋዊ ይኾናል፡፡ መስመሩን የጠበቀ
ስለኾነ በክብር እንጂ በፍቅር እንዲዛመዱት ለማንም ሰው አይፈቅድም፡፡ ፍቅር የሚባል ነገር ለሰውም አይሰጥም፤ ከሰውም አይቀበልም፡፡ ፍቅር በተወራችበት ቦታ እንደተወራች እንኳ አያውቅም፡፡ በጨሰችበት ቦታ መዓዛዋ አይሸተውም፡፡ የጠገበ ሰው እግዚአብሔርን ያቀልላል፤ እግዚአብሔርን ያቀለለ ኃጢአትን ይዳፈራታል፡፡ ኃጢአትን የተዳፈረ በእርኲሰት ረመጥ ውስጥ ይኖራል፡፡

ክርስቲያን ግን ርኲሰትን ስለሚጠላ ከኃጢአት ራሱን ይጠብቃል፡፡ በጊዜአት ኹሉ ኃጢአትን መጸየፍ ስላለበት ለዚህ እንዲያመቸው እግዚአብሔርን ይፈራል፡፡ እግዚአብሔርን እንዲፈራ ደግሞ ራሱን ከጥጋብና ከሥጋዊ ምልዓት እንዲሁም መትረፍረፍ ይከለክላል፡፡ ይህን እንዲችል ደግሞ በጾም ያመክራል/ይለማመዳል፡፡ በጊዜአት ኹሉ ሰውነቱን መግዛትና መቈጣጠር ፣ ጭምትም መኾን ስላለበት ራሱን ይጎስማል፤ ይህንንም ይለምደው ዘንድ በጾም ያመክራል - ለሌላም መከራ ቢኾን ራሱን ኾን ብሎ ይሰጣል፡፡ መከራ እርሱን ቢሸሸውም እርሱ መከራን ፈልጎ ያገኘዋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “የሚታገልም ኹሉ በነገር ኹሉ ሰውነቱን ይገዛል፤” ይላል 1ኛ ቆሮ. 9፣26፡፡ እርሱም ራሱ “ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ ደግሞ የተጣልኩ እንዳልኾን ሥጋዬን እየጐሰምኩ አስገዛዋለሁ” ይላል 9፣27፡፡ ይህም ክርስቲያን በራሱ ጊዜ ወድዶና ፈቅዶ ሥጋውን ለመከራና ጒስቊልና እየዳረገ ሥጋው እንዳይፈነጥዝ ይለጉመዋል ለሚለው ትምህርት ምንጭ ኹኗል፡፡

ጾም ከነዚህ ልጓሞች አንዱ ነው፡፡ ሥጋችንን ለድካም አሳልፈን ስንጥለው፤ ነፍሳችን ጭምት ትኾንልናለች፡፡ የነፍስ ጭምትነት ደግሞ ለዲያብሎስ ኃይለኛ ፍላፃው ነው፤ እርሱን አይቶ መቆም አይችልም፡፡ ትሕትና፣ አፍቅሮ ቢጽና፣ ምስጋና ባሉበት ቦታ መቈየት ይጠዘጥዘዋል፤ ይሸሻል፡፡ ክርስትና ዘራፍ ብለን ዘምተን የምንረታበት ሳይኾን ደክመን የምናሸንፍበት ሕይወት ነው፡፡ ደክመን፣ ወድቀን፣ ተሸንፈን ድል የምንነሳበት ነው፡፡ ራሱ ቤዛ ዓለም ኢየሱስ እየደከመ ሞትን ጉድ አደረገው፡፡ እየተገረፈ አሸነፈ፤ እየተጸፋ አየለ፣ እየተተፋበት ነገሠ፡፡ እየሞተ ገደለ፡፡ ሳይዘምት ድል የነሳ፣ ሳይሰነዝር ያደቀቀ፣ ሳይሳደብ ያበሸቀ፣ የመዠመሪያው ተዋጊ መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ሳይወረውር ያሳመመ፣ ሳያቀባብል የማረከ፡፡ “ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ! ሲዖል ሆይ ድል መንሳትህ የት አለ!” እያልን ክርስቲያኖች በሞትና በሞት ፊታውራሪዎች ላይ እንድናላግጥባቸው ያደረገንን ክብር የሰጠን የእርሱ ላቡ ነጥቦ፣ ደሙ ተንጠባጥቦ ነው፡፡ 1ቆሮ.15፣55 ሥጋና ደም ባልኾኑት በአጋንንት ላይ፣ የዚህ ዓለም ገዢዎች በኾኑት በአስፈሪዎቹ የሞት ሹማምንት ላይ እንድናሾፍባቸው አደረገን፡፡ ስለዚህ ሳጥናኤል ትሕትናና፣ መታዘዝ፣ ጭምትነት አሲድ ኹነው እንደመዘመዙት ስለሚያስታውስ ዛሬም የክርስቲያኖች ኹነኛ መሣሪያቸው እኒሁ እኒሁ ይኾናሉ ማለት ነው፡፡ ጾም ሥጋን ታደክማለች፤ የነፍስን ቊስል ታሽራለች፡፡

የሰባቱ አጽዋማት ፍርቅርቅታው አንድ ዓይነት ክርስቲያናዊ የሕይወት ዘይቤ እንዲሰጥ ተደርጐ የተደዘነ ስለኾነ እጅግ ደስ የሚያሰኝ ሐዋርያዊ ልማድ ነው፡፡ አቤቱ እኔን ወንበዴ ኃጢአተኛህን ተቀበለኝ፤ አሜን!