የ“ቤርያ” ክርስቲያኖች እውነት “በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” የሚያምኑ ነበሩን፤

ዱባይ ውስጥ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም “ኦርቶዶክስ” ተብሎ እንዲሁም በሊቀ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ስም የተጠራ ቤተ ክርስቲያን አለ፡፡ ሰዎቹ ብዙዎቻችን በፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ዓላማቸው የምናውቃቸው  አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡ የምንፍቅና መርዛቸውንም ሲተፉበት ቈይተዋል፤ አሁን አሁን ደግሞ ትፋታቸው ቀስ በቀስ ገሃድ እየወጣ ይገኛል፡፡ በዚያ ከተማ የሚኖሩ ብዙዎች የዋሐን የተዋሕዶ ልዦች ሳያውቁት ከእነርሱ መንፈሳዊ ንቃተ ኅሊና በላይ ኹኖ በተቀነባበረ የምንፍቅና ዘዴ ስተው ሲታደሙ ይገኛሉ፡፡ ይህን በቤተ ክርስቲያን ስም የተቋቋመ የምንፍቅና ማዕከል ተገን አድርጎ ደግሞ በቅርቡ “ቤርያ የነገረ መለኮት ኢንስቲትዩት” የሚባል አዲስ የምንፍቅና የልሕቀት ማዕከል ተከፍቷል፡፡ ይህም የመናፍቃኑ ዓላማ ምን ያክል የረዥም ጊዜን ግብ ይዞ የተነሣና በቤተ ክርስቲያን ጥፋት ላይ ያነጣጠረ መኾኑን ያሳያል፡፡ ክስተቱን አስመልክቶ ምዕመናንን ለማዘጋጀት ታናሽ ተቈርቋረ ክርስቲያን ወንድማችሁ የማስተላልፈው ቃለ ምክር የሚከተለው ነው፡፡

“ቤርያ” የሚለውን ቃል ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶዎቹ ስለምን መረጡት፤ ቤርያ ማለት ምን ማለት ነው፤ ከዚህ በፊት ማን ተጠቅሞበታል፤ እኛስ ምን ቊም ነገር ተገንዝበን ልንዘጋጅለት ይገባል የሚለውን እንመልስ፤ … ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!

“ቤርያ” በመቄዶንያ ግዛት የምትገኝ፣ ሐዋርያት ቅዱሳን ጳውሎስና ሲላስ ያቀኗት ቤተ ክርስቲያን መገኛ ከተማ ነች፡፡ ነዋሪዎቿ  ከተሰሎንቄ ከተማ ሰዎች ጋር በተነጻጻሪነት የቀረቡበት የመጽሐፍ ቅዱስ ስፍራ ላይ የቀደመቺቱን ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያት እንዴት እንዳስፋፏት ለምናጠና ሰዎች ታሪካዊ መረጃን ሰፍሮልን እናገኛለን፡፡ በተሰሎንቄና በቤርያ ከተሞች የሚኖሩ ከአይሁድ ወገን የነበሩ እንደነበሩ ታሪክም መጻሕፍትም ይነግሩናል፡፡ ንኡዳን ሐዋርያት ታዲያ በእነዚህ መሃል እየገቡ አይሁድን በምኵራቦቻቸው አሕዛብንም በተገኙበት (ለሕዝብም ለአሕዛብም) ከክርስቶስ የተቀበሉትን
ሠናይ ዜና ቅዱስ ወንጌልን በቃል ይሰብኩላቸው ነበር፡፡

ይህን “ቤርያ” የሚል ቃል ብዙ ጊዜ ምዕራባውያን መናፍቃን (የአሜሪካና የአውሮጳ ተሐድሶ ፕሮቴስታንቶች) ብዙዎች ሐዋርያውያት ትውፊቶችን የምትቀበል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን ለመረበሽ የተጠቀሙበት ቃል ሲኾን የቤርያ ሰዎችን ታሪክ በዋነኛነት “በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ እመኑ!” ለማለት አዘውትረው ይጠቀሙበታል፤ በዚህ ስም የተከፈቱ መጻሕፍታቸውና የሬድዮ ጣቢያዎቻቸው፣ ቸርቾቻቸው፣ የተራድኦና የስብከት ድርጅቶቻቸው ወዘተ. ቊጥራቸው የበዛ ነው፡፡ “በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ማመን” የሚለው ዶግማ በራሱ ከአምስቱ ዐበይት ሉተረ-ፕሮቴስታንታዊ አስተምህሮዎች መሃል ግንባር ቀደሙ ሲኾን በዋነኛነት አብያተ ክርስቲያናትን ለመረበሽና ምዕመናንን ከቅዱሳን ሐዋርያት ወግና ትውፊት ወጥተው የራሳቸው ግላዊ አመለካከት ተከታዮች እንዲኾኑ ለማወክ የሚጠቀሙበት፣ የመውጊያዎቻቸው ኹሉ ቀዳሚ መውጊያ ነው፡፡ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ለዓለም ያስተዋወቀው የመዠመሪያ ምንፍቅናው ይኸው የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሥልጣን ያንቋሸሸበትና ክብረ ጵጵስናን የናቀበት፣ የቤተ ክርስቲያንን ሃይ ባይነት የካደበትና ምእመናንን የመጻሕፍትን ቃል ለተረዱበት ግላዊ አረዳድ ብቻ የተወ ዋልጌ ትምህርት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የተሳዳቢውን የዲያብሎስን ተልእኮ ከተቀበሉ ዐመፀኞች መናፍቃን አንደበት እንደምንሰማው ክርስቲያኖችን “ወግ ጠባቂዎች” “ወግ አክራሪዎች” “የመንደር ወግ” ወዘተ. በሚሉ ስድቦቻቸው ብዙዎችን ያምሱበታል፡፡

ለኦርቶዶክሳውያን መጽሐፍ ቅዱስ ማለት ከፍተኛ ማዕርግ ያለው፤ የነገር ኹሉ ማሰሪያ አንቀጽ፤ የትምህርት፣ የአምልኮና የሥርዓት ኹሉ ምንጭ የኾነ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ በክብርም እንጠቀምበታለን፡፡ ነገር ግን ቃሉን ለመረዳት ከባድ ስለኾነና ምእመናን ንባቡን ካነበቡ በኋላ ምሥጢሩን በትክክል እግዚአብሔር ለማድረስ እንዳቀደው አድርጎ ለመረዳት መሪ/አጋዥ/መተርጒም እንደሚያስፈልግ እሙን ነው፡፡ ከመጻሕፍት ጋር አንድ ላይ አተረጓጐማቸውንም ከሐዋርያት ተቀብለናል፡፡ ስለዚህ ትውፊት ስንል መጻሕፍቱ የሚተረጐሙበት የትርጒም አቅጣጫ ነው፡፡

አንድ ትውፊትን የሚቀበል ክርስቲያንን ከፕሮቴስታንታዊ መናፍቅ የሚለየው ነገር ቢኖር መናፍቁ መጻሕፍትን ካነበበልን በኋላ ትርጒሙን/አፈታቱን ግን ራሱን እንደገባው በመሰለው ሲያብራራው ክርስቲያን ደግሞ መጻሕፍትን ንባባቸውን አንብቦ ፍቻቸውን ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ጠብቃ ካኖረችው ከሐዋርያት ትውፊት ይቀዳል ማለት ነው፡፡ ከንባቡ ለጥቆ የሚመጣው ማብራሪያ ኹሉ ከመዠመሪያው የቃሉ ተደራሾች ዠምሮ ለሁለት ሺህ ዘመን ያክል እየተነሡ ያለፉ ክርስቲያኖች ያን ኃይለ ቃል እንዴት አድርገው እንደተረዱትና እንዴት እንደተጠቀሙበት መዘርዘር ማለት ነው፡፡ የመናፍቁ አተረጓጐም የቅዱስ ቃሉን ምሥጢር በዚያ ግለሰብ የኅሊና ደረጃ ብቻ እስኪወሰን ድረስ ዝቅ ሲያደርገው፣ የቤተ ክርስቲያን አተረጓጐም ግን ለምልዔሎች ዘመናት ያክል የጸና የምሥጢር መስኮቶችን ከፍቶ፣ መጋረጃውን ገልጦ በሺሆች ዘመናት በክርስቶስ ቤተ ከርስቲያን የታሪክ ጉዞ ላይ ወጥ ምስክርነት ያለውን ኦሪጂናል አረዳድን ይገልጥልናል፤ ማለት በዘመናት የተነሡ የቀደምት አበውን በመንፈሰ ጥበብ ጭምር የታገዘውን ክርስቲያናዊ አረዳድ የምናይበትን መስኮት ወገግ ያደርግልናል፡፡ ለዚህ ነው የእግዚአብሔር መንፈስ መጻሕፍትን ያብራራለትና ምሥጢራቸውን ይገልጥለት ዘንድ መተርጒሙን ፊልጶስን ለጃንደረባው የላከለት --- የሐዋ.8፣26፡፡ ጃንደረባውም ቢኾን “ተአምርኑ እንከ ዘታነብብ” -- የምታነብበውን ታስተውላለህን ተብሎ ሲጠየቅ እንዳላስተዋለና ማስተዋል ላለመቻሉ ደግሞ መንሥኤ የኾነበት የሚያብራራለት ሳይኖር ይህን እንደማይኾን ነው፡፡ ጃንደረባው ቀጥሎ ከጠየቀው ጥያቄ የምንረዳው ደግሞ እንኳንስ በመጽሐፍ የሰፈረውን ረቂቅ የእግዚአብሔር ቃል ትርጒሙን ሊያውቅ አይደለም፣ የጻፈው ነቢይ ስለራሱ ይጻፈው፣ ስለሌላ ሰው ይጻፈው እንኳ ገና አለመረዳቱን ነው፡፡ መጻሕፍትን ለብቻ ቊጭ ብሎ በመሰለኝና በደሳለኝ መተርጐም ለቀውስ ስለሚዳርገን ለመጻሕፍት ኹል ጊዜ ትክክለኛ አረዳዳቸውን የሚያሳውቅ ተርጓሚ ያስፈልጋቸዋል፡፡

ይህንንም ስላወቀ መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን መሠረተና በትምህርቱ ላይ ዐቃቤ/ጠባቂ አደረጋት፡፡ ዋና ተልእኮዋም ይህን የአምላክ ዕውቀት ላልሰሙ ማሰማት፣ የሰሙም በሰሙት እንዲጸኑና ይልቁኑ ደግሞ በአልባሌ ትምህርት እንዳይቀይሩት ማረም፣ መገሠፅና በቀደመው ትምህርት ማጽናት ነው፡፡ በዚህም ነፍሳትን ለመንግሥተ እግዚአብሔር ታበቃበታለች፡፡

የመጻሕፍ ኃይለ ቃላቸው ለመረዳት ከባድ ሊኾን እንደሚችል ብርሃነ ዓለም ጴጥሮስ ሲናገር -- የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፥ በመልእክቱም ኹሉ ደግሞ እንደ ነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ። በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ --- 2ኛ ጴጥ.3፣15-17 ይላል፡፡ ሐዋርያው እዚህ ጋር እያስተማረን ያለው ቅዱስ ጳውሎስ የጻፋቸውን መልእክታት ጠቅሶ በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር መኖሩንና ጥንቃቄ እንደሚያስፈልጋቸው ነው፡፡ በወቅቱ የነበሩ የዮናናውያንን ፍልስፍና ተምረው ወደወንጌል የመጡ ክርስቲያኖች ይዘው የመጡትን የአግኖስቲሲዝም ምንፍቅና ለመቃወም ያስተማሩት ትምህርት ነው ይሄ፡፡ መናፍቃን እነዚህን መጻሕፍትና ትርጒማቸው የታመቀ ኃይለ ቃላትን መደዴና ዱርዬ በኾነ አተረጓጐም እንዴት እንዴት እንደሚያጣምሟቸው ሲገልጽ ደግሞ ይቀጥልና --- “… ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።ይላል ቊጥር 16 ላይ፡፡ በመሠረቱ መናፍቃን ሆዳቸውንና ሥጋዊ ተድላቸውን አሳልፈው ስለማይሰጡ፣ ምግባርና ትሩፋትም ስለሚደክማቸው መጻሕፍቱን ለገዛ ፈቃዳቸው እንዲስማማ አድርገው፣ ማለት ጾም ጹሙ፣ ምግባር ፈጽሙ፣ ጣሩ ድከሙ እንዳይል አድርገው -- ፈታ በሉ! ዘና በሉ! አቅልሉት! እርሱ የሞተው እናተ ዘና እንድትሉ ነው -- እንዲል አድርገው ቃላቱን ይተረጒሟቸዋል ማለቱ ነው፡፡

የዛሬ 4 ወር አካባቢ በድረ ገጽ እየቀዘፍኩ ራሴው እንደቈጠርኩት አሜሪካ ውስጥ ከሠላሳ የማያንሱ የተለያዩ የፕሮቴስታንት ዲኖሚኔሽኖች ግብረ ሰዶማውያንን በአዳራሾቻቸው ጸልየው፣ ባርከው ለማጋባት የሚያስችል ጸሎተ ቡራኬ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት አዘጋጅተው ያጋባሉ፡፡ እነዚህም የዚሁ ውስጣዊ ፍላጎትን ብቻ እየተከተሉ፣ በሥጋ መሻት ውስጥ ኾኖ መጻሕፍትን ለግል የመተርጐምና የቤተ ከርስቲያንን የሃይ ባይነት ሥልጣን የመናድ ውጤቶች ናቸው፡፡ በተለይ ቅዱስ ጴጥሮስ ሐዋርያ መጻሕፍትን ለግል የመተርጐምንና ከቤተ ክርስቲያን አረዳድ ውጪ በኾነ ሥጋዊ መንገድ የመምራትን ተግባር አበክሮ እየተዋጋ በሌላ ቦታ ላይ ሲናገር --- “… ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ኹሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ። --- 2ኛ ጴጥ 1፣20-21 ይላል፡፡

መናፍቃኑ በሐዋርያት ያልተሰበከልንን፣ በነቢያት ያልተከተበልንን፣ ነገር ግን ከሥጋ ፈቃዳቸው ብቻ የሚመነጭ እንዲህ ያለ መደዴ ትምህርት በሚነዙበት ጊዜ ታዲያ እውነተኞች ክርስቲያኖች እንዲጠነቀቁ ቅዱስ ጴጥሮስ ቀጥሎ እያሳሰበ እንዲህ ይላል --- “… እንግዲህ እናንተ፥ ወዳጆች ሆይ፥ ይህን አስቀድማችሁ ስለምታውቁ፥ በዓመፀኞቹ ስሕተት ተስባችሁ ከራሳችሁ ጽናት እንዳትወድቁ ተጠንቀቁ፤ – 2ኛ ጴጥ.3፣17፡፡ ከራሳችሁ ጽናት እንዳትወድቁ ማለት እናስተካክል ብለው መጥተው ከሚያፈርሱ፣ እናድስ ብለው ከሚያበክቱ ሰዎች ተጠንቀቁ፤ እስካሁን ያጸናችሁትን አሁንም ጠብቁ ነው፡፡ ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ቀላል ነው፤ እንደፈለክ ተርጒመው የሚል ሰው ሃይ ባይ እንዲኖር የማይፈልግና በመጻሕፍቱ እንደፈለገ መፈንጨት የሚፈልግ፣ የሥጋዊ ፈቃዱ አገልጋይ የኾነ ጸላዔ ጾም፣ ገፋዔ ምግባር - ውራጅ ሰው ነው ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያሉትን ደግሞ ቅዱስ ጳውሎስ “ለዓመፃ በሚታዘዙ እንጂ ለእውነት በማይታዘዙትና በአድመኞች ላይ ግን ቍጣና መቅሠፍት ይኾንባቸዋል።” ይላቸዋል --- ሮሜ. 2፣8፡፡

ከተማው ውስጥ የሚሰበከው አንድ ሺህ ዓይነት ወንጌልና የሚነገረው ትምህርት እልፍ ኾኖ የሚያስቸግር ቢኾንም ነገር ግን የእግዚአብሔር እውነት አንዱ ብቻ ነው፡፡ ጌታችንም በአንድ ወቅት ሐዋርያቱን ሰብስቦ ሰዎች ማን እንደሚሉት ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም ብዙ የተለያየ ዓይነት እንደሚሉ ነገሩት፡፡ ጌታችን ስለእርሱ በከተማው የሚሰበከው ብዙ ዓይነት እንደኾነ ካረጋገጠላቸውና ስለእርሱ ግን ትክክል የኾነውን - ነፍሳት አርነት/ነጻነት የሚያገኙበትን የእግዚአብሔር እውነት ሌላ እንደኾነ ካሳሰባቸው በኋላ የዚህ እውነት ግምጃ ቤት አድርጎ ቤተ ክርስቲያንን መሠረታት፡፡ እንዲህ ብሎ --- አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም። -- ማቴ. 16፣18-19፡፡ እንደዚህ ያለ የዘለዓለም ቃል ኪዳን የሰጣትን ቤተ ክርስቲያን ታሪክን እንደፈለጋቸው የሚያበስሉና ወዳሻቸው የሚፈተፍቱ መናፍቃን “በ2ኛው መቶ ዘመን ንጉሥ እገሌ .. ባራተኛው መቶ መሥፍኑ እገሌ … እንዲህ አደረጋት፣ እንዲህ አስተማራት፣ እንዲህ አበላሻት፣ እንዲህ አጠፋት” እያሉ ራሳቸውን አዳሽ አድርገው ያቀርባሉ፡፡ በእውኑ ግን ይህ ክርስቶስን መሳደብ ካልኾነ ስድብ ምንድን ነው፤ የመሠረትካት ቤተ ክርስቲያን ከንጉስ እገሌ .. ከመስፍኑ እገሌ .. ጀምሮ ጠፍታ ቈይታለች ስለዚህ እናድሳት ማለት “አነ እሄሉ ምስሌክሙ ወትረ በኵሉ ጊዜ እስከ ኅልቀተ መዋዕል -- እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ኹልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” ያለውን ሊቃችንን ክርስቶስን መሳደብ ነው፤ ማቴ 28፣20፡፡ ክርስቶስ ኹ…..ል ጊዜ እና፣ እስከዓለም ፍጻሜ አብሮን እንደሚኾን ቃል ከገባልን በኋላ ከአቅሙ በላይ የኾነ ምን ነገር መጥቶ ነው ሐዋርያት ሲያልፉ ቤተ ከርስቲያንን ንጉሥ እገሌ አበላሻት፣ ... ሰዉ ኹሉ ስዕል አምላኪ፣ … ማርያምን አምላኪ ከሃዲ ኾነ .. ነገር ኹሉ ተበላሸ 1600 ዓመት ሙሉ ማርቲን ሉተር የተባለ ጀግና ጎረምሳ መጥቶ ክርስቶስን ከጉድ እስኪያወጣውና ቤተ ክርስቲያኑን እስኪያስተካክልለት ድረስ ትውልዱ ኹሉ ጣዖት አምላኪ ኾነ … የሚል ቧልት በጌታችን ላይ መናገር የከፋ ምንፍቅና ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንኳንስ ንጉሥ እገሌ ሊያጠፋት አይደለም የአጋንንት ጭፍሮች፣ የገሃነም ደጆች እንኳ እንዳይችሏት አድርጎ ነው የሠራት፡፡ ማቴ 16፣19 - እርሷ ትውልድን ታድሳለች እንጂ ማንም አያድሳትም፤ ዛሬውኑ ልብ ያደረጋችሁ ወንድሞችና እኅቶች ይህን የዐመፀኞች ባንድ ትታችሁ ውጡ፡፡

ክርስቶስ እንዲህ አድርጎ ቤተ ክርስቲያንን ሲመሠርታትም እውነቱን የምታስጠብቅበትን - በትምህርቷ ላይ የሚያምፁባትን የምታወግዝበት - የገሃነም ደጆች እንኳ የማይችሉትን ጉልበት፣ ማለትም የማስተማር ሥልጣን ጭምር ልትታጠቅ እንደሚገባት ስላወቀ ቀጣይ ቃላቱ እንዲህ የሚሉ ነበሩ --- “… የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ኹሉ በሰማያት የታሰረ ይኾናል፥ በምድርም የምትፈታው ኹሉ በሰማያት የተፈታ ይኾናል።” -- ማቴ. 16፣19፡፡ በሰማይም በምድርም እውነት የኾነውን የእግዚአብሔርን ዕውቀት ከገለጠላት በኋላ ይህን እውነት ዐቃቤ ኾና እንድትጠብቅ፣ ዐመፀኞችን በሥልጣን እንድትቃወማቸውና አውግዛ ከአካሉ እንድትለያቸው ጭምር የሚያስችላት ሐዋርያዊ ሥልጣን ሰጣት - በዚህም ምክንያት ክርስቶስ ነቢይ ነውም የሚሉ፣ ኢልያስ ነውም የሚሉ፣ ጻድቅም ነው የሚሉ ኹሉ “የአብ አካላዊ ቃል - የባሕርይ አምላክ” እስከሚሉት ድረስ በቤተ ክርስቲያን ውጉዛን ይኾናሉ ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው መናፍቃን ሲነሡ (እንደነ አርዮስ፣ ንስጥሮስ፣ መቅዶንዮስ … ዓይነቶቹን) ጉባዔ መሥርታ፣ ዕድል ሰጥታ፣ አልመለስ ሲሉ “ውጉዝ!” እያለች ከምሥጢር የምትለያቸው፡፡

ጌታ ኢየሱስ ለቤተ ክርስቲያኑ ከወንጌሉ ጋራ የስብከተ ወንጌልን ተልእኮ፣ … ከተልእኮውም ጋራ ትምህርቱን የምታስጠብቅበት የመንግሥተ ሰማያት ሥልጣን ሰጥቷት እንደሄደ ሲያጸና በሌላ ቦታ ላይ (ማለትም የስብከተ ወንጌልን ተልእኮ ለቤተ ክርስቲያን በሰጠበት ቦታ ላይ) እንዲህ ይላል ----“ሥልጣን ኹሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ኹሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ኹሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤” --- ማቴ. 28፣19-20፡፡ ስበኩ ብሎ ተልእኮትን ሲሰጣቸው፣ አስቀድሞ የሰማይና የምድር ሥልጣኑን ጠቀሰ፤ ይህ ሥልጣን አላችሁ ሲል፡፡

መናፍቃን ወንጌልን ሲሰብኩና ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን ስትሰብክ ያላቸው ልዩነት እዚህ ጋር ነው፡፡ መናፍቃን ንባቡን አንብበውልን ትርጒሙ ነው ብለው የሚያምኑትን የግል አስተያየታቸውን ይጨምሩልናል፡፡ በዚህም ምክንያት ሠላሳ ሺህ ፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን በዓለም ላይ ሊፈላ የቻለው ኹሉም ካነበበ በኋላ መጽሐፍ ቅዱሱ አለ ብሎ የሚያምነውን የግል እምነቱን ይዞ ቤተ ክርስቲያን ስለሚሠራ ነው፡፡ ዴቪድ ባሬት እና ጆርጅ ኩሪያን የተባሉ አጥኚዎች በዎርልድ ክርስቲያን ኢንሳይክሎፒዲያ ላይ እንደሚነግሩን ከኾነ በአሁኑ ሰዓት በዓለም ላይ ከ33ሺህ በላይ መሠረታዊ የኾነ የነገረ መለኮት ትምህርት ልዩነቶች ያሏቸው የፕሮቴስታንት ዲኖሚኔሽንስ አሉ፡፡ ከእነዚህ 150 አካባቢ የሚኾኑት ብቻ አንድ ሚሊዮንና ከዚያ በላይ ተከታዮች ያላቸው ሲኾኑ ሌሎቹ ከዚያ በታች ተከታዮች አሏቸው፡፡ ኹሉም አንዱ ሌላውን መናፍቅ/ከሃዲ ማለት በሚያስችለው መልኩ የተለያየ የነገረ-ድኅነት አስተምህሮ የሚያራምዱ ናቸው፡፡ የአሜሪካዎቹ ግብረ ሰዶም ተጋቢዎችን ቀድሰው የሚድሩ ፕሮቴስታንት ኮንግሪጌሽኖች የዚሁ ውጤት ናቸው፡፡ ዛሬ ዛሬ ሦስት ወንዶችን በአንድ ጋብቻ - ወንጌል አንብበው ጭምር እየባረኩ የሚያጋቡ ቸርቾች መጥተዋል፡፡ አስተውሉ! የኾነ ሰው አሜሪካ ውስጥ ቁጭ ብሎ፣ መጽሐፍ ቅዱስ አንብቦ፣ ግብረ ሰዶማዊ ጋብቻ ኃጢአት እንዳልኾነ ተረድቻለሁ እያለን ነው፡፡ ማን ነው ሃይ የሚለው! የኾነ አካል ተው፤ ሐዋርያት እንዲህ አላስተማሩም፤ የጠቀስካቸው ጥቅሶችም እንዲህ ለማለት አይተረጐሙም ብሎ ትምህርቱን የሚያቀና አልፎም የሚያወግዝ፣ በሥልጣን ጭምር የሚያስተምር አካል ከሌለ ሐሰተኛውስ ማን ነው፤ እውነተኛውስ ማን ነው፡፡ ለዚህ ነው ጌታችን ቤተ ክርስቲያን የመሠረተው፡፡ ብዙዎች ኢየሱስን የተለያየ ስም ሲያወጡለት በአብ ዘንድ ያለውን ትክክለኛ ክብሩን ለመሰከሩት ደቀ መዛሙርቱ ግን የመንግሥተ ሰማያትን ሥልጣን ሰጥቷቸው ቤተ ክርስቲያንን አቈመ፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ወንጌልን ካነበበች በኋላ ምን ማለት እንደኾነ ትርጓሜውን ስታስረዳ የግል አመለካከት፣ ሰዋዊ አረዳድ ሳይኾን ሥልጣነ ሐዋርያትን ጠቅሳ ታስተምራለች፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ጋር በሐዋርያት መናብርት ኾነው፣ ሐዋርያትን አህለው መንጋውን የሚጠብቁ ኤጲስ ቆጶሳትን ስላኖረልን ይህ ችግር የለም፡፡ ሐዋርያት ታዲያ ይህን ከጌታ የተቀበሉትን የማስተማር ተልእኮ ስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ለተከታዮቻቸው ሲሰጡ --- በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ኹሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። --- የሐዋ. 20፣28 ብለው ተክተዋል፡፡ መንጋ የሚጠብቅ የእረኛ ዋና ሥራው ለኹላችንም ግልጽ ነው፡፡ እረኛ ለመንጋው ኹነኛ የሚለውን ለምለም ሜዶችን አፍላገ ማይን መርጦ ያሰማራቸዋል፣ ነጣቂዎቻቸውን ይዋጋላቸዋል፣ ከመካከላቸው ተለይተው የሚሄዱትን ከመንጋው ኅብረት እንዲኖራቸው ይመልሳቸዋል፤ ይገሥፃቸዋል፡፡ በመንጋው ላይ የተራዳኢነት ወይም የጠባቂነት ሚና ብቻ ሳይኾን የመገሠፅና የማስገደድም ሥልጣን ይኖረዋል፡፡ ምክንያቱም መንጋው የሚበጃቸውን ኹል ጊዜ ስለማያውቁ፡፡ ሐዋርያት በዘመናቸው ለቤተ ክርስቲያን ይህን የእረኝነት ሚናቸውን ተወጥተዋል፡፡ ሲያልፉ ደግሞ ትምህርቱንም ሥልጣኑንም እንዳለ ለተከታዮቻቸው ኤጲስ ቆጶሳት እንዳስተላለፉና ይህ ተልእኮ ከሥልጣኑ ጋር አሁንም በቤተ ክርስቲያናችን እስከዛሬ እንዳለ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቲቶ በላከለት መልእክቱ ላይ --- “ይህን በሙሉ ሥልጣን ተናገር፣ ምከር ገሥፅም፤ ማንምም አይናቅህ” ሲል ፍንጭ ይሰጠናል --- ቲቶ 2፣15፡፡ ልብ ብለን ካስተዋልን እዚህ ጋር ሐዋርያት ትምህርቱን የማስተማር ተልእኮ ብቻ ሳይኾን ለመንጋው ጠባቂዎች የሰጡት፣ ስሕተተኞችን ተመለስ ብለው የማስገደድ ሥልጣን፣ ካልተመለሱም ደግሞ አውግዞ ከመንግሥተ ሰማያት ዕጣ ፈንታቸው የመለየት ሥልጣን ጭምር ነው፤ በምድር ሲያወግዙት በሰማይም ውጉዝ ይኾናል፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ ባይተዋርነት በምድርም በሌላኛውም ዓለም የለም፡፡ እውነትን ማወቅ የፈለገ ግን የእውነት ባለቤት፣ ጠባቂ ግምጃ ወደ ኾነች ወደ ቤተ ክርስቲያን ይምጣ፤ ምክንያቱም እርሷ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳላት --- “… የእውነት ዓምድና መሠረት የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ናት።” --- 1ኛ ጢሞ. 3፣15፡፡

ይህን ካለ በኋላ ሐዋርያው ይቀጥልና “… በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉ፥ ይላል --- 1ኛ ጢሞ 4፣1-2፡፡ መናፍቃን መጽሐፍ ቅዱስ ንባቡን ካነበቡልን በኋላ እነርሱ የተረዱበትን፣ አጋንንት ያቀበሏቸውን የአመፃ አተረጓጐም ሊገልጡልን ቢችሉ እንጂ ከዚያ አልፈው እኛ ስሕተት፣ እነርሱ እውነተኛ እንደኾኑ የሚያረጋግጡበት ቀኖናም የላቸውም፣ የማስተማር ሥልጣንም አይጠቀሙም፡፡ ከምን አንጻር ፈትኖ ነው የእኔን አረዳድ ሐሰት የራሱን አረዳድ እውነት ብሎ መፈረጅ የሚችለው! ማመሳከሪያችን ምንድን ነው! ይህን ማድረግ የሚቻለው በሥልጣነ ሐዋርያት ብቻ ስለኾነ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ብቻ ታደርጋለች፡፡

ቀሪውን ለሌላ ጊዜ እንቅጠርና በእዉኑ የቤርያ ክርስቲያኖች “በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” የሚያምኑ ነበርን ተብሎ ሲጠየቅ የሐዋርያት ሥራ ላይ የቤርያና የተሰሎንቄ ሰዎች ታሪክ ተዘግቦ በምናገኝበት ክፍል ላይ ንባቡ እንደዚህ ይላል፡

“--- ወዲያውም ወንድሞች ጳውሎስንና ሲላስን በሌሊት ወደ ቤርያ ሰደዱአቸው፥ በደረሱም ጊዜ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ፤  እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና። ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ። ስለዚህም ከእነርሱ ብዙ፥ ከግሪኮችም የከበሩት ሴቶችና ወንዶች ጥቂት ያይደሉ፥ አመኑ። በተሰሎንቄ ያሉት አይሁድ ግን ጳውሎስ በቤርያ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ሰበከ ባወቁ ጊዜ፥ ወደዚያው ደግሞ መጡና ሕዝቡን አወኩ።”

--- የሐዋ. 17፣10 – 13 ---

ከላይ እንዳልነው ታዲያ መናፍቃኑ ይህን ታሪክ “የቤርያ ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የሚያምኑ ናቸው! እንደናንተ ወገኞች አይደሉም” ወደሚል ትርጓሜ አስገድደው ይወስዱታል፡፡ ልብ ብለን አይተን ከቤርያና ከተሰሎንቄ ሰዎች የትኞቹ ናቸው “በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” የሚያምኑት ስንል ግን በተቃራኒው ሐዋርያት የወቀሷቸው የተሰሎንቄ ሰዎች ኾነው እናገኛቸዋለን፡፡ የቤርያ ክርስቲያኖች ከተሰሎንቄዎች ይልቅ በመጻሕፍት በተጻፈው ቃለ ነቢያትና በቃል በተነገራቸው ወንጌል የሚያምኑ፣ በብሉያት ላይ የተጨመረላቸውን አዲሱን የሐዋርያት ወግ ጠንቅቀው የተረዱ ብርቱዎች ናቸው፡፡ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶዎቹ ስላላስተዋሉና ኾን ብለው ልባቸውን ስላጨለሙ ነው እንጂ እውነት ለመናገር ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል “በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” ማመንን የሚኰንን እንጂ የሚያበረታ ንባብ አልነበረም፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ማመን የሚገባን ቢኾንና የምንሰማውን ነገር ኹሉ ከመቀበላችን በፊት እንደፕሮቴስታንቶቹ የቱጋር ነው የተጻፈው ብለን መጠየቁ በጎ ልማድ ከኾነ እኔ በበኩሌ በመዠመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጽፎ ማግኘት የምፈልገው ትምሀርት ራሱን “መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተጻፈው ሌላ ማንንም አትስማ!” የሚለውን ትምህርት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ቦታዎቹ ላይ ቤተ ክርስቲያንን እንድንሰማ፣ እረኞቻችንን እንድንከተል፣ ትእዛዛቸውንም እንድናከብር፣ ሥልጣናቸውን እየገለጠ ጭምር ወጋቸውን እንድንቀበል ይመክረናል፡፡ ይህ “በተጻፈ ነገር ብቻ ተመራ!” የሚል ትምህርት ግን ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም፡፡ ብሉያትም ሐዲሳትም ቢበረበሩ፣ እንኳንስ ሌጣውን “ተጽፎ ያነበብከውን ብቻ ተቀበል!” የሚል አይደለም የእምነትና የምግባር ትምህርቶችን ኹሉ ምንጭ ወደተጻፈ ነገር የማጥበብና የመወሰን መንፈስ ያለው ትምህርት የለም፡፡ መናፍቃን እንደዚህ ዓይነት ጥቅስ ለማግኘት ያንንም ይንንም ቧጥጠው ቧጥጠው ለማምጣት ሞክረዋል፤ እስካሁን ያመጧቸው ጥቅሶች ኹሉ ግን በቀጥታም ይኹን በተዘዋዋሪ የዚህን ዶግማ አሳቦች በፍጹም አይቀበሉም፤ አብዛኞቹ እንደውም ይኰንኑታል፡፡ (እነዚህን አንድ ባንድ በሌላ ጽሑፍ እናስረዳለን)

ስለዚህ ተጠራጣሪዎቹ እንዲያው መሬት ኹሉ አሰሳ ሙንጨራ ይዘው እንደዚህ ያለውን ጥቅስ የግዳቸውን አመጡት እንጂ ጥቅሱም ቢኾን የቤርያ ክርስቲያኖችም ቢኾኑ አሳባቸውን የሚነቅፉባቸው እንጂ የሚደግፏቸው አይደሉም፡፡ ለእነዚህ መናፍቃን ትምህርት የሚመችና መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ሙጢኝ ብሎ የያዘ፣ ለሐዋርያት ወግ የማይታዘዝና ለሐዋርያዊ ትውፊት ቦታ የሌለው እውር ትምህርት ይከተሉ የነበሩት ይልቁኑ የቆሮንቶስ ሰዎች ነበሩ፡፡ እነዚህንም ደግሞ ይህን ልማዳቸውን ያዩባቸው ሐዋርያት ይወቅሱባቸው እንደነበር ቊጥር 11 ላይ ይነግረናል፡፡

የተሰሎንቄና የቤርያ አይሁድ የነበራቸው መሠረታዊ ልዩነት ታዲያ የቀደሙቱ ቅዱሳን ሐዋርያት የሰበኩላቸውን ወንጌል በብሉያት ውስጥ ፈልገው፣ መርምረው፣ ተንትነው አላገኙትም፡፡ ከተጻፈው ውጪ አሁን ሐዋርያት በቃል እየሰበኳቸው ያለውን አዲስ ወንጌል/ሐዲስ ኪዳን ለመቀበል ልባቸው አልፈቀደም፡፡ የሐዋርያት አዲሱ ትምህርት ጭብጡ የነበረው -- “የእግዚአብሔር ልዥ ክርስቶስ መከራ እንዲቀበልና ከሙታን እንዲነሣ በነቢያት መሠረት ይገባዋል፤ የናዝሬቱ ኢየሱስ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ነው” -- የሚል ሲኾን ይህን አዲስ ትምህርት የተሰሎንቄ ሰዎች ብሉያት ላይ ፈልገው አላገኘነውም አሉ፡፡ የተሰሎንቄ ሰዎች ልክ እንደዘመናችን ፕሮቴስታንቶች ናቸው፡፡ አነዚህ በአንድ ሺህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንኳ የእመቤታችንን ክብር፣ ክህነተ ሐዲስን፣ ቊርባነ ሐዲስን ወዘተ. መጻሕፍቱ ውስጥ ማግኘት እንደሚቸገሩትና “የታለ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ! …” እያሉ እንደሚያተክኑን ኹሉ እነዚያም ቅዱስ ጳውሎስን መጻሕፍትን ገልጠው ለሦስት ሳምንት ያክል ሞግተውት እንኳ የሚናገረውን ነገር ብሉያት ውስጥ ማየት አልቻሉም፡፡ ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን ጳውሎስን የሚያክል፣ መጋቤ ምሥጢር እናም መጋቤ ብሉይ ወሐዲስ እያራቀቀ መጻሕፍትን በመንፈሰ ረድኤት ጭምር ተርጒሞላቸው ከሦስት ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በኋላ የተሰሎንቄ ሰዎች ይሉ የነበረው -- “የለም! የለም! ይህ አንተ የምትለውን ነቢያት አላሉትም! መጻሕፍት አልከተቡትም!” -- ነበር፡፡ የተሰሎንቄ ምዕመናን “መጻሕፍትን ብቻ!” የሚቀበሉ ፕሮቴስታንታዊ አባዜ የነበረባቸው ስለነበሩ ጳውሎስ የጨመረላቸውን የብሉያት ፍጻሜ/ልዕልና የኾነቸውን ሐዲሲቱን ወንጌልን አልተቀበሉም፡፡

ከሲላስ ጋር ወደ ቤርያ ሰዎች ሲሄድ ግን ሐዋርያው የገጠመው ሌላ ነገር ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ተሰባስበው የነበሩት በምኵራብ እንደነበር ቊጥር 10 ላይ ነግሮናል፡፡ ስለዚህ ብሉያት መጻሕፍትን የሚያውቁ፣ የሚያደንቁ፣ ትንቢተ ነቢያትን የሚጠብቁ ነበሩ ማለት ነው፡፡ ልዑላን ሐዋርያት አዲሲቱን የምሥራች ወንጌልን ይዘው ወደምኵራባቸው ሲገቡና ሲያስተምሯቸው ግን ልክ እንደ ተሰሎንቄዎቹ “ኤዲያ! በ46ቱ ብሉያት ላይ ምነው አዲስ ቃል ትጨምሩብናላችሁ፤ እኛ መጻሕፍቱን ብቻ ነው የምናምነው!” አላሉም፡፡ ነገር ግን ጥቂት ቀናት ብቻ በልበ ብሩህነት ዕለት ዕለት የተነገራቸውን አዲስ ዜና/የምሥራችን፣ የክርስቶስን የሐዲስ ኪዳን ዜና ቀድሞ በነቢያት ከተሰጡን መጻሕፍተ ብሉይ ጋር አጣጥመው፤ አዋሕደው ተቀበሉ፡፡ የቤርያ ሰዎች ብሉያት ከወንጌል ቃል ጋር የተጣጣሙላቸው ነበሩ እንጂ እንደተሰሎንቄዎች የተጣመሙባቸው አልነበሩም፡፡ መጻሕፍተ ብሊትን ከወንጌል ሠናይቲት ጋር አዋሕደው ተረዱ፡፡ ለዚህም ሐዋርያው ቅዱስ ሉቃስ ስለእነዚህ ሰዎች ሲናገር “… እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና። ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ።  --- የሐዋ. 17፣10 ይላል፡፡ አስተውሉ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ ነው የሚለው፤ ማለት ቀድሞ ተጽፈው በነበሩ በብሉያት መጻሕፍቱ ላይ ገና ያልተጻፈችውንና በቃል ብቻ ትሰበክ የነበረችውን ሐዲስ ቃል፣ ሐዲስ ወግ ጨመሩ፡፡ እነዚህ ደግሞ ትክክለኞቹ ኦርቶዶክሳውያን ምዕመናንን ይመስላሉ፡፡ ምክንያቱም ኦርቶዶክሳውያን ዛሬ ወግን ኹሉ ትውፊትን ኹሉ የሐዋርያት ኾኖ ከተገኘና ሐዋርያዊ ምስክርነት ያለው ከኾነ ይቀበሉታልና፡፡ ከሐዋርያት ወግ ውጪ ያለውን ግን ይኰንኑታል፡፡

በነገራችን ላይ የተሰሎንቄዎቹ አይሁድ እንደዚሁ እንደተጣመሙና ልባቸውን እንዳከፉ አልቀሩም፤ ወዲያው ተለውጠው ልባቸው ቀንቶ ክርስትናን ተቀብለው፣ ተጠምቀው ማሕበረ ሐዋርያትን ተቀላቅለዋል፡፡ በዚህም ሳያሰልሱ ወንጌልን አገልግለዋታል፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ክርስትናቸውን ለማጽናትና ምግባራቸውን ለማቅናት ይረዳቸው ዘንድ ሁለት መልእክታትን ኋላ ላይ አከታትሎ የሚልክላቸው፡፡ 1ኛና 2ኛ ተሰሎንቄ መልእክታትን ተመልከት፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ምንም እንኳ የጌታችንን ሐዲስ ኪዳን ወንጌልን አምነው የተቀበሉና የተጠመቁ ቢኾኑም ቅሉ የቀደመ ያሃ አባዜአቸው ግን ወዲያው አልተዋቸውም ነበር፡፡ በዚህም ልክ ቀድሞ ብሉያት መጻሕፍት ላይ ከተጻፈው በቀር አንቀበልም ይሉ እንደነበሩት አሁን ደግሞ ከብሉያት ጋር ሐዋርያት ደግሞ የጻፉትን መልእክት ብቻ እንጂ ሌላችሁን አንሰማም እያሉ በወቅቱ ተሹመውላቸው የነበሩ መምህራንን ያስቸግሩ ነበር፡፡ ይህን ተመልክቶ ታዲያ ብርሃነ ዓለም ጳውሎስ በ2ኛ መልእክቱ ላይ --- “እንግዲህስ ወንድሞች ሆይ! ጸንታችሁ ቁሙ፤ በቃላችንም ቢኾን ወይም በመልእክታችን የተቀበላችሁትን ወግ ያዙ፡፡” – 2ኛ ተሰ 2፣15 ብሎ ፕሮቴስታንታዊ አባዜአቸውን እንዲተዉና የጻፉላቸውን መጻሕፍት ካቀበሏቸው ከትውፊታት አስተባብረው እንዲይዙ መክሯቸዋል፡፡

ሐዋርያት የእነርሱን ወግ እንድንይዝ በጥብቅ አዝዘውናል፡፡ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን ባመሰገነበት አንቀጹ ላይ ይኸው ሐዋርያ ታዲያ --“ወንድሞች ሆይ፥ በኹሉ ስለምታስቡኝና አሳልፌ እንደ ሰጠኋችሁ ወግን ፈጽማችሁ ስለ ያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ።” ይላል --- 1ኛ ቆሮ 11፣2፡፡ ሐዋርያት የጻፍንላችሁን ብቻ ተቀበሉ ብለው አላዘዙንም፡፡ ሲዠመር የተጻፈ ነገር ብቻ ላይ እንድንወሰን አላስተማሩንም፡፡ ይልቁኑ ---- “ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም እነዚህን አድርጉ፤ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል።” ነው የሚሉን --- ፊልጵ. 4፣9፡፡ ስለዚህ ክርስቲያን ኹሉ ሊጠብቃቸውና ሊያስጠብቃቸው የሚገቡ ወጎች ካሉና እነዚህ ደግሞ በሀብተ መንፈስ የበለጸጉ ሐዋርያት ያቀበሉት ወግ መኾኑ የተረጋገጠ ከኾነ እኛን ወገኞች! ወግ አስጠባቂዎች! የመንደር ወግ ተራኪዎች! ለሚሉን ኹሉ መባላችን የሐዋርያትን ወግ መያዛችን ከኾነ ደስስስስ እያለን እንቀበላችኋለን፡፡ ከማርቲን ሉተር ወግ ስለሚሻል! ከጆን ካልቪን ወግ ስለሚሻል! ከዝዊንግሊይ ወግ ስለሚሻል፡፡ እነዚህ በቦታውም ያልነበሩ፣ የነገሩን ሥር አጥርተው የማያውቁ፣ ዝም ብለው ብቻ ባንነው የነቁና የቃዡ ብኩኖች እንጂ ደገኞች መምህራን አይደሉም፡፡ እነዚህን ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ --- “… ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ። ያላቸው --- 2ኛ ጴጥ 3፣16 የተከተላችኋቸው ኹሉ ተራና ተርታ የፈጠራ ወግና ተረት ተረት የተከተላችሁ ስለኾነ አሁኑኑ ልቀቁና ያን ቦታ ውጡ!

ቤተ ክርስቲያን ግን ይህ የሐዋርያት ወግ አላት፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ወግ ያስረከበው በትውልድ ለሚነሡ ትውልደ ክርስቲያን ኹሉ እንደኾነና ኹላችንም ይህን ወግ በስስትና በኃላፊነት ተቀብለን ለልዦቻችን ልናወርስ እንደሚገባ ሲነግረን ከእርሱ በኋላ የተነሡ ጢሞቴዎስን የመሳሰሉ ክርስቲያኖችን እንዲህ ሲል ይመክራቸው ነበር፤ --- “ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ደግሞ ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ።” --- 2ኛ ጢሞ 2፣2፡፡ የሐዋርያትን ወግ ለመጠበቅ እንኳ የሚያስችል ባለአደራነት ያለን እኛ ክርስቲያኖች ነን፤ ይህ ወግ ከሐዋርያት ቀጥሎ ለሌሎች ክርስቲያኖች ተሰጥቷል፤ እነዚያም ታምነው አቀብለዋል፤ እያለ እያለ ዘመናችን ደርሷል፡፡ በዚህ ደግሞ ጠላት ስለሚበሳጭ ልክ እንደእርሱው ያሉ ተሳዳቢዎችን እየላከ “ወገኛ!” “ወግ አስጠባቂ!” ወዘተ. እያለ ይቃወመናል፡፡ እኛ ግን ይህ ቀድሞ ትንቢቱ ስለተነገረን አውቀን ብንዘጋጅበት እንጂ እንደእንግዳ ነገር የምንደነብርበት አይደለም፡፡ ሐዋርያው ራሱ ለእኛ አደራ ብሎ የሰጠንን ወግ እርሱ ራሱ ከየት አገኘው ስንል 1ኛ ቆሮ 15፣3 ላይ ይነግረናል -- “ወንድሞች ሆይ፥ የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን … የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ፤ እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከኹሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ፡፡” ብሎ፤ ሐዋርያትን ይጠቅሳል፡፡ ሐዋርያት ከየት ይህን ወግ ከየት አግኝተው ሰጡት ቢባል ደግሞ ከቤዛ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡

ከዐቃቤ ሰዓት ከብቴ ቃል ጠቅሼ አበቃለሁ፡

“የቀደሙ አባቶቻችን ያስተማሩንን፣ ለአባቶቻችንም ሊቃውንት ያስተማሯቸውን፣ ለሊቃውንትም ሐዋርያነ አበው ያስተማሯቸውን፣ ለሐዋርያነ አበውም ሐዋርያት ያስተማሯቸውን፣ ለሐዋርያትም የፍጥረት ኹሉ ኤጲስ ቆጶስ የሚኾን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማራቸውን የቀናች የሃይማኖት ትምህርት እንጽፋለን፡፡”

--- ዐቃቤ ሰዓት ከብቴ ---

ኃይለ ጊዮርጊስ ነኝ! ጸልዩልኝ!

ይቈየን!