ኒቆዲሞስ፡ ሐወጽከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ (መዝ.16፥3)




ሰባተኛው የዐቢይ ሱባዔ ኒቆዲሞስ ይባላል። ይህ ሳምንት የዐርባ ጾም መገባደጃ ነው። ከዚህ ኋላ የሕማማት ሰሙን ይኾናል። የተከበረ ነገርን (ስጦታን) በውድ ነገር እንደሚሸፍኑ፥ የረቀቀ ምሥጢርን በመጋረጃ ጋረድ አድርገው እንዲያከብሩ ኹሉ፥ አባቶቻችንም እጅግ የምንሳሳለትንና የምናከብረው የጌታችንን የዐርባ ቀን ጾም ፊትና ኋላ በሕርቃልና በሕማማት ሳምንታት ጾም ጋርደው አክብረውታል። በዚህ በሰባተኛው ሳምንት ታዲያ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የምታዘክራቸውና ለምእመናንም በዋናነት የምታሳስባቸው ሦስት ዐበይት ነገሮችን ነው።

      1.      ሥጋዌን፡- (የእግዚአብሔርን ልጅ ከሰው ተወልዶ ሥጋ መልበስ)፥
      2.     ስቅለትን፡- (የእግዚአብሔርን ልጅ በመስቀል ላይ ሞቶ ሞትን መደምሰስ) እናም
      3.     ጥምቀትን፡- (እኛም በጥምቀት ምሳሌ ከርሱ ጋር ሞተን በመነሣት በጸጋ የእግዚአብሔር ልጆች የምንባል መኾናችንን) ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደኾነ፥ እንደተሰቀለና ቤዛነቱን እንደፈጸመ እንዲሁም ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ ይህን ሊያምኑና እንዲሁም የሞቱ ምሳሌ በኾነች ጥምቀት ሊጠመቁ እንደሚገባ ነው። እነዚህ ትምህርቶች ለሌሊቱ ተማሪ ለኒቆዲሞስ እንደተሰጡ ሙሉ ትምህርቱ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 3 ከቊጥር 1 ጀምሮ ተመዝግቦ እናገኛለን።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረጋቸው ተአምራት በኢየሩሳሌምና በአውራጃዎቿ ኹሉ በተሰሙ ጊዜ ከተማይቱ በሦስት መንገድ ነገሩን አስተናግዳዋለች። ገሚሱ ሕዝብ ይህን የሚያደርግ ከእግዚአብሔር ወገን ከኾነ ብቻ ነው በሚል ያመነበት አለ። እሊህ እንደ እውሩ ዘተወልደ (እውር ኾኖ የተወለደው ሰው) ያሉ ናቸው፤ ዮሐ.9፥1-41። ገሚሱ ደግሞ ይህን እንደ ምትሀት አሊያም እንደ አጋንንት ሥራ ቈጥሮ ያመፀበት አለ፤ ሉቃ.11፥14-26። እሊህ ደግሞ ከጸሐፍትና ፈሪሳውያን ብዙዎቹ ናቸው። ገሚሱ ደግሞ ከወደ የት እንደኾነ ሳያጠይቁ በተአምራቱ ብቻ ተጠቃሚ እየኾኑ የቈዩ ናቸው፤ ዮሐ.6፥26። እሊህ ደግሞ ኅብስት ሲያበረክት ይመገባሉ፥ ድውይ ሲፈውስ አይተው በምልክት ይዝናናሉ እንጂ ወገኑን መምጫውን ችላ ያሉ ናቸው። እሊህ ሦስቱም ታዲያ በአይሁድ ማኅበረ ሰብእ በየትኛውም ደረጃ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፥ ከተራ እስከ ሹም፥ ከድኻ እስከ ባለጸጋ ያሉ ናቸው።

ኒቆዲሞስ የአይሁድ አለቃ (መምህራቸው) ነው። በሦስት ጎዳናዎች ከአይሁድ መካከል ተለይቶ ከፍ ያለና የከበረ ገናና ሰው ነበር።

       1.      በትምህርት ለኹሉ መምህራቸው ነው፤
       2.     በሹመት ከኹላቸው ከፍ ያለ ነው፤
       3.     በባለጠግነት (በሀብት) ከፍ ያለ ነው።

የአይሁድ ሸንጎ (ሰንኸርዲን) አባል የኾነ ሽማግሌና በማናቸውም ኹኔታና በኹሉም ደረጃዎች ተደማጭ፥ አሳብ የሚያስቀይር፥ የሚታፈርና እገሌ ብሏል የሚባልለት ልዩ ሰው ነበር። ባኗኗሩም ብልህና አሳቢ፥ በከንቱ የማይፈርድ ሰውም ነበር። ሊቃውንተ ሐዲስ ትሕትናውንና የማወቅ ጉጉቱን አድንቀው ያስተምሩለታል፤ በቤተ ክርስቲያን ከባለ አክሊል ቅዱሳን ጻድቃን ወገን ተመድቦ መታሰቢያውም በወርኃ ነሐሴ አንድ ቀን ይውላል።

ኒቆዲሞስ ጌታችን በኢየሩሳሌም አደረገ የተባለውን ኹሉ ሰምቶ እንዲህ ያለውን ተአምር ከእግዚአብሔር ወገን ካልኾነ በቀር ሊያደርግ አይችልም ከሚሉት መሐል ኹኖ በልቡ አምኖበታል። የአብ ልጅ በሰው መካከል እንደተገኘና ወደ ዓለም እንደመጣ ሲረዳ እንደ አንድ ሊቅ፥ ሱባዔን እንደሚቆጥር፥ ትንቢትን እንደሚያመሠጥር፥ ምሳሌን እንደሚመረምርና ሕግን እንደሚያስተምር ታላቅ መምህር ወዲያው የሚለጥቀው ጉዳይ ከደረሰበት ደርሶ የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን መኾኑን፥ ሲጠበቅ የነበረው ኹሉ መድረስ አለመድረሱን፥ ቀጣዩ የእግዚአብሔር ተግባር ምን እንደሚኾን ከርሱ ለማወቅ መጓጓት ነው። ሄዶ የተላክኸው መምህር አንተ መኾንክን እናውቃለን አለ። ጌታችንም የአብን እውነት ለመቀበል የተዘጋጀ መኾኑን ሲረዳ ረቂቅ ሰማያዊ ምሥጢርን ነግሮታል።

ጌታ ኢየሱስን የተከተለው ሰው በአይሁድ መሐል ቢገኝ ከምኵራባቸው እንዲባረር ተብሎ ነበርና በድብቅ መሄድ ስለነበረበት፥ አንድም ለአይሁድ መምህራቸው ሲኾን ሊማር መሄዱን ያዩ ሰዎች መምህር ሳለ ዕውቀት አልተከተተለትም ኑሯል እንዴ ብለው እንዳያሳንሱት ሲል በሌሊት ሄዶ ተምሯል። በዚህም ጌታችን ስለ ልጅነት ሀብትና መንግሥትን ስለመውረስ ጠለቅ ያለ ረቂቅ ትምህርት ሰጥቶታል።

“ሥጋዌ” ... የአብ ልጅ ሥጋ ስለመልበሱ ...

ኒቆዲሞስ ነገሩን ሲጀምር ጌታችን ያደረጋቸው ተአምራት ከእግዚአብሔር ወገን እንደመጣ የሚናገሩ መኾናቸውን ጠቅሶ ጀመረ። ይህን ጊዜ ጌታችን በቀጥታ “ዘኢተወልደ ዳግመ ኢይሬእያ ለመንግሥተ እግዚአብሔር ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው።” ኒቆዲሞስ ያነሣው ርእስ ወደ እንዲህ ያለው ትምህርት አያመራም ነበር። ርሱ ያለውና ጌታችን ቀበል አድርጎ የተከተለው ርእስ ፍጹም የተለያየ መምሰሉ ዝም ብለን ስንመለከተው ግራ ሊያጋባን ስለሚችል እንዴት ያለ ዝምድና እንዳለው መረዳት አትኩሮት ይጠይቃል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ጊዜ ትንሽ እምነት ይዘው ወደርሱ የሚመጡ ሰዎችን ያችን ጥቂት እምነታቸውን መፈተኑና የበለጠ እምነትን ግድ ማለቱ የተለመደ ነው። ኹል ጊዜም የሚበልጠውንና የሚቀራቸውን እውነት ያሳስባቸዋል። በዮሐ.8፥31 ያመኑትን አይሁድ ተመልክቶ ጥቂቷን እምነታቸውን አይቶ የሚበልጠውን ነገር በነገራቸው ጊዜ በትምክህትና በጀብደኝነት “ዘርአ አብርሃም ንህነ የአብርሃም ዘር ነን ለአንድ ስንኳ ከቶ ባርያዎች ኾነን አናውቅም” ብለው በመመጻደቃቸው በእምነታቸው ታናሽነት በትዝኅርት እዚያው ወድቀዋል። ጌታችንም “አማን አማን እብለክሙ ኵሉ ዘይገብራ ለኃጢአት ገብራ ውእቱ ኃጢአት የሚያደርግ ኹሉ የኃጢአት ባርያ ነው” ብሏቸዋል።

በዮሐ.6፥60 ላይም እንዲሁ ከተከተሉት ሰዎች መሐል (ደቀ መዛሙርቱ ይላቸዋል) ብዙዎች “አማን አማን እብለክሙ እመ ኢበላዕክሙ ሥጋሁ ለወልደ እጓለ እመ ሕያው ወኢሰተይክሙ ደሞ አልብክሙ ሕይወት ላዕሌክሙ እውነት እውነት እለችኋለሁ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም” ባላቸው ጊዜ ይህ የሚያስጨንቅ ንግግር ነው ብለው ትተው ሄደዋል።

በርግጥ ኒቆዲሞስ ከእነዚህ የተሻለ ታሪክ እንዳለው በዮሐንስ ወንጌል ስሙ በተነሣባቸው ቀጣይ ቦታዎች ስለርሱ ከሰፈረው መረዳት ይቻላል። ኋላ ላይ ጌታችን ሲሞት ሥጋውን ከአርማትያዊው ዮሴፍ ጋር ገንዞ በሐዲስ መቃብር ለማሳረፍ ታላቅ የክህነት አገልግሎት በቅቷል። እውነት ደስ ልታሰኝም ላታሰኝም ትችላለች። ነገር ግን የክርስቶስም ኾነ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ተግባር ለሰሚው ሳይሰቀቁ ነጻነት የምታድለውን እውነት እንዳለች መስበክ ብቻ ነው።

ንግባእኬ ኀበ ጥንተ ነገርነ ...

ወደ ቀደመ ነገራችን ስንመለስ፥ የኒቆዲሞስ ብሂል የነበረ “እስመ አልቦ ዘይክል ይግበር ዘንተ ተአምረ ዘአንተ ትገብር ዘእንበለ እግዚአብሔር ምስሌሁ እግዚአብሔር ከርሱ ጋር ካልኾነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች የሚያደርግ የለም” ሲኾን ወንጌላዊው ወንጌሉን መጻፍ ሲጀምር አንሥቶት ከነበረ ጉዳይ ጋር የተሳመረ ንግግር ነበር። ወንጌላዊው ዮሐንስ “ወውእቱ ቃል ኀበ እግዚአብሔር” የአብ ቃል የተባለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ብሎ ወንጌሉን የጀመረ ነውና ኒቆዲሞስም እግዚአብሔር ከርሱ ጋር ካልኾነ በቀር ሲል የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑን እያመነ መኾኑን ልብ ይሏል። በህልውናው ከርሱ ጋር ካለህ ካንተ በቀር ብሎ የህልውናቸውን አንድነት እየተናገረ ነበር። ስለዚህ “ነአምር ከመ እምኀበ እግዚአብሔር መጻእከ ከመ ትኩን መምህረ ከእግዚአብሔር ተልከህ ልታስተምር መምጣትህን እናውቃለን” ሲል እግዚአብሔር ልክ ነቢያትን እንደሚልክ፥ መምህራንን እንደሚያሰማራ ያይደለ፥ ወልደ እግዚአብሔር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ “አነ እምኀበ እግዚአብሔር ወፃእኩ ወመጻእኩ ከእግዚአብሔር ወጥቼ መጥቻለሁ” እንዳለ ከአብ ባሕርይ ዘእምባሕርይ ተወልደህ መምጣትህንና አካላዊ ቃል የባሕርይ ልጁ መኾንህን እናውቃለን ማለቱ ነበር፤ ዮሐ.3፥2 ፤ ዮሐ.8፥42።

በጌታችን ምላሽ ይህን እናውቃለን፤ ጌታችን የመለሰው ምላሽ እጅግ ልዕልና ያለው ነው። እንዲህ ያለው ጠንካራ ምላሽ ለተራ ነገርና ለመናኛ ብሂል አይመለስም። የምላሹ ግዝፈት የሚነግረን የኒቆዲሞስም ብያኔ በዚያው ልክ ላቅ ያለ መኾኑን ነው። የእግዚአብሔር ልጅ ከአብ ወጥቶ ወደ ምድር መምጣቱን ካመነ ዘንዳ ላመኑበት ሰዎች ደግሞ የእግዚአብሔር ልጆች መባልን ሥልጣን የሚሰጣቸውም ርሱ መኾኑን እንደሚያውቅ ተረድቶ ይህን የልጅነት ሥልጣን ማግኘት በምን እንደሚኾን የቀረውን ትምህርት ሰጥቶታል።

ስለዚህ ልብ ካልን ጌታችን ኒቆዲሞስ ካነሣው ርእስ በቀጥታ የደረሰበትን የእምነት ደረጃ ይዞ ወደ ሚቀጥለው ደረጃ ማለፉን ያስተውሏል። ይህም ከሊቅ ጋር በሚያወሩ ጊዜ ነገርን ከሥሩ ውኃን ከጥሩ የሚለውን ብሂል አንዳንዴ ተወት እንደሚያደርጉት፤ የተረዳውን ይዘው ወደሚቀጥለው ማለፍ እንዳለ አሳዪ ነው።

ከሥጋዌ .. ወደ ጥምቀት ...

የክርስቶስን የእግዚአብሔር ልጅነት (የባሕርይ አምላክነት) እዚህ ጋር እንረዳና እኛ ደግሞ እንዴት ከእግዚአብሔር በጸጋ ተወልደን ይህን ልጅነት በተስፋ ቃል እንደምንሳተፍ ቀጥሎ ሰው ድጋሚ ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም ባለው እንረዳለን። ዛሬ ይህ ትምህርት ለሁለት ሺህ ዘመን የተሰበከ እውነት በመኾኑ ለመቀበል ቀላል ሊኾን ቢችልም ለኒቆዲሞስ ግን ምን ያክል ግራ ሊያጋባው እንደሚችል መገመት ይቻላል።

በውኃ መጠመቅ (ውኃ ውስጥ ተዘፍቆ መውጣት) ወዲያው ረቂቅ በኾነ በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅን ይዞ መምጣት መቻሉ፥ ያም ደግሞ ለተጠማቂው ሰው ከቀደመው የእናት የአባት ልደት ላይ ሁለተኛ ልደት ማሰጠቱ፥ ይህም የእግዚአብሔር ልጅ መባል መኾኑ ለኒቆዲሞስ ናላ የሚያናውዝ ትምህርት ነበር። ርሱም “ይህ ይኾን ዘንድ ይቻላል፤” ሲል በመጠየቁ ይህ ይታወቃል። በመሠረቱ ሰው ተወለደ የሚባለው መላ አካላቱ ተከትቶ ከነበረበት ከማሕፀን ፍጹም ሲወጣ እንደኾነ መጠመቅም ልደት የሚባልበት ምክንያት ሰው ፍጹም በውኃ ውስጥ ተዘፍቆ በአሚነ ክርስቶስ (ከእምነት ጋር) ወደ ውጭ ሲወጣ ከማሕፀን ወጣ እንላለን፤ ኢትዮጵያውያን የሐዲስ ሊቃውንት አባቶቻችን በጥምቀት የሚኾነውን “ከማሕፀነ ዮርዳኖስ” “ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ” መወለድ የሚሉት ለዚህ ነው።

ኒቆዲሞስ ከጌታችን ጋር በነበረው ቈይታ የተጓዘበትን የአእምሮ ውጣ ውረድና የአሳብ እላይ ታች ማየት ነው እንግዲህ። አምኖ የመጣው ሰው ወዲያው ወደ ትምህርት ገባ፤ ከዚያ መልሶ ወደ ጥርጥር። ጌታችን በመጨረሻ ነገሩን የማመንና ያለማመን አደረገው። የማያውቅ ሰው ባለማመን አይጠየቅም። ስለዚህ መጀመሪያ እውቀት ይሰጡታል፤ ከዚያ ባወቀው ነገር እምነት ይጠብቁበታል።

በነገራችን ላይ ጌታችን ሲሰብክ/ሲናገር “አማን አማን እብለከ እውነት እውነት እልሃለሁ” ካለ ከዚያ በኋላ የሚናገረው ነገር እጅግ ታላቅ፥ በምሥጢር የታጀለና ፍጹም እምነትን የሚጠይቅ ብሂል እንደሚኾን ተደጋግሞ ታይቷል። ዮሐ.151  33 5 11  519 24 25  626 32 47 53  834 51 58  101 7  1224  1316 20 21 38  1412  1620 23  እና 2118 ይመለከቷል። በዐራቱም ወንጌላት እንዲህ ብሎ የተናገረ ጌታችን ብቻ ነው። በዮሐንስ ወንጌል ብቻ ይህን ለሃያ አምስት ጊዜያት ያክል የተናገረ ሲኾን ኹሉም ቦታዎች ላይ አትኩረን ስናጠናቸው እጅግ ጥብቅ ብያኔዎችንና ግድ የሚሉ መጠይቆችን ያስከተለባቸው ናቸው። በሌላ አባባል ጌታ ኢየሱስ “አማን አማን እውነት እውነት” ብሎ ንግግሩን ከጀመረ የሚከተለው ነገር የሰማይና የምድርን ታሪክ ሊለውጥ የሚችል ነገር ስለኾነ ጆሮን ከፈት አድርጎ መስማት ያስፈልጋል ነው።

በመጀመሪያ ኒቆዲሞስ ተአምራቱንና ዝናውን በከተማ ውስጥ መስማቱ ትምህርት ኾነለት። በዚህ በተማረው ሐዲስ ነገርና ባወቀው ዕውቀት አመነና ሌሊት መጥቶ አስቀድሞ እምነቱን መሰከረ። ሌላ ሐዲስ ትምህርት፥ ከውኃና ከመንፈስ ድጋሚ የመወለድ ነገር በጌታችን ዘንድ ተጨመረለትና ተጨማሪ እምነት ተጠበቀበት ማለት ነው። ወዲያው የጌታችን በወልድ የማመን ትምህርቱ ቀጠለ።

ኒቆዲሞስ ወደ ጌታችን በመጣበት ጊዜ ከተናገረው እምነቱ አንጻር ሥጋዌን በሚገባ ተረድቶ የመጣ ይምሰል እንጂ ነገር ግን አምኖ የተናዘዘው የነበረ እምነቱ የኋላ ኋላ ገና ጎዶሎ ስለነበር ወደ ፊት ሄዶ የዳግም ልደትን ነገር ከመናገር ይልቅ ወደ ኋላ ሄዶ ሥጋዌን ከልሶለታል። “ወሶበ እንዘ ዘበምድር እነግረክሙ ኢተአምኑኒ ስለምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ” ብሎ ስለ ምሥጢረ ሥጋዌ “አልቦ ዘዐርገ ውስተ ሰማይ ዘእንበለ ዘወረደ እምሰማይ ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ላይ የወጣ ማንም የለም” አለ፤ ቊ.13። ከሰማይ ተልከህ ልታስተምር የመጣህ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብሎ ካመነበት ዘንዳ ከሰማይ ከወረደው ሌላ ወደ ሰማይ የወጣ የለም ይላል። ሥጋ ለብሶ በአጭር ቁመትና በጠባብ ደረት ተወስኖ የሚያየው ጌታችን የአብ አካላዊ ቃል የባሕርይ ልጁ መኾኑን ሲናገር። ቃል ከአርያም ወርዶ ሥጋን ሲዋሐደው ሥጋ በፍጹም ተዋሕዶ አርያም ወጥቷልና በሰማይም በምድርም፥ በማሕፀንም፥ ከማሕፀን ውጪ፥ ዓለሙንም ሞልቶ ያለው ክርስቶስ አንድ ብቻ ርሱም አንድ አካል አንድ ባሕርይ (ሥግው ቃል) ነው። ኒቆዲሞስ የቃልን ከሰማይ መውረድ አምኗል፤ ገና ከመምጣቱም የመሰከረ ይህን ነበር፤ የሥጋን ወደ ሰማይ መውጣትና ጠፈሩን ኹሉ መምላት ደግሞ አሁን ጌታችን ጨመረለትና የሥጋዌን ትምህርት አጸና።

በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት የአብ ቃል ፍጹም የራሱ መልክዕና ገጽ ያለው፣ አካላዊ፣ በባሕርዩ ስፉሕ ነው፣ ማለት ቦታ አይወስነውም፤ በኹሉም ያለ፣ የሌለበትም የሌለ ነው። ዘኢይትገመር ተገምረ የማይወሰን ተወሰነ፣ የማይቻል በማሕፀን ተቻለ እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም። እንዲህ ያለው ባሕርይ ከሰማይ ወርዶ ማሕፀነ ድንግል ሲገኝና ሥጋን ሲዋሐድ ከላይ ከዙፋኑ አልጎደለም። ከላይ ሳይጎድል ወረደ፣ በምድር ሳይጨመር ተወለደ ደግሞ እንዳለ ቅዱስ ሕርያቆስ። ሥጋን ፍጹም በመዋሐዱ ምክንያት የሥጋን ውሱንነት ባሕርዩ አድርጎ አሁን በማሕፀን ተወስኗል። ሥጋ ደግሞ በአንጻሩ ውሱን ነው፤ በቦታ ይገደባል። ዳግመኛ ሥጋ መለኮትን ፍጹም ሲዋሐድ የመለኮትን ምሉዕነት ገንዘቡ ስለሚያደርግ ቦታ የማይወስነው ይኾናል። ሲጠቀለል ቃል ከሰማይ ወደ ምድር ሲወርድና ሥጋን ሲዋሐደው ከፍጹም ተዋሕዶ የተነሣ ሥጋ ደግሞ ከማሕፀን በላይ ስፉሕ ኾኖ በሰማይም በአብ ቀኝ ተገኝቷል ነው።

የእግዚአብሔር ልጅ መውረዱን ኒቆዲሞስ አምኖ መጥቷል። ቀጥሎ ጌታችን ይህ ይኾነበትን ምክንያት ነገረው። የሰውን ልጆች የእግዚአብሔር ልጆች ያደርጋቸው ዘንድ እንደኾነ። የኒቆዲሞስ ቀጣይ ጥያቄው ይህ እንዴት ይኾናል ነበር፤ ከዚህ በኋላ ነገሩ የማወቅና ያለማወቅ ሳይኾን የማመንና ያለማመን ጉዳይ ስለኾነ ወልደ አብ (የአብ ልጅ) ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር ሳለ ነገር ግን መለኮት በባሕርዩ ሊሞት ስለማይችል በመስቀል ለሚኾን ቤዛነት ሲል ሥጋን የተዋሐደ ነው፤ በሥጋውም ሙሴ በምድረ በዳ የነሐሱን እባብ እንደሰቀለና በርሱም ባለደዌ የኾኑ ቤተ እስራኤል እንደተፈወሱ የሰው ልጅ (ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም) የሚያምኑበት ኹሉ ይድኑ ዘንድ ሊሰቀል ይገባዋል አለ። ስለዚህ ለኒቆዲሞስ ፍጹም ያልተከተተለት የነበረ ዕውቀት ምሥጢረ ሥጋዌ (ሥጋ የመልበሱ ነገር) መኾኑን ከጌታችን ምላሽ ልብ ይሏል። የኒቆዲሞስ ጥያቄዎች ትክክለኛ ፍሬያቸው (ትርጒማቸው) የሚታወቀው የጌታችንን ምላሾች በማስተዋል ስንረዳ ነው። ለአብርሃም በአረጋዊ ገጽ፣ ለሙሴ በተለያየ ሕብረ አምሳል እንደተገለጠላቸው ዛሬ ለእኛም በአንድ ጎልማሳ ምሳሌ ተገለጠልን ብሎ እንጂ ፍጹም ሰው ኹኖ፣ ሥጋን በተዋሕዶ ለብሶ መጥቶ ነው ብሎ አላሰበም።

ከጥምቀት … ወደ ስቅለት …

በጥምቀት ድጋሚ መወለድን ሲያወራ ቈይቶ ድንገት በመስቀል ከሚኾን ቤዛነት ጋር ጌታችን እንዴት አያያዘው የሚለው  ሌላ ቶሎ ሊረዳን የማይቻል ግንኙነት ነው። ስለ ጥምቀት ከማውራት በአንድ ጊዜ ወደ ስቅለት መሄዱ። ሥጋን የተዋሐደ (ሰው የኾነ) የእግዚአብሔር ልጅ በመስቀል በሚኾን መሥዋዕትነት ሞቶ ከሙታን መሐል ሕያው ኾኖ አንዴ ከተነሣ በኋላ በዚህ የቤዛነት ተግባር የሚያምኑና የሚታመኑ ሰዎች ኹሉ እነርሱም መሰቀልና መሞት ሳይገባቸው ከክርስቶስ ጋር ሞቶ መነሣት በተባለች በጥምቀት ምክንያት ሞተው እየተነሡ ድጋሚ ከውኃና ከመንፈስ ይወለዱና ሕያዋን ይኾናሉ፤ የእግዚአብሔር ልጆችም ይባላሉ ነው።

ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ክርስቲያኖች በጻፈው ክታቡ ላይ “ወተቀበርነ ምስሌሁ ውስተ ጥምቀት በሞቱ እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን።” እንዳለው ነው፤ ሮሜ.6፥4። በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ጥምቀት ማለት ወይም መጠመቅ ማለት ወደ ውኃ ተዘፍቆ መውጣት፣ ይህም ውኃ ውስጥ ስንዘፈቅ ከክርስቶስ ጋር በሞቱ እያበርን ከርሱ ጋር እንደመቀበር፥ ስንወጣ ደግሞ በርሱ ክብር ሕያዋን ኾነን መነሣት ማለት ነው። ሐዋርያው ቀጥሎ ቊጥር 5 ላይ “ወእመሰኬ ተመሰልናሁ በሞቱ ወንትሜሰሎ በሕይወቱሂ ሞቱን በሚመስል ሞት ከርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ከርሱ ጋር እንተባበራለን” ያለው ነው። ለዚህም “ወበከመ ሙሴ ሰቀሎ ለአርዌ ምድር በገዳም ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ኹሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል። ጌታችን ራሱን ሲጠራ እንኳ የሰው ልጅ እያለ ይጠራል፤ ይህ የሚያሳየን ተዋሕዶን ለማስገንዘብና የሥጋ ባሕርይ የኾነን (የመሰቀል ተግባር) እያጠየቀ መኾኑን ነው እስመ ከመዝ አፍቀሮ እግዚአብሔር ለዓለም ከመ ወልዶ ዋሕደ መጠወ በእርሱ የሚያምን ኹሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” አለ ማለት ነው፤ ዮሐ.3፥15-17። ጌታችን የመዳንን ምሥጢር በሥጋዌ፣ ስቅለትና ጥምቀት ለኒቆዲሞስ ከዜሮ ጀምሮ ሐዲስ ትምህርት ነበር ያስተማረው።

መዳን ማለት የእግዚአብሔር ልጅ መባል እንደኾነ ልብ በሉ። የእግዚአብሔር ልጅ መባል ደግሞ ወደ ምድር የላከውን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በመቀበል ነው። በአዳም እንደኾነ አለመዳን ማለት (መሞት ማለት) እንዲሁ የእግዚአብሔርን ልጅነት ማጣት እንደኾነ እግዚአብሔር አምላክ ወደ ቀደመ ክብራችን ያስገባንና የእኛን የእግዚአብሔር ልጅ መባል የመለሰልን ልጁን ልኮ እንደኾነ፥ ወይም በሌላ ቋንቋ ልጅነት የተዋጀው በልጅነት (የጸጋ ልጅነት የተዋጀው በባሕርይ ልጅነት) እንደኾነ የወንጌላችንን ምሥጢር ልብ ይሏል። በዚህም በልጁ ማመን የመዳንና ሰማያዊት መንግሥትን የመውረስ ቊልፍ ነው። ለዚህም ነው “እስመ ኢፈነዎ እግዚአብሔር ለወልዱ ውስተ ዓለም ከመ ይኰንኖ ለዓለም ዘእንበለ ከመ ያሕይዎ ለዓለም በእንቲአሁ ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና። በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።” ብሎ የተናገረው፤ ዮሐ.3፥17።

ይህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለጥምቀት ባወራበት አንቀጽ ያመነ የተጠመቀ ይድናል ካለው ጋር አብሮ ይሄዳል። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ኹል ጊዜም ከውኃና ከመንፈስ በመወለድ እንዲታጀብ ያስፈልጋል።

ከዚህ ቀደም እንዳልነው በዐቢይ ጾም ስምንቱ ሳምንታት የቀደሙቱ ዐራቱ እግዚአብሔር ስለመዳናችን ሲል ለእኛ ያደረጋቸውን ነገሮች ከዘወረደ እስከ መፃጕዕ ሰንበት ድረስ የምንናገር ሲኾን ከእኩለ ጾም (ማለትም ከደብረ ዘይት) ጀምረን የምንናገራቸው ግን ለመዳናችን ወይም የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ ከእኛ ከሰው ልጆች ደግሞ የሚጠበቁትን ነው። በዚህም በዚህ በሰባተኛው ሳምንት መንግሥቱን ለመውረስ በልጁ ፍጹም ማመን፥ መታመንና ምሥጢራትን በመፈጸም የልጅነትን ሀብት ገንዘብ ማድረግ እንዳለብን እናወራና በመጪው በሆሳዕና ሳምንት ግን ይህን ብናደርግ በክብር ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ከርሱ ጋር ነግሠን የምንገባ መኾናችንን እንናገራለን፤ የሳምንት ሰው ይበለን።

እግዚአብሔር አምላክ በጥምቀት ያገኘናትን ልጅነታችንን በንጽሕና ጠብቀናት የክብሩ ወራሾች፥ የስሙ ቀዳሾች እንድንኾን ኹላችንንም ይርዳን።

ይቈየን!