ስምንተኛውና
የመጨረሻው የዐቢይ ሰንበት ሆሣዕና ይባላል፡፡ አሁን አድን ማለት ነው፡፡ ቃሉ ቀድሞ “ሆሼያህ” በሚል በመስፍኑ ኢያሱ ይታወቃል፡፡
“ሆሼያ” ማለት ሆሼ - አዳኝ፥ ያ - ያህዌ በአጠቃላይ “እግዚአብሔር አዳኝ” ማለት ነው፡፡ በርግጥ ይህ ተለውጦ የሆሹዋ ኾኖ በግሪኩ
ኢያሱ ተብሎ ለመስፍኑ ተተርጒሟል፡፡ “ሆሣዕና” በዕብራይስጥ በትክክል “ሆሺያ-ና” ሲኾን እግዚአብሔር ሆይ አሁን አድን ማለት ነው፡፡
ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ የምድር ቈይታውን አጠናቅቆ ቤዛነቱን ሊያከናውን ቀናት ብቻ ሲቀሩት ሊሠዋ ወደ ኢየሩሳሌም የገባበት እለት ነው፡፡
የኢየሩሳሌም ከተማ ሕዝብ በታላቅ ድምቀት “ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው” እያሉ ከሕፃን እስከ ዐዋቂ በክብር እንደተቀበሉትና አብርሃም
ይስሐቅን
ሲወልድ፥ ይስሐቅ ያዕቆብን ሲወልድ፥ እስራኤል ከግብፅ ሲወጡ፥ ዮዲት ሆሉፎርኒስን ስትገድል በደስታ የሰሌን ዛፍ ቆርጠው የዘንባባ
ዝንጣፊ ይዘው እንዳመሰገኑ እሊህም ንጉሣቸውን ክርስቶስን በዚሁ ወግ
ደስ ተሰኝተው የተቀበሉበት ቀን ነው፡፡
ቅድስት
ቤተ ክርስቲያን ይህን እለት ካስዘከረች ኋላ በቀጥታ የጌታችንን የሕማሙን ሳምንት ወደ ማሳሰብ ትገባለች፡፡ ስለዚህ ሆሣዕና በተዝካር
(መታሰቢያ) አገባቡ ብቻ ሳይኾን በጌታችን ሕይወት፥ ሞትና ትንሣኤ ታሪክ ውስጥም የሕማምና መከራ የመጀመሪያ እለት ነው ማለት ነው።
በዐራቱም
ወንጌላት ይህ በታላቅ ክብር የኾነ በአተ ኢየሩሳሌም (ኢየሩሳሌም የመግባቱ ነገር) የተተረከ ሲኾን በዮሐንስ ወንጌልም በብዙ አጀብ
ገብቶ ወደ ቤተ መቅደስ እንዳመራና የማንጻትን ነገር እንዳደረገ የሚተርከው ክፍል ተለይቶ በምዕራፍ ሁለት ላይ ተመዝግቧል፡፡ ጌታችን
ወደ ኢየሩሳሌም የገባበት ምክንያት ይህ ሳምንት ቤዛ ተደርጎ ለዓለም የሚሰጥበትና በመስቀል ላይ የሚሠዋበት በመኾኑ፥ የመሥዋዕት
ደግሞ ትክክለኛ ቦታው ኢየሩሳሌም በመኾኑ ነው፡፡
ኢየሩሳሌም ከተማ …
የኢየሩሳሌም
ከተማ በኹሉም መለኪያዎች ከይሁዳና ከእስራኤል ከተሞች ኹሉ ታላቋ ናት፡፡ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከግብፅ ምድር በሙሴ መሪነት ካወጣቸውና
በኢያሱ ደግሞ ቀዳማዊት ከነዓንን ወርሰው በዐሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል መካከል ዕፃ ዕፃ ከተከፋፈሉ በኋላ ለይሁዳ ልጆች በደረሳቸው
ዕፃ ክፍል ውስጥ የምትገኝ ከተማ ነች፡፡ የሰሎሞን ቤተ መቅደስ የሚገኘው በዚያ በመኾኑ በተለይ በዘመነ ሚጠተ እስራኤል በዓለም
ዙሪያ ተበትነው የሚኖሩ እስራኤላውያን (የእስራኤል ዲያስፖራ ለማለት ይቻላል) ወደ ወገኖቻቸው ሲመኙና ሲሳለሙም የሚመጡባት ናት፡፡
የእስራኤል ፖለቲካዊ፥ ማኅበረ ሰብአዊ፥ ኢኮኖሚያዊ ኹለንተና ሕይወት መናኸሪያ የምትባለው ኢየሩሳሌም የአይሁድ ሊቀ ካህናት፥ የአይሁድ
ንጉሥ (ሄሮድስ) እና የሮም ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የይሁዳ ግዛት መስፍን መቀመጫ ከተማ ስትኾን የአይሁድ ሸንጎ (ሰንኸርዲን)
እና የአይሁድ ታላላቅ ምሁራነ ኦሪት፥ ሕግ ዐቂዎች፥ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፥ የሕዝብ ሽማግሌዎችም በዚህ ናቸው፡፡
ከተማይቱ
ከሞላ ጎደል የሮም ንጉሠ ነገሥት ወታደሮችና የአይሁድ ጭፍሮች በብዛት የሰፈሩባት ጥብቅ ከተማ ስትኾን የሕዝብ አመፅም ኾነ ማናቸውም
ዓይነት በከተማይቱ ሕይወት ላይ ሥር ነቀል ለውጥ የሚያመጡ እንቅስቃሴዎች በፍጥነት የሚዳፈኑባት ነች፡፡ የአይሁድ ሸንጎ፥ የሕዝቡ
ሽማግሌዎች፥ የአይሁድ ሊቀ ካህናት፥ እንዲሁም ንጉሥ ሄሮድስና መስፍኑም ጲላጦስ ጭምር ከእነርሱ ዓላማ ወጻኢ የኾኑ እንቅስቃሴዎችን
በግፍና ዘግናኝ በኾነ አኋኋን ይመልሱ ነበር፤ ሉቃ.13፥1 ሉቃ.13፥31፡፡ ይህ ታዲያ እግዚአብሔር የላከላቸውን ነቢያትም ይጨምራል፡፡
ኢየሩሳሌም በተደጋጋሚ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዲያስታውቋት የተላኩላት ነቢያትንና መምህራንን አሰቃይታ ጭምር የምትገድላቸው ሲኾን
በመጨረሻም ራሱ ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ በተገለጠ ጊዜ ስብከተ ወንጌሉን በተደጋጋሚ ማሰናከሏን ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሉቃስ
ወንጌል ላይ ተናግሮታል፤ ሉቃ.13፥34-35፡፡
ጌታችን
ኢየሱስ በዚህች ከተማ ያደረገው ወንጌለ መንግሥትን የመስበክና የንሥሐውን ጥሪ ማሰማት በአንጻራዊነት ከሌሎች ከተሞች ይልቅ ውጣ
ውረድ ነበረበት፤ በጊዜም ረገድ አጠር አጠር ያሉ ጥቂት ቈይታዎች ብቻ ነበሩ፡፡ የሚሞትበት ጊዜ ገና ስላልደረሰ አብዛኛ ስብከቱ
የተመሠረተው በሌሎቹ አውራጃዎች ነበር፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ላይ አይሁድ ሊገድሉት ድንጋይ የሚያነሡ መኾኑን ወንጌላውያን ሲገልጹ
“ወዲያውም ሊገድሉት ድንጋይ አነሡ” እና “ሊይዙትም ፈለጉ” የሚሉ ተደጋጋሚ ታሪኮችን በመጻፋቸው እናውቃለን፡፡ በአንድ ወቅት በከተማይቱ
ገብቶ ሲያስተምር ብዙዎች በርሱ ስለማመናቸው ሰግቶ ሄሮድስ ሊገድለው እንደፈለገ ፈሪሳውያን መጥተው ነገሩት፡፡ ያን ጊዜ ጌታ የሚሞትበት
ጊዜ ስላልደረሰ “ኢትሬእዩኒ እምይእዜ
እስከ ሶበ ትብሉ ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር በጌታ
ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስከምትሉኝ ድረስ አታዩኝም” ብሎ ከተማይቱን ለቅቆ ወጥቷል፤ ሉቃ.13፥31፡፡
በአጠቃላይ
ጌታችን በኢየሩሳሌም የነበረውን ስብከት በሚመለከት ሰፋ ያለ ትምህርት የምናገኘው በዮሐንስ ወንጌል ሲኾን ከሌሎቹ ወንጌላውያን በተለየ
ርሱ በአጠቃላይ ዐራት ጊዜ ያክል ወደ ኢየሩሳሌም ገብቶ መስበኩን ጽፏል፡፡ ሌሎቹ በአብዛኛው ጌታ በይሁዳ፥ ገሊላና ሰማርያ ያደረገውን
ስብከተ ወንጌል ይዳስሳሉ፡፡ ርሱ በእነዚህ ላይ ኢየሩሳሌምን ሰፋ አድርጎ ያክላል፡፡
በእነዚህ
ምክንያቶች የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ከሌሎች ከተሞች አንጻር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሚመለከት የነበራቸው ግንዛቤ (ትውውቃቸው)
ከሞላ ጎደል ያንሳል ለማለት ይቻላል፤ ብዙዎች እንዲያውም ስለርሱ ገና ያልሰሙ ነበሩባት፡፡
በየትኛውም
ቦታ ቢኾን ጌታ ኢየሱስ ያደረጋቸውን ተአምራት የሚያዩ ሰዎች ብዙ ጊዜ በማድነቅ ይህ ሊመጣ ያለው የአይሁድ ንጉሥ ነው እያሉ ወደ
መናገር ይሄዱ ነበሩ፡፡ በኢየሩሳሌም አሁን የሚያውቁትና የዘመሩለት አብዛኞቹ በተለይም የቃናውን ሠርግ ቤት ተአምርና የአልዓዛርን
ከሙታን መነሣት ተአምር በፈጸመ ጊዜ ዝናውን የሰሙና ርሱ የአይሁድ ንጉሥ ነው ያሉ በመኾናቸው ወደ ከተማይቱ ሲመጣ ስለእነዚህ ተአምራት
ምክንያት ሊያዩት ይወድዱ የነበሩ ናቸው፡፡ ወደ ከተማይቱ በክብር በገባ ጊዜ ከሕዝቡ ምስጋናና ዝማሬ የተነሣ “መኑ ውእቱ ዝንቱ ይህ ማነው” ብለው የተገረሙ ብዙዎች ነበሩ፡፡ “ዝ ውእቱ ኢየሱስ ነቢይ ዘእምናዝሬት ዘገሊላ ከገሊላ ናዝሬት የመጣ ነቢዩ ኢየሱስ ነው” በማለታቸው ይህ ይታወቃል፤ ማቴ.21፥10-11፡፡
መሥዋዕት ዘሐዲስ ሥርዓት …
እግዚአብሔር አምላክ ገና
ያኔ ሕዝበ እስራኤልን ከግብፅ እንዳወጣቸው ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ “ትከውኑኒ
እለ መንግሥት ወእለ ትሠውዑ ሊተ ወሕዝብ ዘጽድቅ የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ትኾኑልኛላችሁ።” ብሎ ተስፋ ቃል ኪዳን ሰጥቷቸው ነበር፡፡ ይህ ቃል ኪዳን እጅግ ታላቅ ቃል ኪዳን ነበር፡፡ ቤተ እስራኤል “ወልድየ ዘበኵርየ የበኵር
ልጆቼ” የተባሉበትና የቀደመው ኪዳን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕዝብ የተባሉበት ከመላው ዓለም የለያቸው አምላካዊ ቃል ኪዳን
ነበር፡፡ በዚህም የእስራኤል ቤት የኾኑ ዐሥራ ሁለቱም ነገዶች በመላ የካህናት ቤተሰብእ (ካህናት) ይባላሉ ማለት ነው፡፡
ይህች
ቃል ኪዳን ታዲያ ለአዳም ተሰጥታው ከነበር ቃል ኪዳን ጋር ትናበባለች፡፡ አዳም ሲፈጠር ካህንና ንጉሥ ተደርጎ ነበር፤ ማለት ጠባቂና
ገዥ ተደርጎ፡፡ ፍጥረታትን የፈጠራቸውና በባሕርዩ ንጉሥ ኾኖ የሚገዛቸው፥ ካህን ኾኖም የሚጠብቃቸው እግዚአብሔር ሳለ ነገር ግን
በአርአያው ልጅ አድርጎ ለፈጠረው ለአዳም በጸጋ ሁለቱንም ሰጠና ምድርን ግዛት ጠብቃትም አለው፤ ዘፍ.1፥28 ዘፍ.2፥15፡፡ ከምድር
ኹሉ ቀድሶ ዔዶምን ቅድስተ ቅዱሳን አደረገለት፤ ክህነቱም በዚያች ኾነ፡፡ ታዲያ በኃጢአት ምክንያት ልጅነትን ሲያጣም ልጅነቱ የሚገለጥባቸውን
እነዚህን ሁለቱንም ነገሮች ንግሥናንና ክህነትን አጣ፡፡ ግዛት የተባለችው ምድር አመፀችበት፥ ካልፋቃት የማትለማ፥ ካላረሳት የማታበቅል
ኾነች፤ አራዊቱም አመፁበት፤ ብላኝ ሲሉት የነበሩት እንስሳት ልብላህ ይሉት ገቡ፡፡ ይጠብቃትም ዘንድ ካህን ኾኖ ከተሾመባት ከዔደን
ገነትም ተባረረ፡፡ ርሷም በሱራፊ ነበልባላዊ ሰይፍ ትጠበቅ ነበር፤ ማንምም ወደርሷ መግባት አይችልም፡፡
እግዚአብሔር
ከቦታ ኹሉ ቅድስተ ቅዱሳን የምትኾንን እየቀደሰና ካህን እየሾመ መስጠቱ ከአዳም ጀምሮ የነበረ ወግ ነው ለማለት ነው፡፡ ታዲያ እስራኤልንም
ከግብፅ ሲያወጣቸው የተስፋይቱን ምድር ከነዓንን ከአሕዛብ ምድር ኹሉ ቀድሷት እነርሱንም “እለ መንግሥት ወእለ ትሠውዑ ሊተ የተቀደሰ ሕዝብ የካህናትም መንግሥት” ሲላቸው የክህነታቸውን እንዲያደርጉባት ርሷን አውርሷቸዋል፡፡
እንደ አዳም ኹሉ እነርሱም በወርቁ ጥጃ አምልኮ ረክሰው ሲቀሩ ግን ክህነታቸው ተወስዶባቸው፥ ዕድል ፈንታቸው ከዚህች መቅደስ ከተባለች
ከነዓን ተሰርዞ ለጥጃው የሰገዱ ኹሉ እስኪሞቱና እስኪያልቁ ሐዲስም ትውልድ እስኪፈጠር ዐርባ ዘመን በምድረ በዳ ሲቀበዘበዙ ኖሩ፡፡
ነገር ግን ከዐሥራ ሁለቱ ነገድ አንዱ ነገድ (ማለት የሌዊ ልጆች) ለጥጃው ያልሰገዱ በመኾናቸው፥ ይልቁንም በሙሴ ትእዛዝ ለእግዚአብሔር
ቀንተው በቊጣ ጭምር ለጣዖት ከሰገዱት መካከል 3000 ያህሉን የገደሉ ስለነበሩ ቃል ኪዳናቸውን የጠበቁ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከእስራኤል
የተነጠቀችው ክህነት ለእነርሱ ተሰጠችና ሌዋውያን የካህናት ነገድ ኾኑ፤ ዘጸ.32፥1-35፡፡
ከዐርባው
ዘመን ኋላ ለጥጃው ያልሰገደ ሐዲስ ትውልድ መፈጠሩን ሲያይ እግዚአብሔር ለነርሱ ከነዓንን አወረሳቸው፤ ሌላም ማንም ወደርሷ መግባት
አይችልም፡፡ በከነዓንም ካሉ የቤተ እስራኤል ምድር ኹሉ በይሁዳ አንዲቱን ቦታ እግዚአብሔር ቀደሳት፤ ያቺም ኢየሩሳሌም ነበረች፡፡
ርሷ የመሥዋዕቱ ቦታ ኾነች፤ በስፋትም “ቅድስቲቱ ከተማ” እየተባለች ታወቀች፡፡ ከኢየሩሳሌምም ደግሞ አንድን ቦታ እጅግ ቀደሰና
መቅደሱ የሚታነጽባት ቦታ አደረገ፡፡ ከመቅደሱም ቅድስቱን ቀደሰ፤ ከቅድስቱም ቅድስተ ቅዱሳንን አድርጎ ሌዋውያን የክህነት ተግባራቸውን
የሚያከናውኑባት፤ መሥዋዕተ ኦሪትን የሚያቀርቡባት አደረጋት፤ ሌላም ማንም ወደርሷ መግባት አይችልም፡፡ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ እንደ
ሙሴ ሥርዓት ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት ኹሉ በኢየሩሳሌም በመቅደሱ ኾነ፡፡
ጌታችን
የሐዲስ ሥርዓት መሥዋዕት ኾኖ የሚሠዋበት ሳምንት ሲደርስ ከቢታንያና ቤተ ፋጌ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ የመሥዋዕት ትክክለኛ ቦታው
ቤተ መቅደስ ስለኾነም ወደዚያ ሄደና በቤተ መቅደስ ርግብ፥ ዋኖስ፥ ላም፥ ጊደር፥ በግና ፍየል የኦሪትን መሥዋዕት እንስሶች የሚሸጡትን
ኹሉ አባርሮ (የኦሪትን መሥዋዕት አሳልፎ) በምትኩ ራሱን የሐዲስ ሥርዓት መሥዋዕት አድርጎ በመስጠት “ንስትዎ ለዝንቱ መቅደስ ወበሳልስ እለት አነሥኦ” መቅደስ ሰውነቴን አፍርሱት በሦስተኛው ቀን አነሣዋለሁ ብሎ ተናገረ፤ ዮሐ.2፥19፡፡
የዳዊት ቤት የነገሥታት ቤት ነው …
መንግሥተ እስራኤል በዳዊት
ንጉሥነት የቆመች ናት፡፡ ዳዊት ንጉሣችን፥ ሙሴ ነቢያችን፥ አብርሃም አባታችን እያሉ ይመካሉ፡፡ ለንጉሥ ዳዊት ያን ጊዜ “ቤትህና መንግሥትህም በፊቴ ለዘላለም ይጠነክራል፥ ዙፋንህም ለዘላለም ይጸናል።” ብሎ ቃል ገብቶለት ነበር፤ 2ሳሙ.7፥16፡፡ በተለይ ደግሞ ከዳዊት ልጆች ኹሉ አንዱ
በዚህች ዙፋን ላይ ለዘላለም እንደሚቀመጥ በነቢያትም ተደጋግሞ የሚነገር፥ በአይሁድም ዘንድ እጅግ የሚታወቅና የሚጠበቅ ነበር፡፡
ብዙዎች ባለማስተዋል የዳዊት ልጅ ዝናር ታጥቆ፥ ቀስት ወርውሮ፥ ሠራዊት አሰማርቶ ድል አድርጎ ነጻ ያወጣናል ብለው የሚጠብቁ
ነበሩ፡፡
ዘመኑ ሲፈጸምና መልአኩ
ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የመሲሑን መወለድና የርሷንም እናት እንድትኾነው መመረጥ ብሥራት በነገራት
ጊዜ “ወይሁቦ እግዚአብሔር አምላክ መንበረ ዳዊት አቡሁ
ወይነግሥ ለቤተ ያዕቆብ ለዓለም የልዑል ልጅም ይባላል፥ ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል፥ ወአልቦ ማኅለቅት
ለመንግሥቱ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።” በማለቱ ጌታችን ኢየሱስ ይህ
ሲጠበቅ የነበረውና ከነገሠ የማይሻረው የዳዊት ልጅ መኾኑን ያሳያል፤ ሉቃ.1፥32-33፡፡
በዚህም ሊሠዋ ወደ
ኢየሩሳሌም በሚመጣበት ወቅት የኢየሩሳሌም ሕዝብ “ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት በጌታ ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው” እያሉ ተቀብለውታል፡፡
እኛም “ሶበ ተአምሪ ኢየሩሳሌም ንጉሥኪ መጽአ ሰላምኪ ዮም” ብለን ይህን እናስዘክራለን፡፡
መስቀሉ የዳዊት ልጅ መንበር ነው …
የክርስቶስ በመስቀል ላይ
መሰቀልና መሠዋት ንግሥናው ነው፡፡ ወይም ክርስቶስ የዳዊትን መንበር የሚረከበው በመስቀል ላይ ነው፡፡ ርሱ እንዳለ “ወአነኒ እምከመ ተለዐልኩ እምድር እስሕብ ኵሎ ኀቤየ አሁን የዚህ ዓለም ፍርድ ደርሶአል፤ አሁን የዚህ ዓለም ገዥ ወደ ውጭ ይጣላል፤ እኔም ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ።” ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ቀጥሎ እንዴት ባለ ሞት እንደሚሞት ሲያመለክት ይህን እንዳለ
ይነግረናል፡፡ በመስቀል ላይ ከምድር ከፍ ከሰማይ ዝቅ ብሎ መሰቀሉን ሲናገር ነው፡፡ ያን ጊዜ ርሱ ይነግሣል የእግዚአብሔር
መንግሥት በምድር ትተከላለች፡፡ እንዲያውም በአንድ ወቅት አንዲት ሴት ቀርባ ሁለቱ ልጆቿ አንዱ በግራ አንዱ በቀኝ በመንግሥቱ
እንዲቀመጡ እንዲያዝ በጠየቀች ጊዜ የምትለምነውን እንኳ እንደማታውቅ ነግሯት ነበር፤ ማቴ.20፥21፡፡ ምክንያቱም ያ ጽዋ
እግዚአብሔር ላዘጋጀላቸው ስለነሚኾን ነበር፡፡ የሚሰቀልበት ጊዜም ሲደርስ እነሆ የሰው ልጅ ሊከብር ነው አለ፡፡ ይህም በክብር
ከፍ ብሎ መንገሡን ያሳያል፡፡
ንጉሥ ዳዊትም በትንቢቱ “እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም ወገብረ መድኃኒተ በማዕከለ ምድር እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፤ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ”
ሲልም የጌታችን ንግሥናው በማዕከለ ምድር ቀራንዮ ለቤዛ ዓለም በመሰቀሉ የሚኾን መኾኑን ጠቁሟል፤ መዝ.73፥12፡፡
ታዲያ
ሊሰቀል (ሊነግሥ) ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ የኢየሩሳሌም ሕዝብ በሙሉ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ በንጉሥ ደንብ ለንጉሥ እንደሚገባ ሥርዓቱን
ፈጽመው የሰሌን ተክል ቅርንጫፎች፥ ልብሶቻቸውን ኹሉ እያነጠፉ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው እየዘመሩ አክብረውታል፡፡
ጥንት
ነቢዩ ኤልሳዕ ከደቂቅ ነቢያት አንዱን ጠርቶ ቀርነ ቅብዕ ያዝና ኢዩን ለእስራኤል ንጉሥ ይኾናቸው ዘንድ ቀብተኸው ና ብሎ ልኮት
ነበር፡፡ ነቢዩም ኢዩ ከሚኖርበት ዘንድ ሄዶ ሊቀባው ቢፈልግ ኢዩ ከባልንጀሮቹ ጋር እየተጫወተ ነበርና ይህን ማድረግ ይቸገራል፡፡
ከዚያም ጠጋ ብሎ በፈሊጥ “መልእክት አለኝ” ይለዋል፡፡ ኢዩም ግራ በመጋባት “ለእኔ ነው ለእኛ” ይለዋል፡፡ ነቢዩም መልሶ ለአንተ
ነው ወደ እልፍኝ ና እዚያ እሰጥሃለሁ ባለው ጊዜ ኢዩ ነቢዩን ተከትሎ ወደ እልፍኝ ይመጣል፡፡ ያን ጊዜ ነቢዩ “ከመዝ ይቤ አምላከ እስራኤል ቀባዕኩከ ትንግሥ ላዕለ ሕዝብየ
እስራኤል የእስራኤል አምላክ እንዲህ ይላል ለሕዝቤ እስራኤል
ንጉሥ ትኾን ዘንድ ቀብቼሃለሁ” ብሎ ዘይቱን በፍጥነት ቀብቶት እየሮጠ ትቶት ወጣ፡፡ ኢዩ በነገሩ እንደተደናገጠ ወደ ባልንጀሮቹ
ሲሄድ ምን ኾነ፥ ምን ተናገረህ ብለው ጠየቁት፡፡ ግድ ባሉት ጊዜም ነገሩን ነገራቸው፡፡ ባልንጀሮቹም ኢዩ ንጉሥ በመኾኑ ተደስተው
ወዲያው ለንጉሥ በሚገባ ክብር ቅርንጫፎችንና አልባሳትን እያነጠፉ ጨርቅም እየጋረዱ አመስግነዋል፡፡
የዳዊት
ልጅ ንጉሥ ክርስቶስም ሊነግሥ ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ ሕዝቡ የሰሌን ዛፍ ቅርንጫፎችን ይዘውና ልብሶቻቸውን አንጥፈው በክብር
ተቀብለውታል፡፡
ጌታችን
ድጋሚ ይመጣል፤ ያን ጊዜ ሰማያዊት ኢየሩሳሌምን አስቀድማ ተስፋ ተደርጋ የተሰጠችንን ርስታችንን ሊያወርሰን ይኾናል፡፡ ጌታችን በክብር፥
በዝማሬና በእልልታ፥ በመላእክት ይባቤ ከቅዱሳኑ ጋር ለፍርድ ይመጣል፡፡ አሁን በአህያ ተቀምጦ በትሕትና ያደረገውን ያን ጊዜ በዘባነ
ኪሩብ ተቀምጦ በፍጹም ልዕልና ንጉሥ ኾኖ በመንበሩ ላይ ኾኖ ሊፈርድ ይመጣል፡፡ በዚህኛው አብነት የዋህና ትሑት፥ በግ ኾኖ ሊታረድ
መጥቷል፡፡ ያን ጊዜ የማይሻረው የዳዊት ልጅ፥ የይሁዳ አንበሳ ኾኖ ይመጣል፡፡ ልበ አምላክ ዳዊት እንዳለ “እግዚአብሔርሰ ገሃደ ይመፅእ፤ ወአምላክነሂ ኢያረምም፤ እሳት
ይነድድ ቅድሜሁ እግዚአብሔር ግልጥ ኾኖ ይመጣል፤ አምላካችን
ዝም አይልም፤ እሳት በፊቱ ይነድዳል፡፡” እኛም በእልልታና በዝማሬ እንቀበለዋለን፡፡ ርሱ ለእኛ ቸርነትንና በጎነትን ኹሉ ፈጽሞ
እንዳደረገልን በሃይማኖትና በምግባር ባለ ትሩፋት ኾነን ርሱን ደስ በሚያሰኝ ሕይወት የተመላለስን ኹላችን ከርሱ ጋር አብረን የምንነግሥ
ነን፡፡
ተዘከረነ ኦ እግዚኦ በውስተ
መንግሥትከ አቤቱ በመንግሥትህ አስበን፡፡
ቸር
ይቈየን!