ዛሬ ግንቦት አንድ ቀን በኦሪት ዘፍጥረት ምዕ.3፣15 ላይ
በሰማይና በምድር ጌታ በእግዚአብሔር ለአዳም ዘር ኹሉ የተሰጠ ቃል ኪዳን ፍጻሜውን ማግኘት የጀመረበት እለት ነው፡፡
እዚያ ምን ተባለ፤
“በአንተና በሴቲቱ በዘርህና በዘሯ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ”
-- ዘፍጥ.3፣15
ይህ ለማን ተባለ፤
በጊዜው በተራቀቀ ጥበብ ሔዋንን ከማረከና ከነባሏ ዕፅን በመብላት
በእግዚአብሔርና በመንግሥቱ ላይ አመፅን እንዲያከናውኑ ያቀደ፣ ያመቻቸና ያሳካ ሰውን ኹሉ የሚያስተው ዘንዶውና የቀደመው እባብ ዲያብሎስ
ነው፡፡ ይህን ተግባር በጀብዱ በፈጸመ ጊዜ የእግዚአብሔርን አርኣያና አምሳል አግኝቶ በጸጋ ልጅ ተብሎ በከበረው በሰው ዘር ላይ
የማያዳግም ውድቀት ያመጣ መስሎት ነበር፡፡
ወዲያው ግን የምሕረት ጌታ እግዚአብሔር መጣና ለጠፋው ጥፋት ፍትሑን ከገለጠና የአምላክነቱን
ካከናወነ ኋላ መለስ ብሎ ደግሞ የሰው ልጅ በዚያ አወዳደቅ ወድቆ እንደማይቀር ይልቁኑ ከዘሩ የምትሆን አሸናፊት ሴት ከተዋጊ ልጇ
ጋር ኾና በእባቡና በቀደመው ዘንዶ በዲያብሎስ ላይ እንደምትዘምትበት፤ ጥብቅ ጠላትነት በመካከላቸው እንደሚኾን እግዚአብሔር አምላክ
መርዶ ብሎ ለእባቡ ምሥራች ብሎ ደግሞ ለሰው ልጅ ነግሮ ነበር፡፡
ይህ በሰው ልጅ ታሪክ የመጀመሪያው የድኅነት የተስፋ ቃል ነበር፡፡
በሕይወታችን ለመጀመሪያ ጊዜ ስለድኅነታችን ተስፋን ያዳመጥነው ያኔ ነው፡፡
ይህ የተስፋ ቃል ሁለት ዓይነት ውጤቶች አስገኝቷል፡
አንደኛው ውጤት በእባቡ በኩል …
ማናት ይህች ሴት … ማንስ ነው ዘሯ ችሎ የሚጣላኝ የሚል መደመምና
በማናቸውም መልኩ እንድህች ያለችቱን ሴትም ኾነ የርሷ ይኾናል የሚባልን ዘር የሚመስል አግኝቶ ለማጥፋት ዘመቻውን ያኔ ጀመረ፤ ሥራ
ፈትቶም አያውቅ፤
አቤል መስሎት ቃየልን አስነሣበት፣ ሴቲቱም ዘሯም አመለጡት፡፡
ሴት ወይ የሴት ዘሮች መሰሉት ደባለቃቸው፣ አመለጡት፡፡
አብርሃም መሰለው እነአቤሜሌክን አስነሣበት፣ አሁንም አመለጡት፡፡
ያዕቆብ መሰለው በዔሳውም በረሃብም አመሃኝቶ ዘመተበት፣ ሴቲቱንም
ዘሯንም ሳታቸው፡፡
ሙሴ መሰለው፤ በኹሉም ፈተነው፤ ሳታቸው፡፡
ዳዊት መሰለው፤ ጎልያድን፣ ሳዖልን፣ የገዛ ልጁን አዘመተበት፣
አጣቸው፡፡
በኹሉ መንገድ ጠላትነቱን አበረታ …
እንዲህ እንዲህ እያለ በላያቸው ላይ አንዳች የርሱን ዙፋን
ሊገለብጥና ያገኘውን ድል ሊነጥቅ የሚችል የሚመስል ቅድስና ያላቸውን ኹሉ አሳደደ፤ እነዚህ ኹሉ ግን መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን
መሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ላይ ነው እንደተባለላት ሴቲቱና ዘሯ የተመሠረቱባቸው (የሚገኙባቸው) እንጂ ራሳቸው አልነበሩም፡፡ እነርሱ
ግን ገና ይመጡ
ዘንድ አላቸው፡፡
ሁለተኛው ውጤት በሰው ልጅ በኩል …
በደረሰበት ውድቀት እጅግ ተሸማቅቆና በነፍስ ሕመም እጅግ ማቅቆ
በሲኦል እሳት ተዘፍቆና በድቅድቅ ጨለማ ተደፍቆ የሚኖረው የሰው ልጅ እንዲያ ወዳለ የቀደመው ክብርና ንጽሕና የሚመልሱትና ይህን
ባለጽኑዕ በትር፣ ባለ እሳት ዛንጅር ጠላት ዘንዶውን ተፋልመው የሚረቱ ጠላቶቹ የተባሉ ሴቲቱና ዘሯ እንዴት ባለ ዘመንና እንዴት
ባለ ኹናቴ እንዲመጡና እንዲታደጉት ይገረም ነበር፡፡
አንዲት ንጽሕት ሴትና አሸናፊ ልጇ ለሰው ልጆች ኹሉ የድኅነትና የዳግም ትንሣኤ የጨለማ መሐል ጽኑዕ ብርሃናት ኾነው በየዘመኑ ነቢያት የሚተነበዩ፣ በየካህናቱ ሱባዔ የሚቈጠሩ፣ በየመምህራኑ የሚተረጎሙና ምሳሌያቸውም የሚመሰል ኾነ፡፡
ነበልባል ተዋሕዷት በሲና ሙሴ ያያት ቊጥቋጦን ተመልክተን ሴቲቱ
የእኛኑ ርጥብ ሥጋ የለበሰች መኾኗንና አሸናፊ ልጇ ደግሞ ነበልባላዊ እሳተ መለኮት መኾኑን ተረዳን፣
10ቱ ቃላት እግዚአብሔር ራሱ በጣቶቹ የጻፈባት ጽላተ ሙሴን
ተመልክተን ሴቲቱ አማናዊት ጽላተ ኪዳን ዘሐዲስ ሥርዓት መኾኗንና አሸናፊ ልጇ ደግሞ እግዚአብሔር ራሱ ቅድመ ዓለም የወለደው የእግዚአብሔር
ቃል መኾኑን ተረዳን፣
በንጹሕ ወርቅ መሶብ የተያዘ ኅብስተ መናን ተመልክተን ሴቲቱ
የሕይወት እንጀራን የያዘች አማናዊት ሙዳየ ወርቅ መኾኗንና አሸናፊ ልጇም ሥጋው ተበልቶ ደሙ ተጠጥቶ ሕይወትና ሥርየት የሚያሰጥ
ከሰማይ የወረደ ኅብስት መኾኑን ተረዳን፣
የካህኑ አሮን ከዘራ የእጅ በትር ኾና ሳለ በማይመረመር አምላካዊ
ሥራ እንዳልተተከለችና ውኃ እንዳላጠጧት ለምልማ ቅጠል ስታበቅል አይተን ሴቲቱ ያለ ወንድ ዘር በድንግልና የምትጸንስ ዘሯም ሕይወትና
ልምላሜ ነፍስን የሚያድለን መኾኑን ዐወቅን፤
ትንቢቱንማ ማን ይቊጠረው …
“የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባላስቀረልን ኖሮ እንደሰዶም
በኾንን ገሞራንም በመሰልን ነበር”፤ ኢሳ.1፣9 ካለው አንሥቶ ስንቱን እንጠቅሳለን ….
እንዴት ባለ አኋኋን መቼ ይኾን ሴቲቱና ዘሯ የሚገኙ ብለው
እስራኤል በጠየቁ ጊዜ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።” እያለ የተናገረው ኹሉ ስለዚያች ሴትና ስለአሸናፊ ዘሯ የተሰጠ ተጨማሪ ፍንጭ ነበር፤ ኢሳ.7፣14፡፡
የዘመኑ ፍጻሜ ይልቁኑ በቀረበ ጊዜ ትንቢቱ ይልቅ እየጎላ እነ ሚክያስን “አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የኾነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚኾን ይወጣልኛል። ስለዚህ ወላጂቱ እስከምትወልድበት ጊዜ ድረስ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፤ የቀሩትም ወንድሞቹ ወደ እስራኤል ልጆች ይመለሳሉ። ርሱም ይቆማል፥ በእግዚአብሔርም ኃይል በአምላኩ በእግዚአብሔር ስም ግርማ መንጋውን ይጠብቃል፤ እነርሱም ይኖራሉ፤ ርሱ አሁን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ታላቅ ይኾናልና።” እስከሚሉ አደረሳቸው፤ ሚክ.5፣2-4፡፡
ዘመኑ እስከደርስና ቃል ኪዳኑ እስኪፈጸም ጊዜ ድረስ ለመዳናችን ተስፋ ተደርገው እንደምልክት ሲሰጡ የኖሩት ይህች ንጽሕት ሴትና አሸናፊ ዘሯ ነበሩ፡፡
እነሆ ዛሬ እርሷ በሊባኖስ ተወለደች፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን በመዝሙሩ “ወዳጄ ሆይ፥ ሁለንተናሽ ውብ ነው፥ ነውርም የለብሽም። ሙሽራዬ ሆይ፥ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፤ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፤” ብሎ እንዳመለከተ በሊባኖስ ዛሬ ተወለደች፡፡
ኋላ ርሷና ዘሯ በቤተልሔም በረት ሲታዩ ተስፋ አድርገው ሲጠብቋቸው የነበሩ ኹሉ “ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥”፤ ማቴ.2፣11፡፡ በታላቅ ደስታ ደስ ተሰኝተውም እጅ መንሻ አቀረቡለት፡፡
ሲጠብቁት የኖሩት ደስ ያላቸው በሌላ በምንም አልነበር፡፡ ሕፃኑን ከእናቱ ጋር ስላዩ እንደኾነ ወንጌላዊው አጥርቶ ተናግሯል፡፡ ምክንያቱም የተሰጣቸው ምልክት እንዲያ ስለነበረ፤ ሱባኤ የተቈጠረ ምሳሌ የተመሰለ እንዲያ ስለነበረ፤ ትንቢት የተነገረች አንዲት ሴት ከተወደደ ዘሯ ጋር እንደምትኾን ስለነበር፡፡ “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።” እንዳለ በትንቢት ኢሳ.7፣14፡፡
ኋላ ዘሯ ወደ ዓለም የመጣውና ራሱን ቤዛ አድርጎ ሕዝቡን የሚቤዣቸው አሸናፊው ልጇ እንደ መኾኑ በመጀመሪያው ተኣምር ከዓለም ጋር በሚተዋወቅበት ጊዜ ሴቲቱ አብራው የምትታወቅ ነችና ዛሬ ተወለደች፤
በመጨረሻም የአምስት ሺህ ከአምስት መቶ ዘመን፣ የ46 ሱባኤ መገባደጃ ላይ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በመስቀል ላይ በነገሠበት ጊዜም የቀደመውን እባብ ከቤዛነቱ ኃይል የተነሣ ከመስቀሉ እግር ሥር ረግጦና ቀጥቅጦ በስምንት የነፋሳት አውታር ጠፍሮ አሥሮ በስምንት የእሳታት ዛንጅር አክሮ በሥልጣን ሲገዛውና ሲያናዝዘውም ከዘሯ ጋር ሴቲቱ አትለይም፤ ዛሬም ድረስ በሕሊናችን ተሥለው አሉ፡፡
ይህ ኹሉ ከመኾኑ በፊት ግን ዛሬ ሴቲቱ ተወለደች …
ዛሬ የሲኦል ቅጽሮች መታወካቸው ተጀመረ፤ የጥልቁ ደጆች መዋወጻቸው ተወጠነ፡፡ ዛሬ የሞት አበጋዞች ፈራ ተባ አሉ፡፡ ዛሬ የጨለማው ዓለም ገዢ ዲያብሎስ .. ጎበዝ! አገር ሰላም ነው ብሎ ፈተነ፡፡ ዛሬ ጨረቃ ተወለደች፡፡ ኋላ ፀሐይን የምትወልድ ናትና የጨረቃይቱ ጥቂት ብርሃን የጨለማውን ግርማ ሰረሰረ፤ ኋላ ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ ሲኦልን የሚመዘብርና ጨለማዋን የሚበዘብዝ ነውና፡፡
ዛሬ የተገባው ቃል ኪዳን ሊፈጸም፣ ተስፋው ተደርጎ የተሰጠው ሊሳካ፣ የተቀጠረው ቀጠሮ መድረሱ ለታዛቢው ኹሉ ገሀድ ኾነ፡፡
ዛሬ ሴቲቱ ተወለደች፤
እልልልልልልልልልልልልልልልልልልልልልልልልልልልል!
መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን፤
ወብእሲ ተወልደ በውስቴታ በውስቴታ ተወልደ፡፡
እልልልልልልልልልልልልልልልልልልልልልልልልልልልል!
“ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች። እርስዋም ፀንሳ ነበር፥ … እነሆም ታላቅ ቀይ ዘንዶ፤ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶችም ነበሩት በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩ፥ ጅራቱም የሰማይን ከዋክብት ሲሶ እየሳበ ወደ ምድር ጣላቸው። ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕፃንዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ። አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች፤ … ዓለሙንም ኹሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ። ዘንዶውም ወደ ምድር እንደ ተጣለ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት። ከእባቡም ፊት ርቃ አንድ ዘመን፥ ዘመናትም፥ የዘመንም እኵሌታ ወደ ምትመገብበት ወደ ስፍራዋ ወደ በረሀ እንድትበር ለሴቲቱ ሁለት የታላቁ ንሥር ክንፎች ተሰጣት። እባቡም ሴቲቱ በወንዝ እንድትወሰድ ሊያደርግ ወንዝ የሚያህልን ውኃ ከአፉ በስተ ኋላዋ አፈሰሰ። ምድሪቱም ሴቲቱን ረዳቻት፥ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠችው። ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ፤ በባሕርም አሸዋ ላይ ቆመ።” -- ራእ.12፣1-18 ፤ ዘፍጥ.3፣15