ጥንተ ነገሩ ለታቦት/ጽላት
ታቦት ትርጉሙ “ማደሪያ” ሲኾን “መገለጫም” ይኾናል፡፡ የተዠመረው ከብሉይ ኪዳን ነው፡፡ ታቦትን ለመዠመሪያ ጊዜ ጠርቦ አበጅቶ የሠራ ንጉሠ ፳ኤል እግዚአብሔር ነበር፡፡ ዘፀ. ፴፩፥፲፰ “እግዚአብሔርም ከሙሴ ጋር በሲና ተራራ የተናገረውን በፈጸመ ጊዜ በእግዚአብሔር እጅ የተጻፈባቸው ጽላት ሰጠው” ዘፀ. ፴፪፥፲፭—፲፯“ሙሴም ሁለቱን የምስክር ጽላት በእጁ ይዞ ከተራራው ወረደ፤ ጽላቱም የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ፤” ይለናል፡፡
ታቦትና ጽላት በሐዲስ ኪዳን
ታቦተ ሕጉ የተሠራው በብሉይ ኪዳን ብቻ እንዲያገለግል ሳይኾን እስከዘለዓለም ድረስ እግዚአብሔር ያሰበለት ግዳጅ፣ ተለእኮ ስላለው ነው፡፡ ንጉሡ ሰሎሞን ታላቁን ቤተ መቅደስ ከሠራ በኋላ ፩ኛነገ. ፰፥፩—፷፮ እንደጨረሰ ወደእግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ለዘለዓለም የሚኖርበት ማደሪያ ቤት እንደሠራለት፣ የእግዚአብሔር ዐይኖች በቤተመቅደሱ እንዲኾኑ፣ ስሙም በቤተመቅደሱ እንዲመሰገን፣ ሕዝቡ ኹሉ በዚህ ቤተመቅደስ የሚጸልዩትን ጸሎት እንዲቀበል ተመኘ፡፡
ወዲያውኑ እግዚአብሔርም በጐ ምላሽ ለሰሎሞን መለሰለት “እግዚአብሔርም አለው፡ - በፊቴ የጸለይኸውን ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቻለሁ፤ ለዘለዓለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዐይኖቼና ልቤ በዘመኑ ኹሉ በዚያ ይኾናሉ” አለ ፩ኛ ነገ. ፱፥፫፡፡ እግዚአብሔርን ንጉሡን ሰሎሞንን ታቦተ ጽዮንን ለማሳረፍ ስለሠራው በጐ ሥራ የዳዊትን አይነት ምርቃት መረቀው “እኔ ከ፳ኤል ዙፋን ከዘርህ ሰው አታጣም ብዬ ለአባትህ ዳዊት እንደተናገርሁ የመንግሥትህን ዙፋን በ፳ኤል ላይ ለዘለዓለም አጸናለሁ”
ታቦትና አገር፣ ታቦትና ጠላት
በአሁን ዘመን የሰሎሞን ቤተ መቅደስም እንዳለ አይታወቅም፤ ታቦተ ሕጉም በ፳ኤል የለም፡፡ ታዲያ እግዚአብሔር “ለዘለዓለምም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ የሠራኸውን ቀድሻለሁ፤ ዐይኔና ልቤም በዘመኑ ኹሉ በዚያ ይኾናሉ” ሲል የሰጠውን ቃልኪዳን አጠፈ ማለት ነዋ፤ አላጠፈም፡፡ ዓለም ታቦተ ሕጉን ሲተዉ ኢትዮጵያውያን በቤተ መቅደስ ስለሚገለገሉባቸው የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ሕያው ኾኗል፡፡
እንዲያውም ታቦተ ጽዮን በኢትዮጵያ የክብር መጠለያ ስለተገኘላት የእግዚአብሔር ዐይኖችና ልቡ በሰሎሞን ቃልኪዳን መሠረት በዚህ ይኾናሉ፤ ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ዳሯ እሳት መሃሏ ገነት ኾኖ ለዘመናት ጠላት እየተንበረከከላት የኖረችው፡፡ “ወቀተለ ነገሥተ ጽኑዓነ” ብርቱዎችንም ነገሥታትን ገደለ እንዳለ ልበ አምላክ ዳዊት መዝ.፩፻፴፭ ታቦተ ጽዮን ሳለቻቸው ፳ኤል ጠላቶችን ኹሉ ድል የሚያደርጉ ነበሩ፡፡ ያለ እርስዋ ግን በጠላቶቻቸው ላይ ወደቁ “እርስዋም የእግዚአብሔር ታቦት ተማርካለችና ክብር ከ፳ኤል ለቀቀች፤” እንዳለ ፩ኛ ሳሙ. ፬፥፲፱—፳፪ በምትኩ ታቦተ ጽዮን የከተመችባት ኢትዮጵያ ጠላት የማይደፍራት ኾነች ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን እንዲህ እያሉ ይዘምራሉ “ንጉሥኪ ጽዮን ኢይትመዋዕ ለጸር ወኢየኃድጋ ለሀገር” ጽዮን ኾይ ንጉሥሽ ለጠላት አይሞትለትም/አይሸነፍም፤ አገርንም አይተውለትም፡፡
ታቦትና ጽላት በሰማይ
መላእክትና የሰማይ ሠራዊትም ታቦተ ሕጉን በዛሬዋ እለት እየተገለገሉበት እንደሚገኙ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ “እነኾም በሰማይ ያለው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተከፈተ በመቅደሱ ውስጥም የቃል ኪዳኑ ታቦት ታየ፡፡” ራዕ ፲፩፥፲፱ ፲፭፥፭ ታቦተ ሕጉ ከምድር ኅልፈት በኋላም በሰማይ እንደሚኖር ይህ አብነት ነው፡፡ ስለዚህ ታቦት በብሉይ ኪዳን የነበረ ብቻ ሳይኾን በሐዲስም እስከዘለዓለምም የሚኖር ነው፡፡
ታቦት፣ ዕጣን፣ ንጹሕ ቊርባን
ታቦተ ሕጉ በ፳ኤል ብቻ የነበረና በሐዲስ የማይኖር ቢኾን ኖሮ “ከፀሐይ መውጫ ዠምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ይከበራልና፤ በየስፍራው ለስሜ ዕጣን ያጥናሉ፤ ንጹሕንም ቁርባን ያቀርባሉ፤ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይኾናልና ይላል ኹሉን የሚችል እግዚአብሔር” ሚል ፩፥፲፩ የሚለው የእግዚአብሔር ቃል ሊታጠፍ ነበር ማለት ነው፡፡ ይህ ትንቢት በቀጥታ ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች መኾኑ ግልጥ ነው፡፡ ምክንያቱም በብሉይ ኪዳን ቤተ መቅደስም ኾነ የዕጣን የቁርባን አገልግሎት እንኳን ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ ላሉ አሕዛብ በኢየሩሳሌም ከሚኖሩ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በቀር ለ፳ኤል ጎረቤቶች እንኳ አልተፈቀደምና፡፡ ነቢዩ ሚልክያስ ንጹሕ ዕጣን ያለው በማቴ ፪፥፲፩ እንደተነገረ ከአሕዛብ ወገን የኾኑ ሰብአ ሰገል በቤተልሔም ለክርስቶስ ካቀረቡት ጀምሮ እስከ ዛሬ በዓለም ያለን ክርስቲያኖች በቤተመቅደስ፣ በታቦቱ ዙሪያ በክርስቶስ ስም ለክርስቶስ የምናቀርበው ቅዱስ ዕጣን ነው፡፡
አንድም በማቴ ፳፮፥፳፮ ጌታ ኅብስቱን አንሥቶ ነገ የሚቆረሰው ሥጋዬ ይህ ነው፤ ወይኑንም አንሥቶ ነገ ስለብዙዎች ኃጢአት የሚፈሰው ደሜ ይህ ነው ብሎ ለሐዋርያት የሰጣቸው የክርስቶስ ሥጋና ደም ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን በኢየሩሳሌም ብቻ መኾን የሚገባቸው ቤተ መቅደሱ፤ ዕጣኑ፣ ቁርባኑ፣ በክርስቶስ ደም በአዲስ ሕይወት፣ በአዲስ ተፈጥሮ፤ በአዲስ ሥርዓት፣ ክርስቲያኖች ለኾንን ለዓለም ሕዝቦች በየሥፍራው (በያለንበት) እንድንጠቀምባቸው ከተፈቀዱልን በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩት ሁለቱ ጽላት ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ በየቤተ መቅደሳችን ለቊርባኑ የክብር ዙፋንነት እንገለገልበታለን፡፡
ታቦት የእግዚአብሔር የክብሩ መግለጫ ዙፋን እንደኾነ ኹሉ ተገቢው ክብር እንዲሰጠው ቅዱስ መጸሐፍ ያዝዛል፡፡ ታቦቱን የተዳፈሩት ፍልስጥኤማውያን ዳጎንን አፈራርሳ እነርሱንም በአባር ቸነፈር እንደመታቻቸውና በክብር የተቀበላትን አቢዳራን ግን ለሦስት ወር ቤቱንና ቤተሰዎቹን እንደባረከችለት መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ ፩ኛ ሳሙ. ፮
ለታቦት ሊሰጥ የሚገባው ክብር
በ፩ኛሳሙ. ፮፥፲፭—፳፫ ዳዊት በታቦተ ጽዮን ፊት በዝማሬ ሲያመሰግን ሜልኮል ደግሞ እርሱ በሰጠው ክብር ስትሳለቅ እንደነበር ይነግረናል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ለዳዊት “እስመ እምፍሬ ከርስከ አነብር ዲበ መንበርከ” ከወገብህ ፍሬ በመንበርህ ላይ አኖራለሁ የሚል ታላቅ ቃል ኪዳን ሲሰጠው ሜልኮል ደግሞ “ኢወለደት ሜልኮል እስከአመሞተት” ሜልኮልም እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ አልወለደችም ተባለ፡፡ ይህ ታቦተ ሕጉ የሚያከብሩትን ሰዎች የሚያከብር የሚያዋርዱትን ደግሞ የሚቀሥፍ መኾኑን ያስተምረናል፡፡
ታቦት ከመነሻው ከምንጩ ጀምሮ በክብር የኾነ መኾኑን በዘፀ. ፫፥፭ ላይ “ወደዚህ አትቅረብ አንተ የቆምክባት ሥፍራ የተቀደሰች መሬት ናትና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ” ብሎ እግዚአብሔር ሙሴን ሲያዝዘው እናያለን፡፡ በኋላም ለ፳ኤል በኢያሱ ሲናገር ኢያ. ፫፥፫ “የአምላካችሁ የእግዚአብሔር የቃልኪዳን ታቦት ሌዋውያን ካህናት ተሸክመው ባያችሁት ጊዜ ከሰፈራችሁ ተነሥታችሁ ተከተሉት፤ በእናንተና በታቦቱ ያለው ርቀት በስንዝር ሁለት ሺህ ክንድ ያህል ይሁን” በማለት ተናግሯል፡፡
በአጠቃላይ ታቦተ ሕጉ በሐዲስ ኪዳን በክርስትና በበለጠ ክብርና አክብሮት አገልግሎት እየተፈጸመበት ነው፡፡ ይህም የኾነው የሚሠዋው መሥዋዕት አማናዊው የክርስቶስ ክቡር ደሙ ቅዱስ ሥጋው ስለኾነ ነው፡፡ የበግና የላም፣ የዋኖስና የርግብ ደም የሚፈስበት የብሉይ ኪዳን ታቦተ ሕግ ይህን ያክል ክብር ካለው “ዝንቱ ውእቱ ደምየ ዘሐዲስ ሥርዓት ዘይትከዐው በእንተ ብዙኃን ለኅድገተ ኃጢአት” ስለብዙዎች ኃጢአት በሐዲስ ኪዳን የሚፈስሰው የክርስቶስ ደም (ማቴ.፳፮፥፳፰) የሚከብርበት የሐዲስ ኪዳን ታቦተ ሕግማ ምንኛ አብዝቶ ይከብር፡፡
“እርስዋም የእግዚአብሔር ታቦት ተማርካለችና ክብር ከ፳ኤል ለቀቀች፤” ፩ኛ ሳሙ. ፬፥፳፪
ይቈየን!
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ