አማናዊት ታቦት እመቤታችን
ከላይ ያሠፈርነው ኃይለ ቃል ታቦተ ጽዮን የፍልስጥኤማውያን
ጣዖት ከሚያርፍበት ከቤተ በኣል ወደ ዳዊት ከተማ በሌዋውያን ካህናትና ሕዝባውያን ታጅባ በደማቅ ሥርዓት ስትደርስ ከድንቅ ሥራዋና ከተገለጠባት የእግዚአብሔር ኃይል የተነሣ ንጉሠ እስራኤል
ዳዊት በመንፈስ ተመርቶ ተናግሮታል። በታላቅ አክብሮትና በፍርኃት “የእግዚአብሔር ታቦት ወደ እኔ እንዴት ይመጣል” አለ፤ 2ሳሙ.6፥9።
በቅድስት ሐዋርያዊት
ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በብሉይ ኪዳን የሚደረግ ማናቸውም ተግባር የሐዲስ ኪዳን ዐቢይ ክስተት ምሳሌነት እንዳለው በጥብቅ ይታመናል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቀዳማዊ አመጣጡ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ወፍ ዘራሽ የሆነ ሳይሆን ብዙ ትንቢት የተነገረለት ፍጻሜ፥ ብዙ ምሳሌ የተመሰለለት አማናዊ እና ብዙ ሱባኤ የተቈጠረለት አመጣጥ በመሆኑ ነው።
ይህም
በቅዱሳን ሐዋርያት ትምህርት በጉልሕ ታይቷል፤ ለአብነት ያክል ቅዱስ ጳውሎስ የእስራኤልን በባሕር መካከል ማለፍ የጥምቀት ምሳሌ
መሆኑን መጥቀሱ፥ ይመገቡት የነበረውን ኅብስትና ውኃ የጠጡበትን ዓለት “ክርስቶስ” ብሎ መጥቀሱ ፤ ዕብ.10፥1 ፤
1ቆሮ.10፥4 ፤ 1ቆሮ.10፥2 ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የኖኅን መርከብ መድኅን የጥምቀት ምሳሌ አድርጎ እንዳስተማረውና ሌሎችም
ይገኙበታል፤ 1ጴጥ.3፥18 ፤ ቆላ.2፥11 ፤ ዮሐ.3፥14። የቀደመውን የቀደመውን እግዚአብሔር ሕዝብ (የሕዝበ
እስራኤልን) ሕይወት ልብ ብሎ መመልከት ለሐዲስ ኪዳን ፍጻሜ አረዳድ ብዙ መሠረትነት ስላለው ሰዎች በጥንቃቄ ሊይዙት ይገባል።
በተለይም የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት
ወንጌልን ሲጽፉልን በብሉይ ኪዳን ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተነገረውን ትንቢትና ምሳሌ የተረጐሙበት መንገዳቸው የእያንዳንዳቸው በተለያየ መንገድ ነው። አንዳንድ ወንጌላውያን በነቢይ የተነገረውን ቃለ ትንቢት መስመር ጠብቀው ደግመው በመጻፍ ትንቢት በክርስቶስ እንደተፈጸመ ሲናገሩ፥ ማቴ.1፥23 ሌሎች ግን የብሉይ ኪዳን ትንቢትና ምሳሌውን ታሪክ ከሐዲስ ኪዳን ፍጻሜና አማናዊ ጋር አዛምዶ በምሥጢር በማስቀመጥ በአተራረክ ስልት አንባቢው እንዲረዳው አድርገው ይጽፋሉ፤ ሉቃ.1፥1-ፍ.ምዕ። ከእነዚህ ሐዋርያት አንዱ ሐዋርያው ወንጌላዊ ቅዱስ ሉቃስ ነው።
በዚህ ጽሑፍ ሐዋርያው ቅዱስ ሉቃስ በብሉይ ኪዳን በእስራኤላውያን ሕይወት ማዕከላዊ ሥፍራ ስለነበረው ስለ ቃል ኪዳኑ ታቦት የሐዲስ ኪዳን አማናዊ ፍጻሜ በረቂቅ ምሥጢር ያሠፈረውን የወንጌል ክፍል እንመለከታለን።
ታቦተ ጽዮን እስራኤላውያን ከግብፅ ምድር በተኣምራት ከወጡ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ በሙሴ በኩል የሰጣቸው የብሉይ ኪዳን ቅድስት ንዋይ ነች። አሠራሯም በእግዚአብሔር ትእዛዝ ነበር። ታቦተ ጽዮን በእስራኤል ዘንድ ከነበራት ሚና አንጻር ስንመለከተው እጅግ አስደናቂ በሆነ መልኩ በሐዲስ ኪዳን በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቤዛነት ተግባር ውስጥ እመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ካላት የነገረ ድኅነት ሚና ተስማምቶ እናገኘዋለን።
እስኪ ታቦተ ሕግ ዘኪዳን የእመቤታችን ምሳሌ እንደነበር ከሚያሳዩ ነጥቦች መካከል ዐሥሩን ከዚህ እንደሚከተለው እንመልከት፡-
1.
|
ታቦተ ጽዮን በእግዚአብሔር እጆች የተጻፉ ዐሠርቱ ቃላት በውስጧ የሚያድሩባት ነች፤ ዕብ.9፥4። እንግዲህ የምድርና የሰማይ ንጉሥ እግዚአብሔር በገዛ ጣቶቹ ቃላቱን
የጻፈባቸውን ጽላት ምን ያክል በክብር እንደምንመለከታቸው ማሰብ አያዳግትም። ሌላ ነገር በጣቱ እንደጻፈ ምንም አለተገለጠምና። አማናዊት ታቦት እመቤታችንም የእግዚአብሔር አብን አንድያ ልጁን አካላዊ ቃል የተባለ
እግዚአብሔር ወልድን በማሕፀኗ መሸከሟ ታቦተ ጽዮን የርሷን ምሳሌነት የያዘች መሆኗን ያሳያል፤ ሉቃ.1፥31-33።
2.
|
ታቦተ ጽዮን በውስጧ ከያዘቻቸው ቅዱሳት ንዋያት መካከል አንዷ የሊቀ ካህናቱ የአሮን በትር ነበረችበት፤ ዘኍ.17፥8። ካህኑ አሮን የእስራኤል የመጀመሪያው ሊቀ ካህን የነበረ ሌዋዊ ሲሆን ርሱም
ለእስራኤል ትክክለኛው የካህናት አለቃ መሆኑን ለማሳየት እግዚአብሔር በትሩ ሳይተክሏትና ውኃ ሳያጠጧት እንድትለመልምና እንድታፈራ በማድረግ አሳይቷል። አንድ ሰው በትር የሚሠራው እንጨት ቈርጦ፥ መልምሎ፥ አለስልሶ፥ አለዝቦ፥ ዘንግ አድርጎ ነው። እነዚህ ተግባሮች በአንድ እንጨት ላይ ከተደረጉበት የሕይወት ምልክቱ ከላዩ ላይ ይጠፋል። ከሥር ከተለየ፥ ከግንድ ከተላቀቀ፥ ከተቀረፈፈ፥ ከተለሰለሰና ከለዘበ በኋላ ድጋሚ ያ እንጨት ሕይወት ኑሮት ቅጠል ሊቀጥል፥ ፍሬ ሊያፈራ፥ ሕይወት ሊመላለስበት አይችልም። ነገር ግን የአሮን በትር በእግዚአብሔር ሥራ እንዲሁ ባለበት ለምልሞ መገኘቱ ተኣምራዊ ነበር። እንደዚሁ ሁሉ እመቤታችንም ወንድ ሳያገኛት፥ ያለ ዘርና ያለ ሩካቤ ሊቀ ካህናት ክርስቶስን ፀንሳ መገኘቷ ምሳሌው የተመሰለላት አማናዊት ፍጻሜ ለመሆኗ አሳዪ ነው፤ ሉቃ.1፥35።
3.
|
ታቦተ ጽዮን በውስጧ ከያዘቻቸው ቅዱሳት ንዋያት ሌላው እስራኤላውያን በምድረ በዳ ለዐርባ ዓመታት ያክል እየተመገቡት በዚያ አስከፊ ምድረ በዳ ሕይወታቸውን አቈይቶ ለቁመተ ሥጋ ያበቃቸው እግዚአብሔር ከሰማይ ያወርድላቸው የነበረ ኅብስተ መና ይገኝበታል፤ ዕብ.9፥4። እንደዚሁ ሁሉ ከሰማይ የወረደ እውነተኛ እንጀራ የተባለ፥ ሰው ከርሱ ከበላ ለዘላለም ሕይወት የሚያገኝበት ጌታችን አምላካችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከእመቤታችን ማሕፀን ተገኝቷል፤
ከሥጋዋ ሥጋን፥ ከነፍሷም ነፍስን ነስቶ ሰው ሆኖባታል። በዚህም እውነተኛ መና የተያዘባት ሙዳይ፤ ኅብስተ መናም የሚያድርባት
ታቦተ ሕግም እርሷ ናት፤ ዮሐ.6፥51።
4.
|
ታቦተ ጽዮን በእስራኤል መካከል በነበረችበት ጊዜ ሁሉ በላይዋ ላይ የእግዚአብሔር ኃይል ይጸልልባት ነበር። መንፈስ ቅዱስ በደመና አምሳል በታቦቱ ላይ በሚረብበት ጊዜ ሁሉ የእግዚአብሔር ክብር ድንኳኑን ይሞላ ነበር፤ ዘፀ.40፥34-37። ያን
ጊዜም ይህን የሚመለከቱ እስራኤልና ሙሴ በታቦቱ ፊት ዐቢይ ሰላምታን እየሰጡ፥ እየማለሉም ይሰግዱ ነበር። እንደዚሁ ሁሉ እመቤታችንም አማናዊት ታቦት በመሆኗ “መንፈስ ቅዱስ ያድርብሻል፤ የልዑል ኃይልም ይጸልልሻል” ሲል ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል አብሥሯታልና
አማናዊት ታቦተ ሕግ እርሷ ናት፤ ሉቃ.1፥35።
5.
|
ንጉሠ
እስራኤል ዳዊት በነገሠበት ወራት ታቦተ ጽዮን ወደ ይሁዳ ተራራ ተጉዛ በጌት ሰው በአቢዳራ ቤት ሦስት ወር ተቀምጣለች፤ 2ሳሙ.6፥1-11። እንደዚሁ ሁሉ አማናዊት ታቦት እመቤታችን
ቅድስተ ቅዱሳን ማርያምም ከሺህ ዘመናት በኋላ በዘመኗ ወደዚሁ የይሁዳ ተራራ ተጉዛ በዘካርያስና ኤልሳቤጥ ቤት ሦስት ወር ተቀምጣለች፤ ሉቃ.1፥39 ፤ ሉቃ.1፥56። (ሁለቱ ቤቶች ዛሬ በሚገኙበት በዚህ አንድ ተራራ በጥቂት ደቂቃዎች የርምጃ ጉዞ ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው ለመሄድ ይቻላል።)
6.
|
ታቦተ ጽዮን በአቢዳራ ቤት ሦስት ወር ስትቀመጥ ርሱንና ቤተ ሰዎቹን በታላቅ በረከት እንደባረከቻቸው ይታወቃል፤ 2ሳሙ.6፥11። አማናዊት ታቦት እመቤታችንም የበረከት እናት ስለሆነች ወደ ኤልሳቤጥ ቤት ስትሄድም ኤልሳቤጥ በመንፈሰ እግዚአብሔር ተቃኝታ ሦስት ጊዜ ቃለ በረከትን አሰምታ ተናግራለች። ርሷን ቡርክት፥ የማሕፀንዋን ፍሬ ቡሩክ፥ ዳግመኛም የጌታዋን ቃል ያመነች የተባረከች ብላ አመስግናለች፤ ሉቃ.1፥39-45።
7.
|
ታቦተ ጽዮን በይሁዳ ተራራ በተገኘች ጊዜ ነቢይና ካህን፥ ንጉሥ ዳዊት ካህናት የሚለብሱትን የበፍታ ኤፎድ ለብሶ በታቦቱ ፊት እየዘለለ አመስግኗል፤ 2ሳሙ.6፥14። እንደዚሁ ሁሉ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ተቀብሎ ለዘላለም የሚነግሠውን ክርስቶስን የፀነሰችው እመቤታችንም ከገብርኤል ብሥራት በኋላ በይሁዳ ተራራ በቤተ ኤልሳቤጥ በተገኘች ጊዜ የበፍታ ኤፎድ ለብሶ ዘወትር በእግዚአብሔር ፊት የሚያገለግለው የካህኑ ዘካርያስ ልጅ ገና በፅንስ ያለው ነቢይና ካህን ቅዱስ ዮሐንስ እየዘለለ በማሕፀን አመስግኗል፤ ሉቃ.1፥43።
8.
|
ታቦተ ጽዮን በዚህ ሁኔታ በዳዊት ከተማ በተገኘች ጊዜ ንጉሡ ዳዊት የጌታ ታቦት ወደ እኔ እንዴት ይመጣል ብሎ ጮኸ፤ 2ሳሙ.6፥9። እመቤታችንም በዚያ በተገኘች ጊዜ ቅድስት ኤልሳቤጥ “የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ አንድ እንዴት ይሆንልኛል፤” ብላ በታላቅ ድምፅ ጮኻለች፤ ሉቃ.1፥43።
9.
|
በታቦተ ጽዮን ፊት በደስታ የዝማሬ ቃል ያሰማውን ዳዊት ተመልክታ ያሾፈችበት የሳዖል ልጅ ሜልኮል እስከምትሞት ድረስ መካን እንድትሆንና እንዳትወልድ ተቀሥፋለች፤ 2ሳሙ.6፥23። በሰውም በጌታም ፊት ያለነቀፋ በጽድቅ የምትረማመደው መካኒቱ ኤልሳቤጥ ደግሞ በእርጅናዋ ወራት ፀንሳ ነቢዩን ወልዳለች፤ ሉቃ.1፥24-25።
10.
|
ታቦተ ሕጉን ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በሰማይ ላይ ሆኖ በራእዩ ተመልክቶታል፤ ራእ.11፥19። ይኸው ሐዋርያ ከዚሁ ራእዩ ቀጥሎ ደግሞ እመቤታችንን ፀሐይ ተጎናጽፋና ጨረቃን ተጫምታ እንዲሁ በሰማይ ተመልክቷታል፤ ራእ.12፥1።
የእመቤታችንን ነገር ቅዱስ ሉቃስ ያሠፈረበት መንገድ የታቦት ዘእስራኤል ፍጻሜ አማናዊት መሆኗን በሚያሳይ መንገድ በጥንቃቄ ነበር። በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም እመቤታችንን እውነተኛዋ ጽላተ ኪዳን ዘታቦት እንላታለን። በታቦተ ሕጉ ላይ ድፍረትን ያሳዩ እነ ዖዛ ወዲያው እንደተቀሠፉ ሁሉ፥ 2ሳሙ.6፥7 በእመቤታችን ላይ በድፍረት የተነሡ እነ ታውፋንያም ተቀሥፈዋል። ከዚህም ባሻገር በኍል.4፥4-6 እንደምናነበው ታቦተ ጽዮን ሰማያዊ መጋረጃን እንደሚዘረጋባት ሁሉ ዛሬም ሥዕለ ማርያም በሚሣልበት ጊዜ ሁሉ ሰማያዊ መጎናጸፊያን ትጎናጸፋለች። በራእይ የተመለከቷት ቅዱሳን ሁሉ በዚህ አኋኋን ተመልክተዋታልና።
ነቢየ እግዚአብሔር ሙሴ በአምላኩ ትእዛዝ በታቦተ ሕጉ
ላይ በወርቅ የቀረጻቸው ቁመታቸው 5 ክንድ ያክል የሚሆን ኪሩቤል የተባሉ ቅዱሳን መላእክት አምሳያ ነው። ኪሩቤል የሚባሉት
ከዘጠና ዘጠኙ ብርሃናውያን ነገደ መላእክት መካከል በሰማይ ቤተ መቅደስ የእግዚአብሔርን ዙፋን የሚሸከሙ ዐሥሩ ነገድ
ብርሃናውያን ቅዱሳን መላእክት ናቸው። እነዚህም ዐራት ሆነው በዐራት ማዕዝን በሰው፥ በእንስሳ፥ በንሥርና በአንበሳ ገጽ እየሆኑ
መንበሩን ይሸከማሉ፤ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉም ስሙን ያመሰግናሉ፤ ራእ.4፥6-9 ፤ ኢሳ.6፥1-5። እግዚአብሔር መላእክት
በጀርባቸው የሚሸከሙት አምላክ ባይሆንም በቸርነቱ ግን ለክብሩ መገለጫ ይሆን ዘንድ መንበሩን የሚሸከሙ አድርጓቸዋል። ይህንንም
አርአያ በመውሰድ ሙሴ ታቦቱን በሚሠራበት ጊዜ የኪሩቤልን ምስል በታቦተ ሕጉ ላይ ይቀርጽበት ዘንድ እግዚአብሔር ትእዛዝ
ሰጥቶታል፤ ዘፀ.25፥18። ይህም ታቦቱ እግዚአብሔር አምላክ ለእስራኤል የሚገለጥበት እንደመሆኑ መጠን የሰማይ መቅደሱ አብነት
በምድር በታቦቱም ላይ እንዲሆን ስለፈቀደ ነው።
በሐዲስ ኪዳን ታቦት ላይ ግን የኪሩቤል ሥዕል
አይገኝም። ሐዋርያዊት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ታቦተ ሕጉን በሐዲስ ኪዳን ቤተ መቅደስ ስትጠቀም በታቦቱ ላይ
የእመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ማርያምንና የተወደደ ልጇ የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሥዕለ አድኅኖ ታደርግበታለች።
ይህም በሐዲስ ኪዳን ኪሩቤል ከተባሉት ነገደ መላእክት በብዙ እጥፍ የምትበልጥ፥ ከአዳም ወገን የተገኘች እናታችን ኪሩቤል
የማይችሉትን አምላክ በማሕፀንዋ ስለተሸከመችው ይልቅም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ስለነሣ ለእነርሱ ካላቸው ክብር የሚበልጥ
እርሷ ስላላት ነው። በዚህም ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ሦርያዊ በውዳሴ ማርያም የረቡዕ ምንባብ “ይእቲ ተዐቢ እምኪሩቤል፤ ይህች
ከኪሩቤል ትበልጣለች” እንዳለ የሐዲስ ኪዳን መንበሩ እመቤታችን በጭኗ ላይ የተወደደ ልጇን አቅፋ ያለችበት ሥዕል ይቀመጣል
ማለት ነው።
እመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም በነገረ ድኅነት ላይ ያላት ሥፍራ እጅግ ታላቅ ነውና ማንም ሰው ሳያውቀው መቅረት የለበትም።
እግዚአብሔር ለእስራኤል ትእዛዝ አድርጎ የሰጣቸውን ዐሠርቱን ቃላቱን በዚህ መልክ ካከበራቸውና እጅግ ንጹሕ በሆነ በውስጥም
በውጭም በወርቅ በተለበጠ ማደሪያ በታቦተ ኪዳን የሚያሳድራቸው ከሆነ የእግዚአብሔር ቃል የተባለ ተቀዳሚና ተከታይ የሌለው
አንድያ ልጁን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያድርባትን አማናዊት ታቦትማ እንዴት ባለ በሚበልጥ ጥንቃቄ አያዘጋጃት። እርሷ ለዘላለም
የማይጠፋው የሐዲሱ ኪዳን ታቦተ ጽላት ነች።
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም በዓሏን ከታቦተ ጽዮን ጋር አወዳጅታ በወርኃ ኅዳር 21ኛ ቀን ታከናውናለች። ቸርነቱ
የበዛች የቀደምቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር በቅድስት እናቱ በእመቤታችን
ረድኤትና ምልጃ ሁላችንንም ያስበን። የእናታችን ቅድስተ ቅዱሳን ማርያምን ፍቅሯን በልባችን፥ ጣዕሟን በአንደበታችን ያኑርልን፤ ይቆየን።
“የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ
ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል፤” ሉቃ.1፥43
kale hiwot yasemalen
ምላሽ ይስጡሰርዝ