ሰንደቅ ዓላማችን


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!

እንደምን ሰንብታችኋል! አሜን! የዘመናት ጌታ፥የጸጋ ኹሉ ባለቤት፥ አምላከ ፀሐይ ወአምላከ ከዋክብት፥ አምላከ ኩሉ ፍጥረት ሥላሴ ይመስገን፡፡ እነሆ ተወዳጇ የጽጌ ሠሙነ ሱባኤአችን ጠባች፥ ከመጥባትም አልፋ በእግዚአብሔር ቸርነት አጋመስናት፡፡ ድሮ ድሮ ይህችስ የፈቃድ ጾም ናት ተብለን እንማር ነበር፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን ለገናናው አምላካችን ምስጋና ይግባው በእመቤታችን ፍቅር የተነደፈው ሕዝበ ክርስቲያን ኹሉ በጾሙም እየተጋ በማኅሌቱም እያበረ ከበዓሉ በረከት እየተሳተፈ ይገኛል፡፡ ለትሩፋት ያተጋን አምላካችን ምስጋና ይግባው፡፡

ሠሙኑን አገራችን ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ልታከብር ተሰናድታለች፡፡ ይህንም ተከትሎ እኛም ስለሰንደቅ ዓላማችን መንፈሳዊ ወግ ልናወጋችሁ መጣን፡፡ መቼም ይህች ቤተክርስቲያን ለአገራችን ታሪክ፣ ትውፊት ያበረከተችው አስተዋፅዖ መብዛቱ፡፡ ዞሮ ዞሮ
የዚህ ሰንደቅ ዓላማ መነሻ ቤተክርስቲያኒቱ መኾኗ፡፡ በኦሪት ዘኁልቊ ምዕራፍ ፳፬ ላይ ውሉደ ያዕቆብ እየበዙ፥ ምድርን የመምላታቸውም ቃልኪዳን እየተፈጸመ ባለበት ዘመን በለዓም የሚባል የ፳ኤል መብዛትና ለመቊጠር ማታከት ያሳሰባቸው ርገማቸው ብለው የላኩት አባት በርግማን ፈንታ መንፈሰ እግዚአብሔር ያቀበለውን ስለ፳ኤል የምርቃትን ቃል ሲናገር፣ የያዕቆብንም ልጆች እየጠራ መፃእያቱን ሰናያት በመተንበይ ጭምር ሲናገር … ይሁዳ አንበሳ ነው… አለ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሱ የሚገኝ ነውና፡፡

ከእምሥርወ ይሁዳ የኾነ ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ቀዳማዊ ምኒልክ በነገሠባት መንበር የሚቀመጡ ኢትዮጵያውያን ነገሥታት ኹሉ ሠሎሞናውያን ናቸው ተብሎ ስለሚታመን ...ሞኣ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ... እየተባለ የበለዓም ምርቃት እተቀፀለላቸው ይነግሣሉ፡፡ ታዲያ በ፲፭ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው አሉ በቤተ መንግሥቱ አካባቢ አንድ የአናብስት ኹሉ አለቃ እስኪመስል ግርማም የኾነ አንበሳ የመስቀል አዕፁቅ ያለው ባለ ቀይ፣ ብጫና አረንጓዴ ቀለማት ዘርፍ የታሰረበት ጦር በትክሻው ላይ አንግቦ በይፋም ባይኾን ውስጥ ውስጡን የንግሥና ምልክት ኾኖ ያገለገለ፡፡ ለክፍለ ዘመናት ያክል በዚህ መልኩ ከቆየ በኋላ ዳግማዊ ምኒልክ በነገሡበት በ፲፱ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ ባንድራ ላይ ብሔራዊ ዓርማ ኾነ፡፡ ግጥጥሞሽ ታያላችሁ፤ ከሦስት ሺህ ዘመን በፊት ቀዳማዊ ምኒልክ የነገሥታቱን ሥረው በትውልድ ከ፳ኤል ነገድ፣ ከአናብስቱ ዘር ሲያገጣጥም ከሦስት ሺህ ዘመን በኋላ ደግሞ ዳግማዊ ምኒልክ ሞኣ አንበሳን በይፋ ብሔራዊ ዓርማ አደረጉት፡፡

በመሠረቱ ዓርማው ያረፈበት ባለ ቀይ፣ ብጫና አረንጓዴ ቀለም ሰንደቅ ዓላማ የሦስት ሺህ ዘመን ታሪክ ያለው አይደለም፡፡ ከታሪክ እንደምንረዳው ግን ከመሣፍንቱ ዘመን ቀደም ብሎም ሦስቱ ቀለማት በተለያየ መልክ ብሔራዊ ዓርማ ኾነው እንዳገለገሉ ተተርኳል፡፡ ነገር ግን እንደዛሬው በ፬ ማዕዝን ቅርፅ ሳይኾን እያንዳንዱ ቀለማት ከግራ ወደቀኝ ረዘም ረዘም ብለው የተጋደሙ ሦስት ሦስት ማዕዝናት ነበሩ፡፡ እንደዛሬውም አረንጓዴ፣ ብጫ ቀይ ያልኾኑ ይልቁኑም ቀይ፣ ብጫ አረንጓዴ ነበሩ፡፡ ሦስቱ ቀለማት የዛሬውን መልክና አኳኋን የያዙ ከከ፲፱ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ኋላ ነው፡፡

ይህ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ያበረከተችው ባለቀስተ ደመና ኅብረ ቀለም ሰንደቅ ዓላማ ፳ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ ከአውሮፓውያን አገዛዝ ነፃ ለመውጣት ሲታገሉ በኖሩ እንዲሁም ኢትዮጵያና ኢትጵያውያንን እንደ ነፃነት አርአያ በወሰዱ አያሌ ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ የትግላቸው መሪ የነፃነት ዓርማም ኾኖ ተወስዷል፡፡ በዓለም ሕዝብ ዘንድ ታላቅ አግራሞት የፈጠረው፣ ለኢትዮጵያውያን ግን የጸሎትና ምህላቸው ውጤት እንደሆነ ከሚታወቀው ከአደዋው ጦርነት ድል ማግስት የልዳው ጊዮርጊስ በነጭ ፈረስ ላይ ኾኖ በጦሩ አውድማ የተጋደለላት፣ ቀድሞም በቅዱሳን ጸሎት ሕልው የኾነች፣ ኧረ እንደውም ቀድሞም ለአምላክ እናት ለእኛ እመቤታችን አሥራት ተደርጋ የተሰጠች ይህች ኢትዮጵያ ዓርማ አድርጋ ያጸናችው ባለቀስተ ደመናው ኅብር ሰንደቅ ዓላማ በአሁኑ ወቅት በ፲፯ ሉዓላውያን አገራት መልኩ እንደየ ፍላጎትና መሻታቸው እየተቀያየረ ሰንደቅ ዓላማቸው ኾኗል፡፡ የጌታችን እናት፣ የጻድቃን መመኪያ፣ የመላእክት ፍስሐቸው፣ የገነት ውበት፣ መሶበ ወርቃችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ! ስለጥበቃሽ፣ ስለቸርነትሽም፣ አምላክን በመውለድሽ ስላለሽ ክብር፣ የቃልኪዳን አገርሽ ኢትዮጵያ ምስጋናን ታቀርብልሻለች፡፡

ኢትዮጵያውያን እመቤታችንን እጅግ ይወዷታል፡፡ የመመኪያቸው ዘውድ ናትና፡፡ መኩሪያም መታፈሪያቸውም እርሷ ናትና፡፡ ገና ሲወለዱ በእናት ማኅፀን ስሟ እየተጠራ ይወለዳሉ፡፡ አዎን! እርሷ ልጇን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደች ያለምጥና ያለፃዕር ነውና፤ የሴቶቿን ምጥ ታቀል ዘንድ ስሟ ይጠራል፡፡ በአራስ ቤትም …እንኳን ማርያም ማረችሽ.. ማርያም በሽልም ታውጣሽ… እየተባለ ኢትዮጵያውያን በአራስ ጆሯቸው ስሟን ይጠግቡታል፡፡ ከእናታቸው ጡት ወተትም ጋር የሠማያዊት እናታቸውን ስም ጣዕም አብረው ያጣጥማሉ፡፡ እባካችሁ ኢትዮጵያውያን ይህ ወግ ይቀጥል፡፡ እንዲጠፋም አትፍቀዱ፡፡

ትንሽ አደግ ሲሉም በሁለት እግራቸው ቆመው መቦረቅ ሲጀምሩ ስመ እግዝእትነ ማርያም አይለያቸውም፡፡ አባርሮሽ ሲጫወቱ አንደኛው አባራሪ ሌላኛው ተባራሪ ኾነው አባራሪው ባለው ኃይል ኹሉ ለመያዝ ሲሮጥ፣ ተባራሪውም በበኩሉ ከመይያዝ ለማምለጥ ይሮጣል፡፡ ታዲያ ከአንድ ጥግ ደርሶ ወጥመድ የኾነበትና መውጫ ማምለጫ መንገድ ያጣ ጊዜ … የማርያም መንገድ… ብሎ ይለምናል፡፡ የማርያም መንገድ ብሎ የለመነ ታዲያ እምቢ አይባልም፡፡ አዎና! በአዳም በደል ምክንያት ለገሀነም ፍርድ የተጣልን ብኩኖች በነበርንበት ጊዜ መውጫ መንገድ የኾነችን፣ ጠላታችንን ያሳፈረልንን መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደች ናትና ኢትዮጵያውያን ከጨዋታቸው እንኳ አይለዩአትም፡፡ ታዲያ ያሃ ተባራሪ ልጅ በተሰጠው ጠባብ የማርያም መንገድ ተጠቅሞ ባለ ኃይሉ ኹሉ ሮጦ ማምለጥ ካልቻለ አባራሪው ባቅራቢያው በንቃት የሚጠብቅ ነውና አፈፍ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ክርስቲያኖችም በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምክንያተ ድኂንነት በተሰጣቸው መንገድ ተጠቅመው የድኅነታችን ቀንድ በኾነ በጌታ ኢየሱስ ቅዱስ ወንጌል አምነው በቃልኪዳኗ ካልተማመኑ የሚገድላቸው ጠላት ኹሌም ባቅራቢያ ነቅቶ የሚጠብቅ ነውና እወጥመዱ ሊያገባቸው ይችላል፡፡ እመቤታችን ሆይ! ቃልኪዳንሽን ክዶ የልጅሽ ጠላት ከመኾን ጠብቂን! አሜን!

እመቤታችን ለኢትዮጵያውያን የእርቃችንም ምልክት ኾናለች፡፡ ከእጆቻችን ፭ ጣቶች መሃል አነስ ብላ መልከ መልካም የኾነችውን ጣታችንን የማርያም ጣት ብለናታል፡፡ አዎና! በአዳም በደል ምክንያት በሰውና በእግዚአብሔር፣ በሰውና በመላእክት፣ በሰውና በሰው፣ በአርያምና በምድር መካከል ኾኖ የነበረ ጥል የተደመሰሰባት ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀን ወደ ቀደመ ጸጋችን የተመለስባት የእርቅ ሰነድ ናትና አሁንም በኢትዮጵያውያን ዘንድ የተጣላ ቢኖር ከአምስቱ ጣቶቹ ፬ቱን ዝቅ አድርጎ ያሃቺን መልከ መልካሚቱን የማርያም ጣቱን ከፍ አድርጎ ያሳየ ኹሉ ምሕረት ይደረግለታል፤ ጥልም በዚህች ጣት ይደመሰሳል፡፡

በኦሪት ዘልደት ምዕራፍ ፮ ላይ በሠፈረው ታሪክ እግዚአብሔር አምላክ በንፍር ውኃ ምድርን ከቀጣ በኋላ እንዲህ ያለው መርገም እጅግ አስፈሪና በኖኅና ቤተ ሰዎቹ ኅሊና ጠባሳ የሚፈጥር እንደኾነ አየ፡፡ እናም ድጋሚ ምድርን በንፍር ውኃ እንዳይቀጣት ለኖኅ ቃል ኪዳን ገባለት፡፡ ኖኅም ቃልኪዳኑ እሙን እንዲኾንለት ዝናም ሊዘንም ባለ ጊዜ ኹሉ በሠማይ ቀስተ ደመናን እንዲያኖር አለ፡፡ ይህንም የቀለማት ኅብር እያየ ኖኅ የእግዚአብሔርን ቃልኪዳን አስታውሶ ይፅናና ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያኑም ብሉያትን ከሐዲሳት ማስማማት ከቅዱሳን አርድዕት የተማሩት ነውና ይህን የቀስተ ደመና የቀለማት ኅብር የማርያም መቀነት ብለው ጠሩት፡፡ አዎና! በቀደመው በደል ምክንያት ባክነን የነበርነውን ከአመድ አንሥቶ ድጋሚ የፈጠረንን፣ ሊገድሉን ሲያስፈራሩን የነበሩትን አስፈሪዎቻችንን ከእግሮቹ መዳፍ ሥር ጥሎ የረገጠልንን መሲሁን ወልዳ መድኃኒት እንካችሁ ማለቷ ሳያንስ ለዘለዓለም ከኃጢአት እየታጠብን እንጠራበት ዘንድ አማላጅነቷ ገንዘብ ተደርጎ የተሰጠን፣ ድጋሚ ላንሞት እስከዘለዓለም እንደዳንን የእርቅ ምልክት ኾና የተሰጠችን ናትና ከኖኅ ቃልኪዳን ጋር ኢትዮጵያውያን አመሳሰሏት፡፡ ቀጠል አደረጉምና በኅብረ ቀለሙ ካሉት ቀለማት መሃል እጅግ ጎልተው ለዐይን የሚታዩትን ሦስቱን ማለትም አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ ቀለማትን መረጡና ቀስተ ደመናውን ለኖኅ ቃልኪዳን ለእመቤታችን አሥራት አገር ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምልክት አደረጉት፡፡ ዓለምም ዐውቆም ሳያውቅ አርኣያውን ተከተለ፡፡

እንግዲህ እንደ ኢትዮጵያውያን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን የነገረ ድኅነት ሱታፌ እንዲህ በኹለንተናው የሚገልጥ አገር የት አለ፡፡ የነቢያት ትንቢታቸው፣ የሐዋርያት የትምህርታቸው ምንጭ፣ የአበው ምስክርነታቸው፣ የሰማዕታት የተጋድሏቸው ሽልማት አክሊል፣ መላእክት አፈጣጠርሽን እያዩ ከኅሊና በላይ የምታስደንቂያቸው፣ የገነት መዓዛና ኅብር፣ የድኅነታችን ምክንያት፣ የክብር አክሊላችን፣ የነፃነታችን ዓርማ ባንድራችን፣ የምንታፈርብሽ ሰንደቅ ዓላማችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ ያመነችሽን የተመካችብሽን ኢትዮጵያን እንዳታሳፍሪያት!!! አሜን!!! ስብሐት ለእግዚአብሔር ልዑል!!!