የማርያም መንገድ ስጡኝ



አሁንስ ተጨነቅሁ ምሮጥበት አጣሁ፤
ማምለጫ የለኝም መንገዶቼን ቃኘሁ፤
ጉልበቴ ዛለብኝ በጭንቅ አለከለክሁ፡፡
አባራሪዬ እርሱ እጁን ሲዘረጋ፣
ጥርሱን እያፋጨ ሊበላኝ ሲተጋ፣
ማምለጫ የኾነኝ አይደል የእርሱ ሥጋ፤
በመንገዴ አላፍርም ጸልዬስ እርሱጋ፤

አሁንም… 
መንገዴ ተዘግቷል አሁኑን ክፈቱ፤
አርዮስ እንደካደው ፍጡር ነው አትበሉ፤
እስቲ እናንተም ተዉኝ ወንድሞቼ ደግሞ!
አማላጅ አትበሉት ስላያችሁት ደክሞ፤
መንገዴ ጽኑዕ ነው .. እንዲሁ ለጊዜው ቢመርጥም አርምሞ፣
ክህደት የጋረደው ዓይናችሁም ታምሞ፣
ባታዩት ነውንጂ ከኃይሉ በስተቀኝ በጸባዖት ቆሞ፤
መንገዴ ነግሮኛል ሕይወት እንደኾኝ … እውነት እንደኾነኝ … መንገድ እንደኾነኝ፤
አማላጅ በኾነስ መሲሕ ባልተሰጠኝ፤
እኔም አላየሁም  የኔታ አልነገሩኝ፤

ያኔ ልጆች ኾነን ጃል! ስታባርሩኝ፣
የማርያም መንገድ ስል እንዳከበራችሁኝ፣

ተዉ አታሳፍሩኝ! … 

ዛሬም ዝምብላችሁ የማርያምን መንገድ ጌታዬን ተዉልኝ፡፡

ዮሐ. ፲፬፥፮ 
 ………………………………………………..…………………………………………..…………………………