በሥመ ሥላሴ ማለት፤ ፈጥሮ በሚገዛ በአብ፣ በደሙ ቤዛ በኾነ በወልድ፣ ዘመናትን ጸጋ አድርጎ በሚሰጥ በመንፈስ
ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፤ እንደምን ሰነበታችሁ፡፡ የጾም ሰበቡና ምክንያቱ፤ ሥርዓቱንም ለማወቅ ጉጉ የኾናችሁ፤
እነሆ ትምህርተ ጾም፡፡
ብዙዎቻችን ጾም ያስፈለገበት ምክንያት ግር የሚለን በተለይ ደግሞ ሞክረነው የፈተነን ጊዜ እግዚአብሔር በእኔ መራብ ምክንያት ምን ያገኝ ይሆን፤ ምግብን ፈጥሮ ሲያበቃ ስለምን አትብሉ አለን፤ ያልን እንኖራለን፡፡ ሌሎቻችን ደግሞ ..ከአፍ የገባ አያረክስም፤ ከወደአፍ የሚወጣ እንጂ.. በምትለዋ የሰሙኗ ዳተኝነት የጾምን መሠረት አናግተን ራሳችንን ከትሩፋት ያገድንም አለን፡፡ ለመኾኑ ግን ጾም ለምን እንጾማለን፡፡
አንድ ክርስቲያን ጾምን የሚጾምበት ምክንያት ዋነኛው … ጾመ እግዚእነ፤ ከመ የሀበነ አርአያ … እንዲል ጌታችን ስለጾመና አርአያውን ስለሰጠን ማቴ. 2 ነው፡፡ መቼም ጌታችን ኢየሱስ ጾምን የጾመ ባለው ጽድቅ ላይ ተጨማሪ ሊያገኝ ሽቶ፣ አሊያም የሃይማኖት ፍሬ ማፍራት የሚጠበቅበት ኾኖም አይደለም፡፡ እርሱ ሎቱ ስብሐት እምይእዜ ወእስከ ለዓለምና በጊዜ ሂደት የሚጸድቅ፣ በትሩፋት የሚያድግ ሳይኾን ጽድቅም ኹሉ አምላክነትም የባሕርይ ገንዘቡ የኾነ፣ ተግቶ ጥሮ ያላገኘው፣ ከማንምም ያልተሰጠው ነው፡፡ ታዲያ ጌታችን የጾመ እርሱ ሲጾም ዐይተን እኛ ልንጾም ነው፡፡ የ3 ዓመት ከ3 ወር የድኅነት ዘመቻን ሲዘምት ጅማሬውን ጾም አደረገ፡፡ ይህም በጾም ከአምላካችሁ ኃይል ካልተቀበላችሁ ወደአገልግሎት አትፋጠኑ ሲል ነው፡፡ አንድም በገዳመ ቆሮንጦስ በጾም ኾኖ የመጣበትን ፈታኝ ዲያብሎስ ሦስት ጊዜ ስለመብል፣ ትዕቢትና ስስት አሳፍሮ መልሶታል፡፡ ይህም ዲያብሎስ የሚያመጣብንን የተለያዩ ዓይነት ኃጢአት በጾም በተሃርሞ መመለስ እንድንችል ሲነግረን፡፡ አንድም … ሰው በእህል ብቻ አይደለም፤ በእግዚአብሔር ቃል የሚኖር ነው እንጂ… እንዳለ ምዕመናን በጾም ወቅት ከእህል ተቆጥበው በሌሊት ማኅሌት፣ በቀን ቅዳሴ፣ በነግኅ ኪዳን፣ በሰርክ ወንጌል ይተጋሉ፡፡ ማቴ. 2
ከዚያም ደግሞ ጾምን የምንጾም አበው ስለጾሙና እኛም .. ተሰአሎ ለአቡከ፤ ወይነግረከ፤ አባትህን ጠይቀው ይነግርህማል … ዘዳ.37፣7 ስለተባልን ነው፡፡ አበው ክርስቶስን ይመስላሉ፡፡ … እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ … 1ቆሮ 11፣1 እንዳለ ብርሃነ ዓለም ጳውሎስ፡፡ ታዲያ አበው ክርስቶስን ሲመስሉ እርሱ ራሱን እንዳዋረደ እየተዋረዱ፤ የአብን አኗኗር እንደተረከ የእግዚአብሔርን ነገር እየመሰከሩ፤ ተአምራትን እንዳደረገ ተአምራትን እያደረጉ፤ መከራ እንደተቀበለ መከራ እየተቀበሉ ሲሆን፣ በገዳመ ቆሮንቶስ እንደጾመ በበአት ተወስነው እየጾሙ፤ … የሚወደኝ እኔ የማደርገውን ከማደርገውም ደግሞ በላይ እርሱ ያደርጋል… እንዳለ ጌታችን እርሱ ዐርባ ቀን ዐርባ ሌት ሲጾም እነርሱ ደግሞ ሕይወታቸውን ኹሉ በድንግልና ኾነው እየጾሙም ደግሞ ነው፡፡ ወርእዩ ፍሬ ሕይወቶሙ ወምሰሎሙ በሃይማኖትክሙ እንደተባልን የእነሱን ፍሬ ለማፍራት ስንል የእነሱን አይነት ሕይወት እንኖራለንና ጾም ደግሞ ለአበው የእለትም፣ የሰሙንም፣ የመንፈቅም ያልኾነች የዓመት ኹሉ የዘመናትም ሕይወታቸው ናት፡፡
እግዚአብሔር አምላክ አእማሪያን/ዐዋቂ ፍጥረታት በሦስት ክፍል ፈጥሯቸዋል፡፡ አንዱ ክፍል መላእክት ሲኾኑ በባሕርያቸው አይበሉም፣ አይጠጡም፣ አይደክሙም፣ አይዝሉም፣ ሩካቤ ሥጋን አይፈጽሙም፣ አይተኙም፡፡ ታዲያ መላእክት ሃይማኖት አላቸው፤ ያመሰግናሉ፤ ይጸልያሉ፤ በጎ ምግባርን ይፈጽማሉ፡፡ ሌላው ክፍል እንስሳት ናቸው፡፡ እንስሳት ደግሞ በባሕርያቸው ይመገባሉ፣ ይጠጣሉ፣ ይደክማሉ፣ ይዝላሉ፣ ሩካቤ ሥጋን ይፈጽማሉ፣ ይተኛሉ፡፡ አይጸልዩም፤ አይቀድሱም፤ ምግባርና ትሩፋትም አይጠበቅባቸውም፡፡ ሦስተኛው ክፍል የሰው ልጅ ነው፡፡ የሰው ልጅ ባሕርይ ታዲያ እነዚህ ሁለት ባሕርያት መሃል ያለ ነው፡፡ እንደእንስሳት ተመጋቢ፣ ጠጪ፣ ደካማ፣ ዛይ፣ በሩካቤ ሥጋ የሚረካ፣ ደክሞ የሚተኛ ሲኾን እንደመላእክት ደግሞ ምግባርና ትሩፋትን የሚያደርግ፣ የሚጸልይና የሚያመሰግን፣ የሚያምንም ፍጡር ነው፡፡ ታዲያ ከእነዚህ ከሦስቱ ባሕርያት ለዘለዓለም ሕይወት የተገቡትና ተስፋ መንግሥተ ሰማያት የተሰጣቸው ሰውና መላእክት ብቻ ናቸው እንጂ እንስሳትስ በዚሁ ዓለም ጠፊና ኃላፊ ናቸው፡፡ በጾም ምክንያት ታዲያ የሰው ልጅ በዚሁ ዓለም ጠፍቶ የሚቀረውን እንስሳዊ ባሕርይውን እየደቆሰ የሚዘልቀውን መልአካዊ ባሕርይውን ይልቁኑ ያሰለጥናል ማለት ነው፡፡ በጾም ወቅት ከእንስሳት ጋር ከሚያመሳስሉን ባሕርያት እየተቆጥበን ከመላእክት ጋር በሚያመሳስሉን ባሕርያት ደግሞ እየጀግንን ሰማያውያን የመኾን ተስፋችንን የምናጎለብትበት አጋጣሚም ጭምር ነው፡፡
አንድም ጾምን የምንጾም ኃጢአት ሁሉ በሥጋ በኩል ትመጣለችና ለሥጋችን በመብልና በመጠጥ በሩካቤ ሥጋና በሌሎችም የሥጋ ተግባራት ለሚገኝ ተድላና ደስታ ከተውን ለዲያብሎስ ውጊያዎች ቶሎ የሚረታ ደካማ እናደርገዋለንና ነው፡፡ በዚህም ጌታችን በጾሙ ወቅት ዲያብሎስን ብላ! እምቢ! ስገድ! እምቢ! ውደቅ! እምቢ! እንዳለ ሥጋችን በጾም ሲታረም ነፍሳችን ዲያብሎስን መቃወም ትችላለች፡፡ በብዙ ሥጋዊ ፍስሐ በሥጋው በምድር የሞላለት በነፍስ በሰማያት ይጎድልበታልና፡፡ ለዚህ ነው ጌታችንም … ዛሬ የሚራቡ የሚጠሙ ብፁአን ናቸው ይጠግባሉና … ማቴ.5፥6 ብሎ ያስተማረን፡፡ … የእግዚአብሔር መንግሥት መብልና መጠጥን አትሰብክም … ሮሜ.14፥16፣ 1ቆሮ.8፥8-13 ደግሞ እንዳለ ጳውሎስ ሐዋርያ፡፡
ጾም የሥጋ መቅጫ ነው፤ ፍትወትም መሻትም ሁሉ በሥጋ የምትመጣና የምትጥለን ናትና ትጋህን ለሥጋችን ለማመከር ስንል እንጾማለን፡፡ … ነፍሴን /ሰውነቴን/ በጾም ቀጣኋት … መዝ.68፥10 እንዳለ ልበ አምላክ ዳዊት፡፡ ሰው በሥጋው በኩል የምትዋጋውን የኃጢአት ጦር ድል ለመንሣት፣ ፍትወትንም ከእርሱ ለማራቅ በሚያደርገው ተጋድሎ በቅድሚያ የምትመጣው መታገያ መንገድ በጾም ሥጋን ማድከም ናት፡፡ እንቅልፍን ቀንሶ በሌሊት ለጸሎት መትጋትም እንዲሁ ጾምን የምታግዝ መሣሪያ ናት፡፡ በዘመኑ ኹሉ እነዚህን የሚጠብቅ ሰው ንጽሕናን ገንዘቡ ማድረጉ አይቀርም፡፡ ጥጋብ የክፉ ሥራ መጀመሪያ እንደኾነች ኹሉ የእንቅልፍ ብዛትም ሥጋዊ ፍላጎትን ያበረታል፡፡ ስለዚህም ከእንቅልፍ ቀንሶ ጸሎት ማድረግና ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ በምግባር በትሩፋት ለማደግ ጥሩ መሠረት ይኾናሉ፡፡
በሌላ አነጋገር በጾም ወቅት የምናስወግዳቸው የሥጋ ተግባራት ኹሉ በእለት ተእለት ኑሯችን ውስጥ የምንፈተንባቸውና ወድቀንም ከጌታችን የተለየን ባይተዋሮች የምንኾንባቸው ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል በመብላት በመጠጣት ምክንያት ለሥጋችን ጥጋብን እናስገኛለን፡፡ ጥጋብ ደግሞ ለኃጢአት ቀርቦ መቆም ማለት ነው፡፡ … ያዕቆብ በላ፤ ጠገበ፤ ወፈረ፤ ገዘፈ፤ ደነደነ፤ ፈጣሪው እግዚአብሔርን ተወ፤ ሕይወቱ ከእግዚአብሔር ተለየ፤ … ዘዳ 32፥15-17 … ከዚህ ዛፍ ብትበሉ የሞትን ሞት ትሞታላችሁ … ዘፍ 2፣37 እንደተባለ፡፡ ሩካቤ ሥጋን በመፈጸም ምክንያት ሥጋ ልዩ አይነት ፍስሐን ያገኛል፡፡ ታዲያ ሩካቤ ሥጋም በዝሙት በመውደቅ የምንፈተንበትም ነው፡፡ በጾም ሥጋን ማረም ማለት ታዲያ ፍስሐን የሚያገኝባቸውን ኹሉ መቀነስ/መተው ማለት ነው፡፡ ሌሎችም ማየት፣ መስማት፣ መናገር፣ መሄድ ኹሉ መጨረሻቸው ኃጢአት በሚኾንበት አንጻር ሲደረጉ ከእግዚአብሔር የምንለይባቸው ይኾናሉ፡፡ በጾም ታዲያ እኒህን የሰው ባሕርያት በመቆጣጠር በኃጢአት ላይ የበላይነት እናገኛለን፡፡
አንድም በጾም ምክንያት ሰውነቱን ያደከመ ሰው ከሰው ጋር ጠብ ለመጣባትና ለመታገል ይቅርና መሳደብ እስካይችል ድረስ ሰውነቱና ኅሊናው በትኅትና ይኾንበታልና፡፡ አንድም በጾም ወቅት ተርቦ ያየ ሰው ጥሪታቸው አልቃ ደኽይተው የተራቡ ወገኖች ያሉበትን ኹኔታ ስለሚረዳ ለምጽዋት ይበረታታል፤ ይራራል፡፡ አንድም በጾም ምክንያት ምግቡን የተወ ሰው ያን ምግብ ለድኾች ለመመጽወት እድል ያገኛል፤ ወይም ለምጽዋት የሚኾን አጣሁ አይልም፡፡
በአገራችን በጾም ወቅት ዓሣ ይበላል፤ አይበላም፤ ክርክር ነበረ፡፡ በጾም ወቅት ዓሣ አይበላም፡፡ ይህም በሦስት ምክንያቶች ነው፡፡ አንድም በፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ … አድልዑ ለጾም.. በጾም ላይ ክርክር በሚነሣ ጊዜ ለጾም አድልታችሁ ወስኑለት ተብለናልና፡፡ ለጾም መልካም የሚሆን ዓሣ ባይበላ ነውና፡፡ አንድም በጾም ወቅት ምእመናን ለቁመተ ሥጋ ያህል ብቻ እንጂ እስኪረኩ ድረስ አይበሉምና፡፡ ዓሣ ደግሞ ለሰው ልጅ ሰውነት ኃይልን በመስጠት ብዙዎችን መባልእት የሚበልጥ መልካም ምግብ ነው፡፡ በጾም ወቅት ዓሣን ብንበላ ሥጋን ከመሳሰሉ ከሌሎች ጥሉላት በመታቀባችን ያራቅነውን ድሎት ስለሚተካልን ታቀብን ተውን ማለት አይቻልም፡፡ አበው ስለጾም ሥርዓት ጥብቅነት ሲናገሩ ከምትጠጣበት ብርጭቆ እንኳ ጨርሰህ አትጠጣ ይላሉ፡፡ ሌሎቻችን ደግሞ በጾም ወቅት የአትክልትና ፍራፍሬ ወጪያችን እጅግ የሚጨምርበት አጋጣሚ አለ፡፡ ጾም ማለት ጥሉላት መባልእትን በአትክልትና ፍራፍሬ መተካት አይደለም፡፡ ሥጋን ከተድላ ማቀብ እንጂ፡፡ ስለዚህ ለቁመተ ሥጋ ያህል ብቻ እንመገባለን ማለት ነው፡፡
ምእመናን በጾም ወቅት የፍስክ በተጨለፈበት ጭልፋ እንኳ ምግባችንን አንጨልፍም፡፡ የፍስክ ምግብ ምግባችን ላይ እንዳይፈናጠር እንኳ እንጠነቀቃለን፡፡ የፍስክ በቀረበበት ገበታ በሳሙናና በሙቅ ውሃ ካልታጠበ በቀር የእኛ ምግብ እንዳይቀርብ እናደርጋለን፡፡ ታዲያ ይህ ኹሉ ከፍስኩ ምግብ የተነሣ ሰውነታችን ተድላ እንዳያገኝ ነውን፤ የምንል እንኖራለን፡፡ በርግጥ ይህ ስለኾነ ሰውነታችን ኃይል አገኘ፤ ተደሰተ ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ጊዜ ጉለበተኛ ነው፡፡ በብዙ ትውልድ መፈራረቅ ምክንያት መልካቸው እየተቀየሩብን ያጣናቸው ብዙ ትውፊት አሉን፡፡ ዛሬ ለፍስክ በተጨለፈበት ምግባችንን ብንጨልፍ፣ ነገ በቅቤ መቆንጠሪያ ወጣችንን እናማስላለን፤ ከነገ ወዲያ ደግሞ ጥቂት ቅቤ ምናላት፤ ለጣዕሙ ነውንጂ ይህች ኃይል አትሰጠኝ ማለትና መቆንጠር እንጀምራለን፡፡ በጥቂት ትውልድም የጥሉላት ሥርዓት ትጠፋና ለልጅ ልጆቻችን እንኳ እንግዳ ትምህርት ትኾንባቸዋለች ማለት ነው፡፡ ይህች ቤተክርስቲያን ሐዋርያት የሰጧትን ዓይነት መልክ ይዛ ምልኤሎችን የተሻገረችው አበው ሥርዓቷን አስፍተው ስላጠሩላት ነው፡፡ አምልኮቱ ያለምክንያት አልጠነከረም፡፡ ከጊዜ ጉልበት ጋር የእኛ ወረተኝነት ተጨምሮበት የአርድእትን ሳይኾን የወረት ሃይማኖትን ለልጆቻችን እንዳናወርስ ነው፡፡
የሥርዓት ባለቤቷ፣ የአምልኮታችን ማዕከል፣ የኃይላትና የሥልጣናት ኹሉ ጌታ አምላካችን እግዚአብሔር የአባቶቻችንን ሃይማኖት ጠብቀን እንደእነርሱው ኾነን በእግራቸው የምንተካ እድለኞች እንዲያደርገን ቅዱስ ፈቃዱ ትኹንልን፡፡ የእመቤታችን ቃልኪዳን፣ የአበው ጸሎት፣ የመላእክት ረድዔት፣ የመስቀሉ ፍቅር ከኹላችን ጋር ይኹን፤ አሜን!!!