እምነት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ አሜን!!!
እንደምን ሰነበታችሁ!

እስቲ ዛሬ ስለ እምነት እንነጋገር፡፡

የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ፣ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለጠጎች ይሆኑ ዘንድ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የተሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድሆች አልመረጠምን ያዕ. 2፣5 ሲል ሐዋርያው የእምነት ባለጠግነት የስጦታዎች ሁሉ ታላቅ የተስፋ መንግሥተ ሰማያት መገኛ እንደሆነች ገልጦልናል፡፡ እንዲህ ያለው የእምነት ባለጠግነት ያላቸው ሰዎች ብዙ ሃብታት ያሏቸው ናቸው፡፡ ከሁሉ በላይ ሕይወታቸው የውስጥ ጸጥታና ሰላም የሰፈነበትና ተስፋቸውም እስከፀፍ ፀፈ ሰማያት የሚደርስ
በመሆኑ እንደ ታዳጊ ትንሽ ትልቁ ሚያስፈራቸውና የሚገርማቸው አይሆኑም፡፡


ዛሬ ዛሬ በማኅበረሰባችን ብርጭቆ ሲሰበር ማንኪያ ሲወድቅ ሌላም ሌላም ቀላል ነገር ሲከሰት ደንግጠው በመጮኽ የወልደ እግዚአብሔርን ስም በተገፈፈ ቆሌ በተሰበረ ቅስም ጠርተው ደንግጦ ማስደንገጡ እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህን ክስተት የተመለከቱ ጊዜ ታዲያ በሐዘኔታ ወደኋላ ዘወር ብለው አበው ቅዱሳን ጻድቃን ተራራ በሚወጡ፣ በረሃ በሚያቋርጡ ጊዜ በዱርም ከፍት ለፊታቸው የሚገጥማቸውን ነፍስና ሥጋን የሚለይ የተራበ አውሬ … በጌታዬ! በመሲሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይዠኻለሁ፤ መንገዴን ተውልኝ! … ብለው በልበ ምሉዕነት ሲገስፁ ስና የእኛን ጊዜ እንነቅፋለን፡፡”ነገር ግን ጌታችን በኋለኛው ዘመን እምነት ታቆለቁላለች ሲል ስለመፃእያት ያወራበትን አንቀጽ እናስታውስና ጸልየን እንተዋለን፡፡


አንድ ወጥቶ አደር ነበረ ይላሉ አበው የአብነት ቤተ ትምህርት ሊቃውንት፤ ከዕለታት ባንዱ ጠብ መንጃውን አንግቶ ረጅም መንገድ ከተጓዘ ኋላ ከፊቱ የሚያስፈራ ባሕር ይገጥመዋል፡፡ ወደ እግዚአብሔር ሲያመለክት ከዳርቻው አንዲት ደረቅ እንጨት ብቅ ትልለታለች፡፡ ይኼኔ ወጥቶ አደሩ አምላኩን አመስግኖ እንጨቷላይ መጭ ይልና እየቀዘፈ እመሃል ይደርሳል፡፡ ድንገት እግዚአብሔር ከፊት ለፊቱ ከጠለል ከፍ ከፍ ብሎ በአረጋዊ አምሳል ይገለጥና … ልጄ ሆይ! ታምነኛለህን፤… ሲለው … እንዴ ጌታዬ! ባምንህማ ወዳንተ አመለከትኩ፤ ጸሎቴንም ሰማህና ይህችን እንጨት ልከህልኝ እነሆኝ እቀዝፋለሁ፤ … አለ፡፡ እግዚአብሔርም መልሶ … ደግ እንዲህስ የምታምነኝ ቢሆን ና! እንጨቷን ተዋትና ተራምደህ ቅረበኝ… ቢለው ወጥቶ አደሩ … አይ ጌታዬ! አንተንም አምንሃለሁ፤ እንጨቷንም አልለቃትም ብሎ መለሰ አሉ፡፡


ይህ ታሪክ የሁላችንም ታሪክ ነው፡፡ ለብዙዎቻችን እምነት መፈተንና ለሕይወታችንም ለርኩሳን መናፍስት መፈንጫ መሆን ተጠያቂው በእግዚአብሔር ላይ እምነት ከማሳደር ባሻገር የምንመካባቸው ሌሎች ዓለማውያን መጠባበቂያዎች ስላበጀን ነው፡፡ ሰንዝረን ብንስት፣ወርውረን ባናደርስ፣ መክተን ቢያቅተን … ኃይል የእግዚአብሔር… እንላለን፡፡ ጸልየን ሳይሳካ፣ታግሰን ስንሰለች፣ተፈትነን ስንዝል ሐልዎተ እግዚአብሔር ያጠራጠረን ብዙዎች ነን፡፡
መቼም እምነት በኪሎ የማይመዘን፣በሊትር የማይለካ፣በሜትር የማይመተር ቢሆንም ቅሉ የእምነታችንን ልኬት ማወቅ የምንችልባቸው ግን መንገዶች አሉ፡፡ የሚከተሉትን እንመልከት፤


አንድ አማኒ እምነቱን ከሚለካባቸው መለኪያዎች አንዱ ስለፍቅር ብሎ በሚፈፅማቸው ተግባራት ነው፡፡ ያለምንም ምክንያት ያለገንዘብ፣ያለዝና፣ ያለክብር፣ አሊያም ደግሞ ማድረግ ስለቀለለው ሳይሆን ስለፍቅር ብሎ ወንድሞችንና እኅቶችን ስለመውደድ ሳቢያ በርኅራኄ በሚያደርጋቸው በጎነት ማለት ነው፡፡ እኒህን ግብሮች እምብዛም አስቧቸው የማያውቅ ሰው ግን እምነት ይጎድለዋል፡፡ ሐዋርያው በስብከቱ .. ፍቅር .. ሁሉን ይታገሳል፣ሁሉን ያምናል፣ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣በሁሉ ይጸናል.. እንዳለ 1ቆሮ. 13፣4


ሌላ መለኪያ፡ ከመልካም ምግባር ብቻ በመነጨ ከሚሠራ ሥራ፡፡ አንድ ወንድም ሌላውን ቢመጸውት ስለቀለለው አሊያ እዩኝ ብሎ ቢሆን እግዚአብሔርን ማመኑን/መፍራቱን አይመሰክርለትም፡፡ ነገር ግን ምጽዋት ልቡ ውስጥ ገብቶ፣ለጋስነት ባሕርይ ሁኖለት ቢሆን ግን ሐዋርያው … እምነቴን በሥራየ አሳያለሁ… ያዕ. 2፣26 እንዳለ ሥራው እግዚአብሔርን መተማመኑን ይነግርለታል፡፡


ሌላ መለኪያ፡ አማኒው ለኃጢአት ያለው ጥላቻ ነው፡፡ሐዋርያው … በእርሱ የሚኖር ኃጢአትን አያደርግም፤… 1ዮሐ. 3፣6 እንዳለ፡፡ አማኒ በሆነ ኃጢአት ደጋግሞ የሚፈተን ከሆነ ያቺን የሚሠራትን ነገር ወዷታል ማለት ነው፡፡ ኃጢአትን የሚወዳት ደግሞ እምነት የለውም/ይጎድለዋል፡፡ ምክንያቱም እምነት እግዚአብሔን ስለሚያስፈረ ዓለምን ያስንቃል፡፡ ለአማኒ እግዚአብሔርና ዓለም ሁል ጊዜ ቢወዳደሩ ሁል ጊዜ እግዚአብሔር ያመዝንበታል፡፡


ሌላ መለኪያ፡ መከራን በመቻልና በመታገስ ነው፡፡ እምነት ያለውና የሌለው ሰው በእኩል መከራ ቢነኩ የሌለው ቶሎ ሲሸነፍ ያለው ግን የሐዋርያውን አደራ አስታውሶ ይመክተዋል፡፡ ይህቺም … ልዩ ልዩ መከራ ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት.. ያዕ. 1፣3 ያላት ናት፡፡ ዳግመኛም በጭንቃቸው ሁሉ እርሱ ተጨነቀ የፊቱም መልአክ አዳናቸው በፍቅሩና በርኅራኄውም ተቤዣቸው ኢሳ. 63፣9 ያለውን ስለሚያስብ እግዚአብሔር ረድኤትን እስኪያወርድ ይታገሳል፡፡
ሌላው መለኪያ፡ ሕግጋተ እግዚአብሔርን በማክበር መጠን ነው፡፡ እነዚህም ምጽዋት፣አሥራት፣በኩራት፣ሰንበትን ማክበር፣ጸሎትን ማፍቀር ናቸው፡፡ በነዚህ ከተዘናጋ እምነቱ ገና ነው ማለት ነው፡፡


እንግዲህ እኒህን መለኪያዎች አይተን… አይ! እምነቴ ደግ ነው፤ ልበረታ ግን ይገባኛል ያልን ቃለ ሕይወት ያሰማን፡፡ … ወየሁ እምነቴ ነቀፋ አለባት.. ያልን ደግሞ ቃለ ሕይወት ያሰማን፤የሚያፀና እግዚአብሔር ነውና መጽናትን ይስጠን፡፡ እስቲ አሁን እምነታችንን ካለበት ደረጃ መላእክት ወደሚደሰቱበት ርኩሳን ወደሚያፍሩበት ከፍ ለማድረግ ምን እናድርግን እንመልከት፡፡


አንድ ተግባር፡ ወደፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ ማቴ. 26፣40 እንዳለ … ጌታ ሆይ አለማመኔን እርዳው… እያሉ መጸለይ ነው፡፡


ሌላ ተግባር፡ አዘውትሮ ወደቤተክርስቲያን መሄድ ነው፡፡ ህ ራስን ወደክበበ እግዚአብሔ እንድናስገባና ከእርሱ ጋር መገናኘትን እንድንለምድ ስችለናል፡፡ በቤተክርስቲያን መገኘት ለጸሎት ዕድል ስለሚፈጥር የእግዚአብሔን ቃልኪዳን እንድናይ፤እንደደጅ ጥናትም ታይቶልን ከእግዚአብሔር ዘንድ የእምነትን መጨመር ያስሰጠናል፡፡


ሌላ ተግባር፡ አዘውትሮ ገድልን ያደረጉ የተለያዩ ቅዱሳንን ታሪክ ማንበብ/መስማት ነው፡፡ የቅዱሳን ሕይወት የክርስቶስን ስሚመስል የእምነትና በመከራ የመፅናትን ታሪክ የሚያነብ ሰው ለመፅናት ብርታትን ያገኛል/ስነ ልቡናው ይነቃቃል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም … የእግዚአብሔርን ቃል የነገሯችሁን ወነኞቻችሁን አስቡ፤የሕይወታቸውንም ፍሬ ተመልክታችሁ በእምነታችሁ ምሰሏቸው፤ ዕብ. 13፣7 የሚል ነውና፡፡ አንድም እነርሱ ኢየሱስን አይተው እንደፀኑ ከሰው ወገን እንደ ኢየሱስ ለመኖር ምስክር ናቸው፡፡ ስለዚህም ሐዋርያው … እንግዲህ እኒህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከብደንን ኃጢአት አስወግደን በፊታችን ለውን ሩጫ በትዕግስት እንሩጥ… ዕብ. 12፣1 አለ፡፡ ሐዋርያውም ይህን ግዳጅ የፈፀመ ነውና … እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ.. 1ቆሮ 12፣1 ብሎ ጠራን፡፡ የቅዱሳንን ሕይወት ለማየት ደግሞ ገድላቸውን ማንበብ ይጠይቃል፡፡


ሌላው ተግባር፡ ትኅትናን ገንዘብ ማድረግ ነው፡፡ ትኁት ያልሆነ ሰው ክርስቲያኖችን ማኅበረ ምዕመናንን ለእኔ የማይመጥኑ ታናናሾች ይላል፡፡ ንዋያትንም፣ ቀዳሾችንም፣ መቅደስንም አያከብርም፡፡ ትኅትናን ለራሱ ያለመደ ግን … በፊትህስ እኔ ማን ነኝ፤ ዕውቀቴ ሁሉ ሞኝነት ነው፤ ጌታ ሆይ ካንተ ዘንድ ያለመመራመር እወስዳለሁ፤ የጠቢባንና የፈላስፎችን ሳይሆን የሕፃናትን እምነት ስጠኝ… ሉቃ.10፣21 ብ ይለምናል፡፡ ራሱን ትኁት ያደረገ የሕይወቱን ጎዶሎ በራሱ ጥበብና ብልጠት ሳይሆን በረድኤተ እግዚአብሔር መሙላት ስለሚሻ እግዚአብሔርን ያምናል፡፡


ሌላ ተግባር፡ የአካባቢን ሁኔታ ሳይሆን ነገረ እግዚአብሔርን መመልከት፡፡ አካባቢውን የሚያይ ሰው እንደ ጴጥሮስ ባሕር ላይ እየተራመደ መሆኑን ሲያስብ እንዳይሰጥም መፍራት ይጀምራል፡፡ ነገረ እግዚአብሔርን የሚያይ ሰው ደግሞ .. እኔ ጠጠር እወረውራለሁ፤እግዚአብሔር ጎልያድን ይጥላል፤ ይላል፡፡ አምስት ቂጣና ሁለት ዓሣ ለአምስት ሺህ ሰዎች ተመጽውቶ ለቁጥር ሥርዓት በማይገዛው በእግዚአብሔር ግብር አሥራ ሁለት መሶብ ይተርፋልን ያስባል፡፡


ሌላ ተግባር፡ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን መጠበቅ ነው፡፤ የማያምን ሰው እግዚአብሔር ቃልኪዳኑን አይጠብቅም፤ይክዳል ብሎ ከማመን የተለየ አያምንም፡፡ በመሠረቱ ግን ቃልኪዳኑን የማይጠብቅ ሰው ሌላውም አካ ቃልኪዳኑን ይጠብቃል ብሎ አያምንም፡፡ ነገር ግን ሐዋርያው እንዳስተማረን … የጠራን እግዚአብሔር የታመነ ነው … 1ቆሮ 1፣9፡፡


እንግዲህ እኒህን ተግባራት ተለማምደን ጥቂት.. እጅግ ጥቂት እንኳ እምነት ብናገን እንቆቅልሻችን በእርሷ ይፈታል፡፡ ምክንያቱም የተራራን መሠረቶች ለማናወጥ እንኳ የተጠየቅን እምነት የሰናፍጭ ቅንጣት ያክል ናትና፡፡
እስቲ አሁን እምነትን ሊያሳጡንና ሊያራቁቱን የሚችሉ ነገሮችን እንወቅና ጸልየን እንቋጭ፤


የመጀመሪያው እምነትን የሚሸረሽር ዝናንና ክብርን መውደድ ነው፡፡ ከሰበክን በኋላ .. ምሁር!.. ከዘመርን በኋላ .. ድምፀ መረዋ!.. መባል ከሻትን ጥበበኛ ብልህ መባልን ከጠበቅን ቃሉ አልሰረፀንም ማለት ነው፡፡ ዝናን መሻት ቀስ እያለ ከእግዚአብሔር እየለየን በሱ ማመንን እያሳጣን ይሄዳል፡፡


ሌላው ደግሞ ትንሽም ትሁን ትልቅ ሥልጣንንና ወንበርን ሀብትንም ያለልክ መፈለግ ነው፡፡ የሚመርጥም የሚሾም እግዚአብሔር ነው፡፡ … እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልሾማችሁኝም .. እንዳለ፡፡እንዲህ ያለችቱን ስጦታ ይጠብቋታል እንጂ አይተጉላትም፡፡


ሌላው ደግሞ እምነትን ከምድራዊ ዕውቀቶች ጋር መደባለቅ ነው፡፡ የአንዳንዶች እምነት እንደፈላስፋ የሚያደርገው ከዓለማውያን ጥበበኞች የቀረበ እምነት ነው፡፡ይህ እግዚአብሔርን ሊታይበት በማይገባ መነፅር እንዲታይ የሚያደርግና ቀስ እያለ ወደአለማመን/ወደመካድ የሚገፋ ነው፡፡ እስካሁን ከተገለጠው አዲስ ዕውቀት ግን የለም ማለት ያሳርፋል፡፡
ሌላው ክፉ ባልንጀርነት ነው፡፡ ሐዋርያው … አትሳቱ፣ክፉ ባልንጀትነት መልካሙን አመል ያጠፋል.. 1ቆሮ. 15፣33 እንዳለ በማይመች አካሄድ መጠመድ ቀስ እያለ እምነትን ስለሚሽር የጓደኞችን ዝርዝር ዛሬውኑ ማጠየቅ ይገባል፡፡


በመጨረሻ ፍርሃትና የሰይጣን ማታለል ናቸው፡፡ በሆነው ባልሆነው መፍራትና መሸበር ወደአለማመን የሚገፋ ኃይል አለው፡፡… እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የመፍራት መንፈስ አልሰጠንም 2ጢሞ.1፣7 እንደተባለ፡፡ ሰይጣንም ድምፅ አውጥቶ አያናግረን እንጂ ዕለት ዕለት በተለያየ መልኩ ጥያቄና መልስ ውስጥ መሆናችንን አስበን ማታለሉን ልንጠነቅቅበት የገባል፡፡


እንግዲህ አምላከ ቅዱሳን ነቢያተ፣አምላከ ቅዱሳን ሐዋርያት፣አምላከ ቅዱሳን አበው ሊቃውንት መምህራን፤አምላከ ቅዱሳን መላእክት፣አምላከ ቅዱሳን አበው ቀደምት እነርሱን እንደረዳ እኛን ልጆቻቸውን ረድቶን ለእነርሱ ያወረሳትን ርስት እኛም እንድንወርስ በአሚነ ሥላሴ መኖርን ያድለን፡፡ የንጽሕተ ንጹሐን ድንግል ማርያም ቃልኪዳን የዕፀ መስቀሉ ኃይል ከእኛ ጋር ይሁን! አሜን!!!