የገነት ጥዑም መዓዛ

ገነትን ጥዑም ናት አሏት ባለግሩም ናርዱ መዓዛ፤
ኅብረ ልምላሜን ያኖረች በጠራ ትርእይት መሃል ብዙ ብርሃናትን ይዛ፡፡

እናት ዓለሜ እማማ! ...
ከታናሺቱ ማኅፀንሽ መድኃኒታችን ሲሠራ የነጻነታችን ዓርማ፣
የገነት መዓዛዋማ …

ገነትኮ የምትሸተው አንቺን አንቺን ነው እናቴ! አንቺው ነሽ የገነት ግርማ፡፡

ቀዳሚት ገነት ትቅርብን ወዳንቺው እንሰደዳ ጽዮን ‘ንክበብሽማ፣

ርስታችንን እንተው ይኽም እንደተሰደዱት መሰደድ ከተባለማ፣

ትምክህታችን አንቺ ነሻ አይደሉም ሠማይ ሰብኡ ኢዮር፣ኤረርና ራማ፣ ...
በገነት ዕፀው መካከል መላእክት እየሰረቁ፣
በዐይኖቻቸው አማትረው ኅብርሽን እየናፈቁ፣
በስስት ሲመለከቱሽ ኪነ ፍጥረትሽን ሲያደንቁ፣
መመኪያቸው ነሽ ለአእላፍ ለእሳታውያን ሰራዊት በሰማ..ይ ላሉ ለራቁ፤
እንደየትኛው ፍጥረት ነሽ፤ .. እንደየትኛው ጌራ ወርቅ፤ .. እንደየትኛው ጳዝዮን፤ .. እንደየትኛውስ ዕንቁ፤
 ...

ለዚህ ነው ‘ንዴ ገብርኤል በፍርሃት ያደገደገው፤
አንገቱን ቀና አድርጎ ዐይኖችሽን ሊያይ የፈራው፤
በመስገድና በመብረክ በሰጊድ ሰላም አምሃ እያስታጠቀ ያስፈታው፤
የመልአኩን አንደበት በድንገት ልጓም ያሰረ ለካ ‘ናቴ ይህ ኅብርሽ ነው … ፤

በቤተ መቅደስ ተቀምጠሸ እንደ ታቦተ ዶር ሲና፣
በጽሩያን እጆችሽ ውስጥ ሐሩ ከወርቁ ‘ሲሣና’፣
ባገለገልኋት ትይ ነበር ውኃ ቀድቼ ከኩሬ .. እንጨት ሰብሬ ከጫካ፤
እናት ዓለሜ እማማ እናቴ ልበልሽማ፤
...
አንቺ እንጨት የምትሰብሪላት የትኛዋ የሔዋን ዘር ኧረ ከወዴት ተገኝታ፤
ከሴቶች ይልቅ ብፅዕት ነሽ.. እንዳንቺ ያለ ከየት መጥቶ .. ገብርኤል ይመስክርልኝ .. ኤልሳቤት ትናገር መጥታ፡፡

ምናለ ባገለገልኩሽ! እንጨትም እየሰበርኩኝ ውኃንም እየቀዳሁኝ፤
ሠማይን የቻልሽው ማኅፀን ጽዮን ሳላይሽ ቀረሁኝ፤
ምናለ በታዘዝኩልሽ
ከዘመን ዘመን ተመርጦ በደረስሽበት ደርሼ ከጓዳሽ ታዛ ዘልቄ፣
ምናል ደርሸ በነበር የወገቤን ትጥቅ ታጥቄ ፣..
ከፍ ስል አምባ ወጥቼ ዝቅ ስል ገደል ወርጄ፣..
ሞቴን በመስቀል ረግጦ .. ከመሬት የዶለልኝን .. አንድዬን የምትጠሪው.. እያልሽው ልጄ ወዳጄ፤
 ...

እሺ መቼ ነው የማልፈው መቼ ነው ልጅሽ ሚወስደኝ፤
የጻድቃን ወግ መዓርጋቸው ለኔ ለትቢያው ሚደርሰኝ፤
አንቺ በክብር አለሽበት እኔም በዚያ ዘንድ የምገኝ፤
ዋልያ ምንጭ እንደሚናፍቅ እናቴ አንቺን ናፈቅሁኝ፡፡

እኅቶችና ወንድሞች …
በታላቅ ውርደት ትሕትና ነፍሴ ለናንተ ክርስቲያኖች ዐቢይ አምሃ ‘ቀረበች፤
ኑ ‘ስቲ! አዳራሽዋን እንወልውል ወንበሯን እንደርድርላት፣
ሰሌዳ ሐረግ እንቀባ በዝማሬ ‘ንመርበት፣
ጉባኤን በጸሎት መክፈት በዐቢይ ጾም በበዓላት፣
በዝክሩ ምንባብ ተቃኝተን አኰቴቱንም እናስታኵት፣
መጻሕፍት አሥራው ቅዱሳት ገድልና ተአምራቱን አዋልዱን ማገላበጥ፣
ኑ ደጀ ሰላም እንዝለቅ መአድ ቤት ወጡን እንወጥውጥ፤
ዝክሯን እንፈጽምላት ስለኪዳኗ ሱታፌ ባርክኒ እማ እንበላት፤
ኑ! ሕፃናትን እንምከር ሃይማኖታቸውን ለማጽናት ምግባራቸውን ለማቅናት፤
በጌታ ኢየሱስ ምሥራች ወንድሞች ይረጋጉበት፤


ይኹንህ ካለችኝማ …

ይኸውም አይደል ቁጭቴ ይኸው ነው እንጨት መስበሬ ውኃም መቅዳቴ ለእማማ፤
ነፍሴ እስክታርግ ተነጥቃ የልቤን የእለት ናፍቆቷን እስካሽ በላይ በራማ፤
... የገነት ጥዑም መዓዛ እናቴ ከፈቀድሽማ፣ ...
እዚሁ ነው ውኃ መቅዳቴ እንጨት መስበሬ ላንቺማ፡፡