በሰሙነ #ሕማማት ጸሊዓ ንዋይ “ገንዘብን (ዓለምን) መጥላት” እና ፍቅረ አምላክን “እግዚአብሔርን መሻትን” እንማርበታለን፡፡
__________________________
ዛሬ በ30 ዲናር ጌታ እንዲሸጥ ምክረ ሞቱ የተወሰነበት የ300 ዲናር ሽቱ በንስሐ መንፈስ በእግሩ የተርከፈከፈበት ልዩ ቀን ነው፡፡ ለመኾኑ የጌታችን ሥጋዌው በዛሬ ዘመን ቢኾን ኖሮ ስለስንት የኢትዮጵያ ብር ይኾን ነበር እያወራን ያለነው፡፡ የሴትዮዋንም ንስሐ የሰውዬውንም ክህደት ጥልቀቱን ለማስረዳት ይህም ጠቃሚ ነው፡፡ ይህ ጉጉቴ በቀጥታ የሥነ ታሪክ (History) እና የሥነ ምጣኔ ሃብት (Economics) ጠበብትን ትንታኔ እንድጐበኝ አደረገኝ፡፡ እግረ መንገዱንም ከኹሉ በላይ በኃጢአት መውደቅ ቢኖርም ቅሉ በንስሐ ታድሶ ለመነሣት የኹለቱም ታሪክ በየአንጻሩ ከፍተኛ አስተማሪነት
አለው፡፡
.
ከሆሣዕና ኋላ ሰኞው “እለተ መርገመ በለስ” ይባላል፡፡ ጌታችን ፍሬ ያገኝባት ዘንድ የበለስ ዛፍን ቀርቧት ፍሬ ያጣባትና የተረገመችበት እለት፡፡ ፍሬው የምግባርና የንስሐ ፍሬ ነው፡፡ ንስሐን ገንዘብ ካላደረግን ጌታ እንደሚያዝንብን ይህ እማኝ ነው፡፡ በዚሁ ቀን ቤተ መቅደስንም ከነጋዴዎች አንጽቷል፡፡ እነዚህ ደግሞ የእግዚአብሔርን ፍቅር በገንዘብ የለወጡ፤ ለገንዘብ ያደሩ፤ ለገንዘብ ሲሉ ምንም የማያደርጉት የኩነኔ ሥራ የሌለ ከእግዚአብሔርና ከማደሪያው ክብር ይልቅ የሚያልፍ ሃብት የሚበልጥባቸው ናቸው፡፡ እሊህን “ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ትሰመይ” ብሎ በኢሳይያስ ትንቢት ገሥፆ አባርሯቸዋል፡፡
.
ማክሰኞው ደግሞ “እለተ ተስእሎት” ይባላል፡፡ አይሁድ ጌታችንን ቀርበው እኩይ ጥያቄ ቢጠይቁትም (ልክ አባታቸው ዲያብሎስ በገዳመ ቆሮንቶስ እንዳደረገ) አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልባቸውን አሳብ አውቆባቸው በጥበብ ምክራቸውን አፍርሶባቸዋል፡፡ እነርሱ ከሰኞ ዠምረው ሞቱ ላይ መክረው ተማክረው በእንዴት ያለ ኃጢአት ወንጅለው እንዲገድሉት ሲያስቡ ጊዜ በእውነት ንጹሕ ኹኖ አግኝተውት በሞቱ ላይ ሳይስማሙ ቢቀሩ ከእነርሱ ወገን ሞቱን አብዝተው የሚፈልጉቱ ሂደው በአንደበቱ ኃጢአት ብናገኝ ብለው ይህን ጥያቄ ጠየቁት፡፡
.
የዛሬው ቀን ረቡዕ
.
ረቡዕ ደግሞ “እለተ ምክር”፣ “እለተ መዓዛ” እና “እለተ አንብዕ” ይባላል፡፡
.
“እለተ ምክር” -- “እለተ ምክረ አይሁድ” ነው፡፡ ይህ ከሰኞው ምክር፣ ከማክሰኞውስ በምን ይለያል ቢሉ የአይሁድ አለቆች፣ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን የተስማሙና እልባት ያገኙለት ዛሬ ነበር፡፡ ዛሬም ይሙት ብለው ወሰኑ፡፡ እዚህ መላ ላይ ለመድረስ ሦስት ቀን ፈጅቶባቸዋል፡፡ ትልቁ ዳገት የነበረባቸው፡
.
1. በመሃላቸው “ይህ ሰው ንጹሕ ሰው ነው፤ ሞት አይገባውም” የሚሉ ርቱዓን ስለነበሩ ነው፡፡ የሚበዙቱ ግን ይህን በክፋታቸው ብዛት አቸንፈው መገደሉ ላይ ተስማሙ፡፡
.
2. ሌላኛው ጭንቅ “እንግደልስ ብንል ምን ምስክር አለን፤ ሰውየው ንጹሕ ነው፤ ተፈትኖም ሐሰት አልተገኘበትም፤ ተስእሎታችንን ኹሉ ገሚሱን በጥበብ ገሚሱን በትሕትና ተላልፏቸዋል” የሚሉቱ ነበሩ፡፡ ይህንንም ታዲያ አይሁድ በክፋታቸው ብዛት የሐሰት እማኞችን እናበጃለን በሚል ከወሰኑ በኋላ ወዲያውኑ ለዚህ ጉዳይ ይጠቅሙናል ያሏቸውን በር ማንኳኳት ሄዱ ማለት ነው፡፡
.
ነገር ግን በዚህች እለት ሞቱ ላይ ቢስማሙም እንዴት እንደሚይዙት ቸግሯቸው ነበር እንጂ መላ አላገኙለትም፡፡ ወቅቱ ከአባቶቻቸው ዠምሮ ለልዦቻችሁ ልዦች ይትረፍላቸው፤ ለዘለዓለምም ሕጌ ይህ ነው ብሎ እግዚአብሔር አምላክ የሠራላቸው ሥርዓት “በዓለ ፋሲካ” ነበርና በበዓል ይህን ደባ እንዴት እንተገብራለን፤ ሕዝቡም እንዳይታወክ ብለው ሰግተው ነበር፡፡ “ከዘመነ ሚጠተ እስራኤል” ወዲህ ደግሞ በየአገሩ ተበትነው የሚገኙ ቊጥራቸው እጅግ የበዛ ቤተ እስራኤል (የእስራኤል ዳያስፖራ) በዓለ ስርየት በዓለ ሰዊትን መጸለትን ፋሲካን በዓለ አምሳ በዓለ ጰንጤ ቆስጤ ማለት ነው፤ እነዚህን ሦስት በዓላት ከያሉበት አገር ወደኢየሩሳሌም (ወደ ቤተ መቅደስ) መጥተው ለአምሳ ቀናት ያክል ሊያከብሩ የሚሰባሰቡበትና የሚሳለሙበት ሕግ ስላላቸው ኹሉም ከየአገሩ መጥተው እከተማ የሚከርሙ ነበሩ፡፡ እሊህም ኹሉ እንዳመኑበት ደግሞ በሆሣዕና እለት “ቡሩክ ዘይመጽዕ በስመ እግዚአብሔር” እያሉ ግልብጥ ብለው ወጥተው በክብር ሲቀበሉት ወደቤተ መቅደስም ሲሸኙት አይተው ፈርተው ነበርና ስለዚህ እንዴት እንደሚይዙና እንደሚገድሉት ተጨነቁ፡፡
.
“እለተ መዓዛ” -- የዛሬው ረቡዕ ዘማዊቷ ሴት (ማርያም እንተእፍረት) ባለሽቱዋ ማርያም ማለት ነች ወደር ከሌለው የጋለሞትነት ግብሯ በጸጸት ወደጌታ የተመለሰችበትና መዓዛውም ዋጋውም እጅግ የተወደደ (300 ዲናር ያህል የሚያወጣ) በአልባስጥሮስ ብልቃጥ የተያዘ ሽቱ በእግሩ ላይ አርከፈከፈችበት፡፡ ለምጻሙ ሰው ስምዖን በቤቱ ድግስ አድርጎ ጌታም ከደቀመዛሙርቱ ጋር ታድሞለት ሳለ ያለማንም ከልካይ ገብታ ይህን አደረገች፡፡ በእውነት የንስሐዋ ጥንካሬ ታላቅ ነው፡፡
.
“እለተ አንብዕ” -- ዛሬ ታዲያ “እለተ አንብእም” ይባላል፡፡ ይህችው ሴት (ማርያም እተእፍረት) ከዚህ ከከበረ ሽቱ ጋር ጌታ አብልጦ ደግሞ የወደደላትን (ዛሬም ከእኛ ዘንድ ፈልጎ ያጣውን) የንስሐ እንባ አብራ አፈሰሰች፡፡ በቀደመ ሕይወቷ እጅግ ተጸጽታ ዳግምም ያን ግብሯን እንዳትመለስበት ቈርጣ ታሪኳን ተለየችውና ከጌታ ጋር ሐዲስ ታሪክ ዠመረች ማለት ነው፡፡
.
በዚህች ሴት ድርጊት ከ12ቱ አንዱ የኾነው የአስቆሮቱ ሰው ይሁዳ ተከፋና ይህ ሽቱ ቢሽሸጥ ኑሮ ለድኾች መብል ልብስም ይኾናቸው ነበር ብሎ የስንፍና ቃል ተናገረ፡፡ ርሱ በወቅቱ ለ12ቱ ዐቃቤ ንዋይ “ገንዘብ ያዥ” ሹም ነበረባቸውና ከሚገኘው ገንዘብ ከ10ሩ አንዱን ለራሱ ወደኪሱ የሚያገባ ሌባ ነበርና ከ300ው ዲናር ማለት 30ው የርሱ ይኾን እንደነበር ተቈጭቶ አለ እንጂ ለድኾች ተገድዶላቸው አልነበረም፡፡ ጌታ ግን ስለዚህ ገሠፀው፡፡ ታዲያ ጌታውን ለ30 ዲናር አሳልፎ የሸጠም ለዝህቹ ላመለጠችው ገንዘብ በነበረው ቊጭት ነበር፡፡ ይህ ቢኾን ማታ በራሱ አንቂነት አይሁድ ዘንድ ሂዶ የጌታችን ሞቱ ላይ ተስማምተው እንጂ እንዴት እንደሚይዙት ቸግሯቸው ያሉትን እኔ አለሁ ብሎ መላ አላቸው፡፡ ዋጋውንም የተመነና በ30 ዲናር ይህ ይኹን ያለ ርሱ ነበር፡፡ ገንዘብ የለመዱ ኹሉ ያን የሚከለክላቸው እውነተኛ ሰው ቢመጣ ዛሬም ቢኾን ነፍስያውን ለመግደል አይመለሱም፡፡
.
“ዲናር” የሚባለው በወቅቱ የሮም ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የሚገበያይበት ገንዘብ ነው፡፡ በርግጥ የይሁዳ ምድር የሮም ንጉሠ ነገሥት ኹነኛ ግዛት ባይኾንም ቅሉ በንጉሠ ነገሥቱ ሞግዚትነት የሚተዳደር (ያው ግዛት በሉት ዞሮ ዞሮ) ነበር፡፡ ስለዚህ ያን ገንዘብ አይሁድም ሊጠቀሙበት ይገባ ነበር፡፡
.
የታሪክና የምጣኔ ሃብት ሊቅነት ያላቸው ሰዎች (በተለይ የምዕራቡ ዓለም ተመራማሪዎች) እንዳጠኑት ከኾነ በ33 ዓ.ም. የሮም ንጉሠ ነገሥት መንግሥቱ ለአንድ እግረኛ ተዋጊ ወጥቶ አደሩ በዓመት የሚከፍለው የደመወዝ መጠን 225 ዲናር ያህል ነበር፡፡ የወቅቱ የሮም ንጉሠ ነገሥትን ምጣኔ ሃብት (ኢኮኖሚ) እንደሚያሳየው ደግሞ 1 ዲናር በዛሬ ዘመን በኢትዮጵያ ገንዘብ እንኳ እስከ 2 ሺህ 370 ብር መድረስ ይችላል፡፡ በዚህ አኋኋን ጌታ የተሸጠበት ገንዘብ በዛሬ ዘመን 71 ሺህ 100 ብር ይደርሳል፡፡ የተነሳሒቷ ሴት 300 ዲናር በአንጻሩ 711 ሺህ አንድ ብር እንደኾነ ስሌቱ ያስረዳል፡፡ ይህ ገንዘብ እንደሊቃውንቱ አተረጓጐም ከኾነ ለወጥቶ አደሮቹ በዓመት ከሚከፈለው ገንዘብ በ177 ሺህ 750 ብር የሚበልጥ እጅግ ብዙኅ ነው ማለት ነው፤ ሴትዮዋ ባርከፈከፈችው ጊዜ ታላቅ አግራሞት ፈጥሮ ነበር፡፡ የሁለቱን በዳዮች ኹኔታ ብናነጻጽር በእውነተኛ ንስሐ በቅንነት ወደአምላኩ የቀረበ ሰው ለዚህ ያክል ትልቅ ገንዘብ የማይሳሳና ዓለምን ከነጣዕሙ የተወ ሲኾን የገንዘብ ፍቅር ልቡናውን የነደፈው እውር ግን ለዚህች ገንዘብ እስኪሳሳ ድረስ ከሰው ሕይወት ያስበልጣታል፡፡ ለሁለት ጌቶች መገዛት ስለማይኾንለት አንዱን ይተወዋል ማለት ነው፡፡
.
ይሁዳ ታዲያ ይህን እኩይ ግብር ካደረገ በኋላ ታላቅ ጸጸት ተጸጽቷል፡፡ ንጹሑን ሰው የገደልኩ እኔ ነኝ እያለ በመሪር ልቅሶ አንብቷል፤ ከሰውነት ተራ በታች እስኪወርድና ባይተዋር እስኪኾን ድረስ በኀዘን ልቡን ጐድቷል፡፡ ነገር ግን ይህ ኹሉ ኀዘንና ጸጸት እንደ ንስሐ አልተቈጠረለትም ነበር፡፡ ምክንያቱም ከጸጸት አልፎ ምሕረተ እግዚአብሔርን ፈልጎ አልተነሣም፣ ቀቢጸ ተስፋ ብቻ መጣበት፡፡ ንስሐ ምሉዕ የምትኾነውና ፈጽመን ወደአምላካችን ይቅርታ መምጣት የምንችለው ስንጸጸት ብቻ ሳይኾን የአምላካችንን ምሕረቱን ከልብ አብዝተን ስንሻና ይቅር በለኝ እያልን ስንናዘዝም ነው፡፡ በንስሐቸው እጅግ የምናደንቃቸው ቅዱሳን መጸጸት ብቻም ማዘንም ብቻም አልነበር ወደአምላካቸው በፍጹም መሻት ምሕረቱን እየፈለጉ ተከትለውታል፤ ርሱም ይቅር ብሏቸዋል፡፡
.
ይሁዳ ግን ጸጸቱን ለጥቆ የመጣ አንዳች ነገር ቢኖር ከንቱ ብልጣ ብልጥነት ነበር፤ ራስን ማጥፋትና የእግዚአብሔርን ምሕረት በእውነተኛ የንስሐ መንገድ ሳይኾን በብልጣ ብልጥነት ለማግኘት መጣር፡፡ ርሱም በቀኝ የተሰቀለውን ወንበዴ ፈያታዊ ዘየማንን ቀድሞ ገነት ለመግባት ዘዴ ዘየደ፡፡ ጌታችን በመስቀል ላይ ነፍሱን ከመለየቱ ቀድሞ ቶሎ ርሱ ቢሞትና በሲዖል ቢገኝ ከሲዖል ነፍሳት ጋር አንድ ላይ ግዕዛንን እንደሚያገኝ አስቦ ራሱን አጠፋ፡፡ ወንበዴው በአንጻሩ እኛ በደለኞች ነን ብሎ ፈጽሞ ከተጸጸተ ኋላ “ተዘከረኒ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ” አቤቱ በመንግሥትህ አስበኝ ብሎ ደግሞ ምሕረቱን ሲሻ ንስሐው ተፈጽማለታለች፡፡ ይህ ግን አዳምንም ቢኾን አብርሃም አባታችንንም ቢኾን ቀድሟቸው በሡራፊ ትንግርት አልፎ ገነት ገብቷል፡፡
.
ከእኛ ብዙዎች እንደበለሲቱ ለራሳችን ብቻ ቃርመን ወዝና ምቾት እናገኛለን፤ ለጌታችን የሚኾን የንስሐ ፍሬ ግን የለንም፡፡ እንደቤተ መቅደሶቹ ለዋጮች ደግሞ ፍቅረ እግዚአብሔርን በፍቅረ ንዋይ የተካን፤ ለሥጋ ብቻ እንጂ ለነፍስ ግድ የሌለን ብዙዎች ነን፡፡ ብዙዎቻችን ከይሁዳ ያልተናነሰ ፍቅረ ንዋይ አለን፤ ብሶም ከእርሱ የተሻለ ንስሐ ይጐድለናል፡፡ እንጸጸታለን እንጂ ኃጢአታችንን ተናዝዘን ይቅር በለኝ ማለት ላይ እንሰንፋለን፡፡ አንዳንዶቻችን እንደውም ከይሁዳም ያነሰ ንስሐ ይታይብናል፡፡ ይህ ኃጢአት ነውን፤ አይደለም እያልን ራሳችንን እንሸነግላለን፡፡ የሠራነው ሥራ ኃጢአት ካልኾነ ጽድቅ ነው ማለት ነው፡፡ ጽድቅ ከኾነ ለርሱ ስለንስሐ አናወራም፡፡ የሠራነው ሥራ ግን ኃጢአት ከኾነ ሞት ያመጣብናልና ሄዶ መናዘዝ ነው፡፡ የሠራነው ሥራ ኃጢአት ይኹን አይኹን ግራ ከገባን ደግሞ ይህንም መናዘዝ ነው፡፡ ልንናዘዘው ከፈራን ኃጢአት መኾኑን አምነን ተቀብለናል ማለት ስለኾነ፡፡ የሚያሳፍር ኃጢአት ካልኾነ መናዘዝ ምን ያመራምራል፡፡ ነገር ግን ብዙዎቻችን ባጓጒል ፍልስፍና ራሳችንን ሸብሽበን ይዘናል፡፡ እናም ሞተ ነፍስ ሳይደርስብን ዛሬ ኃጢአታችንን ብንናዘዘው “ይቅር ይለን ዘንድ የታመነ ነው” – 1ኛ ዮሐ.1፣8፡፡
.
ሚያዝያ 19 ቀን 2008 ዓ.ም.
ዓ.ም.