ኢይረክቦ ሞት ከመ ዝ ዳግመ እምዝ


ዳግመ እምዝ ዳግመ እምዝ
ኢይረክቦ ሞት ከመ ዝ ዳግመ እምዝ
ከእንግዲህ በኋላ እርሱን ዳግመኛ ሞት እንዲህ አያገኘውም
እንኳን አደረሳችሁ፤

ይህ ሰሙን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤና ሕይወትነት፣ በሞትም ላይ ያሳየው ባለ ሥልጣንነት የሚነገርበት ነው፡፡ የሰው ልጆች በሞት መውጊያ ተወግተው በመቃብር መያዣ ተይዘው ሲኖሩ በመጨረሻ ግን ጌታችን ሞቶ ሲነሣ ባሳየው ኃይል የሞትን ሥልጣን ሽሮ የትንሣኤያችን በኵር ኾኗል፡፡

ከላይ ያሰፈርነው ዚቅ መሠረቱን ያገኘው በዮሐንስ ወንጌል ምዕ.11 ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዐራት ቀኑን ሬሳ ከመቃብር ወደ ሕይወት በጠራበት አብነት ላይ ከእኅቱ ማርታ ጋር በተነጋገረበት ወቅት ከተናገረው ቃለ ሕይወት ቃለ ትንሣኤ ነው፡፡ በዚህ በወርኃ ትንሣኤ ይህን ማውራታችን ታዲያ በሚከተለው ምክንያት ነው፡፡

የክርስቶስ ትንሣኤ ከኹሉ በላይ የእኛንም ትንሣኤ ያረጋገጠልን በመኾኑ ደስ እንሰኝበታለን፡፡ ክርስቲያኖች “አይቴ እንከ ቀኖትከ ሞት ወአይቴ መዊዖትከ ሲኦል ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?” እያልን በሞት ላይ እንድንዘባበትበት ያደረገን ነገር ቢኖር ይኸውም የሊቀ ካህናት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሞት መንገድ ውስጥ ተጉዞ በትንሣኤው ሕያው ኾኖ መነሣቱ ነው፤ 1ቆሮ.15፣55፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ …

በብሉይ ኪዳን መሥዋዕት ተደርገው የሚቀርቡት እንስሳት ኹሉ ጊዜያዊ ፈውስን፣ ከለምጽ መንጻትን፣ ከደዌ ማገገምን የመሳሰሉ ጥቃቅንና ትንንሽ ድኅነቶችን ይሰጡ ነበር እንጂ ዋናውን የሰው ልጆች ቀበኛ ሙሰና መቃብርን አጥፍተው ታሪካችንን ከሲኦል ወደ ገነት የሚለውጡ አልነበሩም፡፡ የብሉይ ኪዳን መሥዋዕተ እንስሳ ይህን ታላቅ ግዳጅ መፈጸም የማይችሉ የነበረበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ ይኸው ነው፡፡ እነርሱ ከተሠዉ በኋላ ታሪካቸው እዚያው ጋር ያበቃል እንጂ ሕያዋን ኾነው ትንሣኤን ይዘው የሚነሡ አልነበሩም፡፡ ሞት እነርሱንም ይይዛቸዋል እንጂ እነርሱ በሞት ላይ ሥልጣን አልነበራቸውም፡፡ በዚህ ምክንያት በዘመን ኹሉ አሁንም አሁንም እየደጋገሙ ይሠዋሉ፤ መሥዋዕትነታቸው ይደጋገማል፤ ሌላ በግ አልፎ ሌላ ይሞታል፤ ዳግም ዳግም ይሞታሉ እንጂ አንዱ ብቻውን በቂ አልነበረም፤ ዕብ.9፣9-14፡፡

የጌታችን መሥዋዕትነት ግን ፍጹም የሚያደርገውና ጌታችንን ፍጹም መሥዋዕት ንጹሕ ቊርባን (ኢዩ.1፣11) ነው፡፡ በዚያውም ላይ ደግሞ አንድ ጊዜ ተሠውቶ ድጋሚ መሥዋዕት መኾን (መሰቀልና መሞት) የማይገባው ምክንያትም በዚሁ ነው፡፡ አንድ ጊዜ ሞቶ ከሦስት ቀን በኋላ በገዛ ሥልጣንና ኃይሉ ሕያው ኾኖ ተነሥቷልና፡፡ አንድ ጊዜ ከሞተ በኋላ ሕያው ኾኖ በፍጹም ድል አድራጊነት ስለተነሣ ድጋሚ መሞት አያስፈልገውም፤ አሁንም አሁንም አይሰቀልም፡፡ ስለዚህም “ዳግመ ኢይረክቦ ሞት ዳግም አይሞትም/ሞት አያገኘውም” እንላለን፡፡ በዚህም ርሱ የትንሣኤ ጌታ ይባላል፤ እኛንም የምናምንበትን ኹሉ የትንሣኤ ልጆች አድርጎናል፤ የምናምንበትም እኛ ድጋሚ ሞት አያገኘንም፡፡

“አነ ውእቱ ትንሣኤ ወሕይወት፤ ዘየአምን ብየ እመኒ ሞተ የሐዩ ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይኾናል፤ ሕያው የኾነም የሚያምንብኝም ኹሉ ለዘላለም አይሞትም፤” እንዳለ ነው፤ ዮሐ.11፣25-26፡፡ ስለዚህ በሞትና በትንሣኤ ታሪክ ውስጥ ጌታችን ያለው ስፍራ ማዕከላዊ ነው፤ ማለት ጌታችን ራሱ “ትንሣኤና ሕይወት” ነው፡፡ የጌታችንን ሕያውነት ለመግለጽ መሞከር ራሱ ጭንቅ ነው፤ ምክንያቱም ርሱ የሕይወት ኹሉ መገኛና ምንጭ ስለኾነ ነው፡፡ “ቦቱ ኩሉ ኮነ በርሱ ኹሉ ኾነ” እንደተባለ ፍጥረት ኹሉ ህልውናውን የሚያገኝ ከርሱ ሕይወትነት የተነሣ ነው፡፡ ስለዚህ ርሱ ሞቶ ቢነሣ ለሚያምኑበት ኹሉ ሕያዋን መባልን ሊሰጣቸው አቅሙ ስላለው ከሰማይ ወርዶ መዋቲ ሥጋን ለበሰና ሞቶ ተነሣ፤ በዓል ማድረጋችን ኹሉ ስለዚህ ነው፤ ዮሐ.1፣3፡፡

በሁለተኛ ደረጃ …

ከክርስቶስ በፊት ከሞቱ በኋላ ሕያዋን ኾነው የተነሡ ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ያክል የኤልሳዕ መበለቲቱ ልጅ (1ነገ.4፣18-37)፣ የኢያኢሮስ ልጅ (ማቴ.9፣18)፣ አልዓዛር (ዮሐ.11፣1-ፍ.ምዕ) ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ኹሉ ሞተው በመነሣታቸው ምክንያት ለእኛም ትንሣኤን ሊያረጋግጡልን አልቻሉም፤ ማለት የእነርሱ ትንሣኤ ለሰው ዘር በሙሉ በሞት ላይ ሥልጣንን የሚያሰጥ ትንሣኤ አልኾነም፡፡ በአጭር ቋንቋ የእነርሱ ትንሣኤ ለሌላ ሰው የሚተርፍ ምንም ገንዘብ የለውም፤ ለርሳቸው ብቻ የሚጠቅም ነበር፡፡ ይህም በብዙ ምክንያት ነው፤ አንደኛ በራሳቸው ኃይልና ሥልጣን ሙስና መቃብርን አቸንፈው አልተነሡም፡፡ ይልቁኑም ሌላ አስነሺ ይፈልጉ ነበር፡፡ 

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ራሱ እንዳለ እስመ አነ እሜጡ ነፍስየ ቤዛ አባግዕየ ከመ ካዕበ አንሥኣ ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል፤ እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝእንዳለ፤ ዮሐ.10፣17 በገዛ ሥልጣኑ ያለማንም ጋባዥ፣ ያለማንም ጠሪ ሕያው ኾኖ ተነሥቷል፡፡

ከዚያም ሌላ ዋነኛው ምክንያት ግን እነዚያ ከሞት የተነሡ ሰዎች ኹሉ እንደተነሡ ሕያዋን ኾነው አልኖሩም፤ ድጋሚ ሌላ ሞት መጥቶ ኹሉንም ዳግም ወስዷቸዋል፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤው ግን “ኢይመውት እምዝ ዳግመ” እንዲል ለሰው ዘር ኹሉ በሞት ላይ አቸናፊነትን የሚያቀዳጅ፣ ሕያው አድርጎ ሌላውንም የሚያስነሣ፣ ሙስና መቃብርን እስከ ወዲያኛው የማጥፋት ለሌላም ሰው የሚተርፍ ገንዘብ ያለው ፍጹም ትንሣኤ የኾነበት ምክንያት ዳግም ሞት የማያገኘውና ለዘላለሙ ሕያው ኾኖ የተነሣ መኾኑ ነው፡፡ በዚህም ዳግም አይሞትም እንላለን፡፡ 

ጌታችን የተነሣው ትንሣኤ እኛ ኋላ ከሞትን በኋላ በትንሣኤ ዘጉባኤ በዳግም ምጽአት የምንነሣውን ትንሣኤ ነው፡፡ የትንሣኤያችን በኲር የምንለውም በዚህ ነው፤ እኛ ገና እንነሣው ዘንድ ተስፋ የምናደርገውን ትንሣኤ ርሱ ተነሥቶታል፡፡ እነ አልዓዛር የተነሡት ትንሣኤ ግን የረድኤት ትንሣኤ እንጂ የትንሣኤ ዘጉባኤ ትንሣኤ አለመኾኑ ከክርስቶስ ይለየዋል፡፡ ጌታችንን ድጋሚ ሞት አይይዘውምና፤ ይህም ምሥጢር እኛ ያመንንበት ኹላችን ሕያዋን የኾንበት ነው፡፡ ከትንሣኤው በረከትን ያድለን፤ ይቈየን፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ሚያዝያ 2009 ዓ.ም.