በዚህ
ጽሑፍ ላይ ብዙ ነገሮችን እነካካለሁ፤ .. ብዙ ቦታ ረግጣለሁ። አንዳንዶቹ ከእኔ ይልቅ በትዳር ሕይወት ውስጥ ያለ፣ ያገባ ሰው
ቢያወራቸው እኔም የምመርጣቸው ነበሩ። ምን ያደርጋል … ይኸው ምክንያት እስከ ዛሬ ከልክሎ እንዳከረመኝ ኹሉ እንዲያሰነብተኝ ደግሞ
አልፈለኩም። ውይ … ዝምታው!
ዳግመኛ
እነያንም ቢኾን ጨምሬ እኔው ለማውራት በቂ ምክንያትና የልብ ምልዐት እንዳለኝ ሲሞግቱኝ በቦታው አመጣላቸዋለሁ … እያልኩ ነገሩን
በልክ እንደማደርገው ግን ቃል እገባለሁ።
በቀረው
ግን ልከኛና ምጥን ነው .. የእናንተ ሥራ ምንድነው፤ .. ብትፈቅዱ ማንበብ ...
አነሳሥ …
ዛሬ
በጠዋቱ ዩቲዩብ የተሰኘውን ድረ ገጽ ስከፍት .. የደስተኛ ያልኾነ ስሜት ተሰማኝ፤ ሳያውቁ ዘው ብለው የገቡበት የጠንቅ ዋይ ቤት
ያክል የሚያቈየኝ አልመስልህ አለኝ። ወደ ላይ ወደ ላይ የሚል ነገር ያዘኝ … ምንም እንኳ በዚያ ድረ ገጽ ላይ ጥሩ ጥሩ ቪዲዮዎችን
ቢኾንም የማየው ውጣ ውጣ የሚለው ስሜቴ ግን አየለ። ኋላ ከራስጌ ቀኙ ጠርዝ ዘወር ስል የዩቲዩብ ዋና ገጽ ማስፈንጠሪያዋ (ምልክቷ)
ጎን ከሰሞኑ የግብረ ሰዶማዊነት ተግባር ማስፋፋት ዘመቻ ፊት መሪ የኾነውን መለዮ ባለኅብረ ቀለማት ዓላማ ተመለከትኩ።
“ዩቲዩብ!
.. አንተም! ..”
ዩቲዩብ
የሚባለው ዓለማቀፋዊ ተቀባይነት ባለው ግዙፍ አውታር ላይ ጉግል የሚባለው ድርጅት ግብረ ሰዶማዊነትን አስመልክቶ ያለውን የበጎነትና
የድጋፍ አቋም የገለጠበት (ሶሊዳሪቲ ይሉታል የቃየል ልጆች) መኾኑ ነው።
በነገራችን
ላይ ይህ የግብረ ሰዶማውያን ምልክት ሌላ ምንም አይደል ቀስተ ደመና (የማርያም መቀነት) ነው።
በእንተ ትእምርቶሙ …
ግብረ
ሰዶማውያኑ በምልክታቸው ለመወከል የፈለጉት ሰማይ ዝናም ባቈረ ጊዜ በደመና ላይ የሚኖርን ቅስት (ሬይን ቦው) ነው። ቀስተ ደመና
ደግሞ ታሪኩ ወደ ቅዱሱ መጽሐፍ ይሄድና ኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 6 እስከ 11 ይወስደናል።
በዚህ
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ እግዚአብሔር እምነትንና መታዘዝን እምቢ ያሉትን ሰብአ ትካትን በማየ አይኅ (ከሰማይ ላንቆች በወጣ የጥፋት
ዝናም) ካጠፋ ኋላ በእምነትና በመታዘዝ አካሄዳቸውን ከርሱ ጋር ላደረጉትና መርከብ ሠርተው እንዲተርፉ ለመራቸው ለኖኅና ቤተ ሰዎቹ
እንደ አዲስ እንዲበዙና ምድርን እንዲመልዋት፣ ዘራቸው ከእንግዲህ ወዲህ ቢበድል እንኳ በእንዲህ ያለ ቅጣት እንደማይቀጣቸው ቃል
ኪዳን ገባለት። በዚህም ዝናም ከሰማይ ሊዘንም ደመና ባቆረ ጊዜ ጠለ በረከት እንጂ እንደቀደመው የጥፋት ውኃ እንዳልኾነ ሊነግረው
ቀስተ ደመናን ያደርጋል።
ታዲያ
የዛሬ ዘመን ግብረ ሰዶማውያንን ከዚህ ታሪክ ጋር ምን አገናኝቷቸው ስንል እግዚአብሔር ያኔ የሰውን ዘር በጥፋት ውኃ ለማጥፋት ለምን
ወሰነ ብለን እናበጃለን። የሰው ልጅ በኃጢአት እጅግ ከመርከሱ የተነሣ ለሁለተኛው ኪዳን (ለኪዳነ ክርስቶስ) ያልተገባ ወራዳ ፍጥረት
ኾኖ ላድንህ እንኳ ቢሉት ለመዳን የማይበቃ የአመፃ (አመፀኛ) ፍጥረት ኾኖ ነበር። ከእነዚህ የአመፃ ተግባራት ዋነኛና ጉልሕ የነበረው
“የሥጋዊ ተራክቦ ግብረ ገብነት” (ሴክሹዋል/ሴክስ ዲሲፕሊን) እጅግ ተራክሶ የሰው ልጅ ካገኘው ጋር ከወንዱም፣ ከሴቱም፣ ከእንስሳውም
ጋር በማኅበርም በደቦ፣ በጓዳም በመንገድ መራከቡ ነበር። ኋላ ላይ ግብሩንም ግብረ ሰዶም (የሰዶም ሰዎች ተግባር) ሲለው ተገኘ።
ስለዚህ
የዛሬ ዘመን ግብረ ሰዶማውያን ይህን ምልክት ለግብራቸው ዓይነተኛ አላማ አድርገው ሲወስዱት የመልእክታቸው ዋነኛ ተደራሽ ሰዎች አይደሉም፤
ዓለምም ሳይኾን … ያሃ ለጻድቁ ሰው ለኖኅ የተናገረ ባለ ቃል ኪዳኑ አምላክ እግዚአብሔር ነው። ነገርየውም በርሱ ላይ መዘባበት
ይባላል፤ “አንታዘዝህም!” ያሉት ሰብአ ትካት ጠፍተው የታዘዙትና ያመኑበት ኖኅ እና ቤተ ሰዎቹ እንደተረፉ ነገ ለፍርድ የሚጣሉ
ሰዎች ደግሞ ዛሬ “አንታዘዝህም” እያሉት ነው።
እንዲህ
ያሉ በቀጥታ እግዚአብሔርን ተደራሽ ያደረጉ ምልክቶች በዓለማችን እንዳሉ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ለአብነት ያክል የአፕል ካምፓኒ የተገመጠ
ዕፅ ምልክት የበለስ ፍሬ፣ ግማጩም የሔዋን ግማጭ እንደኾነ በጥርጣሬ የሚያዩ ጥቂት አይደሉም፡፡ እንዴት እንዴት ብለን እዚህ ደረጃ
ላይ እንደደረስን ጉድ ነው፤ ነገር ግን ይህች የግብረ ሰዶማውያን ምልክት ዛሬ ደግሞ በጠዋቱ ቤታችን የምንለው ዩቲዩብ ላይ እንኳ
ቂብ አለች።
የግብረ ሰዶማዊነት ትልቁ ጠንቁ ምንድን ነው፤ …
ግብረ
ሰዶማዊነት በዋነኛነት በግብረ አዳማዊነት (የወንድና የሴት የተቀደሰ ሥጋዊ ተራክቦ) ላይ ጠላት ኾኖ የተነሣ ምቀኛ ነው። ይህን
ለማስረዳት ብዙ መፈላሰፍ ያለብን አይመስለኝም። ከግብረ አዳማዊነት ልጅ ይገኛል፤ ከግብረ ሰዶማዊነት ልጅ አይገኝም።
ኢማኑኤል
ካንት የተባለ የ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የጀርመን ፈላስፋ በሜታፊሲክስ (በካታጎሪካል ኢምፔራቲቭ መስመር በተፈላሰፈው) ፍልስፍናው
ላይ ግብረ ገብነትን (ሞራላዊነትን) ሲፈታው አስቀድሞ አንድን ተግባር ትክክል ነው ስሕተት የሚያስብሉትን የራሱን ቁንጽል መለኪያዎች
አወጣ። አንደኛው እንዲህ የሚል ነው፡- ከሞራላዊነት (ግብረ ገብነት)
ጋር ተያይዞ “ትክክል” ይኹን “ስሕተት” የሚያጠራጥር ተግባር በገጠመህ ጊዜ በመጀመሪያ ያንን ተግባር “ዩኒቨርሳላይዝ” አድርገው/ማለት
የዓለም ሕዝብ ኹሉ ተቀብሎት ቢተገብረው ውጤቱ ምን ይኾናል ብለህ ጠይቅ፤ ውጤቱ አፍራሽ/ፈራሽ ከኾነ ተግባሩ “ስሕተት” ነው፤ ግብረ
ገብነትም የለውም፤ ውጤቱ ገንቢ የሚኾን ከኾነ ያ ተግባር “ትክክል” ነው፤ ግብረ ገብ ነው፤ ይለናል (በእኔው አገላለጥ ሲቀመጥ
እንጂ ርሱስ ዘለግ ያደርገዋል)።
ይህ
መለኪያ ፈላስፎቹ “ኮንሲኩዌንሻሊስት” ከሚሏቸው ትወራዎች ዘንድ የሚመደብ ነው፡፡ እኒህ ትወራዎች ግብረ ገብነትን በሙሉ ከድርጊቶቹ
ተግባራዊ ውጤቶች በመነጨ የሚመዝኑ ናቸው፡፡ ይህ የካንት አተያይ በተለይ በበኩሌ የበዙ እውነታዎች አሉት ባይ ነኝ። (ይህ እኔን
የካንታዊ ፍልስፍና ተከታይ አያደርገኝም፤ ነገሩንም ከነግሳንግሱ በጀ ብየዋለሁ ማለት አይደለም፤ … ልብ አድርጉ … ኋላ ብያለሁ!)
ግብረ
ሰዶማዊነትን ጠንቀኛ እና ሊጻረሩት የሚገባ እኩይ ተግባር የሚያደርገው ኹሉም ሰው ግብሩን ግብሬ ብሎ ቢይዘው (ሥራውን ሥራዬ ብሎ
ቢይዘው) በሰው ዘር መቀጠል ላይ እንቅፋት አኑሮ ብቻ የማይመለስ፣ ይልቁን ጋሬጣ የሚጋርጥ፤ የማያቸንፉት ብርቱ ግድግዳ የሚገደግድ
ተግባር ስለኾነም ነው።
በሌላ
ቋንቋ ግብረ ሰዶማዊነትን “ዩኒቨርሳላይዝ” ብናደርገው (ኹሉም የዓለም ማኅበረ ሰብእ በጊዜ ሂደት ግብረ ሰዶማዊ ቢኾን ብለን ብናስብ)
ልጅ መውለድ የሚፈልግ ሰው አይኖርም ማለት ነው (ምክንያቱም ይህ ግብር ልጅ የመውለድ ሐሞትን ፍስስ ከሚያደርጉ ዐበይት ሰበቦች
አንዱ ስለኾነ)። ልጅ ካልተወለደ ደግሞ … እንደውም ርሱን ተዉትና ልጅ በሚፈለገው ቊጥር ባግባቡ ካልተወለደ እንኳ .. የሚፈጠረውን
ማኅበረ ሰብአዊ ቀውስ ለማወቅ ኢማኑኤል ካንት አያስፈልገንም .. ጠጋ ብላችሁ እጅግ በሠለጠኑት የስካንደኒቪያና አውሮጳ አገራት
ተመልከቱ። መንግሥታቱ ለሚወልዱ ሰዎች ይህን ያክል ተብለው የማይገለጹ ልዩ ልዩ ገጸ በረከቶችንና ሽልማቶችን ለመስጠት ቃል በመግባት
ጭምር ዜጎቻቸው እንዲዋለዱላቸው በምልጃም በአማላጅም እየተማጸኑ ይገኛሉ። ይህ ማኅበረ ሰብአዊ ቀውስ አይፈለጌና እንደ አገር ለመቀጠል
ምን ያክል አስፈሪ ጭራቅ እንደ ኾነ የየአገራቱን ነባራዊ ኹኔታ ቀረብ ብሎ በመመርመር ማወቅ ያስፈልጋል።
ለዚህ
ከላይ ላቀረብኩት ... (ማለትም ግብረ ሰዶማዊነትና ግብረ አዳማዊነት ልጅ ለመውለድና ለሰው ዘር በምድር ላይ መቀጠል በሚያበረክቱት
አስተዋፅኦ አንጻር ለሚዘረጋ የተቃውሞ መከራከሪያ) ሁለት ዓይነት ግብረ መልሶች በግብረ ሰዶማውያኑ ዘንድ ተሰጥተው ያውቃሉ።
(1) የግብረ ሰዶማውያኑ ግብረ መልስ አንድ፡- “አዲስ! … ዓለም ኹሉ ግብረ ሰዶማዊ አይኾንም፤ ዝም ብለህ
አትቀባጥር።”
የእኔ
የግብረ መልስ ግብረ መልስ ደግሞ! .. ይህን ዋስትና መስጠት የሚችለው ማን ነውሳ፤ … ዓለም ኹሉ ግብረ ሰዶማዊ ይኾናል ብዬ እኔ
መከራከር የማይፈቀድልኝ ከኾነ ቢያንስ ቢያንስ ዓለም ኹሉ ግብረ ሰዶማዊ አይኾንም ብሎ መሞገትስ ለእነሱ ማን ይፈቅድላቸዋል።
ወዲያውስ
አሁን በዓለማችን እየታየ ያለው ዝንባሌ እና የግብረ ሰዶማዊነት ፈጣን (ባለሁለት ዲጂት ግሮውዝ .. ባለሦስት አኃዝ በሉት ከፈለጋችሁ
.. ቊጥሮች ኹሉ ይገልጡታል) መዋቅራዊ እድገቱን ማየት በራሱ ሌላው ቢቀር “ሊኾን ይችላል፤ .. ምን ታውቃለህ፤” በሚል ማስጠርጠር
እንኳን አይችልምን ትላላችሁ። ብዙ ድርጅቶች እጅግ ብዙ ሚሊዮን ቢሊዮን ዶላሮች እያፈሰሱ በብዙኃን መገናኛ ነገርየው በፈሊጥና በዘይቤ
እንዲገባላቸው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ ነገርየው ቀስ እያለ እየተጸደቀ፣ መኰነኑ እንዲቀር የማስለመድ ተግባር፣ … የአገራት ለግብሩ
አወንታዊ እና ድጋፍ የመላበት ግብረ መልስ መስጠት፣ የሕግና ፍትሕ አካላት ተባባሪነት፣ የብዙ እምነት ተቋማትና መንግሥታዊ ያልኾኑ
ድርጅቶች ሳይቀር በጉዳዩ ላይ ፍጹም ጣልቃ ገብቶ ፊት ኾነው እያቀነባበሩ መሥራትን ስትመለከቱ ወደ እኔ ዘወር ማለታችሁ አይቀሬ
ነው፤ .. ያኔ እኔ ፈገግ .. … አላልኳችሁም፤
ሕዝብ
በጣም የወደደውና በዓለም የተሰራጨ አዲስ ተከታታይ የሆሊውድ ፊልም ከመጣ ግብረ ሰዶማውያኑ መልቲ ሚልየነሮች፣ ቢልየነሮች ቀረብ
ይሉና ፊልም አሠሪውን “ጥቂት የግብረ ሰዶማዊነት ትርእይቶች ያዝ አድርገህ አውጣና ይህን ያክል ሚልዮን ዶላር እንውረድብህ” ይሉታል።
የፊልም ሠሪዎች ትልቁ ቀውስ ምን እንደኾነ ታውቃላችሁ፤ … ጨላ! … ትልቁ አጋጅ ነገር ገንዘብ ነው። አእምሯቸው ስንት እያሰበ፤
… ጥበብ ኮምፒተር ላይ እንደጉድ እየተቀመረች .. በገንዘብ ችግር ግን እንዴት ውጪ ትውጣ፤ ጥበበኛው አእምሯቸው በድህነት ናወዘ
… ታዲያ በስንቶቹ ፊልሞች ውስጥ ነው የምትወዱት ልዝብ ገጸ ባሕርይ ድንገት ሳይታወቅ የግብረ ሰዶማዊነት ጠባይዕ ደብቆ አኑሮት
እንደነበር ኹሉ ድንገት ከሌለበት መዘዝ ሲያደርገው ምላሳችሁ ካፎቱ ምዝዝ ያለባችሁ፤ … የእኔ ብዙ ነው።
ሰዎችስ ራሳቸው ቢኾኑ …
ከላይ
ካልኳቸው ይህ እኩይ ልማድ እንዲለመድ በብርቱ ከሚጣደፉ ኃይሎች ይበልጥ ደግሞ የራሱ የግለ ሰዎች ተራክቧዊ ዝንባሌ (ፐርሶናል ሴክሹዋል
ኢንክሊኔሽን) በራሱ ያለማንም ደጋፊ የኔን ፍራቻ እውነት ለማድረግ በቂ ነው የሚል ብዙ የተፈተነና እንደ ጥሩ መሠረት የጠነከረ
አቋምም አለኝ። እንዴት እንደ ኾነ ላመልክታችሁ፤ …
የትውልዳችንን
የተራክቦ (የሴክስ) አቋም ልብ ብላችሁ ተመልከቱት። የአደባባይ ሐቅ ነው፤ ግብረ ሰዶማዊ ባልኾነ የተራክቦ ልማድ ውስጥ የሚፈጸሙ
የተራክቦ “ፋውሎች” ለግብረ ሰዶማዊነት ምንጭ ናቸው። ግብረ ሰዶማዊነት በአንዴ ተነሥተው ዘፍ የሚሉበት ሦስት እግር ወንበር (በርጩማ)
አይደለም። ወደዚያ የሚያመሩት ነገሮች በሙሉ በወንድና ሴት የተለመደ ዓይነት ተራክቦ ውስጥ በሚሠሩ የተለያዩ ከግብረ ገብነት ማነስ
የሚመነጩ ስሕተቶች ነው።
አንድ፡ ከትዳር በፊት ተራክቦን መፈጸም …
ዛሬ
ዛሬ ታዳጊ ወንዶችም ሴቶችም ገና አካላቸው እንደ ጸናላቸው የሚጠይቁት ጥያቄ .. በእኩዮቻቸው ዘንድም የሚመክሩበት ነገር “ለማን
ልስጠው” ነው። ተራክቦን (ሴክስን) መፈጸም ዕድሜ ጠብቀው በትዳር ዐውድ ውስጥ በተቀደሰ መኝታ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያደርጉት ተግባር
… አምላካዊ ፈጠራ … መላእክት ሳይቀሩ የሚያግዙት፣ የሚራዱት … እግዚአብሔራዊ ክንውን መኾኑ ቀርቶ ቊርስ የመብላትን ያክል ቀላል፤
.. ምሳ የመድገምን ያክል የሚደገም .. ሲጃራ የመሳብን ያክል የሚደጋገም ተራ ራስን የማዝናናትና “ሪላክስ” የማድረጊያ መንገድ
እየኾነ ነው። ትንሹም ትልቁም በጊዜውም አለ ጊዜውም ይፈጽመዋል።
ስለዚህ
ተራክቦ በልጅነት ይጀመራል፣ .. ብርቁም፣ ደስታውም፣ መፍነክነኩም ኹሉ በአፍላነት ይለመዳል … በጥሬነት ይሰለቻል። ልጁ አፍላ
እንጭጭ ኾኖ የተራክቦ ልማዱ ብስል ይኾንና ትዳር ውስጥ ሲገባ ማርች ማርች እያለ ይገባል፤ ወይም ነገር ኹሉ እንደ ዋዛ ማርች ማርች
ይለዋል (ትዳሮቻችንን ተመልከቷቸው .. ብዙዎቻችን የታዘብነውን ጉድለት ምንድን ነው ያመጣው፤ .. ብዙ አትፈላሰፉ ... ቀላል
ነው)
ይህ
ተራክቦን ያለ ጊዜው ያለ መጠን የማንኳተት ነገር ውጤቱ ብዙ ነው፤ … ጥቅልል አድርጎ ግን በአንድ አገላለጥ ማስቀመጥ ይቻላል።
ተራክቦን ለተራክቧዊ ግብረ ገብነት በሚስማማ መንገድ ካልፈጸሙት
በትዳር ውስጥ የሚያስገኘው ደስታና ምቾት በእጅጉ የቀነሰ የመነመነ እየኾነ ይሄዳል። በጥቂት ነገር እንደ ዋዛ ረክቶ
በቃኝ የሚል ስብእና በዚህ ልማድ ውስጥ ከጤዛ ዕድሜ በላይ አይሰነብትም።
ከትዳር
በፊት ንጽሕናን፣ ድንግልናን ከማርከስ አንሥቶ ዛሬ ላይ ታዳጊዎችና ወጣቶች የሚፈጽሟቸው የተራክቦ “ፋውሎች” በኋላ ሁለት የተጋቡ
ሰዎች ብቻቸውን በሚፈጥሩት ደስታ ረክተው፣ ያው በቅቷቸው የሚኖሩበት ትዳር ማግኘትን ከባድ የሚያደርጉት ናቸው። የብዙ ሰዎች ትዳር
ከውጪም ጭምር በሚደጎም የደስታና ርካታ ድጎማ የሚንቀሳቀስ እንጂ ሁለት ሰዎች የሚበቁት (በሁለት ሰዎች በጀት ብቻ የሚንቀሳቀስ)
አለ መኾኑ በአያሌው የዚሁ ውጤት ነው። ትዳር ውስጥ ለመግባት የሚሹ ወጣቶችም በተራክቦ ረገድ ብዙ ናላ የሚያዞር “የክራይቴሪያ”
መአት መደርደራቸውም የዚህ “የማየት” ውጤት ነው።
አስምሩልኝማ
… በትዳር መታመን የሚጀምረው ከሠርጋችን እለት ብዙ ዓመታት፣ በርካታ ዘመናትም በፊት ጀምሮ ነው። የ14 እና የ15 ዓመት ኮረዳ
በትዳሯ መታመን ትችላለች፤ ዛሬውኑ። የ15 ዓመት ጉብል በትዳሩ መታመንን እለት እለት ማከናወን ይችላል። (ከዚያ በፊት ያሉት ቢፈልጉትም
ሲያምራቸው ይቀራል ብዬ ነው፤ -- ከሞገታችሁኝም ቢያንስ ኮረዳና ጉብል አይባሉም፤ … በቃ)
ከትዳር
በፊት ከተራክቦ መከልከል የሚባለውን ፈታኝ፣ ... ጽናትን ከማስተዋል ጋር የሚጠይቅ፣ … ልባም ሰው ብቻ የሚወጣው ባለ ብዙ አቀበት
ቁልቁለት መንገድ በመጓዝ ተፈትኖ፣ አመክሮውን ፈጽሞ በርትቶ የተገኘ ጀግና ሰው ትዳር ውስጥ ከገባ በኋላ የሚመጡ ማናቸውም ፈታኝ
ነገሮችን በብቃት የመወጣት አቅምና ሥነ ልቡና በዚያው ሂደት ውስጥ የሚያዳብር በመኾኑ በሰፊ ክብ ውስጥ ሳይኾን ራስን በመግዛትና
በመጠን መኖር በምትባል መድኃኒት በኾነች የሕይወት ዘይቤ የሚኖር ንጹሕ .. ከምኑም የሌለበት ደስተኛ ሰው ይባላል።
ብዙ
ጋለሞታ ጋር ዞረው የቃረሙትን ፍትወታዊ ደስታ በመጠን ከማይገለጥ የሕሊና ወቀሳና የልብ መቆሸሽ ጋር ይዘው ከሚኖሩም ሰዎች ይልቅ
ከውስጥ ሰላም ጋር ያንን የሚያክል ደስታ ይዞ የሚኖር ይሻላል የሚለውን የተቀደሰ ትምህርት ልጆቻችን፣ ታዳጊዎቻችንና ወጣቶቻችን
ኹሉ ሊሰሙት ይገባልና አትሽኮርመሙ፤ በየሚገባቸው ልሳን በሉላቸው፤ … አሂዱላቸው።
ሁለት፡ ከትዳር ውጪ ተራክቦ መፈጸም …
ትዳር
ውስጥ ላሉት ሰዎችም ከዚህ የባሰ ነው። በትዳር ብቻ ውስጥ ይህን ተግባር የሚያደርገው ሕዝብ ቊጥር እየመነመነ ይገኛል። ባልም ሚስትም
በየራሳቸው መንገድ የፍትወታቸውን ዕዳ የሚያወራርዱባቸው በርካታ መንገዶች እንዳሏቸው እመሐሉ የምንኖረው ሐቅ ነው።
ትዳርንና
“ሁለት” ቊጥርን የሚያዋሕዳቸውን ምሥጢር ተመልከቱልኝ። አንድ ሰው በአንድ ሰው ብቻ ረክቶ፣ አንድ ሰው ብቻ በቅቶት መኖር መቻሉ
ለብዙ በዚህ እኩይ ሰይጣናዊ ሕይወት ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች አስቂኝ ወይም አስፈጋጊ ተረት የሚኾንባቸው ያሳለፉት ሕይወት/እየኖሩበት
ያሉት የጨለማ ውስጥ ድጥና ማጥ የኾነ ኑሮ ይህን አዳማዊ ተፈጥሯዊ ስብእና ሸርሽሮ እጥብ ስላደረገባቸው ነው። በሌላ አባባል ስለ
ተራክቦ ጤነኛ አስተሳሰብ መያዝና በዚሁ አስተሳሰብ ሕይወትን መምራት ተፈጥሮ ከሰጠችን የአስተሳሰብ ብሩህነት ጋር መቈየትንና የሰብአዊ
ተፈጥሮን አለ መወየብ የሚጠይቅ ነው (መወየብ ማለት ማርጀት፣ መበላሸት ነው - ብዙውን በቀለም መጥፋት ይገለጣል)።
ከነዚህ
በልማዱ ቅኝ ከተገዙ ሰዎች ጋር መግባባት መቻል በራሱ አንድ የሚጠይቀው ቁልፍ ነገር አለ፤ ነገሬን እንዳያወሳስብብኝ ርሱን አሁን
አልናገርም፤ አኖረዋለሁ። ለዚሁ ብዬ ከተውኳቸው ብዙ ሌሎች ነገሮች ጋር ደብዬ አንድ ቀን እወረውረዋለሁ።
ንጽሕናንና
የድንግልናን ክብር ጠብቀው ለትዳር ለበቁ ሁለት ጥንዶች በትዳራቸው ውስጥ የሚኖር ማናቸውም የተራክቦ ሕይወት ከበቂ በላይ ይኾናል።
አይቻለሁ፤ .. ሰምቻለሁ፤ .. ተምሬአለሁ፤ … በቂዬ ነው። ይህ ወግ የማይደርሳቸው እንኳ ቢያንስ ድጎማን የመፈለግ ዝንባሌው በብዙ
እጥፍ ስለሚቀነስላቸው፤ በዚህም ደግ ያደርጋል። ንጽሕናንና ድንግልናን በመደገፍ፣ በማበርታት የሚደረጉ ማናቸውም ቤተ ክርስቲያንም
ኾነ ሌሎች አካላት የሚያደርጓቸው ተግባሮች ኹሉ ወደዚህ እውነታ ያነጣጠሩ ናቸው።
ሦስት፡ በትዳር ውስጥ አልባሌ ተራክቦ መፈጸም …
በደምብ
ሊታሰብ የሚገባው (ነገር ግን እዚህ ላይ ብዙ የማልናገርበት) ጉዳይ በተቀደሰ ትዳር ውስጥም ያልተቀደሰ የተራክቦ ሕይወት ሊኖር
እንደሚችል ዐውቆ መጠንቀቁ ነው።
ያልተገራ፣
ሥርዓትና ድንበር ያልተከለለለት የተራክቦ ሕይወት በራሱ ልቅ እና አልባሌ ነው። መጠን ሊኖረው ይገባል። ለዚህም ክርስቲያናዊው የአኗኗር
ዘይቤ የራሱን መላዎች ያስቀመጠ በመኾኑ ያን በአግባቡ መከተል በራሱ ደኅንነቱ በተረጋገጠ ጎጥ ለመገኘት በቂ ነው። ያለዚያ ሲመሽም
ሲነጋም እዚያ ግብር ላይ መገኘቱ በራሱ ጠንቆች እንዳሉት ትምህርተ ቤተ ክርስቲያንም ያረጋግጣል።
በአጠቃላይ
እንግዲህ … እነዚህ ሦስት “ፋውሎች” በቀጥታ ማኅበረ ሰብእን የማፍረስ አቅም አላቸው ልል ፈልጌ ነው። (ግብረ ሰዶማዊነት የቅርብ
ውጤታቸው ብቻ ነው) ይህንም ደብዬ በቦታው አመጣዋለሁ።
ውይ! … ብትተወን … !
(ጠባየኛ
ስለኾናችሁ …) ምነው አዲስ! ዛሬ ምን በልተህ ነው .. ይህን ጦስ የኾነ ወሬ የምታወራ፤ … እነዚህን ኹሉ ነገሮች ባናደርጋቸውና
… በመሰለን ብንሄድስ ምን ይመጣል፤ … ሺ ዓመት አይኖር .. ምነው ሸዋ! (… አትሉኝም እንጂ የሚለኝማ ቢኖር)
በመሰለን
ብናደርገውማ እደግመዋለሁ በትዳር ውስጥ ከተራክቦ የሚገኘውን ደስታና
ምቾት በእጅጉ ይቀንሰዋል። የዚህ ደግሞ ትልልልልልልልልልልቁ ጠንቁ ገና የሚመጣ ነው … እስኪ ትንሽ እንቈርቊረው፤
…
ሰዎች
ከተራክቦ (ሴክስ) ማግኘት የሚችሉት ደስታ በከሳና በመነመነ ጊዜ ደስታውን ለመጨመር (ማክሲማይዝ ለማድረግ) አሉ የተባሉት ኹሉ
የሚዘይዷቸው ዘዴዎች … አንዱ ዘዴ ወደ አንዱ ዘዴ .. ርሱም ሲሰለች … ሌላው ዘዴ .. ርሱም ሲሰለች … ወደ ሚቀጥለው ዘዴ እያለ
ቀስ ብሎ የተራክቦ ሕይወታቸው ከእንስሳት ጋር ፍጹም ወደሚመሳሰል አሳፋሪ ቅርጽ ይለወጣል።
በዘመናችን
ልብ እንበልና በእንስሳት ከሚታይ የተራክቦ ጠባይዕ በሰዎች ያላየነው የትኛውን ነው፤ .. አንዲት ሴት ከብዙ ወንድ ጋር መገናኘት
መፈለጓ ነውን፤ … ብዙ ወንድ ከብዙ ሴቶች ጋር መገናኘት መፈለግ ነውን፤ … በየመንገድ ዳር ግንብ ተደግፎ መገናኘቱ ነውን፤
… በአፍም፣ በእጅም፣ በእግርም ኹሉ ነገሩን ማከናወን ነውን፣ …
ከእንስሳት ጋር ሳይቀር በሥጋ መገናኘቱ ነውን፤ … (እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ተሞሽረውና አምረው እየተቀለቡ የሚኖሩ እንስሶች ብዙ
ቤቶች አሉ - ይውጣላችሁ)
ታዲያ
ሌላው ሌላውም ኹሉ ጤነኛ በሚመስል ተራክቦ ውስጥ እንኳ ሲፈጸሙ የምናያቸው የወሲብ ተቀጽላዎች ኹሉ የመጡበት ምክንያት ሰዎች ተራክቦን
ተፈጥሯዊ በኾነ መንገድ በማድረግ ብቻ የሚያገኙት ደስታ ከላይ ጠቅሻቸው በነበሩ “ፋውሎች” ምክንያት ያለልክ ተቀንሶባቸው “ምሌ”
ሲኾንባቸው ጊዜ ቁጭ ብለው በመቷቸው መላዎች ነው። ከእነዚህ መላዎች አንዱ “ግብረ ሰዶማዊነት” ይባላል።
(ልብ
አድርጉ ይህ ደግሞ እንስሳትንም ጭምር በብቃት በልጠናቸው ያደረግነው የራሳችን ፈጠራ መኾኑን)
ግብረ
ሰዶማዊነት ማለት በተራክቦ “ፋውሎች” (ሴክሹዋል ዲቪዬሽንስ) ምክንያት ግብረ አዳማዊነት ብቻውን ያልቻላቸውና በግብረ አዳማዊነት
መንገድ ብቻ የፈለጉትን ርካታ ማግኘት ያልቻሉ ዋልጌ ሰዎች ፍትወታዊ ደስታቸውን እጥፍ ያደርግላቸው እንደሁ የመቱት የስግብግብ ጅል
መላ ነው።
ባክህ
ስድቡን ተውና “ፍቺ” አምጣ … …
ግብረ
ሰዶማዊነት ማለት በሰው ልጆች ልማደ ተራክቦ (የግብረ ሥጋ ግንኙነት) ውስጥ የሚመጣ የጾታ ልቅነት ወይም የወንዴና ሴቴ ቸልተኝነት
ነው።
(ይህች
ፍቺ ኤል.ጂ.ቢ.ቲ. የሚሉትን ኹሉንም የግብረ ሰዶማዊነት ዝንባሌዎች የምታካትት በመኾኗ ትመዘገብልኛለች እላለሁ) (ኤል.ጂ.ቢ.ቲ.
ምንድን ነው፤ …. አቆዩልኝማ)
ምንም
እንኳ የግብረ ሰዶማዊነት ብቸኛው ጠንቁ ልጅ አለ ማስገኘቱ ብቻ ባይኾንም እውነት ለመናገር እንደ ማኅበረ ሰብእ ሊያስፈራን የሚገባው
ጠንቁ ግን ርሱው ነው፤ … ግብረ ሰዶማዊነት ልጅ አይገኝበትም። ልጅ የሚገኘው በግብረ አዳማዊነት ነው። ግብረ ሰዶማዊነት ሲያድግና
ሲስፋፋ የሚስፋፋው በግብረ አዳማዊነት መቆርቆዝ ላይ ተመሥርቶ ብቻ ነው። በሌላ ቋንቋ ግብረ አዳማዊነት እየከሰመ፣ እየመነመነ በሄደበት
መጠን ካልኾነ በቀር ግብረ ሰዶማዊነት ሊሰፋ አይችልም። አንድ ግብረ አዳማዊ ሰው ወደ ግብረ ሰዶማዊነት ሲቀየር አዳማዊውን ግብር
ፍጹም የመጥላትና በርሱ የመዘግነን ዝንባሌ እንደሚታይበት እሙን ነው።
ልጅ
የሚገኝበት፣ ሕፃን የሚወለድበት ግብር እየተተወ ክቡሩ የወንድ ልጅ ዘር ዝም ብሎ የትም ተዝረብርቦ በሚባክንበት ግብር እየተተካ
ይሄዳል። (ልጅ ይገኝበትም አይገኝበትም የወንድ ልጅ ዘር ትክክለኛ ቦታው ወይ የወንድ ልጅ ወገብ ነው፣ አለያም የሴት ልጅ ማሕፀን
ነው - አለቀ፤ ደቀቀ፡፡ ይህን የምለው ከነገርየው ክብር አንጻር ነው፤ የእግዚአብሔር የፈቃዱ ውጤት፣ መለኮታዊ ፈጠራ፣ አምላካዊ
ሥራ ነው - የወንድ ዘር፤ በየቦታው ማዝረክረክም፣ በየላስቲኩ መጠቅለልም፣ በየቆሻሻ ቅርጫቱና በየግንቡ ሥር ማርከስም … ሌላ ሌላውም
ተገቢ አይደለም፡፡ እነዚህ ተግባሮች እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሰጠውን ጸጋ አያሳዩም፡፡)
አዳማዊነት
እና ሰዶማዊነት ሁለቱ ተጠፋፊ ኃይሎች ናቸው እንጂ በጉርብትና አይኖሩም። አሁን ዓለማችን ተግባሩን በተመለከተ እያየችው ካለቸው
ብዙ አዳዲስና አዝማሚ አካሄዶች አንጻር ደግሞ በጊዜ ሂደት ይህ ነገር የትኛው መጠን እንደሚበቃው፣ … በሰው ዘር መቀጠል አለመቀጠል
ላይ የመጣ ጥፋት እስከ መኾን እንደማያደርሰው ማንም ዋስትና ሊሰጥ አይችልም፤ ኹሉም ነገሮች እያሳዩ ያሉት ያንን አቅጣጫ ስለኾነ።
(2) የግብረ ሰዶማውያኑ ግብረ መልስ ሁለት፡- “ግብረ ሰዶማውያንምኮ ይወልዳሉ፤ የማይወልዱትምኮ ቢኾን በጉዲፈቻ
እየወሰዱ እያሳደጉ … እንደውም ለማኅበረ ሰብኡ ግብረ ሰናይ ተግባር (ቻሪተብል አክቲቪቲ ወይም ቻሪቲ ይሏታል ይህቺን ደግሞ) እየፈጸሙ
ይገኛሉ። በዚያ ላይ በአርቴፍሻል መንገድ የሚወልዱም አሉ … ዝም ብለህ ነው አንተ፤ የፍቅር ጠላት ስለኾንክ … ክፋት ይዞህ ነው፤”
የእኔ
የግብረ መልስ ግብረ መልስ ደግሞ …
(“የሌባ
ዐይነ ደረቅ መልሶ ልብ አድርቅ” አሉ ነቄዎች … ደግሞ ማነውሱ “የአይጥ ልጅ ድንቢጥ” ያለው … የግብረ ሰዶማዊ ግብረ ሰናይ መልሶ
ግብረ ሰዶማዊ።)
እነርሱ
ዘር አልባ የወላድ መካኖች ኾነው ማመፃቸው አንሶን ደግሞ .. ተጨማሪ ዜጋ እነርሱ ባያሳድጉት ኖሮ በአዳማዊው ግብር ኖሮ ስንት
ዘር ተክቶ ወግ አይቶ ሊያሳይ የሚችለውን ልጅ ወስደው የወላድ መካን (ግብረ ሰዶማዊ) አድርገው ቢያሳድጉት ይህ እውነት አሁን ማሳደግ
ነውን፤ … አሁን ይህ ግብረ ሰናይ ይባላል ወይስ ግብረ ሰዶ…! (አንዱ ባልንጀራዬ እንዳለው “እዚያው አሳድገው ለሚለምጡት ደግሞ”
… አይ እሱን ተዉት፤ ባለጌ ነውሱ!)
ቢወልዱም ራሱ …
ግብረ
ሰዶማውያኑን (ኤል.ጂ.ቢ.ቲ.) ይሏዋቸዋል “የቃየል ልጆች”። … በሉ እንግዴህ “ኤ ፎር አፕል” ዓይነት ነገር እኛም እዚህ እንጀምርና፤
… ኤል ፎር ሌዝቢያን (ወንድ የተወች ሴት ግብረ ሰዶማዊት)፤ … ጂ ፎር ጌይ (ሴት የተወ ወንድ ግብረ ሰዶማዊ)፤ … ቢ ፎር ባይሴክሹዋል
(ጾታ ሳይመርጥ የሚሄድ ግብረ ሰዶማዊ)፤ .. ቲ ፎር ትራንስቨስታይል/ትራነስጀንደር (ሴት ኾኖ እንደ ወንድ፣ ወንድ ኾኖ እንደ
ሴት የሚኖር ግብረ ሰዶማዊ - በቀደመው በአብዛኛው በአለባበስ የሌላውን ጾታ ፍጹም በመምሰል ኾኖ በወንዶች ይነገራል)።
ከእነዚህ
ሰዎች ውስጥ ዘር ለመተካት ትንሽ ተስፋ ያለቻቸው “ቢ” እና “ቲ” ናቸው፤ … ምክንያቱም በአዳም ግብር የምናውቀውንም የተራክቦ
ተግባር ይፈጽሙታልና፤ .. ላድርገው ካሉ ልጅ መውለድ የእነያን ያክል እምቢኝ አሻፈረኝ አይላቸውም።
ትልቁ
ችግር …
አንደኛ
እነዚህም ቢኾን ልጅ መውለድ ያን ያክል ጉዳያቸውም አይደለም፤ በዚሁ ቢኖሩ ይመርጣሉ። ሁለተኛ ከአጠቃላይ የግብረ ሰዶማውያን ቊጥር
ሁለቱም ተደምረው በመቶኛ ከ50 አይበልጡም። ግብረ ሰዶማዊነት እጅግ እየፈረጠሙ ያሉት ጡንቾቹ በ “ኤል” እና “ጂ” በኩል ያሉት
በመኾናቸው በዚህ መስመር ግብረ ሰዶማውያን የሚያነሱት መከራከሪያ በሙሉ ውኃ አያነሣም።
በሰው ሠራሽ ዘዴ መውለድ ያዋጣ ይኾንን …
የወንድ
ዘር እየተለገሰ/እየተሰጠ በክፍያ በብልቃጥም እየወለዱ የሚያሳድጉ ግብረ ሰዶማውያንም ቢኾኑ በእነዚህ የጭንቅ ቀን መላዎች ተጠቅሞ
የሰውን ዘር እንዲቀጥል ማድረግ ይቻላል ወይ የሚለውን አይመልሱም። የሰው ዘር በአግባቡ እየተዋለደ የሚራባው በአዳማዊው የተራክቦ
መንገድ ነው፤ ያለ አጋዥ ያለ አባባይ።
አዳማዊው
የተራክቦ መንገድ ይህን የሚያከናውንበት የራሱ ተፈጥሯዊ ስልት አለው። ሲጀመር የሰው ልጆችም ኾኑ እንስሳት በተራክቦ ረገድ በውስጣቸው
ያለው ፍትወት (አምጡ አምጡ የሚለው ወሲባዊ ስሜት) ዓላማው ፍጥረታቱ ቢወዱም ባይወዱም በግድ እንዲፈላለጉና እንዲገናኙ፣ ዘራቸው
ያለ ተጨማሪ አጋዥና አሳላጭ መራባት መቀጠሉን ማረጋገጥ ነው። ወንድና ሴት የሚል ጾታ ያላቸው ፍጥረታት በሙሉ፣ አትክልትና ዕፀው
ሳይቀሩ ይራባሉ (“ራ” እና “ባ” ቢጠብቁልኝ ምኞቴ)። በአግባቡ ቁጥራቸው ተወስኖ አንድ ጊዜ የተፈጠሩት ቅዱሳን መላእክት ጾታ
እንኳ የላቸውም፤ ግብሩም አልፈጠረባቸውም። በሰዎችና በእንስሳት ያለው ልማደ ተራክቦ ይዞት የሚገኘው እንዲህ ያለ ሥጋዊ ደስታና
የማይጠገብ ርካታ ዓላማው ፍጥረታቱ በራሳቸው ቸልተኝነት ከግብሩ በመቆጠብ በዘራቸው ሊያደርሱ የሚችሉትን ውድመት በማስቀረት በእግዚአብሔር
እቅድ መሠረት መራባት መቀጠላቸውን ማረጋገጥ በመኾኑ እንኳንስ ዘራቸው በምድር ላይ ይቀንሳል ብለን ልንፈራ እናቁምህ ብንለው እንኳ
የሚቆም ሳይኾን እየተቋቋመ ነው።
ግብረ
ሰዶማዊው ልማድ ግን “ወላጅነት” ወይም “ወላጅ መኾን” የሚለው አጀንዳ በራሱ እጅግ የተወሳሰበበት የዝሙት ሥርዓት እንደኾነ ግልጥ
ነው፡፡ አጠቃላይ ሥርዓቱ ከላይ በተባሉት ሰው ሠራሽ አጋዦች እየታገዘ የሚፈጥራቸው አዳዲስ ልደቶች (አዳዲስ ልጆች) ከዚህም በላይ
ሌሎች ፈጠራዎች ቢታከሉበት እንኳ ውስጣዊ ወጥነት ያለውና ራሱን የሚያዝዝ (ሰልፍ-ዳይሬክቲንግ) መላ ስላልኾነ አትነዝንዙኝ ልፈንጭበት
በሚል ገገማ አቋም ብቻ የመጣ ልፍስፍስ መላ ነው።
ግብረ
ሰዶማዊነትን የሚያወግዙ ሰዎችንም “ፍቅር” በተባለው ጽንሰ አሳብ ላይ እንዳመፁ ሊቈጥሯቸው መሻታቸው ሌላው መናኛ ክርክር ነው።
ፍቅር ገንቢ እንጂ አፍራሽ አይደለም። በሁለት ሰዎች (በጥንዶች) ፍቅር የሰው ዘር ኹሉ እንደ ዘር ይጠቀማል እንጂ አይጐዳም፤ ፍቅራቸው
የሚፈጥራቸው ልጆች ትውልድ ኾነው በትውልድ ሰንሰለት ውስጥ የየራሳቸውን ሐረግ በማዋጣት የሰው ዘር እንዲቀጥል ያበረክታሉ። ግብረ
ሰዶማዊነት ይህ ትሩፋት ሳይኖረው፤ ዘር እያከሰመ እና ትውልድ እያቀጨጨ “ፍቅር” ተብሎ እንዲጠራ የሚጥሩት ጥረት አስቂኝ ይኾናል።
ስንጠቀልለው …
ወደድንም
ጠላንም ግብረ ሰዶማዊነት አሳፋሪ ተግባር መኾኑ እየተቀየረ የአደባባይ ጠባይዕ እየኾነ የመምጣቱ ነገር ረጅሙን ጉዞ በቁርጠኝነት
ጀምሮታል። ዛሬ ዛሬ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው አካላት ኹሉ ዝንባሌው ቢኖራቸውም ባይኖራቸውም ዓላማውን እየደገፉት ይገኛሉ።
አንግበውም የተነሡት “የባምፐር” እና “ስቲከር” ምልክታቸው “የግለ ሰብእ ነጻነት” የሚል ነው። ሰዎች የግብረ ሰዶማውያንን የነጻነት
መብት ሲያከብሩ የሰውን ዘር ከምድር የማመንመንና ብሎም የማጥፋት ነጻነት እያወጁ እንደ ኾነ ሊያውቁት ይገባል።
መንግሥታትም
ነገርየውን ሊወነጅሉት የሚገባው ከዚህ አንጻር ነው። የጤናማ ቤተ ሰብእ መሠረት የኾነው ግብረ አዳማዊው ተራክቦ ነው። የማኅበረ
ሰብእ መሠረት ደግሞ ቤተ ሰብእ። የአገር መሠረት ደግሞ ማኅበረ ሰብእ። እዚህ ላይ ያለውን ሰንሰለታማ የጥገኞች ግንኙነት ማስተዋል
ካልተቻለ በቀር አሁንም ቢኾን ሠለጠነች የምንላት አሜሪካ መሪዎችም ኾኑ ቆርቁዘዋል የምንላቸው የአፍራቅያና እሴያ መንግሥታት ሁለቴ
እንኳ የታሰበበት የሚመስል አቋም ለመያዝ ገና መንገዱን አይጀመሩም።
በዚህ
ሳምንት የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ከነባለቤታቸው በካናዳ ተደርጎ በነበረው “ጌይ-ፕራይድ” (በየዓመቱ ግብረ ሰዶማውያኑ በዓለማችን
በተለያዩ ክፍሎች የሚያከናውኑት የአቋም ቊርጠኝነት ሰልፍ ነው) ተሳታፊ ኾነው ከፊት አብረው መጓዛቸው በዚያች አገር ላይ ብዙ አንድምታዎች
እንደሚኖሩት እሙን ነው። ለግብረ ሰዶማውያኑ የልብ ልብ ይሰጣል፣ ግብሩን ያበረታታል፤ ግብሩን የሚቃወሙና ተፈጥሯዊ ዝንባሌያቸውን
ተከትለው ነገሩን የሚነቅፉ ንጹሕ ሰዎችም ቀስ እያለ ይህን በማድረጋቸው የወንጀለኝነት ስሜት እንዲፀነስባቸው ያደርጋል፣ የአገሪቱን
ሕፃናትና አዲስ ትውልድ አእምሮ ለዘለቄታው ያበላሻል።
ኢትዮጵያችንም
ብትኾን …
በዓለም
አቀፍ ደረጃ እንቅስቃሴው የያዘው አቅጣጫ ደግሞ የአገራችንንም መጪ ኹኔታ አመልካች ነው። ከእኛ ዝምታና አገር ሰላም ብሎ እጅ አጣምሮ
ቁጭ ማለት ጋር አስተያይተው ሲመለከቱት ግርምት በሚፈጥር መጠን ነገርየው ሥር ሰዷል (ማብቀልና ዛፍ መኾን ነው የሚቀረው)። የውጪ
አካላትም አገራችን ላይ በተለየ አጽንዖት በዚህ ጉዳይ ዘርፈ ብዙ (ያልነኩት ዘርፍ የለም እስኪባል ድረስ) ሥራ እየሠሩ ነው። ሰሞኑን
ፌስቡክ ላይ ሦስት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች (እንጦጦ ተራራ ላይ ይመስላል) ይህንኑ የግብረ ሰዶማውያኑን ባለ ኅብረ ቀለማት ዓላማ
ከኢትዮጵያ ባለ አረንጓዴ፣ ብጫ እና ቀይ ዓላማ ጋር ይዘው ፊታቸው እንዳይታይ ተጠንቅቀው የጀርባ ፎቶ ተነሥተው የለቀቁትን ፎቶ
አገር እየተቀባበለው ይገኛል።
በአንጻሩ
በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግም ግብረ ሰዶማዊነት የተቀመጠለት የወንጀለኝነት ቅጣት ከማኅበረ ሰብአዊ ስምምነቱ ጋርና ተግባሩ በኢትዮጵያውያን
ዘንድ ካለው አይወደዴ፣ አንገፍጋፊ አንዘፍዛፊነት ጋር ፈጽሞ የማይመጣጠን ቀላል እስራት ብቻ ነው። በአንዳንድ አገራት ሕጋዊ ተግባር
እየኾነ ከመምጣቱ ጋር ይህን ዝም ብለው ሲያጤኑት ነገን አጨልሞ ያሳያል።
እና
ምን ይጠበስ …
መንግሥት፡
ካለው ማኅበረሰባዊ መግባባት ጋር የሚመጣጠን የወንጀል ቅጣት ለዚህ ተግባር ሊያስቀምጥ ይገባል። አልፎም ይህን ግብር የሚጻረሩ ማኅበረ
ሰብአዊ ተግባራት ላይ ገንዘብም ማፍሰስ፣ አሳብም ማሰብ፣ መላም መምታት፣ ተግባርም መተግበር፣ አቅዶ፣ አልሞ መንቀሳቀስ ያሻዋል!
ቤተ
እምነቶች፡ ተግባሩን ሰይጣናዊ ከማለት ባሻገር እንዴት እንደ ኾነ ማሳየትም ይጠበቅባቸዋል። የየቤታቸውን ትምህርተ መለኮታዊ ገጽታውን
በደምብ አስፍቶና አጉልቶ ማስተማር፣ አማኙም ራሱም መዝኖ ግብሩን የሚኰንንበትን የሃይማኖት ትጥቅ ማስታጠቅ ያሻል (በኦርቶዶክሳዊት
ቤተ ክርስቲያኔ በዚህ ረገድ ፍጹም ለውሳኔ የሚያነቃ ትምህርተ ተራክቦ መኖሩን እመሰክራለሁ)። ከዚሁም ጋር ደግሞ ማኅበረሰባዊ ጠንቆቹንም
አጉልቶ በማሳየት ግብሩን የሚነቀፍ የሚያደርጉት ምክንያቶች ምንኛ የበዙ መኾናቸውን ማሳየት ይገባል።
ሰንበት
አብያተ ትምህርት፡ ትምህርተ ቤተ ክርስቲያንን መሠረት አድርገው ወጣቱን ሊያስገነዝቡትና ሊያምሉት ጭምር ይገባል። (ወጣቱን ማኅበረ
ሰብእ የሰንበት አብያተ ትምህርትን ያክል የቀረበ የለምና) ሰው እምነቱን አክብሮ እንዲኖር የሚደረግ ማንኛውም ጥረት ያለ አጋዥና
ያለ አስተማሪ ከዚህ ግብር እንዲጠበቅ ለማድረግ ይረዳል።
ትምህርት
ቤቶች፡ (የእናንተ ተስፋ አስቆራጭ በመኾኑ እዚህ ልዘረዝረው አልወድም፤ ሌላ ጊዜ እንቅጠር። በአጭሩ ግን ብዙዎቻችሁ ገና “ትምህርት
ቤት” መኾናችሁን ማረጋገጥ ይገባችኋል እላለሁ። ማኅበረ ሰብኡ በአንድነት ተስማምቶባችኋል - ትውልድ መቅረጽም ማነጽም የማትችሉ
መኾናችሁን። በተለየ አዲስ አበባ ውስጥ ትምህርት ቤት ማለት ልጅ የሚረገምበት እንጂ የሚያድግበት ቦታ እንዳልኾነ ከእናንተ በቀር
ኹሉም አምኗል፡፡)
ወላጅ፣
አሳዳጊ፣ ቤተ ሰዎች፡ እስኪ ቴሌቭዥኑን ተመልከቱት፤ … ልጆቻችሁ የሚያዩትን ነገር ወስኑላቸው። ምነው ይህ ነገር ደርሶ በእኛ ዘመን
ወንጀል ኾነሳ፤ .. ልጅ ሺህ ነገር ቢመኝ አይገርምም። የሚበጀውን መርጦ መስጠት የወላጅ፣ አሳዳጊ ድርሻ ነው። ልጅ በመውለድ ብቻ
ጀግና መባል ሊታሰብበት ይገባል። ማሳደጉ ነው እንጂ እኮን ጠቢብ የሚያሰኘው መውለዱማ አልጋ ላይ መውጣት የሚባል ለእንስሶች እንኳ
የማይረቅባቸው ቀላል ተግባር ነው የሚጠይቀው። የልጃችሁን ሕይወት ኹሉንም ገጾች እለት እለት መመልከትና መቆጣጠር የእናንተ ነው።
አድጎ ልጅ ለሚፈላሰፈው ፍልስፍናና፣ ለሚሞላቀቀው መሞላቀቅ ተመልካቹ ኹሉ እናንተኑ የሚኰንን ከኾነ በአንጻሩ ደግሞ ምስጋናም ቢኖር
ያው ነው። እልጃችሁ ዐይን የምትገባውና ጀሮው የምትዘልቀው እያንዳንዷ ነገር በልጃችሁ እድገት ላይ ምን ዓይነት አካላዊና ሥነ ልቡናዊ
ውጤት እንደሚኖራት እየፈናችሁ ካልተንቀሳቀሳችሁ (ቢያንስ በቤት ከእናንተ ጋር ሲኾን) ገና ወላጅ፣ አሳዳጊ ለመባል አልበቃችሁም።
ግለ
ሰዎች፡ እያንዳንዳችን ወሲባዊ ጠባያችንን እንመልከተው፤ በሕሊናችን ዐይን እንየው ... እንቃኘው .. እንቆጣጠረው። ሙሉ ለሙሉ
እንስሳዊነት ያልተጠናወተው ጤናማ የተራክቦ ዝንባሌ እንዲኖረን አድርገን ራሳችንን በመቅረጽ ጊዜ ወስደን ስብእናችንን ልንገነባ ያስፈልጋል፤
ትንሽ ሳይል ትልቅ፤ ታዳጊ የለ አዕሩግ፤ ጎበዝ የለ ጎልማሳ የተራክቦ ሕይወት ውስጥ የለመድናት እያንዳንዷ አላፊነት የጎደላት ትንሽ
ተግባር ነገ አደባባይ የሚወጣን ግንዲላ የሚያክል ስብእናችንን የምትገነባ አላባ ናት ብለን ማሰብ አለብን፤ ለራሳችን ሙሉ አላፊነት
መውሰድ አለብን።
በቀረው
…
ኹላችንም
ንስሐ እንግባ፤ … ኃጢአታችንን እንናዘዝ … በተጋድሎ እና በትሩፋት ላጌጠ ኑሮ ስንዱ እንኹን።
እግዚአብሔርን
እንደ ማኅበረ ሰብእ አንፈልግህም ያልነው እለት የማኅበረሰባችንን የውድቀት ድግስ ያኔ መደገስ እንጀምራለን። የምንበዛው ሰዎች ግብረ
ሰዶማውያንን በተጠየፈ ዐይን ለመመልከት ብቃት የሌለን እነርሱን የደረሱበት ቦታ ያደረሳቸው ፎግረው የሚፎገሩበት አሳፋሪ ሕይወት
ውስጥ እኛም ያለን (አሊያ እንደያ ያለ ልማድ የተጠናወተን) ሰዎች ነን።
ተራክቦ
(ሴክስ) ደስ የሚል ነገር አይደለም! .. የ.ተ.ቀ.ደ.ሰ. ነገር እንጂ። የሚያዝናና ነገር አይደለም፤ .. እግዚአብሔርም ደስ
የሚሰኝበት .. ሰውም የሚከብርበት ተግባር እንጂ።
ተራክቦን
ከዐውዱ ውጪ ስናደርገው፣ ወዲያውም ደግሞ ያለ ልክና ሥርዓትም ስናደርገው፣ … ከዚህ የሚበልጥ በብቸኛዋና ምትክ በሌላት አንድያ
ነፍሳችን ላይ የጨበጣ ቁማር መቆመር፣ መሻሻጥ፣ በእግዚአብሔርና በመንግሥቱ ላይም የማመፅ ተግባር የለም።
ይህን
ግብር በማናቸውም “ፋውሎች” አንኳቶ .. አዝረክርኮ መገኘት በኋላ “ስሙን ቄስ ይጥራውና” ለሚል ርግማን እንኳ የማንመጥን ሰዎች
ያደርገናል። ዛሬ እኛን ባይገባንና ባንረዳው እንኳ የተራክቦ “ፋውሎች” ሰውነታችንን “መንፈሳዊ ግንፍሌ” ልቦናችንን “የልቡና ቆሼ”
የሚያደርጉ መኾናቸው ባለማወቅ ብቻ የማንቀይረው እውነት ነው። ትውልዱ ከዚህ ወጥቶ ንጹሕ ኾኖ እንዲኖር ደግሞ ሊነገረው ይገባል!
ኹሉም ይህን ማውራት አለበት!!!
_____________________________________________________________________
እግዚአብሔር
በፈቀደ ጊዜ ወደ ፊት ዩቲዩብን ሳንጠብቅ
-
ኦርቶዶክሳዊ
የተራክቦ ሥነ ምግባር
-
የተራክቦ
ብልሹ ሥነ ምግባር ጣዖት ከማምለክ ጋር እኩል የሚኾንበት ምክንያት
እና
ሌሎችንም ለዚህ ቦታ በሚገባ ልክ ብቻ እንመሰክራለን።
ይቈየን!
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ