“የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን
ፍቅር እንደሰጠን እዩ
እንዲሁም ነን።”
--- ፩ኛ ዮሐ.፫፥፩ ---
የመንበረ ጸባዖት
ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፤ አዲስ አበባ
|
“ሥላሴ” የእግዚአብሔር ድንቅ አኗኗሩ ነው። በባሕርይ፥ በሥልጣን፥ በአገዛዝ
አንድ ያዕ.፪፥፲፱ በአካላት፥ በግብርና በስም ሦስት ነው፤ ማቴ.፳፰፥፳። በቤተ ክርስቲያናችን ይህ “ሥሉስ ቅዱስ” (ልዩ ሦስት)
ይባላል። አምላካችንን እንደ አይሁድ “አንድ”፥ እንደ ጽርዕና ሮም (ጣዖት አምላኪዎች) “ብዙኅ” ከማለት ይልቅ በአካላት፥ በግብር፥
በስም ሦስት “አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስ” በባሕርይ፥ በአገዛዝ፥ በሥልጣን “እግዚአብሔር” - አንድ አምላክ እንላለን።
“ልዩ ሦስት” ስንል ሂሳባዊ፥ ቀላልና ቀጥተኛ ሦስት ሳይሆን ረቂቅ፥ ሰማያዊና
ባሕርያዊ አንድነት በውስጡ ያለው ሦስት ማለታችን ነው። “አብ” የሥላሴ ልብ፥ “ወልድ” የሥላሴ ቃል፥ “መንፈስ ቅዱስ” የሥላሴ
ሕይወት ነው። አብ ወልድን ወለደ፤ መንፈስ ቅዱስን አሠረጸ ስንል ይበልጣቸዋል ግን አንልም። ለፍጡር ብቻ የሚገባ ተዋረድ ለፈጣሪ
አንቀጽልም። ከአብ የባሕርይ ተወራጅነት የለባቸውም፤ አያንሱም። ወልድም ሥጋ በመልበሱ ምክንያት ራሱን ቢያዋርድ በባሕርይ ያንሳል
ግን አንልም። መለኮት አንድ ነውና በሦስቱ አካላት ቅድምናና ተከታይነት የለባቸውም።
መለኮት ለሦስት አይከፈልም፤ አካላት በአንድ አይጠቀለሉም። አንድ ሲሆን ሦስት፥ ሦስት ሲሆኑ አንድ ነው።
“ሥላሴ” የፍቅር ህላዌ (አኗኗር)
ነው። እግዚአብሔር በባሕርዩ ፍቅር፥ ያለዋጋ የሚያፈቅር የዋህ አምላክ ነው። ታዲያ ፍጥረታትን ከመፍጠሩ በፊት ብቻውን ሳለ በባሕርዩ
ፍቅር የሌለው ነበረን? ተፈቃሪ አልነበረምና? ስንል የልዩ ሦስትነት አኗኗሩ ፍቅርን የሚያስችል፥ ፍቅርን የሚቀበል፥ ለፍቅር የተመቸ
መሆኑን እንረዳለን። በዚህም አብ ወልድን፥ መንፈስ ቅዱስን፥ ወልድም አብን፥ መንፈስ ቅዱስን፥ መንፈስ ቅዱስም አብን፥ ወልድን፥
በፍጹም ፍቅር አፍቅሮ የሚኖሩበት፥ ሦስት አካላት በመለኮታዊ ፍቅር ፍጹም አንድ አምላክ የሚባልበት ረቂቅ አኗኗር ነው። (ዮሐ.፩፥፩)
ምሥጢረ ሥላሴ በገሃድ ለሰዎች የተገለጠው
ጌታ ሲጠመቅ ነበር። ወልድ ሲጠመቅ፥ መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ሲወርድ፥ አብ ለልጁ ሲመሰክር “ወልድየ ዘአፈቅር” የማፈቅረው ልጄ ብሎ ከጥንት የነበራቸውን ፍቅር
ጠቅሶ ከዓለም ጋር አስተዋውቆታል። ፍቅር በሥላሴ ህላዌ ያላትን ትርጕም ይህ ያሳያል። የሥላሴን ምሥጢር መጀመሪያ ያወቅነው ዘመን
ከማይሽረው መለኮታዊ ፍቅሩ ጋር አንድ ላይ ነውና። (ማቴ.፫፥፲፯)
ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ ሰውን ሲፈጥርም ከዚህ የፍቅር ምሥጢር ተካፋይ እንዲሆን
ነበርና በልጁ አርአያ “ልጆቹ” አድርጎ ፈጥሮናል። ዮሐ.፲፯፥፳፪-፳፮
፩ኛ ዮሐ.፫፥፩ ወልድ በባሕርዩ ያለውን የልጅነት ሥልጣን እኛ በጸጋ አገኘን። እንደ አብ ለባዊት (የምታስብ፥ ልብ የምታደርግ)፥
እንደ ወልድ ነባቢት (ተናጋሪ) እንደ መንፈስ ቅዱስ ሕያዊት (ዘላለማዊት) ነፍስ ፈጠረልን። በዚህም ነፍሳችን አርአያ ሥላሴን አርአያ
ይዛለች።
ከዕፀ በለስ በመብላት ልጅነትን ባጣንበት ወቅት ወደ ምድር ልኮ በልጁ
ልጅነታችንን ከዋጀ በኋላ በጥምቀት ታትመን ከመንፈስ የምንወለድበት ሥልጣን አደለን፤ ዮሐ.፩፥፲፪። ምሥጢሩም ሲፈጸም “በአብ፥ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ” በመጠመቅ ነው፤ ማቴ.፳፰፥፳።
ጥምቀት ከእግዚአብሔር ተወልደን በባሕርይ ልጁ አርአያ እኛም የጸጋ ልጆችና ወራሾች የምንሆንበት ነውና ከመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል መሆን የሚባለው ይህ ነው፤
፪ኛ ጴጥ.፩፥፬።
ጥምቀትን ስናስብ የተጠራንለት የሥላሴ ልጅነት፥ ልዩ ሦስትነት፥ ምሥጢረ
ሥላሴ ሊዘነጋ አይገባም። ስለ ምሥጢረ ሥላሴም ስናስብ በጸጋ ልጅነት መንግሥቱን የምንወርስባትን ጥምቀትን አንዘነጋም። ሁለቱ የተሳሰሩና
የድኅነት ውጥኑ፥ ለፍጥረቱ ያለው ወደር የለሽ ፍቅር የሚገለጥባቸው ናቸው።
ሥላሴን ሳያምኑ (አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስ ሳይሉ) ጥምቀትን መፈጸም
ምሥጢሩ ከታሰበለት ዓላማ ውጭ ነው። ሥላሴንም ሲናገሩ በጥምቀት የምትገኘውን ልጅነት ሳያስተውሉ መተረክ ተራ ንግግር ብቻ ይሆናል።
እግዚአብሔር የጥምቀት ልጅነታችንን በሃይማኖትና ትሩፋት ጠብቀን በመጽናት የምንድንባት ያድርግልን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር፥ ወለወላዲቱ
ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር፤ ይቆየን!
“አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ።”
--- ዮሐ.፲፯፥፳፬---
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ