ሰባ ሁለቱ የጌታ አርድእት (ተከታዮች)

እንኳን ለከበሩ #ሐዋርያት በዓል በሰላም አደረሰን!

በዛሬው እለት ሰባ ሁለቱ የጌታ ተከታዮች እንደሚታሰቡ ስንቶቻችን እናውቃለን? የሐዋርያትን ጾም "የሐዋርያት" ከሚያሰኙ መካከል እኒህ ተላውያነ ሐዋርያት ይገኙበታል። 

ሰባ ሁለቱ የጌታ አርድእት (ተከታዮች)

++++++++++++++++++++++++++++++++++++

ሰባ ሁለቱ አርድእት አስቀድመው ጌታ ኢየሱስን ተከትለው ከነበሩት መካከል  ናቸው፤ ሉቃ.10፥1። በውጪ አገር የታሪክ ሰነዶችም ሆነ በእኛው ስንክሳር የተመዘገበ የእያንዳንዳቸው ታሪክ ሲጠና ሁል ጊዜ ጎልተው ከሚታዩ መረጃዎች መካከል አንዱ እነዚህ በተለምዶ ሰባ ሁለቱ አርድእት (ሰባው) ተብለው የሚታወቁት በተለያዩ ጊዜያት ከቀዳማውያን አባላቱ ላይ አንዳንዶች ሲቀነሱለትና ሌሎችም ሲጨመሩበት የኖረ መሆኑ ነው። 

ከእነርሱ ውስጥ ብዙዎቹ አስቀድመው ጌታን በተለያየ መጠንና ሁኔታ የተከተሉት መሆናቸው አንዱ ነጥብ ነው፤ ሁሉም ግን እንደዚያ አይደሉም - ለምሳሌ እነ ቅዱስ ቆርኔልዮስ ኋላ በሐዋርያት ስብከት የሚገቡት ናቸው።(መጽሐፈ ስንክሳር፥ ዘመስከረም 11።) ስለሐዋርያው ቅዱስ ሉቃስና ቅዱስ ማርቆስም የተመዘገቡ ታሪኮች ይህን የሚያሳዩ ናቸው። በእነዚህ ምክንያቶች ቁርጥ ዝርዝራቸውን በተመለከተ ታሪካዊ መረጃዎች በየአገሩ እንደ አገሩ ልማድና ዘይቤ የሚተረኩ ስለ ሆነ ወጥ የሆነ ስም ዝርዝር አናገኝላቸውም። በእነዚህ ደቀ መዛሙርት መካከል ጌታችን በሚሰብክበት ጊዜ ከስብከቱ ጽናት የተነሣ አንዳንዴ ትተውት የሚሄዱ ነበሩባቸው፤ ዮሐ.6፥60-61። 

ፈርጃቸው ልዩ ልዩ የሆኑ ይገኙበታል። ከእነዚህ መካከል ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ጋር በጥብቅ የሚተሳሰር ታሪክ ያላቸው (እንዲያውም ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ እየተባሉ እስከ መጠራት የሚደርሱ) አሉ። ለአብነት በይሁዳ ፈንታ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ቁጥር የገባው ሐዋርያው ማትያስ አስቀድሞ ከሰባ ሁለቱ ነበር፤ ኋላ ከዐሥራ ሁለቱ ለመቆጠር በቅቷል፤ የሐዋ.1፥26። ብዙ ጊዜ የኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ፥ የጌታ ወንድም እየተባለ የሚጠራው ቅዱስ ያዕቆብም ይህ ቅርበት ስለሚነገርለት በሰባ ሁለቱ ዝርዝር በተነሣበት ሁሉ ቀድሞ ሲነሣ እንመለከታለን። መልእክተኛው ሐዋርያው ቅዱስ ይሁዳ ታዴዎስን ከእነዚህ ቁጥር የቆጠረውም ተገኝቷል (መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ሰኔ፥ 25)። 

መጽሐፈ ቅዳሴ በቅዱስ ጴጥሮስ የጀመረውን የሐዋርያት ዝርዝር "፲ቱወ፪ቱ ሐዋርያት" ብሎ ሲጨርስ፣ በቅዱስ ጳውሎስ የጀመረውን ዝርዝር ደግሞ "ሰባ ወ፪ቱ አርድእት" ብሎ ይጨርሰዋል። ቅዱስ ጳውሎስን በአርድእት ወገንመቅቁጠርመወ ያለ ልማድ ነው ለማለት ያህል።

ስለዚህ ከሰባ ሁለቱ መካከል በታሪክ አተራረክ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቱች ከዐሥራ ሁለቱ ወገን እንደ ዐሥራ ሁለቱ የሚሆኑ አሉ።

ከእነዚህ ጋር የሚቀራረብ ዓይነት ጥብቅ ረድእነት ሲሰጣቸው ከምናያቸው ሌሎች ተከታዮች መካከል:

1. ሐዋርያው ቅዱስ ቀሌምንጦስ (ፊልጵ.4፥3 ለሮም ሰዎች ሐዋርያ የሆነ ኅዳር 29)፥ 

2. ሐዋርያው ቅዱስ ጢሞቴዎስ (የሁለት መልእክታተ ጳውሎስ ተደራሽ)፥ 

3. ሐዋርያው ቅዱስ አልዓዛር ዘቆጵሮስ (ዮሐ.11፥1 ከሞት ያነሣው የማርያምና የማርታ ወንድም፤ መጋቢት 17 ፤ ግንቦት 27)፥ 

4. ሐዋርያው ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንጾኪያ ሰዎች ሐዋርያ የሆነ ታኅሣሥ 24 ፤ ሐምሌ 1)፥ 

5. ሐዋርያው ቅዱስ አቡሊካርዮስ (ለእዝሚርና ሰዎች ሐዋርያ የሆነ የካቲት 29)፥ 

6. ሐዋርያው ቅዱስ ስምዖን ኔጌር (የሐዋ.13፥2 ፤ 8፥26-42 ለኖብ እና ኢትዮጵያ ሰዎች ሐዋርያ የሆነ፤ ጥር 18) 

እነዚህን ከ72ቱ ወገን የሚቆጥራቸውም ሆነ የሚለያቸው ዝርዝር በልዩ ልዩ ቦታ አይታጣላቸውም። እነዚህ ከሰባ ሁለቱ መካከል እንደ ሆኑ በግልጽ ከተጠቀሱት ጋር በተመሳሳይ አገልግሎት፥ ማለትም በመንፈሰ ረድኤት የበለጸጉ፥ ታላላቅ ከተሞችን በሊቀ ጳጳስነት ማዕርግ በመምራት የሚታወቁም ናቸው። በተጠቀሰው አገልግሎታቸው ስንክሳራችን ያውቃቸዋል፤ በፈረንጅ ምንጮች ደግሞ ከሰባው መካከል የተጠቀሱበት የተለያየ ዝርዝር በየቦታው ይገኛል።

ሌላው ፈርጅ ሰባቱ ዲያቆናት ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል እነ ሐዋርያው ቅዱስ እስጢፋኖስ፥ ቅዱስ ፊልጶስ የጸኑት ናቸው። ኒቆላዎስ የተባለው ግን በኋላ ላይ እንደ ዴማስ በዓለም ተስቦ ከሐዋርያት ማኅበር የወጣ ነው፤ የሐዋ.6፥5 ፤ ቆላ.4፥14 ፤ 2ጢሞ.4፥10። 

እነዚህን ፍሬ ነገሮች ስንመለከት የሰባ ሁለቱ ቁጥር ሁሌም ሰባ ሁለት ነበር ወይ የሚል ጥያቄ ማንሣት እንችላለን። ጌታ ጠርቶ የላካቸውን ወንጌላዊው በቁጥር ሰባ እንደ ሆኑ ይነግረናል፤ ሉቃ.10፥1። ከዚህ በኋላ ከዚህ ቁጥር ወጥተው በሌላ የሚቆጠሩ ከላይ እንደ ጠቀስናቸው ያሉ የመኖራቸውን ያህል ኋላ ሐዋርያት አስተምረው የጨመሯቸውም ግን ቁጥራቸው ከዚህ ገብቶ በታሪክ መተረኩ የተለመደ ነው። በመሆኑም በመቶዎች የሚቆጠሩ ስላሉበት ከቁጥራቸው ይልቅ በቤተ ክርስቲያን የቀደመ አገልግሎት ውስጥ የነበራቸው ተለይቶ የሚታወቅ የረድእነት ድርሻ ላይ ማሥመሩ ጠቃሚ ነው፤ ሁላቸውም “ሰባው” ይባሉ ነበርና - ለታሪክ ጉዳይ ሰባ መሆናቸው ላይ አይሠመርበትም። 

በሐዋርያት የወንጌል ተልእኮ ላይ አንዱን ሁለት ሁለት፥ ሦስት ሦስት እየሆኑ ተከትለው በመሄድ አገልግለዋል። በመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን አዲስ ረድእ በሚመጣበትና ሐዋርያት ረድእነቱን ተቀብለው በሚያሰማሩት ጊዜ ከሰባው ቊጥር ተደመረ፤ ተጨመረ፤ እየተባለ ስለሚነገር ወገኑም ከሰባ ሁለቱ ወገን እየተባለ መጠቀሱ የተለመደ ነው። በሌላ በኩል ከሰባ ሁለቱ አርድእት ታዋቂና ታሪካቸው ጎልቶ የሚወጡ ሐዋርያው ቅዱስ ሉቃስና ሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ ናቸው። 

በማናቸውም መለኪያ የቅዱስ ሉቃስን ያህል የገነነ ግን ከሰባ ሁለቱ የለም፤ እርሱ ስለእነዚህ አርድእት በመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኝ ብቸኛ ታሪካቸውንና አገልግሎታቸውን የተረከልን ወንጌላዊ ነውና፤ ሉቃ.10፥1። ዳግመኛም ዛሬ ከምናውቃቸው የሐዲስ ኪዳን የምእመናን መማሪያ የሆኑ ሃያ ሰባት መጻሕፍት ውስጥ በመጠን አንድ ሦስተኛ የሚያክለውን የጻፈ እርሱ ነውና። የሉቃስ ወንጌል ከወንጌላት በመጠን ትልቁ ሲሆን985 ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፉ ጋር ሲደመር የጽሕፈቱ መጠን ከቅዱስ ጳውሎስ ዐሥራ ዐራት መልእክታት ተወዳድሮ እጅግ ጥቂት ብቻ ቢያንስ ነው።


ሌሎች ሐዋርያት ለምሳሌ ሳውልን ያጠመቀው ሐዋርያው ቅዱስ ሐናንያስ፥ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባን ያጠመቀው ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ፥ ቀዳሜ ሰማዕት የሆነው ሐዋርያው ቅዱስ እስጢፋኖስ፥ የኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ ሐዋርያው ቅዱስ ቀለዮጳ፥ የሚላን ኤጲስ ቆጶስ ሐዋርያው ቅዱስ በርናባስ፥ ወዘተ. በልዩ ሁኔታ ጎልተው የሚወጡ ከአርድእት መካከል ናቸው።


በመጽሐፈ ስንክሳር ከሰባ ሁለቱ ወገን እንደ ሆኑ በግልጽ የተጠቀሱትን የሚከተሉትን በረከታቸው እንድታድርብን፥ ጸሎታቸው እንድትረዳንና ከቃል ኪዳናቸው ተጠቃሚ እንድንሆን ለሚጠቀሙበት ሁሉ እንዘረዝራለን።


1. (መስከረም 21) ሐዋርያው ቅዱስ ጤባርዮስ፤

2. (መስከረም 24) ሐዋርያው ቅዱስ ቤድራጦስ (ቆርጦስ)፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘቤሪጦስ፤

3. (ጥቅምት 4) ሐዋርያው ቅዱስ ሐናንያስ ኤጲስ ቆጶስ ዘደማስቆ የጠርሴሱን ሳውል ያጠመቀው የሐዋ.9 – 11፤

4. (ጥቅምት 14) ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስ፥ ዲያቆን የሐዋ.6 (ሳምራውያንን እና ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ያስተማረ)፥ በታናሽ እስያ የትሬልስ ኤጲስ ቆጶስ፤ የሐዋ.8፤

5. (ጥቅምት 22) ሐዋርያው ቅዱስ ሉቃስ፥ የሐዋርያት ሥራ እና የሦስተኛው ወንጌል ጸሐፊ፤

6. (ጥቅምት 26) ሐዋርያው ቅዱስ ጢሞና፥ ዲያቆን የሐዋ.6፤

7. (ኅዳር 23) ሐዋርያው ቅዱስ ቆርኔሌዎስ፤

8. (ኅዳር 27) ሐዋርያው ቅዱስ ፊልሞና፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘጋዛ የመልእክተ ፊልሞና ተደራሽ ሐዋርያ፤

9. (ታኅሣሥ 21) ሐዋርያው ቅዱስ በርናባስ፥ ከሳውል ጋር ዞሮ የሰበከ

10. (ጥር 20 ፤ ጥር 4) ሐዋርያው ቅዱስ አብሮኮሮስ፥ ዲያቆን የሐዋ.6 በቢታንያ የኒቆሜዲያ ኤጲስ ቆጶስ፤ የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ረድእ፤ ስንክሳር ነሐሴ 4 ላይ ይዘክረዋል፤

11. (የካቲት 4) ሐዋርያው ቅዱስ አጋቦስ፤

12. (የካቲት 10) ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ የጌታ ወንድም፥ የኢየሩሳሌም ኢጲስ ቆጶስ፤ የያዕቆብ መልእክት ጸሐፊ፤ (ከሰባ ሁለቱ ወገን እንደ ሆነ አይጠቅስም፤ ሌሎች ምንጮቻችን ግን ይላሉ)

13. (መጋቢት 19) ሐዋርያው ቅዱስ አርስጦቦሎስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘብሪታንያ፤

14. (መጋቢት 25) ሐዋርያው ቅዱስ ኦኔስጶራስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘቀሬና፤

15. (ሚያዝያ 15) ሐዋርያው ቅዱስ አጋቦስ፥ የሐዋ.11፥28 ፤ 21፥10፤

16. (ሚያዝያ 30) ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ማርቆስ፥ የእስክንድርያ ኤጲስ ቆጶስና የሁለተኛው ወንጌል ጸሐፊ፤

17. (ግንቦት 3) ኢያሶን፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘጠርሴስ 

18. (ግንቦት 22) ሐዋርያው ቅዱስ አንድሮኒቆስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘፓኖኒያ፤

19. (ግንቦት 23) ሐዋርያው ቅዱስ ዮልዮስ፤

20. (ግንቦት 23) ሐዋርያው ቅዱስ አፍሮዲጡ፤

21. (ግንቦት 30) ሐዋርያው ቅዱስ ቆሮስ፤

22. (ሰኔ 25) ሐዋርያው ቅዱስ ይሁዳ፥ የጌታ ወንድም፥ የይሁዳ መልእክት ጸሐፊ፤

23. (ሐምሌ 6) ሐዋርያው ቅዱስ አሌምፐስ፤

24. (ሐምሌ 9) ሐዋርያው ቅዱስ ስምዖን ቀለዮጳ፤

25. (ጳጉሜ 2) ሐዋርያው ቅዱስ ቲቶ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘቀርጤስ፥


በሌሎች ቦታዎች ግን ከሰባ ሁለቱ እንደ ሆኑ የሚባልላቸው አሉ። ከሚባሉትም መካከል ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ይገኙባቸዋል፤ ማጥናት የሚችል እያጠና ከላይ ከሰፈሩ ጎራዎች ወገን 

እየመደበ ቢያቀርብ ጠቃሚ ጥናት ይሆናል። 


1.ሄሮድዮን፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘፓትራስ 

2.ሉቅዮስ ዘቀሬና፥ በሦርያ የሎዶቅያ ኤጲስ ቆጶስ 

3.ልኒዮስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘሮም 

4.ሔርማስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘድልማጥያ 

5. ሔርሜስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘፍሊጶጶሊስ 

6.ማርቆስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘአፖሎኒያ 

7.ሩፉስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘቴቤስ 

8.ሐዋርያው ቅዱስ ሲላስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘቆሮንጦስ 

9.ሲልቫነስ፥ 

10.ሶሴፓተር፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘኢቆንያ 

11.ቀለዮጳ 

12.ቀሌምንጦስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘሰርዴን 

13.ቆድራጦስ 14.ቲኪቆስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘቆሎጶን 

15.ታዴዎስ (ከዐሥራ ሁለቱ ያይደለ ሌላኛው) 

16.ኒቃሮናን፥ ዲያቆን 

17.ናርኪሱስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘአቴና

18.አቤሌስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘሄራቅሊዮን 

19.ሐዋርያው ቅዱስ አብራሜናስ (ፓርሜናስ)፥ ዲያቆን 

20.አምጵልዮስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘኦዲሳ 

21.አርስታርቆስ፥ የአጳሚያ ኤጲስ ቆጶስ 

22.አርጤማስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘልስጥራ 

23.አርኪጶስ 24.አሲንክሪቶስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘሄራቅኒያ 

25.አስታቂዮስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘቢዛንቲዩም 

26.አናሲሞስ (በመልእክተ ፊልሞና የተጠቀሰው ያይደለ ሌላኛው)

27.አካይቆስ፥ 1ቆሮ.16፥17 ላይ የተጠቀሰው 

28.አጵሎስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘቂሣርያ 

29.ኢዮዲያስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘአንጾኪያ 

30. ኡርባን፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘመቄዶንያ 

31.አፔሌስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘሄራቅሊዮን 

32.ኡርባን፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘመቄዶንያ 

33.አቂላ

34.ኤጳፍራስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘእንድርዬቃስ (አንድሪያካ) 

35.ኤቤንጤዎስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘቅርጣግና 

36.ኤጳፍሮዲጦስ፥ 

37.ኤራስጦስ፥ ኢጲስ ቆጶስ ዘጵንያ 

38.ሐዋርያው ቅዱስ እስጢፋኖስ፥ ሊቀ ዲያቆናት፥ ቀዳሜ ሰማዕት 

39.ዮስጦስ 

40.ካርጶስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘቤሮያ 

41.ክሬሰንስ፥ 

42. ክሪስጶስ፥ በገሊላ የኬልቄዶን ኤጲስ ቆጶስ 

43.ዜናስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘዲዮስጶሊስ

44.ዞስቴናስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘቆሎጶን 

45.ጋይዮስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘኤፌሶን 

46.ጠርጦስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘሮም፥ የሮሜ መልእክት ከታቢ 

47.ሐዋርያው ቅዱስ ጢሞቴዎስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘኤፌሶን፥ ወልደ ጳውሎስ በትምህርት 

48.ጥሮጲሞስ 

49.ዮሐንስ ማርቆስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘቢብሎስ (ወንጌላዊው ማርቆስ ነው ይላል) 

50.ፊሎሎጎስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘሲኖጴ 

51.ፎርቱናጦስ

52.ፑዴንስ 

53.ፓሮቡስ፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘፖቶሌ 

54.ፕሌጎን፥ ኤጲስ ቆጶስ ዘመራቶን። 

እያንዳንዳቸው በስፋት እየተጠኑ መታወቅ ባለበት መጠን መታወቅ አለባቸው። በኅዳግ የሰፈረው ዝርዝር አንዳንዶች በመሃል ከክርስትናው የወጡትንም የሚጨምር መስሎ ይታያል፤ በቅድስና የምናውቃቸውንም ግን ያሳያል።

እግዚአብሔር በገድል ከከበሩት ተላውያነ ሐዋርያት ረድኤት የክፈለን። የጾመ ሐዋርያትን በረከት አያጓድልብን። ሰናይ በዓል። 

ሐምሌ 05፣ 2010 ተጻፈ፣ 

ሐምሌ 05፣ 2017 ተለጠፈ።

አስተያየቶች